ማሕደረ ዜና፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርሕና 79ኛዉ ጉባኤ
ሰኞ፣ መስከረም 13 2017
ሁለተኛዉና የዓለም በተባለዉ ከባድ ጦርነት የወደመችዉ ዓለም አስከሬኗን ቀብራ፣ፍርስራሽ፣ትቢያዋን አራግፋ አዲስ ድርጅት መሠረተች።ለሠላም፣እኩልነት፣ ለፍትሕ የቆመ የዓለም ማሕበር።ደንቡንም አፀደቀ።ነሐሴ 26፣ 1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሳንፍራንሲስኮ-ዩናይትድ ስቴትስ።ለድርጅቱ መመሥረት አበክራ የጣረችዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን ሐገራቸዉን ጨምሮ ጉልበተኞችን አደራ አሉ።
«ኃይልና ጥንካሬ ጦርነት ለመክፈት ሳይሆን የዓለምን ሠላም ለመጠበቅ፣የጦርነት ሥጋትን ለማስወገድ መዋል አለበት።የዓለም ኃያላን መንግሥታት ለዓለም አቀፍ ፍትሕ መከበር አብነት ሊሆኑ ይገባል።የዚሕ ደንብ መሠረት የዚያ የፍትሕ መርሕ ነዉ።»
ዘንድሮ 79ኛ ዓመቱ።ዓለም በርግጥ ሰላም ነች? ኃያላንስ ለፍትሕ ቆመዋል?የግዙፉ ድርጅት ደንብስ ተከብሯል? ብዙ ጥያቄዎች።የሰላም፣ ፍትሕ፣ እኩልነት መጥፋት፣የኃያላን ምግባር የሚያሳስበዉ ወገን በመልስ የለሽ ጥያቄዎች ሲብሰለሰል-የዓለም መሪዎች ለ79ኛ ጊዜ ጉባኤ ተቀምጠዋል።ትናንት።ጉባኤዉ መነሻ፣ የድርጅቱ ዓላማ ማጣቃሻ፣ ጥያቄዎቹ መድረሻችን ናቸዉ።
አንዳዶች የሐገራት መሪዎች ኒዮርክ ቅምጥል ሆቴሎች ዉስጥ የሚንደላቀቁ፣ የሚቀብጡ፣ የሚገባበዙበት ዓመታዊ ድግስ ይሉታል።መሪዎች ላጭር ጊዜም ቢሆን ለዓለም የልባቸዉን የሚናገሩበት አጋጣሚ የሚሉትም አሉ።የደካማ-ድሆቹ ሐገራት መሪዎች የኃያላን-ሐብታሞቹን ድጋፍና ርጥባን ለማግኘት የሚሻሙበት ሥብሰባ ባዮችም አሉ።ብዙዎች ግን ሐብትና የፖለቲካ ሥልጣን የሌላቸዉ ለዓለም ፍትሕ፣ ለሰላም መከበር ድምፃቸዉን የሚያሰሙበት እንዲሆን ይመኛሉ።ሌሎች ሌላ።ጉባኤዉ በርግጥ ሁሉንም ነዉ።ትናንት በይፋ ተጀምሯል።
«በሩን ከፍተናል።ሁላችሁም ግቡበት» ጉተሬሽ
ጉባኤተኞች ትናንት ዉሏቸዉን «ሥምምነት ለወደፊቱ» የተባለዉን ሰነድ አፅድቀዋል።የሐሳቡ አመንጪና አርቃቂዎች እንደሚሉት በ42 ገፅ የተጠረዘዉ ሰነድ ዓለም በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የገጠማትን ፈተናዎች ለማስወገድ ያለመ ነዉ።ከዓየር ንብረት ለዉጥ እስከ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ከተደጋጋሚ ግጭቶች አለቅጥ እስከ እስከሰፋዉ የሐብታም ድሆች ልዩነት የሚጠቀሱ ችግሮችን ለማቃለል ይረዳል ተብሏል።
የሐሳቡ አፍላቂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ናቸዉ።ሰነዱን ያዘጋጀዉ ደግሞ ጀርመንና ናሚቢያ በጋራ የመሩት ኮሚቴ ነዉ።በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላት ሩሲያ ግን ሰነዱ መሻሻል አለበት በሚል ዉድቅ አድርጋዋለች።የሰነዱ ይዘት በአባል ሐገራት ዘንድ መከፋፈል ይፈጥራል ብለዉ የሰጉት ጉተሬሽ ሰነዱ ከመፅደቁ በፊት ሶስት ዓይነት ንግግር አዘጋጅተዉ ነበር።
የጉተሬሽ ቃል አቀባይ እንዳሉት ከተዘጋጁት ንግግሮች የመጀመሪያዉ ሠነዱ-ከፀደቀ፤ ሁለተኛዉ ካልፀደቀ፣ ሶስተኛዉ -«ግልፅ አይደለም» ከተባለ የሚደረግ ነበር።ሠነዱ ፀደቀ።የዓለም ትልቅ ዲፕሎማት ተደሰቱ።«በሩን ከፈትን» አሉም-ግቡበት።
«በሩን ከፍተናል።ከእንግዲሕ በበሩ መግባት የሁላችንም ፈንታ ነዉ።ምክንያቱም ይሕ አንዳችን ሌላችንን ሥለመገንዘብ አይደለም።እርምጃ ሥለመዉሰድ ጭምርም እንጂ።ዛሬ እርምጃ እንዲትወስዱ አሳስባለሁ።»
የወደፊቱ ሰነድ ዘንድሮ ፀደቀ።ብዙዎች እንዳሉት መፅደቁ ጥሩ ነዉ።8 ቢሊዮን የሚገመተዉ የዓለም ሕዝብ እስካሁንና አሁን የገጠመዉን ፈተና የሚያቃልል፣ በጦርነት፣ረሐብ፣በሽታና ድሕነት የሚያልቅ፣ የምትደፈር፣ የሚሰደደዉን ሕዝብ የሚያድን እርማጃ አለመሆኑ እንጂ ቀቢፀ ተስፋዉ።
የምጣኔ ሐብትና የሰላም ተቋም የተባለዉ የአሜሪካ አጥኚ ድርጅት እንደዘገበዉ 56 ሐገራት በጦርነትና ግጭት እየወደሙ ነዉ።የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ማይክል ኮንስ እንዳሉት በየጦርነት ግጭቱ 92 ሐገራት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ይሳተፋሉ።
«ባሁኑ ወቅት በ56 ሐገራት ዉስጥ ግጭት ይደረጋል።ባለፈዉ ዓመት 92 ሐገራት ከየሐገራቸዉ ዉጪ በሚደረጉ ግጭቶች ተካፍለዋል።በሌላ አባባል ጦርነትና ግጭት ዉስጥ የሚካፈሉ መንግሥታትን ወይም ለሥልጣን የሚዋጉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ኃይላትን ይደግፋሉ።»
ከጋዛ-ሊባኖስ-እስራኤል እስከ ዩክሬን፣ ከኮንጎ እስከ ምያንማር፣ ከሱዳን እስከ አፍቃኒስታን፣ ከየመን እስከ ማሊ፣ ከሶሪያ እስከ ኢትዮጵያ ሌሎችም እንድም በርስበርስ አለያም በድንበር ተሻጋሪ ጦርነት፣ ግጭትና ሥርዓተ አልበኝነት መቶ ሺዎች ያልቁባቸዋል።ሚሊዮኖች ይሰደዱ ወይም ይፈናቀሉባቸዋል።
የ3ኛዉ የዓለም ጦርነት ሥጋት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ በየጦርነት፣ግጭቱ መቶ ሺዎች ረግፈዋል።ሴቶችና ልጃገረዶች ይደፈራሉ።ትምሕርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ይወድማሉ።ጦርነት፣ ጭቆና፣ ረሐብና ድሕነት ያሰደደና ያፈናቀለዉ ሕዝብ 120 ሚሊዮን ደርሷል።
ሁለተኛዉና የዓለም በሚባለዉ ጦርነት የተካፈሉት ሐገራት ቁጥር 70 ነበሩ።የአሜሪካዉ አጥኚ ተቋም እንዳለዉ ዘንድሮ ከ193ቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል መንግሥታት 56ቱ ዉጊያ ላይ ናቸዉ።92ቱ ሌላ ሐገር በሚደረግ ጦርነት ወይም ግጭት ይካፈላሉ።ማን ቀረ? ጦርነቶቹ የዓለም የሚባሉትስ ማን እና እንዴት ሲዋጋ ነዉ የሚሉ ጥያቄዎች አጭረዋል።ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ተስፋ አልቆረጡም።
«እንደሚመስለኝ ወደ ሶስተኛዉ የዓለም ጦርነት የሚያስገቡ ርምጃዎችን ለማስወገድ ተገቢዉ ሰዓት ላይ ነን።የምናየዉ ተጠያቂነት በሌለበት ስሜት ግጭቶች መበራከታቸዉን ነዉ።የተጠያቂነት ስሜት የጎደለዉ፣ የዓለም ጦርነትን ሊጭሩ በሚችሉ ትላልቅ ኃይላት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ጋ ማን ይጠይቀኛል የሚል ስሜት እየታየ ነዉ።»
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደንብ ገቢራዊነት
አምናና ዘንድሮ ዓለም ከጋዛ-እስራኤል እስከ ዩክሬን-ሩሲያ እንደታዘበዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጠቅላላ ጉባኤዉን፣ የፀጥታ ምክር ቤቱን ዉሳኔዎች፣ደንቦች፣ የራሱን ፍርድ ቤት ብይን ማስከበር ቀርቶ ራሱ ድርጅቱ የቀጠራቸዉን ሠራተኞቹን ሕይወት ማዳን፣ አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ወይም ማስቀጣት አልቻለም።
እስራኤል በፍልስጤም ግዛት ጋዛ ላይ በከፈተችዉ መጠነሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ብቻ 200 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ተገድለዋል።አብዛኞቹ UNRWA በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ ፍልስጤሞችን የሚረዳ የተባበሩት መንግሥታት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ባልደረቦች ነበሩ።ጉተሬሽ ባለፈዉ ሳምንት ለጋዜጠኞች እንደነገሩት የድርጅቱ ሠራተኞች መገደላቸዉን «የማይታገሱት» ብለዉታል።
«የኡንርዋ ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች ድርጅቶት አባላት የነበሩ 200 ሠራተኞች በጦርነት ሰበብ ሲገደሉ ይሕ ፈፅሞ ሊታገሱት አይገባም።ይሕ ዉጤታማ ተጠያቂነት ያስፈልገዋል።»
የተባበሩት መንሥታት ድርጅትእንደየትኛዉም ማሕበር የአባላቱን ስምምነት፣ ፍላጎትና ዉሳኔን የሚያስፈፅም፣ በባላት መዋጮ የሚተዳደር ማበር ነዉ።ማሕበሩን የመሠረቱት ከ79ኝ ዓመታት በፊት እንዳሉት የማሕበሩ መሠረታዊ ዓላማዎች የዓለምን ሠላም፣ፍትሕ፣ የሰዎችን እኩልነት ማስከበር ነዉ።ይሕ ዓላማዉ ገቢር የሚሆነዉ አባል መንግሥታት በተለይ ኃያላኑ ያኔ ላፀደቁት ደንብ ወይም ቻርተር በመገዛታቸዉ ልክ ነዉ።
«ከጥቂት ዓመታት በፊት ይሕ ደንብ ኖሮን ቢሆን፣ ደንቡን ገቢር የማድረግ ፅናት ኖሮን ቢሆን ኖሩ እስካሁን የሞቱ ሚሊዮኖች በሕይወት ይኖሩ ነበር።ወደፊት ደንቡን ገቢር የማድረግ ፍላጎታችንን ካጠፍን ደግሞ አሁን በሕይወት ያሉ ሚሊዮኖች ይሞታሉ።»
ሐሪ ኤስ ትሩማን።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንትበ1945።
ትሩማን ያደነቁ፣ ያንቆለጳጰሱት ደንብ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነትን ያሸነፉት አምስት መንግሥታት ዓለምን ባሻቸዉ እንዲዘዉሩ ልዩ የፖለቲካ-ዲፕሎማሲ ስልጣን ስለሚሰጥ ደንቡ እንዲሻሻል፣ የዓለም አቀፉ ድርጅት አወቃቀርም እንዲለወጥ በርካታ መንግሥታት ከረጅም ጊዜ በፊት እየጠየቁ ነዉ።
ጥያቄዉ ፈጣን መልስ ባለማግኘቱ የተበሳጩት የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ በ2009፣ የደንቡን ቅጂ ቀደዉ አሽቀንጥረዉ ጥለዉታል።ብዙ አልቆየም ቃዛፊም በገዛ ሐገራቸዉ በምዕራባዉያኑ የጦር ተሻራኪ ድርጅት ኔቶ የሚደገፉ ጠላቶቻቸዉ ቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ጭንቅላታቸዉን በርቅሰዉ ገደሏቸዉ።ሊቢያም ከሐብታም፣ሰላማዊ፣ ሥልጡን ሐገርነት ወደ ወርሮበሎች መፈንጫነት ተለዉጣለች።
የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኢርዳን ደግሞ ባለፈዉ ግንቦት የዚያን መከረኛ ደንብ ቅጂ በጫጭቀዉታል። እንደጠላት የሚተያዩት የሊቢያና የእስራኤል ባለሥልጣናት ትሩማን ያደነቁ፣ በ50 ሐገራት ያስፀደቁትን ደንብ የቀደዱት ተቃራኒ ፍላጎታቸዉን አላስከበረም በሚል ነዉ።
ደንቡ በፀደቀ በ79ኛ ዓመቱ ዘንድሮ በሚደረገዉ ጉባኤ ላይ የ130 ሐገራት መሪዎች ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።ንግግር፣ መግለጫ፣ዉሳኔዉ፣ ስምምነቱ ግን የጉልበተኞችን ማንአሕሎኝነት ማረቅ መቻሉ፣ የዓለምን ምሥቅልቅል ለማቃለል መጥቀሙ ወይም ጉተሬሽ «ተከፈተ» ባሉት በር የሚገባ መገኘቱ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።
የ79ኝ ዓመቱ አዛዉንት ግዙፍ ድርጅትም የጉልበተኛ-ቱጃር አባላቱን ፍቃድ እሥኪያገኝ ድረስ አስከሬን-ቁስለኛ ከመቁጠር፣ ረሐብተኛ-ስደተኛ ከማስላት ከማስላት ሊላቀቅ አይችልም።
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ