1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የተረሳዉ ግን አዉዳሚዉ የሱዳን ጦርነት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2016

ጦርነቱ ርዕሠ ከተማ ካርቱምን በመሰሉ ትላልቅ ከተሞች የተደረገና የሚደረግ በመሆኑም በሰላማዊ ሕዝብ ሕይወት፣ ኑሮና በመሰረተ ልማት አዉታሮች ላይ ያደረሰዉ ጥፋትም ከባድ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ በጦርነቱ በትንሽ ግምት ከ15 ሺሕ በላይ ሰዉ ተገድሏል።ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ አድም ተፈናቅሏል አለያም ተሰድዷል።

ለገሽ ሐገራት ገንዘብ ለመርዳታ ቃል ቢገቡም ጦርነቱ ካልቆመ ለሱዳን ችግረኛ ሕዝብ ርዳታ የሚቀርብበት መነገድ የለም
ለሱዳን ሕዝብ መርጃ 2 ቢሊዮን ዶላር የተዋጣበት የፓሪሱ የለጋሽ ሐገራት ተወካዮች ስብሰባምስል Sarah Meyssonnier/REUTERS

ማሕደረ ዜና፣ የተረሳዉ ግን አዉዳሚዉ የሱዳን ጦርነት

This browser does not support the audio element.

በእስራኤል-ሐማስ፣ በሩሲያ-ዩክሬንና በየተባባሪዎቻቸዉ መካከል በሚደረገዉ ጦርነት የተጠመዱት የአረብ-ምዕራባዉያን ፖለቲከኞች በርግጥ ዘንግተዉታል።የምዕራባዉያን መገናኛ ዘዴዎችም ረሰተዉታል።አምና ሚያዚያ ካርቱም ላይ እንደዘበት የተጫረዉ ጦርነት ግን ያቺን ጥንታዊ፣ ሰፊ አፍሪቃዊ-አረብ ሐገርን እያወደመ፣ያን የዋሕ፣ ዕንግዳ ተቀባይ ደሐ ሕዝብን እየገደለ፣እስራበ፣ በተፈናቃይ ስደተኛ ቁጥር ከዓለም አንደኛ አድርጎታል።የጦርነቱ ዳፋ የአፍሪቃና የዓረብ መንግስታትን የኃይል አሰላለፍ አዘበራርቆ ዛሬም ቀጥሏል።የሱዳን ጦርነት፣ ያደረሰዉ ጥፋት፣የኃይል አሰላለፉ ልዩነትና መፍትሔዉ ያፍታ ዝግታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።

ሱዳናዊዉ ሽማግሌ በሽር አዋድ በቅርቡ ባስተርጓሚ እንዳሉት ኃያሉ ዓለም ለሱዳኖች እልቂት፣ስቃይ ሰቆቃ የሚጠነቅ፣ የሚያስብበት ምክንያት የለም።«እኛ ሰወስተኛዉ ዓለም ነን።የሚያስብልን የለም።»

ሱዳኖች «እጓለ ሙታን መቼ ማልቀስ እንዳለበት ነገሪ አያስፈልገዉም» የሚል አባባል አላቸዉ።የተመቸዉ ዓለም ጩኸታቸዉን ሰማ፣ አስታወሰ-ዘነጋቸዉም ሱዳኖች ማልቀስ፣መቆዘም መጨነቁን አላቆሙም።በቅርቡ ከባልደረቦቿ ጋር ካይሮን የጎበኘችዉ ሱዳናዊቷ የፊልም ተዋኝ ኢማን የሱፍ እንዳለችዉ ዓመት የደፈነዉ ጦርነት ያደረሰና የሚያደርሰዉ ጥፋት ከጦርነቱ የተረፈዉን ሕዝብ ሥነልቡናን እያደቀቀዉ ነዉ።

«የደቡብ ሱዳን መገንጠል ለሱዳን ከፍተኛ ቀዉስ ነዉ ያስከተለዉ።ያሁኑ ጦርነት ሲታከልበት ደግሞ እኔንም ጨምሮ በሱዳን ሕዝብ ላይ ያሳደረዉ ሥነልቡናዊ ቀዉስ ከፍተኛ ነዉ።በጭንቀት ነዉ የምንኖረዉ።»

የሕዝብ የለዉጥ ተስፋና የቀጨዉ ጦርነት

 

ሱዳን 60 ዘመን በዘለቀዉ የነፃነት ታሪኳ መፈንቅለ መንግስት፣ የደቡብ ሱዳን ጦርነት፣ የዳርፉር ጦርነት፣የኮርዶፋን ጦርነት እየተባለ ከፖለቲካዊ ቀዉስ፣ ከግጭት ጦርነት ተላቅቃ አታዉቅም።አምና የተጀመረዉ ጦርነት ግን ለሥርዓት ለዉጥ ባንድ አብረዉ በነበሩ፣ለዉጡን ለመምራት በጋራ በቆሙ ወገኖች መካከል የሚደረግ በመሆኑ ለለዉጥ የታገለዉን ሕዝብ በጎ ተስፋ የቀጨ ነዉ።

ጦርነቱ  ርዕሠ ከተማ ካርቱምን በመሰሉ ትላልቅ ከተሞች የተደረገና የሚደረግ በመሆኑም በሰላማዊ ሕዝብ ሕይወት፣ ኑሮና በመሰረተ ልማት አዉታሮች ላይ ያደረሰዉ ጥፋትም ከባድ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ በጦርነቱ በትንሽ ግምት ከ15 ሺሕ በላይ ሰዉ ተገድሏል።ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ አድም ተፈናቅሏል አለያም ተሰድዷል።

«እጓለ ሙታን ማልቀስ እንዳለበት ነጋሪ አያስፈልገዉም» የሱዳኖች አባባል።በጦርነቱ ወዳጅ ዘመዶቹን ያጣዉ ሕዝብ እያለቀ እየተፈናቀለም ነዉ ምስል Michael Kappeler/picture alliance/dpa

ሰሞኑን የከፋ ጦርነት የሚደረገዉና ምናልባት ከእስካሁኑ የከፋ ጥፋት ያስከትላል ተብሎ የተፈራዉ ዉጊያ አል ፋሽር በተባለችዉ ከተማና አካባቢ የሚደረገዉ ዉጊያ ነዉ።ኤል ፋሽር ከምዕራብ ሱዳን ዳርፉር ግዛት እስካሁን ድረስ በሱዳን መከላከያ ሠራዊት እጅ የምትገኝ ብቸኛ ከተማ ናት።ሌትናንት ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ) የሚያዙት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር የአል ፋሽር ከተማን ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ከብቧል።

የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ RSF ተብሎ የሚጠራዉ ፈጥኖ ደራሽ ጦር ከተማይቱን ከተቆጣጠረ ሌትናንት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን የሚመሩት የሱዳን ጦር ሠራዊት (SAF) ከዳርፉር ግዛት ጠቅልሎ መዉጣቱ ነዉ።

«አል ፋሽር ከዳርፉር አንድ ክፍል ናት።የአንድ አካባቢ ዋና ከተማ ናት።የሐምዲቲ ኃይሎች (ፈጥኖ ደራሽ ጦር) አል ፋሽርን ከተቆጣጠሩ ዳርፉርን በሙሉ እንደተቆጣጠሩ የሚቆጠር ይመስለኛል።»

በ18ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን የያኔዉ የዳርፉር ሡልጣን አብደል ረሕማን መናገሻቸዉን ወደ ፋሽር ወደተባለችዉ ቀበሌ ካዞሩ ወዲሕ ያቺ በረሐማ አካባቢ ከሱዳን ትላልቅ ከተሞች አንዷ ለመሆን በቅታለች።የደቡባዊ ዳርፉር ግዛት ርዕሰ ከተማ ናት።

ዘመናይ ዩኒቨርስቲ፣ በርካታ ትምሕርት ቤቶች፤ ወደ 800 ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ ይኖርባታል።ከሰሐራ በረሐ መሐል ዉኃ ከሚፈልቅባቸዉ ጥቂት አካባቢዎችም አንዷ ናት።የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር እንደ ሚለዉ ካለፈዉ ሚያዚያ መጀመሪያ ጀምሮ አል ፋሽርን ለመያዝና ላለማስያዝ ተፋላሚ ኃይላት ከተማይቱን በአዉሮፕላን ቦምብ፣ በመድፍና ሚሳዬል እየቀጠቀጧት ነዉ።

የኮሚሽነሩ ቃል አቀባይ ሰይፍ ማጋንጎ እንደሚሉት ካየርና ከሩቅ የሚተኮሰዉ መሳሪያ መኖሪያ ቤቶችን  አዉድሟል።በትንሽ ግምት 43 ሰዉ ገድሏል።የከተማዉ ሕዝብ ካካቢዉ መሸሺያም፣ ከዉጪ የሚገባ ርዳታም አያገኝም።

ዓመት ያስቆጠረዉ ጦርነት የተጫረባት የካርቱም ከተማ አዉራ መንገድ ከመኪና መሔጃነት ወደ መኪና መንደጂያነት ተቀይሯል።ምስል El-Tayeb Siddig/REUTERS

«በSAF፣ በRSF እና በየደጋፊዎቻቸዉ ሚሊሻዎች መካከል በሚደረገዉ ዉጊያዉ ሴቶችና ልጆችን ጨምሮ 43 ሰዎች ተገድለዋል።እስካሁን ድረስ SAF በሚቆጣጠራት ብቸኛ ከተማ ሰላማዊ ሰዎች መፈናፈኛ አጥተዋል።ከከተማ እንዳይወጡ እንገደላለን ብለዉ ይፈራሉ።በጦርነቱ ምክንያት የንግድ ሸቀጥም ሆነ ሰብአዊ ርዳታ ወደ ከተማይቱ ሥለማይገባ ሕዝቡ አሳሳቢ ሁኔታ ዉስጥ ነዉ።ፈጥኖ ደራሹ ያሕል በሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች ርዳታ የጫኑ ካሚዮኖች መጓዝ አይችሉም።»

የርዳታ እጦትና የአቅርቦት ችግር

ለወትሮዉ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ የደቡብ ሱዳን፣የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ፣ የሶሪያና የየመን ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎችን የምታስተናግደዉ ሱዳን ባለፈዉ አንድ ዓመት ካጠቃላይ ሕዝቧ ከግማሽ የሚበልጠዉ ለከፋ ችግር ተጋልጧል።ለችግር ከተጋለጠዉ ሕዝብ 18 ሚሊዮኑ አስቸኳይ ሰብአዊ ርዳታ ፈላጊ ነዉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ 4ኛ ወሩን ላገባደደዉ የግሪጎሪያኑ 2024 ብቻ ለሱዳን ሕዝብ መርጃ 2.17 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል።ባለፈዉ ሚያዚያ አጋማሽ ፓሪስ ላይ የተሰበሰቡ ለጋሽ ሐገራት ለሱዳን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለመርዳት ቃል ገብተዋል።ይሁንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ለጋሽ ተቋማት እንደሚሉት ርዳታዉ ቢገኝ እንኳ ጦርነት እየተደረገ ሰብአዊ ርዳታ ማቀበል እይቻልም።

ተፋላሚ ኃይላት ዉጊያዉን እንዲያቆሙ የሚደረገዉ ጥሪና ግፊት አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት ባለፈዉ ቅዳሜ ተፋላሚዎች ዉጊያ አቁመዉ እንዲራደሩ እስካሁን የሚደረገዉን ጥሪ በድጋሚ አሰምተዋል።

የተኩስ አቁሙ ጥሪ፣ ጥያቄ፤ ማሳሰቢያና ጂዳና ካምፓላን በመሳሰሉ ከተሞች የተሞከረዉ ድርድር ከአደረጉ ወይም አሉ ከማሰኘት አልፎ ጠንከር ባለማለቱ እስካሁን ያመጣዉ ዉጤት የለም።የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን እንደሚሉት ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ሌሎች የአረብ ሐገራት ለየተፋላሚዎቹ ሐገራት የሚሰጡት ድጋፍ የሰላም ጥሪና ጥረቱን እያደናቀፈዉ ነዉ።

«ግብፅ፤ ሳዑዲ አረቢያም ሆነች የተባበሩት አረብ ኢማራት ከጦርነቱ መጀመሪያ ጀምሮ ነዉ አንዱን ወይም ሌላዉን ወገን ሲያግዙ የነበሩት ግብፅ ከማን ጋር እንደሆነች ብዙም የሚያከራክር አልነበረም።አል ቡርሐን ከሚመሩት ከሱዳን መንግስት ወይም ወታደሮች ጎን ነኝ።ሳዑዲ አረቢያም በጂዳዉ ድርድር ዋና አደራዳሪ ብትሆንም ከግብፅ የተለየ አቋም አልነበራትም።የተባበሩት አረብ ኢማራቶቹ ነዉ ለየት ያለዉ።የሐምዲቲ ኃይሎችን በተለያየ ሁኔታ ሥትረዳ ቆይታለች።»

ዉጊያ የሚደረግበትን አካባቢ ጥለዉ ለመሸሽ ሲሞክሩ አቅም አጥተዉ የተቀመጡ አባትምስል AFP/Getty Images

የጠላትሕ ጠላት ---መርሕ የኃይል አሰላለፍ

የሱዳኑ ጦርነት የምሥራቅ አፍሪቃ መንግስታትን በተለይም ራስዋ ሱዳን መሥራች አባል የሆነችበት የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን የ(ኢጋድ) አባል ሐገራትንም አሰላለፍ ከፍሎታል።ተንታኖች እንደሚሉት ኬንያ፣ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳንና ኤርትራን  የመሳሰሉ የባለስልጣናቱ አባል መንግስታት አል ቡርሐን ከሚመራዉ ወታደራዊ መንግስት ይልቅ ዳጋሎ ለሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ጦር ያዳላሉ።

ጅቡቲና ሶማሊያን የመሳሰሉ የኢጋድ አባል መንግስታት እስካሁን አንድም ራሳቸዉን ገለልተኛ ለማድረግ እየጣሩ ነዉ፣ ሁለትም የካይሮና የሪያድን አቋም እያጤኑና እያጠኑ አሰላለፋቸዉን ይቀያይራሉ።

አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የዉጪ መንግስታት በተለይም የአፍሪቃ ሐገራት የኃይል አሰላለፍ ለመከፋፈሉ፣ ለጦርነቱ እልባት ለማግኘት የሚደረገዉ ጥረት ለመዳከሙም አንዱ ምክንያት ከየተዋጊዎቹ ጀርባ ያሉት የሱዳን ፖለቲከኞችና ማሕበራት አቋም መቃረን ነዉ።ብዙዎች ዓመት የዘለቀዉን ጦርነት የሁለት ጄኔራሎች የሥልጣን ሽኩቻ ዉጤት አድርገዉ ያቀርቡታል።የሁለቱ ጄኔራሎች ጠብ ለጦርነቱ መጫር ሰበብ አልሆነም ማለት በርግጥ ያሳስታል።

ይሁንና  ጠቡን ወደ አዉድሚ ጦርነት ለማቀጣጠል «ቤንዚን» የሆነዉ ከሁለቱ ጄኔራሎች ጀርባ ያሉት የኃይማኖት፣ የፖለቲካና የማሕበረሰብ አስተሳሰቦች ናቸዉ።አቶ ዩሱፍ «የርዕዮተ ዓለም ልዩነት» ይሉታል።በጥቅሉ እሁለት ከሚከፈሉት ኃይላት አንዱና ቀዳሚዉ በዘመነ አል በሽር ለካርቱም ፖለቲካዊ ጉዞ ጎዳና ይቀይሱ የነበሩት አፍቃሬ ሸሪዓና የሙስሊም ወንድማማቾችን መርሕ የሚጋሩት የኃይማኖትና የፖለቲካ ኃይላት ናቸዉ።እነዚሕ ኃይላት የጄኔራል አል ቡርሐንን ጎራ ይደግፋሉ።

ሁለተኞቹ የአል በሽርን ሥርዓት ለማስወገድ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉት አንዳዶች «ዴሞክራሲያዉያን ኃይላት» የሚሏቸዉ የተለያዩ የሙያ ማሕበራት፣ አቀንቃኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸዉ።60 ማሕበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያሰባስበዉ ይሕ ኃይል በቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር በአብደላ ሐምዶክ ይመራል።

ስብስቡ ለዉጡን ያደናቀፈዉ የጄኔራል አል ቡርሐን ኃይል ነዉ ብሎ ስለሚያምን፣ «የጠላትሕ ጠላት ወዳጅሕ ነዉ» በሚል ፖለቲካዊ ስሌት የጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ፈጠኖ ደራሽ ጦርን ድልን ይናፍቃሉ። ዶክተር ሐምዶክና ጄኔራል ዳጋሎ ባለፈዉ ጥር አዲስ አበባ ዉስጥ ስምምነት እስከመፈራረምም ደርሰዋል።እንደገና አቶ ዩሱፍ

የቀድሞዉ ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታሕ አልሲሲና ተከታዮቻቸዉ የግብፅን የመሪነት ሥልጣን የያዙና  ያጠናከሩት የግብፅ ሙስሊም ወድማማቾ ማሕበር መሪዎችን በመፈንቅለ መንግስት አስወገደዉ፣አስረዉ፣ ገድለዉ፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸዉን ባደባባይ ጨፍጭፈዉ ነዉ።ግብፅ ላይ የሚያጠፉ፣የሚያሳድዷቸዉን  የሙስሊም ወንድማማቾች ኃይላትን ወይም ደጋፊዎቻቸዉን ካርቱም ላይ የሚደግፉበት ፖለቲካዊ ምክንያትና ጥቅምን አንጥሮ ማግኘት በርግጥ ግራ አጋቢ ነዉ።

የሱዳን ሕዝብ ዉጊያ የሚደረግባቸዉን አካባቢዎች እየለቀቀ እግሩ ወደመራዉ በገፍ ይሰደዳል ወይም ይፈናቀላልምስል LUIS TATO/AFP

ከኢጋድ አባል ሐገራት መካከል አንዳዶቹ ወደ ፈጥኖ ደራሹ ኃይል የማጋደላቸዉ ምክንያት ግን በአል ቡርሐን በኩል የአልበሽር ሥርዓት መልኩን ቀይሮ ዳግም እንዳይጠናከር ከመፈለግ፣ከመፍራት ወይም የሱዳን ለዉጥ ፈላጊ ኃይላትን ከመደገፍ የመነጨ ነዉ ቢባል ያስኬዳል።

በልማዱ አለም አቀፍ ማሕበረሰብ የሚባለዉ ኃያሉ ዓለም፣ የአፍሪቃም ሆኑ የአረብ መንግስታት ሱዳን ዉስጥ ትክክለኛ ሰላም ማስፈን ከፈለጉ ቀጥታ ከሚፋለሙት ኃይላት እኩል ተፋላሚዎቹን ከጀርባ የሚዘዉሩ ኃያላትን በሙሉ ያሳተፈ ድርድር ማድረግ አስፈላጊ ነዉ።ጦርነቱ ፈጥኖ ካልቆመ አሁን ቻድ ዉስጥ  የተያዉ የጦር መሳሪያ ማስተላለፍ፣ የሱዳን ፖለቲካ ቡድናት ማቆጥቆጥና የስደተኞች መጨናነቅ ብዙዎች እንደሚሉት ሌሎቹን ያካባቢዉን ሐገራት ማዳረሱ አይቀርም።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW