ማሕደረ ዜና፣ የሸረሪና ዉጊያ፣ «የክተት» አዋጅና የፕሪቶሪያ ዉል
ሰኞ፣ ሐምሌ 27 2018
ዕዉቁ የሶቭየት ሕብረት ጠንካራ መሪ ጆሴፍ ስታሊንየዲፕሎማሲ-ጦርነት ተቃርኖን የምታረጋግጥ አንድ አባባል ነበረቻቸዉ ይላሉ-የሚያዉቁ።«የአንድ ሐገር ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሰላም ጉባኤ እንዲደረግ እስከመጨረሻዉ እታገላለሁ ካለ» አሉ አሉ ስታሊን ባንድ ወቅት «መከላከያ ሚንስትሩ ለዉጊያ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠርጥር።» ባለፈዉ ሳምንት እስከ ቅዳሜ አዲስ አበባና መቀሌ ላይ የተደረገና የተባለዉ የስታሊንን አባባል የሚያጠናክር መሆን አለመሆኑን በርግጥ አናዉቅም።እርግጡ እንዲሕ ነዉ። አዲስ አበባ ላይ የምክክር አስፈላጊነት፣ የፕሪቶሪያ ሥምምነት ጠቃሚነት ሲነገር-ሲተነተን ከወደ መቀሌ የጦርነት መርዶ-የክተት ጥሪ ታወጀ።ቅዳሜ።የዳግም እልቂት ጅምር ይሆን? ላፍታ አብረን አብረን እንጠይቅ።
የፕሪቶሪያ ሥምምነት የገጠመዉ እንቅፋት
ጥቅምት 2015 ከወደ ፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪቃ አፅናኝ ቃል ተሰምቶ ነበር።የተለያዩ ወገኖች እንደገመቱት 600 ሺዎች ያለቁ፣ ሚሊዮኖች አካላቸዉ የጎደለ፣ሴቶች የተደፈሩ፣ ብዙ ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት ዘግናኝ ጦርነት ፍፃሜ ተነግሮ ለቀሪዎች የሰላም ተስፋ ፈንጥቆ ነበር።የጠመንጃዉ ላንቃ ተዘጋ-የአፍሪቃ ሕብረት አደራዳሪዎች ቡድን መሪ ኦሌ ሴጎን ኦባሳንጆ-እንዳሉት።
«ዛሬ ለኢትዮጵያ አዲስ ጎሕ ቀደደ፣ ለምስራቅ አፍሪቃ፣ በርግጥ ለመላዉ አፍሪቃም አዲስ ጎሕ ቀደደ።ይሕ ለአፍሪቃ ችግሮች የአፍሪቃ መፍትሔ (አብነት) ነዉ።በዛሬዉ የሰላም ስምምነት (የአፍሪቃ ሕብረትን) አጀንዳ 2063 አካል የሆነዉ ገቢር ሲደረግ አይተናል።ይሕም አፍሪቃ ዉስጥ የጠመንጃ ላንቃን ማዘጋት ነዉ። በኢትዮጵያዉ ግጭት የሚዋጉ ሁለቱ ወገኖች ግጭቶችን ለማቆም በይፋ ተስማምተዋል።»
ይሕ ቃል፣ ይሕ ተስፋ፣ይሕ የአፍሪቃ አብነት ስምምነት ይዘት፣ ሒደትና ገቢራዊነቱ ገና ከጅምሩ ማወዛገብ፣ ማከራከር፣ ማሻኮት-አልፎ አልፎ ማጋጨቱም አልቀረም።የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማትና የሕግ ባለሙያ ባይሳ ዋቅወያ እንደሚሉት አክራሪ የትግራይ ፖለቲከኛና የጦር አዛዦች ስምነቱን እንደ ሽንፈት ሥለቆጠሩት ገና ከጅምሩ ለገጠመዉ ፈተና አንዱ ምናልባትም ዋናዉ ምክንያት ነዉ።
«በኋላ ግን አንድም ባሕላችን ችግር አለበት ይኼ መሸነፍን መቀበል በጣም ከባድ ነገር ነዉ።ተመልሰዉ ሲሄዱ (ተደራዳሪዎቹ) ብዙ ሐርድ ኮር የቲ ፒ አል ኤፍ አባላት--»
ስምምነቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን ሆነዉ የህወሓት ኃይላትን ሲወጉ የነበሩ ኤርትራንና የአማራ ታጣቂዎችን ቅር ማሰኘቱም ይነገራል።ይሁንና ባለፉት ሁለት አመታት ከመቀሌም-ከአዲስ አበባም ከመቀሌ እኩል የፕሪቶሪያ ሥም ሲጠራ፣ ሲጠቀስ፣ ሲነገረዉ፣ ከኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት በላይ የስምምነቱ ይዘት፣ የተግባራዊነቱ እንዱትነት ሲተነተንለት የከረመዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅዳሜ ዋዛሜም የስምምነቱ ፋይዳና ዉጤት ሲንቆረቆርለት ነበር።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ለአማራ መገናኛ ብዙሐን እንደነገሩት።
«የፕሪቶሪያ ሥምምነት ለትግራይ፣ ለአማራ፣ ለአፋር ለኢትዮጵያ ያስገኘዉ ነገር የጥይት ድምፅ፣ የተኩስ ድምፅ እንዳንሰማ ማድረግና አንፃራዊ በሆነ መንገድ ወደ ልማት እንድናተኩር ማድረግ ነዉ።»
የጦርነት መርዶና የ«ክተት» ጥሪ ከትግራይ
የጠቅላይ ሚንስትሩ መልዕክት ተተንትኖ-ምናልባት ተደምጦ ሳያበቃ ግን ሸረሪና, ምዕራብ ትግራይ ጦርነት መጀመሩ ከመቀሌ ታወጀ።ህወሓት መራሹ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባወጣዉ መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ጦርና የትግራይ ኃይል የሚባለዉ የህወሓት ታጣቂዎች ቅዳሜ ሐምሌ 25፣ 2018 ከማለዳዉ እስከ ቀትር ድረስ ሲዋጉ ነበር።
በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ የተሰራጨዉ መግለጫ «የትግራይ ሕዝብን ለማጥፋት ያለመ ጦርነት» ያለዉን ግጭት ለመመከት የትግራይ ሕዝብ በሙሉ የኃይማኖት ተቋማት ሳይቀሩ እንዲዘጋጁ ጥሪ አድርጓልም።
«በሐገር ዉስጥና በዉጪ የምትኖር የትግራይ ሕዝብ፣ ዲያስፖራዎች፣ ሁሉም የትግራይ ሠራዊትና የፀጥታ አካላት፣የትግራይ ብሔራዉያን ኃይሎች፣ የትግራይ ሲቪል ማሕበራት፣ የትግራይ ኃይማኖታዊ ተቋማት----ጥሪ እያቀረብን»
የኢትዮጵያ መንግሥት ሥለቅዳሜዉ ግጭትም ሆነ፣ የትግራይ ክልልላዊ መንግሥት ሥላደረገዉ «ክተት» አይነት ጥሪ እስካሁን በይፋ ያለዉ ነገር የለም።በትግራዩ ጦርነት ወቅት የትግራይ ክልልን የሽግግር አስተዳደርን ላጭር ጊዜ የመሩት፣ ኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስር ና አሁን የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚንስትር አብረሐም በላይ ግን ግጭቱ መቀስቀሱን አስታዉቀዋል።
የቃላት ጦርነቱ ተፋፍሟል
ዶክተር አብረሐም ለግጭቱ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤልን ተጠያቂ አድርገዉ «ጦርነት ይብቃ« ብለዋልም። የፌደራሉ መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች፣ በመንግሥት የሚደገፉ የሚመስሉ ወገኖችም በየማሕበራዉ መገናኛ ዘዴዎቹ ሸረሪና ላይ ሥለተደረገዉ ዉጊያ፣ ሥለ መከላከያ ጦር ድል-ገድል ማዥጎደጎዳቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።
ሥለቅዳሜዉ ዉጊያ የህወሓት ጥሪ፣የመንግሥት ዝምታ፣የመንግሥት የካቢኔ አባል ማረጋገጪያና የመንግሥት ደጋፊዎች የቃላት ዘመቻ ቢደጋገም ዉጊያዉ ቢያንስ እስከ ዛሬ የቀጠለ አይመስልም።ከእንግዲሕ ላመቀጠሉ ግን ምንም ዋስትና የለም።አቶ ባይሳ እንደሚሉት ሁለቱም ወገኖች የሚያደርጉት ዝግጅት፣ የገጠሙት የፕሮፓጋዳ ዘመቻ ንረትና የቅራኔዉ ክረት፣ ምናልባት አጠቃላይ ጦርነት መግጠማቸዉ አይቀርም የሚል ሥጋት ማሳደሩ አልቀርም።
«ለአጠቃላይ ጦርነት የተዘጋጁ ይመስላል።እንደምታዉቀዉ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ ትራንስፓረንሲ ስለሌ የመንግሥትም ሆኑ ተቃዋሚ ጋዜጠኞች በቦታዉ ተገኝተዉ ሁኔታዉን መግለፅ ሥለማይችሉ፣ ሞስት ላይክሊ ከሁለቱም ወገኖች በሚወጡ መግለጫዎች ነዉ የምንገመግመዉ። እና ለጦርነት እየተዘጋጁ ይመስላል።»
የረጅም ጊዜዉ ዉዝግብ፣ሽኩቻና ዝግጅት
የቅዳሜዉ ዉጊያም እንግዳ ከሆነ እንግዳ የሚሆነዉ ጊዜና ሥፍራዉ እንጂ በሁለቱ ወገኖች መካከል ጦርነት ሊጫር እንደሚችል ከብዙ ወራት ምናልባትም ከዓመት በፊት ብዙ ተንታኞች ሲያሳስቡ- ሲያስጠነቅቁም ነበር።ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ከታገደበት-እሁለት እስከተከፈለበት፣ አንደኛዉ አንጃ በፌደራሉ መንግሥት ከታቀፈበት፣ «አክራሪ» የሚባለዉ ሌላዉ አንጃ ከኤርትራ መሪዎች ጋር ፅምዶ በሚል ቅንጅት እስከተወዳጀበት የነበሩ ሽኩቻዎች የሥጋት ምልክቶች ነበሩ።
የመቀሌዉ አንጃ -የትግራይን ጊዚያዊ አስተዳደርን አስወግዶ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በአዲስ አበባና በመቀሌዎች መካከል የነበረዉ እሰጥ አገባ፣ የትግራይ ገዢዎች የክልሉን ወጣቶች በግዳጅ ለተዋጊነት መመልመላቸዉም የጦርነቱ ዝግጅት አካል ነዉ።
ተለዋዋጩ የኃይል አሰላለፍና የጦርነት ዝግጅት
ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚደረጉ ግጭቶች፣ የግብፅና የኢትዮጵያ ነባር ጠብ፣ የሱዳኑ ጦርነትም የአዲስ አበባና የመቀሌ ገዢዎችን ጠብ የሚያጋግም ነዉ።ባለፈዉ ሰኔ 30 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ለሐገሪቱ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ህወሓት ከኤርትራ (ሻዕቢያ)፣ ከሱዳን (ምናልባት በጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን) ከሚመራዉ ኃይል ጋርና ከሌሎች በሥም ካልጠቀሷቸዉ ወገኖች ጋር መተባበሩን አስታዉቀዉ ነበር።
«በርካታ የትግራይ ልጆች በጉልበት ታፍሰዉ ሱዳን ላለዉ ጦርነት ተሽጠዋል።TPLF እንደመጥረቢያ ነዉ።መያዣዉ እንጨት እንደ ሻዕቢያ ነዉ።ዋናዉ አዛዦች፣ ባለጉዳዮች ሌሎች ናቸዉ።እንኳን ሻዕቢያና ወያኔና ሱዳን ሌላም ቢጨመር በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ቅንጣት ታክል ሥጋት የለንም።»
ለጠቅላይ ሚንስትሩ ማስጠንቀቂያ ከኤርትራ መልስ የሰጡት የሐገሪቱ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረ መስቀል በX በሰጡት አፀፋ ጠቅላይ ሚንስትሩንና የሚመሩትን ፓርቲ «ዋዣቂ፣ ግራ ቀኝ የሚወዛወዙ------ የሐገር ዉስጥ ችግር ሲያይልባቸዉ በዉጪዎች የሚላክኩ---» በማለት»
የህወሓት ቃል አበይ አቶ ሚካኤል አስገዶም በሰጡት መልስም ፓርቲያቸዉ ከሌሎች ጋር አብሯል የሚለዉን ወቀሳ አስተባብለዋል።ይሁንና ቃል አቀባዩ «የህልዉና አደጋ» ያሉትን ለመከላከል ህወሓት እየተዘጋጀ መሆኑን አረጋግጠዋል።
«የዉስጥ ተቃዉሞዉ እያየለ፣ ሥርዓቱ መቆየት ይፈልጋል፣ በጎረቤት ሐገራትና በተለይም በኛ በህወሓት፣ በትግራይ ህዝብ፣ በትግራይ አመራሮች ማላከክ ይፈልጋል።እንደዚሕ ዓይነት እንቅስቃሴዎች የሉንም።የራሳችንን የህልዉና አደጋ ለመከላከል፣ የራሳችንን ዝግጅት እያደረግን እንደሆን እየገለፅን መጥተናል።»
አሁን «ብቻችንን አይደለንም» የህወሓት ዋና ፀሐፊ
ከሰኔ 30 በኋላ ከህወሐት ያፈነገጠዉ አንጃ አዲስ አበባ ዉስጥ የትግራይ ተወላጆችና ደጋፊዎቻቸዉን «ጦርነት አንፈልግም» በሚል በአደባባይ ሲያሰልፍ፣ መቀሌ ዉስጥ ደግሞ ህወሓት የጠራዉ ተቃራኒ ህዝባዊ ሥብሰባ ተደርጓል።ስልፍና ስብሰባዉ የቃላት ጦርነቱን ወደየደጋፊዎቻቸዉ ለማስረፅ ያለመ መሆኑ አላከራከረም። የህወሐት ዋና ፀሐፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ለትግራይ ወጣቶች «አሁን ብቻችን አይደለንም» ማለታቸዉ ግን ከቃል አቀባያቸዉ አባባል ጋር የሚጣረስ በተገላቢጦሹ የጠቅላይ ሚንስትር አብይን ወቀሳ የሚያረጋግጥ ነዉ።
ከመደበኛ ሥማቸዉ ይልቅ ሞንጆርኖ በሚለዉ ቅፅል ሥም የሚታወቁት ወይዘሮ ፈትለወርቅ
«ባለፉት ጥቂት አመታት ባደረግነዉ ብልሕ ትግል፣ ብልፅግና ፓርቲ በኛ ላይ አዝምቷቸዉ የነበሩ ኃይላት አሁን አሰላለፋቸዉን ቀይረዋል።ባንድ ወቅት በኛ አንፃር ቆመዉ የበሩ (ኃይላት) በሙሉ አሁን የብልፅግና ሥርዓትን ይቃወማሉ።ዛሬ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር በምናደርገዉ ትግል ብቻችንን አይደለንም» ብለዋል።
የኃይል አሰላለፍ መለዋወጥ ለህወሓት፣ ለኢትዮጵያ፣ ለአካባቢዉ ሐገራት፣ ለመላዉ አፍሪቃ፣ ለብዙ ዓለም ፖለቲከኞችም በርግጥ የተለመደ ነዉ።አቶ ባይሳ እንደሚሉት ለጦርነት የሚደረግ ትብብር፣ መደጋገፍና ወዳጅነት የሰዉ ነብስ ከማጥፍ ሌላ ለሕዝብ የሚጠቅመዉ አለመኖሩ እንጂ ድቀቱ።
እስካሁን ግን የአዲስ አበባና የመቀሌ ገዢዎች በጠመንጃ ካልሆነ በቃላት መነጋገር፣ መደራደር፣ መስማማቱንም የፈቀዱት አይመስልም።አንዱ ሌላዉን ካላጠፋ ለአግባቢ መፍትሔ የሚገዙም አልመሰሉም። የመጠፋፋት፣ ፉከራ፣ ዛቻ፣ ግጭቱ ግን በርግጥ ቀጥሏል።ከዚያስ??ቸር ያሰማን
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ