1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የአፍሪቃ ቀንድ የጦርነት ሥጋት

ሰኞ፣ ነሐሴ 27 2016

እንደ አይዲድ ሁሉ ከሐዉያ ጎሳ የሚወለዱት፣አይዲድ ላጭር ጊዜ የነበሩበትን ቪላ ሞቃዲሾን የያዙት ሐሰን ሼሕ ማሕሙድ ከዚያድ ባሬ ዉድቀትም ሆነ ከአይዲድ ምክር እንዳልተማሩ ሁሉ፣ አል ሲሲ ከገማል አብድናስር፣ከሳዳት ይሁን ከሙባረክ፣ ዓብይ ከመንግስቱ ይሁን ከመለስ ሥሕተቶች ተምረዋል ማለት የዋሕነት ነዉ።ታሪክ ግን በርግጥ ራሱን ደገመ።

የታጁራ ወደብ ከኢትዮጵያ ድንበር አንድ መቶ ኪሎ ሜትር የሚርቅ በቅርቡ የተገነባ ወደብ ነዉ።
ከጅቡቲ ወደቦች አንዱ።ጅቡቲ የታጁራ ወደብን ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት ፈቅዳለች።ምስል Solomon Muchie/DW

ማሕደረ ዜና፣ የአፍሪቃ ቀንድ የጦርነት ሥጋት

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያና የሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻ ንሯል።ዉዝግቡ አይሏል።የቃላት ጦርነቱ ግሟል።የሁለቱን መንግስታት ጠብና ዉዝግብ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ያየችዉ ግብፅ ለሶማሊያ ጦር መሳሪያ እያስታጠቀች ነዉ።የካይሮ ገዢዎች እስከ 10 ሺሕ የሚደርስ ጦር ሠራዊት ሶማሊያ ዉስጥ ለማስፈር ማቀዳቸንም አስታዉቀዋል።ኢትዮጵያ ግብፅን በሥም ባትቀስም የካይሮ-ሞቃዲሾዎችን እርምጃ አጥብቃ አዉግዛለች።ዓለም አቀፍ የመንግሥትነት ዕዉቃ ከሌላት ሶማሊላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር አምባሳደር ሾማለችም።ጁቡቲ ጠብ-ዉዝግቡን ለማርገብ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን እንድትጠቀም ፈቅዳለች።የጠብ ዉዝግቡ ንረት መነሻ፣ ያለፈዉ ታሪክ ማጣቀሻ በጎ-መጥፎ ዉጤቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ዉጊያ ይጫር ይሆን?

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመንግሥትነት እዉቅና የሌላት የሶማሊላንድ ወደብን ለመኮናተር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን የሶማሊያ ፌደራዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሶማሊያን ሉዓላዊነትን እንደጣሰ ወረራ ነዉ የቆጠረዉ።ሞቃዲዎች መሪዎች ጉዳዩን ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አቅርበዉ ኢትዮጵያን ለማስወገዝም ብዙ ደክመዋል።ከቱርክና ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋልም።ይሁና ቱርክ ጠቡን በድርድር ለማርገብ የሁለቱን ባለሥልጣናት በስማ በለዉ ማነጋገር ጀምራለች።

ከዚሕ ቀደም አንካራ ላይ ቢያንስ ሁለቴ የተደረገዉ ድርድር ለሁነኛ ዉጤት ባይበቃም ድርድሩ በያዝነዉ መስከረም ወር እንደሚቀጥል የቱርክ ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።የአንካራዉ ቀጠሮ ሲጠበቅ፣ የድርድሩ ሒደት እንዴትነት ሲያጠያይቅ ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ ግብፅ ለሶማሊያ የመጀመሪያዉን የጦር መሳሪያ ልካለች።

C-130 የተባሉት ሁለት አሜሪካ ሰራሽ ወታደራዊ አዉሮፕላኖች የጫኑት የጦር መሳሪያና ጥይት ዓይነት በዉል አልተነገረም።ይሁና ግብፅ ለሶማሊያ ከምታስታጥቀዉ ጦር መሳሪያ የመጀመሪያዉ እንጂ የመጨረሻዉ እንዳልሆነ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።

ግብፅ ከዚሕ በተጨማሪ በመጪዉ ታሕሳስ ባዲስ መልክ ይዋቀራል ለተባለዉ በሶማሊያ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት 5000፣ ለሶማሊያ መንግሥት በቀጥታ ድጋፍ የሚሰጥ ሌላ 5000 ጦር ኃይል ሶማሊያ ዉስጥ ለማስፈር ማቀዷም በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ኢትዮጵያ የሶማሊያና የግብፅን እርምጃና እቅድ አዉግዛለች።

የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼህ ማሕሙድ።ከኢትዮጵያ ጋር የገጠሙት ዉዝግብን እያቀጣጠሉት ነዉምስል REUTERS

የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባለፈዉ ሳምንት ባወጣዉ መግለጫ ግብፅን በሥም ሳይጠቅስ ግን «ሌሎች ተዋኞች» ያላቸዉ ወገኖች «አካባቢዉን የሚያመሰቃቅል እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ እጇን አጣጥፋ አትቀመጥም» በማለት አስጠንቅቋል።የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ባለፈዉ አርብ በጠሩት ጋዜጣዊ ጉባኤም ለሥለስ ባሉ ዲፕሎማሲያዊ ቃላት ሞቃዲሾና ካይሮን ጎሻሽመዋል።

 ሶማሊያ ለቃላት አፀፋ አልሰነፈችም።የሐገሪቱ መከላከያ ሚንስትር አብዲቃድር መሐመድ ኑር ባለፈዉ ቅዳሜ ኢትዮጵያ «ማላዘኗን ማቆም» አለባት ብለዋል።«ሁሉም የሚያጭደዉ የዘራዉን ነዉና።»የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ ደግሞ ከሚንስትራቸዉም አልፈዉ እስከ ዚያድ ባሬ ድረስ የነበሩ የሶማሊያ መሪዎች እንደሚሉት ሁሉ አላማ-ምኞታቸዉ የኢትዮጵያ ሶማሌ ግዛትንም እንደሚጨምር መናገራቸዉ ተዘግቧል።

ከዲፕሎማሲ ሽኩቻ፣ ከቃላት እሰጥ አገባ አልፎ የግብፅን ጦር መሳሪያ የጎተተዉ ጠብ ዉጊያ ያስጭር ይሆን።ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን አይ አዎ ነዉ መስላቸዉ።

«የዉጪ መንግሥታት ግብፅም ትሁን፣ ቱርክም ትሁን ሌሎች የአረብ መንግሥታትም ይሁኑ ወደዛ አካባቢ በሚመጡበት ጊዜ ያስፈራል።ጦርነት ይኖራል? እኔ እንኳን ወደ ጦርነት የሚመራ ነገር ይኖራል ብዬ አልገምትም።----ተዘዋዋሪ ጦርነት ግን ሊኖር ይችላል።»

 

  ታሪክ ራሱን ይደግማል

የሰሜን የመን የርስ በርስ ጦርነት በጋመበት በ1960ዎቹ መጀመሪያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኮሎኔል አብዱላሕ ያሕያ አል ሳላል የሚመሩትን የየመን ሪፐብሊክ የሚባለዉን አብዮታዊ መንግስትን የሚረዳ 70 ሺሕ ጦር ግብፅ አዝምታ ነበር።

የግብፅ ፕሬዝደንት ገማል አብድናስር ጦሩን ያዘመቱት የየመንን ንጉሳዊ አገዛዝን የሚደግፉት የሪያድ፣የአማን፣የቴሕራን፣ የለንደን ነገሥታትና የቴልአቪቭ ተባባሪዎቻቸዉ በቀይ ባሕር አካባቢ የሚኖራቸዉን የበላይነት ለመስበር ጭምር ነበር።አልሆነም። የግብፅ ጦር በየመን ጉጥ፣ሥርጓጥ አለቀ።የግብፅ ጦር የመን ላይ የገጠመዉ ኪሳራ ግብፅና ተባባሪዎችዋ በ1967 ከእስራኤል ጋር በገጠሙት ጦርነት ለመሸነፋቸዉ እንደ አንድ ምክንያት ሲዘከር ይኖራል።

እንደ ናስር ሁሉ የግብፅ ጦር ያፈራቸዉ የቀድሞዉ ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ የሳዑዲና የአረብ ኤምሬቶች ነገስታትን ለማስደሰት የየመን ሁቲዎችን የሚወጋ የአየር ኃይል ጦር በ2015 አዝምተዉ ነበር።የሳዑዲ አረቢያና ግብፅን የመሳሰሉ ተባባሪዎችዋ ጦር ያዘመቱበት ዋና ዓላማ ኢራን በየመን ሁቲዎች በኩል በቀይ ባሕር አካባቢ የሚኖራትን ተፅዕኖ ለማስወገድ ነበር።

የመንን ለ7 ተከታታይ አመታት የቀጠቀጠዉ የአረብ ተባባሪ ጦር «ተሸነፈ» ባይባል እንኳ ሁቲዎችን ማሸነፍ ግን አልቻለም።የመን ላይ ታሪክ ራሱን ደገመ።

የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አል ሲሲ።ለሶማሊያ ጦር መሳሪያ መላክ ጀምረዋልምስል Egyptian Presidency Media Office via AP/picture alliance

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በ1977 የገጠሙት ጦርነት ዋና መነሻ የሶማሊያዉ የረጅም ጊዜ መሪ መሐመድ ዚያድ ባሬና ተከታዮቻቸዉ የሚያቀነቅኑትን «ታላቋ ሶማሊያን» የየመመስረት ሕልማቸዉን እዉን ለማድረግ በመሞከራቸዉ ነበር።ግብፅን ጨምሮ የአረብና የምዕራባዉያን መንግስታት ድጋፍ ያልተለየዉ የሶማሊያ ጦር በሶቭየት ሕብረት፣ ኩባና ደቡብ የመን በሚደገፈዉ የኢትዮጵያ ጠላቱ ተሸነፈ።የዚያድ ባሬ ዉድቀት፣የሶማሊያ ትርምስም  ያኔ ተጀመረ።

በ1990ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ የሶማሊያን የርስበርስ ጦርነት «በሰላም ለመፍታት» በሚል ሰበብ ኢትዮጵያና ግብብፅ ግራ ቀኝ ሲጓተቱ ያስተዋሉት የያኔዉ የሶማሊያ ዕዉቅ ጄኔራል  መሐመድ ፋራሕ አይዲድ «ከእንግዲሕ ለዓባይ ዉኃ ሲባል የሶማሊዎች ደም አይፈስም» ዓይነት ብለዉ ነበር።

ኢትዮጵያ በኢጋድ በኩል የያኔዉን የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን ዉክልና ይዛ፣ ግብፅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ በነበሩት ዜጋዋ በኩል የዓለም አቀፉን ድርጅትና የአሜሪካኖችን ተዘዋዋሪ ድጋፍ አንግባ ሶማሊያ ላይ የገጠሙት ሽኩቻ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይለይበት፣ለሶማሊያም ሁነኛ መንግስት ሳያቆም ተዳፈነ።

ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ወደብን ለመኮናተር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲሕ ግን በ1990ዎቹ ቢያስ ሶማሊያ ላይ ተዳፍኖ የነበረዉ የኢትዮጵያና የግብፅ ሽኩቻ የዓመታት አመድ ከሰሉን እያራገፈ አሁን ይቀጣጠል ገባ።

እንደ አይዲድ ሁሉ ከሐዉያ ጎሳ የሚወለዱት፣አይዲድ ላጭር ጊዜ የነበሩበትን ቪላ ሞቃዲሾን የያዙት ሐሰን  ሼሕ ማሕሙድ ከዚያድ ባሬ ዉድቀትም ሆነ ከአይዲድ ምክር እንዳልተማሩ ሁሉ፣ አል ሲሲ ከገማል አብድናስር፣ከሳዳት ይሁን ከሙባረክ፣ ዓብይ ከመንግስቱ ይሁን ከመለስ ሥሕተቶች ተምረዋል ማለት የዋሕነት ነዉ።ታሪክ ግን በርግጥ ራሱን ደገመ።

ኢትዮጵያ 120 ሚሊዮ ሕዝብ የሚኖርባት ታሪካዊ፣ ሰፊ፣ ትልቅ፣ የአፍሪቃ የነፃነት አብነት ሐገር ናት።በ1991 የአዲስ አበባ ቤተ መንግስትን የተቆጣጠሩት የሕወሓት-ኢሕአዲግ መሪዎች ያቺን ትልቅ ሐገር እንበለ የባሕር በር አስቀርተዋታል።ያሁኖቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ወዳብ መፈለግ፣መመኘት፣ መሞከራቸዉም ብዙዎች እንደሚያምኑት ተገቢ ነዉ።

ይሁንና የሐገሪቱን ሕግና ሥርዓት ሳያስከብሩ፣ በነፍጥ የሚዋጉ ኃይላትን ጥያቄ ሳይመልሱ፣ የሕዝቡን ሰላምና ደሕንነት በቅጡ ሳያስከብሩ ከሌሎች መንግስታት ጋር የሚያቃቅር እርምጃ መዉሰዳቸዉ ለፖለቲካ ተንታኞችም ለሕግ አዋቂዎችም ግራ አጋቢ ብጤ ነዉ።

አቶ የሱፍ ያሲን እንደሚያምኑት ያለፈዉን ሥሕተት ላለመድገም ይሁን አሁን የሚያሰጋዉን ቀጥታ ይሁን ተዘዋዋሪ ግጭት ለማስቆም አብነቱ ሰላማዊ ዉይይትና ስምምነት ነዉ።

«አካባቢው ያለዉን ዉጥረት ብቻ ሳይሆን፣ወደቦቹ የሚገኙበትን ባሕሩን ራሱን የቀይ ባሕር ይሁን የባሕረ ሰላጤ ይሁን ከየባሕሮቹ ዳርቻ ሐገራት ጋር ስምምነት ተደርጎ በምን መልክ ነዉ አካባቢዎቹን ሰላም ማስፈን የሚቻለዉ ተብሎ አንድ ስምምነት የሚደረግበት ሁኔታ ቢኖር ነዉ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም የሚኖረዉ።»  

 

አስተማኝና ዘላቂ ሰላም የሚፈልግ መሪ አለ ይሆን?

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የገጠመችዉን እሰጥ አገባ የግብፅ ገዢዎች እንደ ጥሩ አጋጣሚ የተጠቀሙበት ብዙዎች እንደሚያምኑት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በመገንባቷ ብቻ አይደለም።በግብፅ ሕዝብ የተመረጡትን ፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲን በ2014 በመፈንቅለ መንግስት ያስወገዱት የያኔዉ ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ ሥልጣናቸዉን ያደላደሉት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የዲሞክራሲ ኃይላትን ገድለዉ፣ አስረዉ፣ የቀሩትን አምቀዉ ነዉ።

ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ባሒ አብዲ የመግባቢያ ስምምነቱን ሲፈራረሙምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

እስራኤል ጋዛ ላይ የምትፈፅመዉን ግፍ  አል ሲሲ በዝምታ መመልከታቸዉም ከግብፅ ሕዝብ ምናልባትም ከጦር ኃይሉ አባላት ጭምር ተጨማሪ ቅሬታና ተቃዉሞ አስከትሎባቸዋል።

ግብፅ ዉስጥ የሚትመከመከዉን ሕዝባዊ ቅሬታና ተቃዉሞ ለማስተንፈስ አል ሲሲ የኢትዮ-ሶማሊያን ጠብ እንደ ጥሩ አጋጣሚ መጠቀማቸዉን ጥሩ ብልጠት አድርገዉታል።በመሠረቱ ለግብፅ ገዢዎች ከሶማሊያ ይልቅ የሊቢያ ወይም የጋዛ ሰላም ባሳሰባቸዉ ነዉ።

ወትሮም ሰላም የራቀዉን የአፍሪቃ ቀንድን ትርምስ ለማባባስ ግብፅ መሐል ግብታ ስታነኩር ጅቡቲ አዲስ መፍትሔ ይዛ ብቅ ብላለች።የጀቡቲ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሐመድ ዓሊ የሱፍ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ እንዳሉት ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን እንድትጠቀም ጅቡቲ ትቅዳለች።

«ሰሜን የሚገኘዉን  ወደብ ኢትዮጵያ አስተዳደሩን መቶ በመቶ እየተቆጣጠረች እንድትጠቀምበት እንፈቅዳለን።ሥለዚሕ የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ ችግር አይደለም። ከኢትዮጵያ ድንበር 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘዉ (አዲስ የተገነባ) የታጁራ ወደብ ነዉ።ፕሬዝደንት (ዑስማኢል) ጌሌ ይሕን የፈቀዱት ሶማሊያና ኢትዮጵያ ለድርድር መንገድ እንዲፈልጉና ዉጥረቱን እንዲያቆሙ በማሰብ ነዉ።»

ዝርዝሩ ገና አልታወቀም።ይሁንና የጅቡቲ ሐሳብ ከተሰማ ወዲሕ አንዳዶች ሐሳቡ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችዉን ስምምነት እንድታፈረስ አጣብቂኝ ዉስጥ የሚከት ነዉ እያሉ ነዉ።ሌሎች ጠቃሚ ይሉታል።

የጅቡቲዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከዲፕሎማሲ ብልጠት ይልቅ ስሜት፣ሆይ ሆይታ፤ የግል ጥቅምና እልሕ ከሚጫጫናቸዉ ከብዙዎቹ የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲከኞች ሁሉ ረጋ፣ ሰከን ያሉ ናቸዉ ይባላል።በቅርቡ ለሚደረገዉ የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንትነት እየተወዳደሩ ነዉ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ እንዳሉት የሐገራት ሉዓላዊነት መከበር፣ ጠብም በድርድር ሊፈታ ይገባዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ባደረገችዉ ስምምነት መሠረት የበርበራ ወደብን ከተጠቀመች ከጅቡቲ ለኢትዮጵያ የምትሰጠዉ የወደብ አገልግሎት በዉጤቱ ገቢዋም መቀነሱ አይቀርም።ፕሬዝደንት ዑሳማኢል ጌሌ የጅቡቲን ጥቅም ለመጠበቅ፣የሶማሊያና የኢትዮጵያን ጠብ ለማብረድ ይሁን ወይም ድሬዳዋ ማደግ መማራቸዉ ስቧቸዉ አሁን ያቀረቡት አማራጭ ዉጥረቱን ለማርገብ መርዳቱ አይቀርም።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW