1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የተመድ 78ኛ ጠቅላላ ጉባኤና የዓለም ቀዉስ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ መስከረም 7 2016

ሐዋይ በእሳት፣ ካሊፎርኒያ በአዉሎ ነፋስ፣ ሊቢያ በጎርፍ፣ ግሪክ በእሳትም-በጎርፍም፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኬንያ ከግጭት ጦርነት ባለፍ በድርቅ ሺዎች እያለቁ፣ ሚሊዮኖች እየተራቡ ወይም እየተፈናቃሉ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት በ2015 የነደፈዉ የዘላቂ ልማት ግብ (SDG) እስከ 2030 ድረስ ገቢር ይሆናል ተብሎ ነበር።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ቱተሬሽ ለ78ኛዉ ጉባኤ ንግግር ሲያደርጉ
78ኛዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ሲጀመር ምስል Mike Segar/REUTERS

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤና የዓለም ቀዉስ

This browser does not support the audio element.

ሁለቱ መሪዎች 

78ኛዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ኒዮርክ ዉስጥ ተጀምሯል።የዓለም መሪዎች ወይም ተወካዮቻቸዉ የሚታደሙበት ይሕ ጉባኤ እስከ መጪዉ ሳምንት ድረስ ለስምንት ቀን ይነጋገራል።ጉባኤዉ የሚደረገዉ ጦርነት፣ ረሐብ፣ ድሕነት፣የኑሮ ዉድነትና የዓየር ንብረት ለዉጥ አለቅጥ በከፋበት፣ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ የዓለም ኃያላን ጠብ በናረበት ወቅት ነዉ።ጉባኤተኞች ለተደራራቢዉ አስከፊ የዓለም ቀዉስ መፍትሔ ይጠቁሙ ይሆን? ወይስ ኒዮርኮች በየዓመቱ ጉባኤ ማቅቢያ እንደሚያሽሟጥጡት «መጡ፣ አወሩ፣ ሄዱ» ይባል ይሆን? ጉባኤዉ መነሻ፣ የጉባተኞች ዕቅድ-ጥያቄ ማጣቃሻ፣ የዓለም ዉጥንቅጥ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ያለፈዉ ሳምንት ለዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጥሩ አልነበረም።ወንድ ልጃቸዉ ሐንተር ባይደን ሕገ-ወጥ ጠመጃ ገዝተዋል ወይም ታጥቃዋል ተብለዉ ተከሰሱ።በስልጣን ላይ ያለ ፕሬዝደንት ልጅ ሲከሰስ በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ሐንተር የመጀመሪያዉ ናቸዉ።

ሪፐብሊካን የሚበዙበት የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ኬቪን ማክካርቲይ የባይደን ቤተሰብ «የሙስና ባሕል» ሳይሰፍንበት አይቀርም በሚል ፕሬዝደንቱን ለመክሰሰ ምክር ቤታቸዉ ምርመራ እንደሚያደርግ ያስታወቁትም ባለፈዉ አርብ ነበር።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ተክዘዉምስል Luong Thai Linh/AP Photo/picture alliance

ባይደን  በፖለቲካ እሰጥ-አገባ፣ በቃላት  ፍትጊያ እየጋለች የምትበርደዉን ዋሽግተንን  ትተዉ ትናንት ኒዮርክ ገቡ።እዚያዉ ኒዮርክ ከቤተሰባቸዉ ጋር  የልጅ ልጃቸዉን ልደት ቀለል፣ ገለል መጠን ባለ የእራት ግብዣ አክብረዋል።ማታዉኑ ከወደ ዶሐ-ቀጠር የሰሙት ዜና ደግሞ ባለፈዉ ሳምንት የሆነና የተሞከረባዉን መጥፎ ሁነት ባያካክስ እንኳ «ቸር» ዜና ዓይነት ነበር።

መስተዳድራቸዉ በቀጠር ሸምጋይነት ከቴሕራን ጠላቶቹ ጋር ባደረገዉ ድርድር ኢራን አስራቸዉ የነበሩ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸዉ ተለቀዉ ዛሬ ወደ ሐገራቸዉ ይጓዛሉ።የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ዛሬ በሰጡት መግለጫም ለባይደን መስተዳድር ትንሽ ግን የዲፕሎማሲ ዉጤትን አረጋግጠዋል።

«የእስረኞች ልዉዉጡ ጉዳይ በዚሕ ቀን (ዛሬ) ይፈፀማል።አምስት የኢራን ዜጎች ዛሬ ከዩናይትድ ስቴትስ እስር ቤት ይለቀቃሉ።ባለን ወቅታዊ መረጃ፣ በእስረኞቹ ፍላጎት መሠረት ሁለቱ ዛሬ ወደ እናት ሐገራቸዉ ኢራን ይመለሳሉ።አንደኛዉ ቤተሰቦቹ ዋዳሉበት ወደ ሶስተኛ ሐገር ይሄዳል።»

 

ለባይደን «ቸር ዜና» ለኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሒም ረሱልሳዳቲ (ራሲ) ከምስራችም አልፎ «የድል ብስራት» ብጤ ነዉ።ባለፈዉ ነሐሴ መጀመሪያ በተደረገዉ ስምምነት መሠረት የራሲ መንግስት አምስት የአሜሪካ ዜጎችን ከእስር ፈትቶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አስራቸዉ የነበሩ አምስት የኢራን ዜጎችዋን አስለቅቋል።

«የእስረኞች ልዉዉጥ» በተባለዉ የዋሽግተን-ቴሕራኖች ስምምነት መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ላይ ማዕቀብ ስትጥል በዋሽግተኞች ትዕዛዝ የደቡብ ኮሪያ መሪዎች  አግደዉት ከነበረዉ የኢራን ገንዘብ 6 ቢሊዮን ዶላሩ ዶሐ-ቀጠር ወደሚገኝ ባንክ ተላልፏል።የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ ጠመዝመዝ አድርገዉ ገልፀዉታል።

«የኢራንን ሐብት ዛሬ ሙሉ በሙሉ እንቆጣጠራል የሚል ተስፋ አለን።ገንዘቡ የኢራን እስላማዊት ሪፐብሊክ ባስታወቀችዉ የሒሳብ ቁጥር ባካባቢዉ ወዳለች ወዳጅ ሐገር ይተላለፋል።»

የኢራኑ ዲፕሎማት በግድምድሞሽ የገለጡትን ቀጠር አረጋግጣለች።6 ቢሊዮን ዶላሩ ዶሐ የሚገኝ ግን በስም ያልጠቀሰ ባንክ ገብቷል።

የኢራኑ ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራሲ ባለፈዉ ሳምንት የዲፕሎማሲ ድል አግኝተዋል።ምስል Iran's Presidency/Mohammad Javad Ostad/WANA/REUTERS

ሰላም የናፈቃት ዓለም

የዋሽግተን-ቴሕራኖች ተዘዋዋሪ ስምምነት ለሁለቱ ሐገራት መሪዎች እንደ ዲፕሎማሲያዊ ጥሩ ወይም ድል ቢታይም ለዓለም ሠላም አይደለም የሁለቱን ሐገራት ጠብ ለማርገብም ብዙም የሚተክረዉ የለም።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒ ጉተሬሽ እንዳሉት ደግሞ ዛሬ ማስተናገድ የጀመሩት የድርጅታቸዉ ጠቅላላ ጉባኤ ዋና ዓላማ  ሠላም ማስፈን ነዉ።

«ማዕከላዊ ዓላማዉ ሠላም ነዉ።ሰላም ሲባል ግን ፍትሐዊ መሆን አለበት።የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ደንብ ያከበረ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የሚፀና ሠላም መሆን አለበት።»

ሠላም ግን የለም።ለዓለም ሰላም አለመኖር ትልቁ ዕቅፋት፣ ትልቁ የዓለም ዲፕሎማት እንዳሉት በዩክሬን ጦርነት ሰበብ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ዉጊያ የገጠሙት የኃያላን መንግስታት ጠብ ነዉ።በዓለም ብቸኛ የጋራ ማሕበር በኩል የዓለምን ሠላም ለማስከበር ቃል የገቡት መንግስታት በተለይም በድርጅቱ ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣኑን የያዙት አምስቱ ሐገራት ጥቅማቸዉን ከማስከበር ባለፍ የአብዛኛዉን ዓለም ህዝብ ከጦርነት፣ግጭት፣ስደት፣ረሐብና ድሕነት አላላቀቁትም።የተባበሩት መንግሥታት የአዳጊ አገሮች ስብሰባ

የዓለም የሠላም መዘርዝር የተሰኘዉ ተቋም ባለፈዉ ኃምሌ ባወጣዉ ዘገባ እንዳለዉ ኢትዮጵያ፣ሱዳን፣ዩክሬን፣ እስራኤልና ምያንማርን ጨምሮ 79 ሐገራት በጦርነትና ግጭት ብዙ ሺዎች ይገደሉ፣ መቶ ሺዎች  ይቆስሉ፣ ሚሊዮኖች ይፈናቀሉባቸዋል።በ2023 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከ238 ሺሕ በላይ ሕዝብ ተገድሏል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ጦርነት፣ ግጭትና የተፈጥሮ መቅሰፍት ያሰደደ ወይም ያፈናቀለዉ ሕዝብ ቁጥር ከ100 ሚሊዮን በልጧል።በድርጅቱ ዘገባ መሠረት እስከ መጪዉ ታሕሳስ ድረስ የስደተኛና የተፈናቃዩ ቁጥር ከ117 ሚሊዮን ይበልጣል።

78ኛዉ የተመድ ጉባኤ በሚደረግበት አዳራሽ አካባቢ ድሮኖች የመብራት ትርዒት ሲያደርጉ፤ዓለም እየነደደች ነዉምስል Ed Jones/AFP

በ2011 በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጣልቃ ገብነት ማዕከላዊ መንግስቷ ከፈረሰ ወዲሕ ከግጭት-ሥርዓተ አልበኝነት ያልተላቀቅችዉ ሊቢያ ዘንድሮ የግጭትና የተፈጥሮ መቅሰፍት ቅይጥ ጥፋት አሳዛኝ አብነት ሆናለች።

ትናንት ኒዮርክ አደባባይ የተሰለፉ የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች እንድሚሉት በሠዓታት መቅሰፍት ሺዎች ሕይወት፣ ሐብት፣ ንብረት ኑሯቸዉን ካጡ፣ ዓለም ሰላምነች ማለት ሲበዛ ከባድ ነዉ።

«የዘንድሮዉ በጋ፣ እስካሁን ከተመዘገበዉ የበጋ ዓየር ሁሉ በጣም ሞቃቱ ነዉ።ሊቢያ ዉስጥ ሰሞኑን የሆነዉን ስናይ፣ 11 ሺሕ ሰዎች ሞተዋል።በ24 ሰዓታት ዉስጥ ብቻ 16 ኢንቺ ዝናብ ወርዷል።በየቦታዉ  የጎርፍ፣የእሳት፣ የአዉሎ ነፋስ አደጋ እየደረሰ ነዉ።የዓየር ንብረት ለዉጥ አደጋ ዉስጥ ነን።የዓየር ንብረት ለዉጥ አደጋ ዉስጥ መሆናችንን ፕሬዝደንት ባይደን ማወጅ አለባቸዉ።እርምጃ መዉሰድ አለባቸዉ።»የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ

 

ሐዋይ በእሳት፣ ካሊፎርኒያ በአዉሎ ነፋስ፣ ሊቢያ በጎርፍ፣ ግሪክ በእሳትም-በጎርፍም፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኬንያ በድርቅ ሺዎች እያለቁ፣ ሚሊዮኖች እየተራቡ ወይም እየተፈናቃሉ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሽታ፣ ድሕነት፣ ማይምነትን፣ ለማቃለል የሴትና የልጆች እኩልነትና መብትን ለማስከበር በ2015 የነደፈዉ የዘላቂ ልማት ግብ (SDG) እስከ 2030 ድረስ ገቢር ይሆናል ተብሎ ነበር።የድርቅና የረሐብ ዑደት፤ ቃለ መጠይቅ

የዕቅዱ የግማሽ ዘመን ጉዞ ዘንድሮ ሲገመገም ግን ዓለም ከ2015 የበለጠ ስደተኛ፣ ተፈናቃይና ረሐብተኛ ሰፍሮባትል።የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF ዛሬ ባሰራጨዉ ጥናቱ እንዳስታወቀዉ በSDG ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠዉ የሕፃናትና የልጆችን መብትን የማስከበሩ ዕቅድ በአብዛኛዉ ገቢር አልሆነም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 78ኛ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት ኒዮርክ ዉስጥ የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች ያደረጉት ሰልፍምስል Ron Adar/TheNEWS2/ZUMA/picture alliance

በድርጅቱ ጥናት መሰረት የዕቅዱ ግማሽ ሂደት ዘንድሮ ሲሰላ የዕቅዱ ሐምሳ ከመቶ ከግብ መድረስ ነበረበት።ይሁንና የሕፃናትና የልጆች የመማር፣ የመመገብ፣ የመታከም መብትን በማስከበሩ ሒደት እስካሁን 50 በመቶዉ ከግብ የደረሰላቸዉ በ11 ሐገራት የሚኖሩ 150 ሚሊዮን ሕፃናት ብቻ ናቸዉ።ከ180  ሐገራት የሚበልጡ 3 ቢሊዮን የሚደርሱ ሕፃናትና ልጆች የዕቅዱ ሩብ እንኳን ገቢር አልሆነላቸዉም።

ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ

የሴራሊዮኑ ዋና ሚንስትር ዴቪድ ሞይኒና ያዉ መቼም እንደ ሥልጣን ተጋሪ ሹመኛ ጥሩ ተስፋ አላቸዉ።ዓለም በተለይ የተፈጥሮ መቅሰፍትን ለማቃለልና የልማት ግቡን ከግብ ለማድረስ የቆረጡ መሪዎች አሏት ይላሉ-ሚንስትሩ።

78ኛዉ የተመድ ጉባኤ በሚደረግበት አዳራሽ አካባቢ ድሮኖች የመብራት ትርዒት ሲያደርጉ፤ዓለም እየነደደች ነዉምስል Ed Jones/AFP

«ከግብ የሚያደርሰን አመራር ነዉ።ያጋጠመንን ፈተና የሚረዱ አዳዲስ መሪዎች ያሉንና እያገኘን መሆናችን ይሰማኛል። ጉዳዩን ማጣደፍ እንደሚያስፈልገን የተረዱና ገቢር ለማድረግ የቆረጡ መሪዎች ያሉ ይመስለኛል።እነሱን መደገፍ አለብን።ያኔ ከግብ እንደርሳል።»

ለማየት ያብቃን ከማለት ሌላ-ሌላ የሚመኝ በርግጥ አይኖርም።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እንዳሉት ግን የልማት ግቡን ገቢር ለማድረግ፣ የተፈጥሮ መቅሰፍትን ለመቀነስ፣ የዓየር ንብረት ለዉጥን ለማቃለል፣ ረሐብተኛ፣ ስደተኛና ተፈናቃዩን ለመርዳትም ሆነ ቀዳሚዉ ጉዳይ ሠላም ማስፈን ነዉ።ሠላም ለማስፈን ደግሞ የኃያላኑ ስምምነት ወሳኝ ነዉ።

በዘንድሮዉ ጉባኤ የሚፈለገዉን መቀራረብ፣ ሠላምና ስምምነት ማስፈን መቻሉ ጉተሬሽ እንዳሉት አጠራጣሪ መሆኑ ነዉ-ድቀቱ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ለተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር ሲያደርጉምስል Mike Segar/REUTERS

«እዉነቱን ለመናገር ይሕ ጠቅላላ ጉባኤ ሠላም ለማስፈን በሚረዱ ሐሳቦች ላይ የምር ምክክር እንዲያደርግ ሁኔታዎች የተመቻቹ አይመስለኝም።ባለጉዳዮቹ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከሰላማዊ ምክክር በጣም የራቁ ናቸዉ።ይሁንና ዩክሬን ዉስጥ ሠላም ለማስፈን መጣራችንን ምንጊዜም ቢሆን አናቋርጥም።የዓለም የጆኦፖለቲካዊ ዉጥረት ለመናሩ የዩክሬኑ ጦርነት ዋና ምክንያት ነዉ።የጆኦፖለቲካዊ ዉጥረት መናር ደግሞ ዓለም የገጠሟትን ችግሮች ለማቃለል የምናደርገዉን ጥረት የሚያደናቅፍ ነዉ።»

የዩክሬን ጦርነት በርግጥ የኃያላኑን ጠብ አንሮ-ዓለምን እየከፋፈላት ነዉ።ከዩክሬኑ ጦርነት በላይ ሕዝብ ያለቀዉ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ።የዩክሬኑ ጦርነት ከተጀመረ ዓመት ከመንፈቁ ነዉ።የዓለም የልማት ግብ ከተነደፈ 7 ዓመት ከመንፈቁ።የአፍሪቃ ቀንድን በድርቅ፣እስያን በጎርፍና ናዳ፣ አሜሪካንና  አዉሮጳን በቃጠሎና ጎርፍ የሚያወድመዉን መቅሰፍት ዓለም ማስላት ከጀመረች በትንሽ ግምት 10 ዓመት አስቆጥራለች።የዓመት ከመንፈቁ ጦርነት የዓለም ችግሮች ሁሉ መጀመሪያና መጨረሻ መባሉ ያነጋግራል።ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ሥርየሰደዱ የዓለም ፈተናዎችን ለመፍታት ኃያላኑ ያደረጉትን ጉተሬሽ አለመንገራቸዉ ደግሞ በርግጥ ያስተዛዝባል።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW