1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የትራምፕ ተቃራኒ የአፍሪቃ መርሕ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ኅዳር 8 2018

ለመሆኑ በቅርብ ዓመታት የዘር ማጥፋት ወይም የጦር ወንጀል የተፈፀመዉ ናይጄሪያ ይሆን? ብቻ ዶናልድ ትራምፕ 8 ጦርነት አስቁሜያለሁ ይላሉ፣ትራምፕ እንደ ጠቅላይ አዛዥ የሚያዘምቱት ጦር ሶማሊያን፣ የመንን፣ ኢራንን፣ የቬኑዙዌላ ጠረፍን ይደበድባል አሁን ደጎሞ ናጄሪያ ላይ እየዛቱ ነዉ

ትራምፕ በአፍሪቃ ፀጥታ፣ ፖለቲካ፣ ምጣኔ ሐብታዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ ትንሽ ተፅዕኖ የሚያሳድሩትን የጋቦን፣ የጊኒ ቢሳዉ፣የላይቤሪያ፣ የሞሪታኒያና የሴኔጋልን መሪዎችን ሲያነጋግሩ።
ትራምፕ በአፍሪቃ ፀጥታ፣ ፖለቲካ፣ ምጣኔ ሐብታዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ ትንሽ ተፅዕኖ የሚያሳድሩትን የጋቦን፣ የጊኒ ቢሳዉ፣የላይቤሪያ፣ የሞሪታኒያና የሴኔጋልን መሪዎችን ሲያነጋግሩ።ምስል፦ Kevin Lamarque/REUTERS

ማሕደረ ዜና፣ የትራምፕ ተቃራኒ የአፍሪቃ መርሕ

This browser does not support the audio element.

አባባሉ ቀልድም-ምርም፣ ፌዝም-ምፀትም ሊሆን ላይሆንም ይችላል። ባንዱ ወይም በሁሉም ምክንያት አንዳዶች «የእስከ ዘመኑና የዘመኑ ዓለም ጉልበት፣ ሐብቷን ይሁን ኃይማኖቷን ከዘር ነጮች፣ ከፆታ ወንዶች፣ ከኃይማኖት ክርስቲያኖች የሚጠቀሙና የሚቆጣጠሩባት ናት» ይላሉ።አባባል፣ አስተሳሰብ ምናልባት ግብሩንም ለመቀየር የሚደረገዉ ትግል ግን በየፈርጁ እንደቀጠለ ነዉ።

የዓለም ቁጥር አንድ ሐብታም፣ ጉልበታም ሐገር ፕሬዝደንት ዶንልድ ትራምፕ ሥለተቀረዉ ዓለም በጣሙን ሥለ አፍሪቃ የሚሉ የሚያደርጉት የዘር፣ሐብት ኃይማኖት ተባለጡን እንዳያጠናክረዉ እያሰጋ ነዉ። የዩናይትድ ስቴትስ መሪ የሚከተሉት መርሕ ወይም አስተሳሰብ ለአፍሪቃዉያንና ለእኩልነት አቀንቃኞች ግራ ከማጋባት አልፎ አናዳጅ፣ አስፈሪ፣ አሳሳቢም ብጤ ሆኗል። ጥቂት አብነትን እያነሳን ላፍታ አብረን እንቆዝም።

የአሜሪካኖች ምርጫ፣ የትራምፕ መርሕ ምሰሶ

መጀመሪያ ከ2017 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እስከ 2021፣ ሁለተኛ ከጥር 2025 ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን የያዙት ቱጃር ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ በቅርብ የሚያዉቋቸዉ እንደሚሉት ለተቺ፣ ተቃዋሚ፣ ተፎካካሪዎቻቸዉ በርግጥ ምሕረት የለሽ ናቸዉ።በ2016 በተደ,ረገዉ ምርጫ ትራምፕን የተፎካከሩት የዴሞክራቲክ ፓርቲዋ ዕጩ ሒላሪ ክሊንተን ነበሩ።

ክሊተን ፖለቲካ-ዲፕሎማሲን እንደ ቀዳማዊት እመቤት ከባለቤታቸዉ፣እንደ ሕዝብ ተወካይ ከእንደራሴነት፣ እንደ ዲፕሎማት ከዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነት 24 ዓመታት ለምደዉታል፣ሰርተዉበታልም።አሜሪካ ዋዛ አይደለም።ከዘመናት ልምድ-ዕዉቀት፣ ሴት ይልቅ፣ሐብታም፣ ነጋዴ ወንዱን መረጠ።

በ2020 ሁለት ወንድ፣ ነጭ፣ አዛዉንት ፖለቲከኞች ለዉድድር ሲቀርቡለት ግን አሜሪካ ከሐብት ይልቅ በዘመናት ሒደት የካበተ የፖለቲካ ልምድ-ዕዉቀት ብስለትን መረጠ።ጆ ባይደንን።በ2024 ትራምፕን የገጠሙት የሕንድ-ጃማይካዋ ክልስ ዉልድ፣ የሕግ አዋቂ፣ ሴናተር፣ ምክትል ፕሬዝደንት ግን ሴት ፖለቲከኛ ነበሩ።ካሜላ ዴቪ ሐሪስ።ትራምፕ በቀላሉ አሸነፉ።ከፖለቲካ ጥበብ ይልቅ ንግድን፣ ከዲፕሎማሲ ይበልጥ ኃይልን፣ ከድርድር ይብስ ማን አሕሎኝነትን፣ ከመተባበር በላይ ግለኝነትን የሚመርጡት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያዉ ይሁን በሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ የአስተዳደራቸዉ አብይ መርሕ አሜሪካ ትቅደም ነዉ።

«ዛሬ እዚሕ የተሰበሰብነዉ፣አዲስ መመሪያ ለማወጅ ነዉ።አዋጁ በከተሞች በሙሉ፣በመላዉ የዉጪ ርዕሠ-ከተሞች፣ በሁሉም የሥልጣን ማዕከላት መሰማት አለበት።ከዛሬ ጀምሮ ሐገራችንን አዲስ ርዕይ ይመራታል።ከዛሬ በኋላ (መመሪያዉ) አሜሪካ ትቅደም ብቻ ነዉ።አሜሪካ ትቅደም።»

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።ጥር 2017።

ከግራ ወደ ቀኝ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲሪያል ራማፎዛና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።ትራምፕ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ በነጮች ላይ ተፈፀመ ያሉትን ግፍ የሚያሳይ ያሉት ፎቶ ሲያስረዱምስል፦ Evan Vucci/AP/picture alliance

ርዳትን ማቆም፣ ስደተኛን ማባረር ታሪፍ መጨመር-ትራምፕ 

ሁለተኛ ዘመነ ሥልጣናቸዉን ከጀመሩ ጀምሮ አሜሪካን ለማስቀደም በሯን በሌሎች ሐገራት ዜጎች ላይ ዘጉ።ስደተኞችን ያባርሩ፣ከዉጪ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ግብር ወይም ታሪፍ ይጨመሩ ያዙ።USAIDን ጨምሮ በተለይ ለአፍሪቃ ከፍተኛ ርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶችን ዘጉ።

USAID በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የአሜሪካ የርዳታ ድርጅት ከሰሐራ በስተደቡብ ለሚገኙ የአፍሪቃ ሐገራት በ2024 ብቻ 12.7 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የምግብ፣ የኤድስ መከላከያን ጨምሮ መድሕኒትና የሕክምና መገልገያዎች ርዳታ  ሰጥቶ ነበር።የርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት የትራምፕ መስተዳድር ባለፈዉ ጥር ድርጅቱ እንዲዘጋ መወሰኑ 5.7 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብን ወደ ከፋ  ድሕነት ይገፋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ እንዳሉት ግን መስተዳድራቸዉ ከአፍሪቃ ጋር የሚኖረዉ ግንኙነት ርዳታ በመስጠትና መቀበል ላይ ሳይሆን በንግድና ሸቀጦች ልዉዉጥ ላይ የተመሠረተ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሐራ በስተደቡብ ከሚገኙ የአፍሪቃ ሐገራት  ሁሉ ከፍተኛ የንግድ ልዉዉጥ የምታደርገዉ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ነዉ።የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲሪያል ራማፎዛን ባለፈዉ ግንቦት ዋይት ሐዉስ በጋበዙበት ወቅት ግን ከንግድ ልዉዉጥ ይልቅ የደቡብ አፍሪቃ መንግስት ነጮችን ይጨ,ቁናል የሚል ወቀሳና ዉንጀላ ነበር የደ,ረደሩት።

ትራምፕና አፍሪቃ፤ ንግድን ማጠናከር፣ግን ታሪፍ መጨመር

ሐምሌ ላይ በተቃራኒዉ ግን በአፍሪቃ ፀጥታ፣ ፖለቲካ፣ ምጣኔ ሐብታዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ ትንሽ ተፅዕኖ የሚያሳድሩትን የጋቦን፣ የጊኒ ቢሳዉ፣የላይቤሪያ፣ የሞሪታኒያና የሴኔጋልን መሪዎች ዋይት ሐዉስ ጋብዘዉ መስተዳድራቸዉ፣  ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍሪቃ ጋር ያላት ግንኙነት ከርዳታ ወደ ንግድ መለወጡን አሰታወቁ።

«አስተዳደሬ ከአፍሪቃ ጋር ያለዉን ግንኙነት፣ ዩናይትድ ስቴትስንና ሸሪኮቿን በሚጠቅመዉ በምጣኔ ሐብታዊ ልማት መስክ ለማጠናከር ይጥራል።ከርዳታ ወደ ንግድ እየለወጥን ነዉ።ንግድ መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ እችላለሁ።»

የትራምፕ ቃል ለብዙ አፍሪቃዉያን «አስደሳች» ባይባልም ተስፋ አስቆራጭ ባልሆነ ነበር።ትራምፕ ሐገራቸዉ ለአፍሪቃ ርዳታ ከመስጠት ይልቅ ንግድ እንደምታጠናክር ቃል የገቡት ከአፍሪቃ ሐገራት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገቡ ሸቆጦች ላይ እስከ 51 በመቶ የሚደርስ የቀረጥ ወይም የታሪፍ ጭማሪ ከጫኑ በኋላ መሆኑ እንጂ ቀቢፀ ተስፋዉ።

እርግጥ ነዉ በተለይ ሌሶቶ ላይ የተጣለዉ የ51 በመቶ ታሪፍ ጭማሪ ኋላ ተሻሽሏል።ከ10 እስከ 30 በመቶ የተጣዉ ታሪፍ ጭማሪ ግን እንደፀና ነዉ።32 የአፍሪቃ ሐገራት ይጠቀሙበታል የተባለዉንና AGOA በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የዩናይትድ ስቴትስ ደንብም ከጥቅምት በ,ኋላ አልተራዘመም።

ከፍተኛ ታሪፍ ከተጣለባቸዉ የAGOA ንግድም ከተቋረጠባቸዉ የአፍሪቃ ሐገራት አንዷ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ከፍተኛ የንግድ ልዉዉጥ የምታደርገዉ ደቡብ አፍሪቃ ናት።

ከግራ ወደ ቀኝ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና መሪና ከሐገሪቱ ኮሚንስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ጋር እንደ ጥሩ ወዳጅ ሲመክሩምስል፦ Andrew Harnik/Getty Images

«ደቡብ አፍሪቃ ኮሚንስት ናት» ግን ቻይናስ?

ትራምፕ ባለፈዉ ግንቦት እንዳሉት ደቡብ አፍሪቃ ላይ ያላቸዉ ቅሬታ ወይም ጥላቻ ከምጣኔ ሐብት፣ከንግድ ወይም ከፖለካም የዘለለ ነዉ።የዘር።የነጭ ዘር።ትራምፕ፣ የደቡብ አፍሪቃ እንግዳቸዉ ራማፎዛ ፊት ቪዲዮና ፎቶ ግራፍ ደርድረዉ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ነጮችን እንደ,ሚጨቁን፣ ሐብታቸዉን እንደሚዘርፍ፣ እንደሚያሰቃያቸዉም ሲተቹ፣ ሲያወግዙ፣ሲያስፈሩም ነበር።

አንዳዶቹ ፎቶ ግራፎች ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዉስጥ የተነሱ መሆናቸዉ ቢረጋገጥም የነጮችን የበላይነት ለማስከበር ቆርጠዉ የተነሱት ዶናልድ ትራምፕ ግን ነጭ ደቡብ አፍሪቃዉያን ወደ አሜሪካ እንዲሰደዱ ፈቀደዋል።አሜሪካ ጥግ የምትገኘዉን የጃማይካ ስደተኛን ሳይቀር ከአሜሪካ ወደ አፍሪቃ ያስግዛሉ።መሰደድ የማይፈልጉትን የደቡብ አፍሪቃ ነጭ ዜጎችን ወደ አሜሪካ ይጋብዛሉ።ከአፍሪቃ ጋር የንግድ ግንኙነትን ማጠናቀር እሻለሁ ይላሉ፤ ደቡብ አፍሪቃን በዘረኝነት ያወግዛሉ።

በሚቀጥለዉ ቅዳሜ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ በሚደረገዉ የቡድን 20 ጉባኤ ላይም ዩናይትድ ስቴትስ እንደማትካፈል ትራምፕ አስታዉቀዋልም።እንዲያዉም ደቡብ አፍሪቃ ከቡድኑ መዉጣት አለባት ብለዋልም። ምክንያት ደቡብ አፍሪቃ ነጮችን የምትጨቁን «ኮሚንስት» ሥለሆነች።

«ማያሚ ለትዉልዶች፣ ከ,ደቡብ አፍሪቃ ኮሚንስታዊ ጭቆና ላመለጡ ሰዎች መጠጊያ ናት።ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ የቡድን 20 ጉባኤ ይደረጋል።እዚያ አልሄድም።ደቡብ አፍሪቃ ጂዎች  (G’S) ዉስጥ መኖር አይገባትም።እዚያ የሚፈፀመዉ በጣም መጥፎ ነዉ።አልሄድም።አባል መሆን የለባትም።»

የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲሪያል ራማፎዛ፣ ባለሥልጣኖቻቸዉና የመብት ተሟጋቾች የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ዉንጀላ አልተቀበሉትም።ሰዉዬዉ ግን ሐቅ-ሲጋለጥ ሕቅ እያላቸዉ በጉባኤዉ ላይ  ምክትላቸዉን ለመላክ የገቡትን ቃል አጥፈዉ ዩናይትድ ስቴትስ በጉባኤዉ ላይ ጨርሶ እንደማትወከል አስታዉቀዋል።

ትራምፕ ደቡብ አፍሪቃን ነጮችን «የምትጨቁን ኮሚንስታዊት ፈላጭ ቆራጭ» እያሉ የወነጀሉት የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ሺ ጂፒንግን ለማነጋገር ደቡብ ኮሪያ ደ,ርሰዉ በተመለሱ በሁለተኛ ሳምንቱ ነዉ።ኮሚኒስቱ ማነዉ?

ክርስቲያኖችን ለማዳን ናይጄሪያ የመደብደብ ዕቅድ 

ከቡድን 20 ወይም ከደቡብ አፍሪቃ በፊት የትራምፕ ዉንጀላ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ ናጄሪያ ላይ ያነጣጠረ ነበር።ትራምፕ እንዳሉት የናጄሪያ ጀሐዲስቶች በክርስቲያኖች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እያደረሱ ነዉ።የናጄሪያ መንግሥት ጥፋቱን ባለመከላከሉ ጀሐዲስቶቹን ለማጥፋት ዩዩናይትድ ስቴትስ ጦር አፍሪቃዊቱን የ230 ሚሊዮኖች ሐገርን ይደበድባል።

ሰሜናዊ ናጄሪያ ዉስጥ የሸመቁ የቦኩ ሐራም ወይም የሌላ ቡድናት ታጣቂዎች ግፍ ከዋሉባቸዉ የሐ,ገሪቱ ሴቶች አንዷምስል፦ Kola Sulaimon/AFP

 «የናጄሪያ መንግሥት በክርስቲያኖች ላይ የሚፈፀመዉን ግድያ መፍቀዱን ከቀጠለ፣ ዩ ኤስ ኤ ለናጄሪያ የምትሰጠዉን ርዳታና ድጋፍ በሙሉ ታቋርጣለች።የጦር ሚንስትራችን ሊወሰድ የሚችለዉን እርምጃ እንዲዘጋጅ መመሪያ ሰጥቻለሁ።የምንደበድብ ከሆነ ፈጣን፣ ጠንካራና ጣፋጭ ነዉ-የሚሆነዉ።»

ትራም የናጄሪያ ፅንፈኛ ታጣቂዎችን ማዉገዛቸዉን የናጄሪያ መንግስት ባለሥልጣናት፣አንዳድ  የኃይማኖት መሪዎችም ደግፈዉታል።ጂሐዲስት ያሏቸዉ ወኃያላት ከሚያደርሱት ጉዳት ለክርስቲያኖቹ ብቻ መቆርቆራቸዉ ከሁሉም በላይ ሉዓላዊት ሐገርን ለመዉር መዛታቸዉ ግን ከአቡጃ አልፎ የአፍሪቃ ሕብረት ተቃዉሞን ቀስቅሷል።የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ ዓሊ የስፍ እንዳሉት የትራምፕ ዓይነቱን አስተያየት ከመስጠት በፊት ሁለቴ ማሰብን ይጠይቃል።

ለመሆኑ በቅርብ አመታት የዘር ማጥፋትወይም የጦር ወንጀል የተፈፀመዉ ናይጄሪያ ይሆን? ብቻ ዶናልድ ትራምፕ 8 ጦርነት አስቁሜያለሁ ይላሉ፣ትራምፕ እንደ ጠቅላይ አዛዥ የሚያዘምቱት ጦር ሶማሊያን፣ የመንን፣ ኢራንን፣ የቬኑዙዌላ ጠረፍን ይደበድባል አሁን ደጎሞ ናጄሪያ ላይ እየዛቱ ነዉ።ትራምፕ ከአፍሪቃ ጋር የንግድ ልዉዉጥን አጠናክራለሁ ይላሉ፤ የአፍሪቃ ትላልቅ ሐገራትን ይወነጅላሉ፣ ያስፈራራሉም። ወንጀለኛ የሚባሉ ስደተኞች ደግሞ ወደ አፍሪቃ ሐገራት ያስግዛሉ።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

                          

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW