ማሕደረ ዜና፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ80 ዓመት አዛዉንት ወይስ ጨቅላ?
ሰኞ፣ መስከረም 12 2018
መሥራቾቹ እንዳሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓብይ ዓላማ መተዳደሪያ ደንቡም የዓለምን ሠላም በጋራ ማስከበር ነዉ።ሰኔ 26፣ 1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) መተዳደሪያ ደንቡ ወይም ቻርተሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ያኔ አባል በነበሩት 50 ሐገራት ፀደቀ።በዚያዉ ዓመት ጥቅምት ድርጅቱ በይፋ ተመሠረተ።ዘንድሮ 80 ዓመቱ።የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የድርጅቱን የ80 ዓመት ጉዞ «ጦርነት የተገታበት፣ ልጆች የመማር፣ ሕሙማን የመታከም ዕድል ያገኙበት» ይሉታል» በእርግጥ እንዲያ ነበር?።ላፍታ እንጠይቅ?
የጦርነት ማግሥቱ ጦርነት ዉድመት
መጀመሪያ ጦርነት ነበር።ጦርነቱም ሁለት ነበር።አዉሮጳ ላይ በ25 ዓመት ልዩነት ሁለቴ የተቀጣጠለዉ ጦርነት ከ70 ሚሊዮን እስከ 90 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ፈጅቷል።ብዙ መቶ ሚሊዮኖችን አሰድዷል፣ የሐገራት ድንበሮችን አለዋዉጧል።ከመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት እልቂት የተማረ መስሎ የነበረዉ ኃያሉ ዓለም የጋራ ማሕበር መሥርቶ ነበር።ሊጎ ኦፍ ኔሽንስ-የመንግሥታት ማሕበር።
የማሕበሩ መስራች ኢጣሊያ የማሕበሩ አባል የሆነችዉን ኢትዮጵያን በ1935 ለሁለተኛ ጊዜ ሥትወር ብሪታንያና ፈረንሳይን የመሳሰሉ የዘመኑ ልዕለ ኃያላን ወራሪዋን መደገፋቸዉ ማሕበሩ አዉሮጳ ላይ ሥርየሰደደዉ የኃያል-ደካሞች፣ የነጭ-ጥቁሮች ተባለጥ አስተሳደብ ማስፈፀሚያ መሆኑን አስመሰከሩ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሥረት፤ የኃላን ተስፋና ቃል
ብዙም ሳይቆይ አዉሮጶች ራሳቸዉ ለሁለት ተገመስዉ ዳግም ዉጊያ ገጠሙ።ዓለምምንም ከጦርነቱ መሠጉት-ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት።ማሕበሩም ፈረሰ።በጦርነቱ ትቢያ ላይ ዓለም ሁለተኛዉን የጋራ ማሕበር መሠረተ።መተዳደሪያ ደንቡንም አፀደቀ።ሰኔ 26፣ 1945።ሳንፍራንሲስኮ-ዩናይትድ ስቴት።
«በዘር፣ በ,ኃይማኖት፣ በቋንቃና ባሕል በጣም በሚለያዩት በእነዚሕ 50 ሐገራት መካከል ሥምምነት መደረጉን የሚጠራጠሩ ብዙ (ሰዎች) ነበሩ።ይሁንና እነዚሕ ልዩነቶች ጦርነት የሚቆምበትን መንገድ በመፈለግ በአንድ በማይናወጥ ፅኑ ዉሳኔ ተሻሩ።»
የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን።ቻርተሩ የፀደቀበት 80ኛ ዓመት ባለፈዉ ሰኔ ሲዘከር የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ዓለም «በጦርነት አመድ ላይ የተስፋ ፍሬ ዘራ» ብለዉታል።ጥር 10፣ 1946።ለንደን። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤ ተደረገ።ጉባኤተኞች በተለይ የዓለም ኃያላን በጦርነት አመድ ላይ የምትዳክረዉ ዓለም ለሰላም ስርፀት አበክራ እንደምትጥር ተስፋ ሰጥተዉ፣ ቃል ገብተዉም ነበር።
የጉባኤዉ አስተናጋጅ የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ክሌሜንት አትሌ። «እዚሕ የተሰበሰቡት መልዕክተኞች ወደዚሕ የመጡት (ሰላም የማስፈን) ዉሳኔ መንፈስን ብቻ ሳይሆን የተስፋ መንፈስንም ይዘዉ ነዉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።አምናለሁም።»
«የሰዉ ልጅ ከተባበረ ሰላም ማስፈን እንደሚቻል የሚያረጋግጥ አንድ ደንብ፣ አንድ ርዕይ፣ አንድ ቃል።» አሉት ጉተሬሽ-ባለፈዉ ሰኔ።
የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ኮሚሽንና የኑክሌር ጦር መሳሪ እሽቅድምድም
ቱርማን «የማይናወጥ» ያሉት፣አትሌ ተስፋና እምነት የጣሉበት ሰላም የማስፈን ፅናት፣ጉተሬሽ የጠቀሱት የሰዉ ልጅ የጋራ ርዕይ፣ቃልና ደንብ ገቢር ሆኖ ይሆን? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጀመሪያ ካሳለፋቸዉ ትላልቅ ዉሳኔዎች ቀዳሚዉ የድርጅቱ የአቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ ኮሚሽን እንዲመሠረት ያፀደቀዉ ደንብ ነዉ።
ጥር 24፣ 1946 በፀደቀዉ ዉሳኔ ቁጥር 1 እዝባር 1 መሰረት የተመሠረተዉ ኮሚሽን መንግስታት የአቶሚክ ጦር መሳሪያ እንዳያመርቱ፣ የተመረተዉም እንዲጠፋና የአቶሚክ ኃይል ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ እንዲዉል የማድረግ ኃላፊነት አለበት።ኮሚሽኑ ሲመሠረት የአቶሚ ጦር መሳሪያ ያላት አንዲት ሐገር ብቻ ነበረች።ዩናይትድ ስቴትስ።
ኮሚሽኑ በተመሠረተ በሶስተኛዉ ዓመት በ1949 ሶቭየት ሕብረት አዉዳሚዉን ጦር መሳሪያ በመታጠቅ ሁለተኛ ሐገር ሆነች።በ1952 ብሪታንያ፣ በ1960 ፈረንሳይ፣ በ1964 ቻይና፣ በ1974 ሕንድ፣በ1998 ፓኪስታን፣ በ2006 ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ እንዳላቸዉ ተረጋግጧል።እስራኤል ከ1960 እስከ 1979 በነበረዉ ጊዜ ኑክሌር ቦምብ ማምረቷ ይታመናል።
የእስራኤል መሪዎች ግን ሐገራቸዉ አዉዳሚዉን ጦር መሳሪያ መታጠቅ-አለመታጠቋን እስካሁን በይፋ አላስታወቁም።79 ዓመት የደፈነዉ የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ኮሚሽንም እስራኤል አስፈሪዉን ቦምብ መታጠቅ-አለመታጠቋን ለማረጋገጥ ያደረገዉ ጥረት፣ ፍተሻና ምርመራ በግልፅ አይታወቅም።
ታወቀም-አልታወቀ ኮሚሽኑ ሲመሠረት አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ታጥቃዉ የነበረዉን አዉዳሚ ጦር መሳሪያ ዛሬ እስራኤልን ጨምሮ ዘጠኝ ሐገራት ታጥቀዉታል።የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ኮሚሽን የተለያዩ ሐገራት የኑክሌር መርሐ-ግብራቸዉን እንዲያቆሙ መጠየቅ፣ ግፊት ማድረግ፣ የምዕራባዉያን ጠላት በሚባሉት እንደ ሰሜን ኮሪያና ኢራንን የመሳሰሉትን ደግሞ በማዕቀብ ማስቀጣቱ አልቀረም።
ደቡብ አፍሪቃ፣ የኑክሌር ቦምብ አምርታ ያጠፋች ብቸኛ ሐገር
እስካሁን ድረስ የሠራችዉን የኑክሌር ቦምብ ያጠፋቸዉ ግን አንዲት ሐገር ናት።ደቡብ አፍሪቃ።አፍሪቃዊቱ ሐገር ታጥቃዉ የነበረዉን ቦምብ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ያጠፋቸዉ አንዳዶች እንደሚሉት ጥቁሮች ሥልጣን መያዛቸዉ ሥለተረጋገጠ ኑክሌሩን እንዳይቆጣጠሩት ለማድረግ ነዉ። የደቡብ አፍሪቃ የነጭ ዘረኞች የመጨረሻ ፕሬዝደንት ፍሬድሪክ ዊሊያም ደ ክላርክ እንዳሉት ግን ሶቭየት ሕብረት በመፈራረሷ ነዉ።
«የነበረን ቦምብ የተሠራዉ ሌሎችን ለማጥቃት ሳይሆን የሚደርስብንን ጥቃት ለመከላከል ነበር።እኔ ፕሬዝደንት ስሆን በደቡብ አፍሪቃ ላይ የነበረዉ ወታደራዊ ሥጋት ተለዉጠ።መጀመሪያ የተለወጠዉ ኮሚንዝም በመፍረሱ ነዉ።እስከዚያ ጊዜ ድረስ የዓለም ኃያል ሐገር የነበረችዉ የሶቭየት ሶሻሊስት ሪፐብሊኮች ሕብረት (USSR) በደቡባዊ አፍሪቃ የምትከተለዉ መርሕ ወታደራዊ መስፋፋት ነበር።እዚሕ ያለዉን የማዕድን ሐብትና ሥልታዊ አቀማመጣችንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መቆጣጠር ትፈልግ ነበር።»
ደቡብ አፍሪቃ የኑክሌር ቦምቧን ያጠፋችዉ አንድም ተጠራጣሪዎች እንዳሉት ቦምቡ ከጥቁሮች እጅ እንዳይገባም ሊሆን-ሁለትም ደ ክላክ እንዳሉት የሶቭየት ሕብረት ሥጋት በመወገዱ ሊሆን ይችላል።ሁለቱም ምክንያት-ሆነ አንዱ አዉቶሚክ እንዳይመረት፣ የተመረተዉም እንዲጠፋ ኃላፊነት የተሰጠዉ ኮሚሽን ባደረገዉ ጥረትና ግፊት እንዳልሆነ ግን ግልፅ ነዉ።
የኑክሌር ቦምብ ታጣቂዎች ብዛት ለሰላም ፈይዶ ይሆን?
ዓለም ከአንድ ሐገር የአቶሚክ ሥጋት ወደ ዘጠኝ ሐገራት የኑክሌር ሥጋትና ፍጥጫ ያደገችበት 80 ዓመት የሰላም ዘመን ነበር ማለት ይቻል ይሆን? አንዳድ ጥናቶች እንደጠቆሙት የዓለም የጋራ ማሕበር ከተመሠረተ ከ1945 ወዲሕ ዓለም ከ300 በላይ ከባድ ጦርነቶችን አስተናግዳለች።
በአብዛኞቹ ጦርነቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች፣ የዓለም ልዕለ ኃያላን መንግሥታት በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተካፍለወል። ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ በየዓመቱ በአማካይ 7 መቶ ሺሕ ያክል ሕዝብ ያልቃል።ዛሬም ከሱዳን እስከ ጋዛ፣ ከዩክሬን እስከ ኮንጎ ዴምክራቲክ ሪፐብሊክ ዓለም ሰላም የላትም።በጉተሬሽ አገላለፅ በጦርነት ዓመድ ላይ የተተከለዉ የተስፋ ፍሬ ፀደቆ ይሆን?«ቢሆንም» ይላሉ እሳቸዉ የከፋ አልደረሰም ለማለት።
«ቀላል አልነበረም።ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ነበር።አንዳዴ ደግሞ አደገኛ ነበር።ግን መሥራትን መርጠናል።ምክንያቱም 8 አሥርተ-ዓመታት (ብዙ) ጦርነቶች ቆመዋል።ልጆች መማር ችለዋል።በሽታዎች ታክመዋል።ሕይወት ተርፏል።ይሕ አንድነገር ይነግረናል።በጋራ ከቆምን ሁሉምና ምንም ነገር ይቻላል»
በ78 ዓመታት በኋላም ዓለም ገቢር ያላደረገዉ ዉሳኔ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጀመሪያ ካሳለፋቸዉ አወዛጋቢ ግን ትላልቅ ዉሳኔዎች አንዱ ፍልስጤም ይባል የነበረዉ ሰፊ ግዛት ለሁለት ተገምሶ ባንደኛዉ ገሚስ ግዛት አይሁድ፣ በሌለኛዉ አረብ (ፍልስጤም) ሁለት መንግሥታት እንዲመሰርቱ የተዘጋጀዉን ዕቅድ ማፅደቅ ነበር።
ዕቅዱ ሕዳር 29፣1947፤ በ33 የድጋፍ፣ በ13 ተቃዉሞ፣ በ10 ድምፀ ተዓቅቦ ፀደቀ።የሁዲዎች ግንቦት 1948 መንግሥት መሠረቱ።አዲሱ የእስራኤል መንግሥት ከአረቦች ጋር ዉጊያ ገጠመ።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዉሳኔ መሠረት እየሩሳሌም በራሱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወ,ይም በሌላ ገለልተኛ ተ,ቋም እንድትተዳደር አልተደረገም።
ፍልስጤሞች ሐገር፣ ነፃነት፣ ፍትሕ እንደተመኙ እስከ ዛሬ አንድም ይገደላሉ፣ ይሰደዳሉ፣ወይም ይገዛሉ።78 ዓመታቸዉ። ጋዛ ዉስጥ ባለፉት 23 ወራት የሚፈፀመዉ ግፍ ደግሞ ለብቻዉ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በረጅም ጊዜ ታርኩ ባንድ ዓመት፣በአንድ ሥፍራ በርካታ ሠራተኞቹ የተገደሉበት አምና ነዉ።2024።የት-ጋዛ፣ ሥንት 181 የርዳታ ሠራተኞች።
ሥለዓለም ሠላም፣ሥለፍትሕና ነፃነት፣ ሥለሰዉ ልጅ እኩልነት የሚሰብኩት የለንደን-ፓሪስ፣ መንግሥታት ዛሬ በ78ኛ ዓመታቸዉ እንደ አዲስ የፍልስጤም መንግሥት መመሥረቱን እንደግፋለን እያሉ ነዉ።የዋሽግተን ባለሥልጣናት ግን የፍልስጤም መሪ ኒዮርክ እንዳይገቡ እንኳን አግደዋል።የተቀሩት አባላት የዘንድሮዉ ጉባኤ ከኒዮርክ ወደ ዤኔቭ እንዲዛወር እየጠየቁ ነዉ።
ለፍትሕ ቆመናል የሚሉት መንግሥታት ፍትሐዊነት
ነፃነት፣እኩልነት፣ ፍትሕ ከሁሉም በላይ የሰዉን ሰዉ የመሆን ክብርን የሚደፈልቀዉን፣ርዳታ ሰጪዎችን-ከተቀባዮች፣ ጋዜጠኞችን-ከነዋሪዎች፣ ሐኪሞችን-ከበሽተኞች ሳይለይ የሚገድለዉን ኃይል በሕግ ለመጠየቅ ግን የአዉሮጳና የሰሜን አሜሪካ መንግስታት ትንፍሽ አላሉም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ሕይወትን፣ የርዳታ ተቋማቱን ሕልዉና አልፎ ተርፎ የሠላም አስከባሪ ሠራዊቱን ደሕንነት መጠበቅና ማስጠበቅ ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉ መንግስታት ከጥቅማቸዉ አልፈዉ ለዓለም ሠላምና ደሕንነት መቆማቸዉን ማመን በርግጥ ሲበዛ ከባድ ነዉ።
የ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ዓለምና በነበረበት የቆመዉ ድርጅት
በ1945 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል መንግስታት 50 ነበሩ።ዘንድሮ አባላቱ 193 ናቸዉ።የድርጅቱን ከፍተኛ ሥልጣን የየያዘዉን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ባሻቸዉ የሚዘዉሩት ኃያላን መንግሥታት ግን ድሮም ዘንድሮም 5 ናቸዉ።አዲሲቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝደንት አናሌና ቤርቤክ ድርጅቱ ለ21ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን የሚመጥን መሆን አለበት ይላሉ።
«የኛ ስራ ዛሬ-ከ80 ዓመት በኋላ-(ድርጅቱ) እንዲኖር ማድረግና ማጠናከርና ለ21ኛዉ ክፍለ-ዘመን እንዲመጥን ማድረግ ነዉ።ለዚሕም ነዉ-ይሕ ተራ ጉባኤ የማይሆነዉ።ዓመቱ የምናሻሻልበት፣የምንለዉጥበትና ለሚቀጥሉት 80 ዓመታትና ለልጆቻችን እድሜ ልክ የሚያስፈልገንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የምንገነባበት ነዉ።
ዘግይተዋል።ግን ከእንግዲሕስ ይሳካላቸዉ ይሆን።ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ