ማሕደረ ዜና፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ቃል፣ መርሕና እርምጃ ቁንፅል ትዉስታ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2017
የካቲት 28፣ 2025 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዋሽግተን።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሐዉስ ድረስ የጋበዟቸዉን የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮልዶሚየር ዜሌንስኪን ወቅሰዉ፣ ዘልፈዉ ከቤተ-መንግሥታቸዉ አባረሯቸዉ። የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንስ ሞተዉም ትራምፕንና ዘለንስኪን እንደ ወዳጅ አወያዩ። ቫቲካን። ቅዳሜ። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ስብዕና፣ መርሕ፣ ጥሪ።
ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎጁሊዮ «የመጀመሪያዉ» ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት የሚባሉበት ቃል-ምግባራቸዉ ዝርዝር ብዙ ነዉ።ዘገቦች እንደሚጠቁሙት የአንድ የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ዓመታዊ ገቢ እስከ 800 ሺሕ ዶላር ይደርሳል።
«ደኻዉ»ና የድሆች ተቆርቋሪዉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት
መጋቢት 13፣2013 አርጀንቲናዊዉ ካርዲናል ለዚያ ማዕረግና ገቢ ተመረጡ።የቅድስና ሥማቸዉም በጥንታዊዉ የደሐ ተቆርቋሪ ሥም ተጠራ።ፍራንሲስ ተብሎ።ሰነድ-ጥቂት ቅያሬ ልብሶቻቸዉን በቦርሳ-ሻንጣቸዉ ሸከፉ።እንደተራ ያዉም ወጣት መንገደኛ ሻንጣቸዉን ራሳቸዉ ይዘዉ ቦኒስ አይሪስ አዉሮፕላን ጣቢያ ደረሱ።ሶስተኛ ማዕረግ (ኤኮኖሚክ ክላስ) ተሳፍረዉ ሮም-ገቡ።
«ሕዝቤ ደኸ ነዉ» ይሉ ነበር አሉ ደጋግመዉ «እና እኔም ደኸ ነኝ።» በስጦታ፣ በሽልማት ያገኙት ወይም የገዙት ንብረት አንዳዶች እንደሚሉት በሚሊዮን ዶላር ይገመታል።«ደሞዛቸዉ» ብሎ ለሚጠይቅ ግን የሚያገኘዉ መልስ «ዜሮ» የሚል ነዉ።ሁሉንም ለነዳያን ይሰጣሉ።
«በተለይ ድሆችን፣የተገለሉ-የተገፉትን በልዩ ሁኔታ ይመለከቱ ነበር።ይሕ መለያቸዉ ነበር።እኛ እዚሕ የዓለም የመጨረ,ሻ ጠርዝ ላይ ነን።ጠረፍ ላይ ያለነዉን አይዘነጉም ነበር።»
አርጀንቲናዊቱ ወይዘሮ ፋቢያና ሉኢዛራ።ሜርሴዴስ ካራሲሳይ ደግሞ ዓለም የሁሉም መሆኗን አሳይተዉናል ይላሉ።
«ዓለም የተወሰኑ ወገኖች ማዕከል ብቻ እንዳልሆነች አሳይተዉናል።እኛም የዓለም አካል መሆናችንን አስገንዝበዉናል።»
የስደተኞች መብት ተሟጋቹ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት።
ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎጁሊዮ የኢጣሊያን የቤኒቶ ሙሶሊኒን ፋሽታዊ አገዛዝ ሸሸቶ አርጀንቲና ከተሰደደ አባትና እዚያዊ አርጀንቲና ከተወለዱ ኢጣሊያዊት እናት የተወለዱ ናቸዉ።የስደተኞች ልጅ።በልጅነቱ ሙዚቃ፣ ታንጎ፣ ዳንስ፣ እግር ኳሱንም ሞካክሮታል።
ሕይወቱን ለኃይማኖት ከሰጠ በኋላ ግን እንደ ድሆች ሁሉ ለስደተኞችም ሲሟገት አድጎ፣ጦርነትን ሲቃወም በስሎ አርጅተዋል። ፍራንሲስ። በ 12 ዓመታት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሥልጣናቸዉ ዘመን 68 ሐገራትንና በመቶ የሚቆጠሩ ግዛቶችን ጎብኝተዋል።ከሮም ዉጪ መጀመሪያ የጎበኙት ግን በአብዛኛዉ የአፍሪቃ ስደተኞችን የሜድትራንያንን ባሕር ለማቆረጥ ሲቀዝፉ በብዛት የሚልቁበትን ባሕር፣ ከዳኑ የሚያርፉበትን ደሴት ነበር።ላፔዱዛን ሐምሌ 8፣ 2013።
በአሳ አጥማጆችና በጀልባዎቻቸዉ ታጅበዉ ብዙ ስደተኞች ባለቁበት ባሕር ላይ ያበበ ጉንጉን ጣሉ፣ ሟቾችን አሳፍረዉ ይቀዝፉ የነበሩ ጀልባዎች ስብርባሪ አጠገብ ፀለዩ፣ በሕይወት የተረፉን አፅናኑ።በስደተኞች ላይ በራቸዉን የዘጉትን የአዉሮጳ-አሜሪካ መንግስታት «ለስደተኞች የወንድማዊ ኃላፊነት ስሜትን አጥተናል» በማለት ወቀሱ።
በ2016 ሜክሲኮን ሲገበኙ ርዕሠ ከተማ ሚክሲኮ ሲቲ ብቻ ደርሰዉ አልተመለሱም።አምስት ቀን በቆየ ጉብኛታቸዉ፣ ከጎበኟቸዉ አምስት አካባቢዎች አንዱ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመግባት የሚፈልጉ በርካታ የደቡብ አሜሪካ ስደተኞች የሚገኙበት ሌለኛዉ ብዙ የተገለሉ ግን አንጡራ የሐገሬዉ ተወላጆች የሰፈሩበት፣ እስረኞች የሚገኙበትንና በጣም አደገኛ ወንጀሎች ይፈፀሙበታል የሚባል አካባቢ ነበር።በዚያዉ ዓመት ሊዝበን-ፖርቱጋልን ጎበኙ።
በአዉሮጳ ሕብረት ሕግ መሠረት ወደ ቱርክ ይጠራዛሉ ከተባሉ የሶሪያ ስደተኞች መካካል በጣም የተጎዱትን 12ቱን በገዛ አዉሮፕላናቸዉ፣ ከራሳቸዉ በፊት አሳፍረዉ ሮም ገቡ።ዋፋዕ ኢድ፣ ሁለት ልጆቸና ባለቤቷ ይገኙባቸዋል።ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳቱን «እንደ መለአክ ናቸዉ» አለች ዋፋዕ-አለ የቢቢሲዉ ዘገባ።«የልጆቼን መፃኤ ዕድል አዳኑት» አከለች ዋፋዕ -እንደ ዘገባዉ።
ተፈጥሮን አድናቂ፣ የተፈጥሮ ሐብት እንዲከበር የሚጣጣሩም ነበሩ።
የፈጣሪ ፍጡር መከበር፣ መጠበቅ፣ በተገቢዉ መንገድ መያዝ አለበት የሚል ጠንካራ አቋም ነበራቸዉ።የዓለምን የዓየር ንብረት ለዉጥን ለመቆጣጠር ታሕሳስ 2015 ፓሪስ ላይ የተፈረመዉን ዓለም አቀፍ ሥምምነት በግልፅ ደግፈዋል።ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ለተፈጥሮ ያላቸዉን ፍቅርና ክብር ከጆን ኬሪ በተሻለ መንገድ የገለፀዉ ፖለቲከኛ የለም።
በነገራችን ላይ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ አሜሪካን ወክለዉ የፓሪስን ሥምምነት የፈረሙ ፖለቲከኛ ናቸዉ።የዓየር ንብረትን በተመለከተ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ጋር በመሥራቴ «ዕድለኛ ነበርኩ» አሉ ኬሪ በቀደም።ፍራንሲስ የጋራ መኖሪያችንን እንጠብቅ የሚል መርሕ ነበራቸዉ።« encyclical "Laudato si". ይላሉ ኬሪ
«አዎ የጋራ መኖሪያችንን እንጠበቅ የሚለዉን መርሐቸዉን አወጡ- Laudato si". ።አከታትለዉም ዱባይ ከመገናኘታችን በፊት Laudato Deum (እግዚአብሔር ለፈጠረዉ ሁሉ ምስጋና ይግባዉ» የሚለዉን ጠቃሚ መግለጫ አወጡ።የሰዉ ልጅ በራሳችን ላይ የምናደርሰዉን በጥልቅ ይከታተሉ፣ ነበር። የፈጣሪ ፍጡር የሆነዉን ተፈጥሮን ለመጠበቅ ሁሉም ሰዉ የሚችለዉን፣ የተሻለና በፍጥነት እንዲያደርግ ግፊት ያደርጉም ነበር።»
ነበር።
ጦርነት፣ ግጭትና ዉዝግብን አጥብቀዉ ይቃወማሉ።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነቱን ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ከምያንማር እስከ ኮሎምቢያ፣ ከየመን እስከ ቬኑዙዌላ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ሶሪያ፤ ከደቡብ ሱዳን እስከ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ እስከ ሊቢያ የተደረጉና የሚደረጉ ዉዝግብ፣ ግጭት ጦርነቶች እንዲቆሙ ተማፅነዋል።
በቅርብ ዓመታ ደግሞ የ,ጋዛን እልቂት፣ የእስራኤሎችን መታገት፣ የዩክሬንን ጦርነት፣ የሱዳኖችን መተላለቅ፣ የደቡብ ሱዳኖችን መዛዛት፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን ፍጅት ተቃዉመዋል።ግጭት፣ ጦርነት፣ዉዝግቦች በድርድር እንዲፈቱ ተማፅነዋል።የሰላማዊ ሰዎች ደሕንነት እንዲጠበቅ፣ርዳታ እንዲደረግላቸዉ ጠይቀዋል።ፀልየዋልም።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንትና ምክትላቸዉ ለየግል ሥልጣናቸዉ የበላይነት ሲሻኮቱ በመጣላታቸዉ ከጭቆና፣ ግፍና በደል ነፃ አወጣንሕ ያሉትን ሕዝባቸዉን ከጦርነት በማገዱበት መሐል ቫቲካን ተጋብዘዉ ነበር።ሚዚያ 2019።በ2013 የተጀመረዉ ጦርነት እስከ ሚያዚያ 2019 ድረስ ብቻ 400 ሺሕ ሰዉ ማርገፉን፣ ተጋባዦች ለሸምጋይ አደራዳሪዎች ጥረት፣ለሰላም ወዳዶች ጥሪና ጩኸት እንቢኝ ማለታቸዉን ጋባዥም፣ ተጋባዦችም ያዉቃሉ።
ያኔ ቫቲካን ዉስጥ ይማሩ የነበሩት ያሁኑ የደቡብ ሱዳን ቄስ ጄምስ ሮምቤ ደግሞ የጦርነቱን ዘግናኝ ዉጤት ከጋባዥ ተጋባዦችም በላይ ያዉቃሉ።ሳላቫ ኪር፣ ሪያክ ማቸርና ተማሪ ሮምቤ የማያዉቁት ግን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሚያዉቁት ግን አንድ ነገር ብቻ ነበር።አደረጉት።የ1. 4 ቢሊዮን ሕዝብ የመንፈስ አባት ተጋባዦቹ እግር ላይ ወደቁ።«ደገጥን» ይላሉ የዛሬዉ ቄስ።በርግጥም ዓለምም ያን ቪዲዮ-ፎቶ ሲያይ ደነገጠ።
«መሪዎቻችን ተጋብዘዉ ሮም ሲመጡ እኛ እንደተማሪ እዚያ ነበርን።የተለመደ ፕሮግራም ነዉ ብለን ነበር።ተንበርክከዉ የእንግዶቹን እግር ሲስሙ ግን ሁሉም ነገር ተለወጠ።ደነገጥን።ሁሉም ሰዉ ደነገጠ። እራስን ዝቅ የማድረግን ክብር፣ ለሕዝብ የማገልገልን ልዕልና፣ መሪ አገልጋይ መሆኑንም ለመሪዎቻችን አስተማሩ።»
መሪዎች ተምረዉ ይሆን? ብቻ ሳዉዬዉ ብዙዎች እንዳሉት «የሕዝብ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳጳሳት፣ የድሆች ተቆርቋሪ፣ የስደተኞች ተሟጋች፣የጦርነት ተቃዋሚ ነበሩ።» ባንድ ወቅት ሐይማኖት የለሾች «ይፀድቃሉ» ተብለዉ ተጠየቁ። «ፈጣሪ መሐሪ ነዉ።» መለሱ-ሰዉዬዉ ።
«አጥር ሳይሆን ድልድይ እንገንባ»
ከ2018 ወዲሕ ከወደ አዲስ አበባ «ግንቡን እናፍርስ፣ ድልድይ እንገንባ» ዓይነት አባባል በተደጋጋሚ ይሰማል።በቃል-ያሉት፣ እንደ መርሕ-ያራመዱት፣ በምግባርም ያደረጉት ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳጳሳት ፍራንሲስ ናቸዉ።«አጥር ሳይሆን ድልድይ ይገንባ» ነዉ ብሒላቸዉም።
«ይሕ አስተሳሰብ በክርስቲያኑ ማሕበረሰብ ዉስጥ ብቻ ታጥሮ መቅረት የለበትም።በጤናማ፣በማሕበራዊና ሥነ ምግባራዊ አዉዱ ወደ ዉጪም (ለሌችም ጋ) መድረስ አለበት።ለእኩይ ምግባር እኩይ መለስ ሳይሆን፣ ለእኩይ ምግባር ጥሩ አፀፋ መስጠትን፣ ጥቃትን በይቅርታ ማለፍን፣ አጥር ማጠር ሳይሆን ድልድይ መገንባት እንደሚያስፈልግ የሚደረግ ጥሪ ነዉ።»
በእምነቶች መካከል «ድልድይ ለመዘርጋት» አይሁዳዊቱን ሐገር እስራኤልን፣ ሙስሊሞች የሚበዙባቸዉን ፍልስጤምን፣ ቱርክን፣ ኢራቅን፣ ዮርዳኖስን፣ ግብፅን፣ ሞሮኮን፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን፣ ባሕሬንን፣አዘርበጃንን ጎብኝተዋል።ኢራቅ ዉስጥ ከሺአ ሙስሊሞች መሪ ከታላቁ አያቶላሕ ዓሊ አል ሲስታኒ ጋር ተወያይተዋል።
«ለዓለም ሰላምና አብሮ ለመኖር የሰብአዊ ወዳጅነት ሰነድ» የተባለዉን ሥምምነት ከአል አዝሐር ኢማም ከፕሮፌሰር አሕመድ ኤል ጠይብ ጋር ተፈራርመዋል።ዱባይ።2019።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳጳሳት ፍራንሲስ አንዳዶች በጣም ወግ አጥባቂ፣ ሌሎች ለዘብተኛ እያሉ በተቃራኒ ይወቅሷቸዋል።የኮቪድ ሥርጭት ባሰጋበት ዘመን ተከታዮቻቸዉ መከላከያ እንዲከተቡ በመምከራቸዉ የተቿቸዉም አሉ።
ለብዙዎች ግን የናጄሪያዊዉ የካቶሊክ ቄስ በቀደም እንዳሉት «ለካቶሊኮች አባት፣ ለሌሎች እምነት ተከታዮች ወንድም፣ ለድሆች ተቆርቋሪ፣ የሰላም ጠበቃም ነበሩ።» በ8ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከነበሩት ከሶሪያዊዉ ጆርጅ ሳልሳዊ ወዲሕ ከአዉሮጳ ዉጪ ተወልደዉ ያደጉ የመጀመሪያዉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የእየሱሳዉያን (ጀስዊትስ) ሐራጥቃ ተከታይ የመጀመሪያዉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ነበሩ።ሰኞ ሞቱ።
ቱጃሩ ዶናልድ ትራምፕም-ደኻይቱ ሉኢዛራም እኩል አዘኑ።ወይም አዘንን አሉ።የተፈጥሮ ሐብት እንዲከበር የተፈራረሙት ጆን ኬሪም፣ ሥምምነቱን ያፈረሱት ትራምፕም እኩል ለቅሶ ደረሱ።ከሞቱ በኋላም ባለፈዉ የካቲት ከዋይት ሐዉስ አባራሪዉ ትራምፕና ተባራሪዉ ዘለንስኪ ቫቲካን ዉስጥ ሥለሠላም ተነጋገሩ።እሳቸዉ ግን ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊኒ እንዳሉት ሩጫቸዉን ጨረሱ-------አዲዮስ
«ጌታ ለሕዝቡ የሰጠዉ የበግ እረኛ ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ የዚች ምድር ሕይወታቸዉ አበቃ።ከእኛም ተለዩን።»
88 ዓመታቸዉ ነበር። ቅዳሜ ተቀበሩ።
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ