ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ቀዉስ
ሰኞ፣ መጋቢት 22 2017
የአዲስ አበባና የአሥመራ መሪዎች ለኖቤል ሽልማት ያበቃ ፍቅራቸዉ ባጭር ጊዜ በጠብ ተለዉጦ የቃላት ቴኒስ እየተወራወሩ ነዉ።የትግራይ ገዢዎች በጦርነት ፍፃሜ ማግሥት የገጠሙት የሥልጣን ሽኩቻ የዚያን ግዛት ሕዝብ የሰላም ተስፋ እያቀጨጨዉ ነዉ።የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ሕዝብ ዛሬም በግጭት ጦርነት መከራዉን እያፈሰ ነዉ።ማብቂያ ያጣዉ ጦርነት፣ዉዝግብ፣የኑሮ ዉድነትና ሥራ አጥነት ተስፋ ያስቆረጠዉ ወጣት በየአቅጣጫዉ ሲሰደድ በየበረሐ፣ባሕር፣ጠፍ ምድሩ ይጠፋል።ወይም ከሊቢያ እስከ ምያንማር በሚገኙ ማጎሪያ ሠፈረች ፍዳዉን ይቆጥራል።ዘረፋ፣ እገታ፣አሰቃቂ ግድያአንድ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደ ወረርሽኝ እየተዛመተ ነዉ።የኢትዮጵያ ሠላም፣ ልማትና ዕድገት ያለዉ ማንጋ እና የት ነዉ?ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
እገታ «እንደ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ነዉ
ዓሊ ዶር ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኦሮሚያ ክልል፣ መጋቢት 7 ቀን 2017።ታጣቂዎች እንደገና የዋሕ መንገደኞችን «ማረኩ።»
«ጊዮን ባስ ነበረ።ጊዮን ባስ ጎማዉን ነዉ የመቱት መጀመሪያ።ሲቆም እዚያ እንዳለ ሙሉ ፀጉሩን ያሳደገ ነዉ።ረዳት ፣ሾፌሩን ጨምሮ 58 ነዉ የሔደ።»
ያይን እማኙ እንደዘበት «ሔደ» ያሉት ሐምሳ ስምንት መንገደኞች ታገቱ።ብርቱካን ተመስገን የተባለች ወጣት ሥለመታገት፣ መደፈር መሰቃየቷ የተረከችዉ ገጠመኝ ዕዉነት ሐሰትነት የኢቢኤስ፣የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ፣የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ፀሐፍት አስተያየት ሰጪዎችን እሁለት ገምሶ በሚያነታርክበት በዚያ ሰሞን የዓሊ ዶሮ ታጋቾች ከጥቂቶች በስተቀር የኢትዮጵያ መገናኛ ዘዴዎችን፣ ፀሐፍትና ተንታኞችን ትኩረት ለመሳብ በርግጥ አቅም አልነበራቸዉም።
የኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት፣ የትግራይ ፖለቲካዊ ትኩሳት ንረት
አዲስ አበባም ለዓመታት እንደለመደችዉ የኢትዮጵያ ልማት፣የምጣኔ ሐብቷ ዕድገት ከባለሙያዎች ግምት በላይ የመሆኑ ድንቅ ዉጤት ይዘረዘርባት ነበር።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ።
«የዓለም አቀፍ ፋይናስ ተቋማት ያለፈዉ ዓመት የሰብ ሰሐራ ሐገራት ኤኮኖሚክ ዕድገት 4.2 ፐርሰንት እንደሚሆን ገምተዉ ነበር።ይሁንና በባለፈዉ ዓመት ሪፖርት እንደተመለከተዉ ኢትዮጵያ 8.1 ፐርሰንት የኤኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች።»
ባለፈዉ ሳምንት ሮብ።የብርቱካን ተመስገን ትረካ እዉነት-ሐሰትነት ለብዙዎች በጣሙን እሁለት ለተገመሱት ለማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አስተያየት ሰጪ-ተከታታዮች ማከራከሩን እንደቀጠለ ነበር።ግን እንዲያዉ ለመጠየቅ ያሕል 120 ሚሊዮን የሚሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐቁን የሚያወጣ አንድ መርማሪ ፖሊስ፣ አንድ መርማሪ የሕግ ባለሙያ፣ አንድ መርማሪ ጋዜጠኛ፣ አንድ የምክር ቤት ኮሚቴ እንዴት አጣ?
ብቻ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ ደሳለኝ ጫኔ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ያቀረቡት ጥያቄና የጠቅላይ ሚንስሩ ምፀታዊ መልስ ሰሞኑን በየመገናኛ ዘዴዉ ደመቅ፣ ደገምገም ይል ገባ።
በዚሕ መሐል ጠቅላይ ሚንስር ዓብይ አሕመድ የትግራይ ሕዝብ ለክልሉ ጊዚያዊ ፕሬዝደንት ዕጩ እንዲጠቁም ያስተላለፉት መልዕክት የመቀሌዉ ዘጋቢያችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ እንደዘገበዉ ወትሮም የልበረደዉን የትግራይን ፖለቲካዊ ትኩሳት አንቻረረዉ።
የምያንማር ግፍ
የቻይና ባለሐብት መሰል ደላሎች ጠቀም ባለ ደሞዝ ሊያሰሯቸዉ አማልለዉ ከየሐገሩ የወሰዷቸዉ ወጣቶች ምያንማር ዉስጥ የሚደርስባቸዉ ግፍ ገሐድ ከወጣ በርግጥ ዋል አደር ብሏል።በሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንም ከኤሌክትሪክ ንዝረት እስከ ግርፋት፣ ከመራብ መታረዝ፣ እንቅልፍ እስከማጣት በሚደርሰዉ ግፍ ተሰቃይተዋል። ከሰሐራ በረሐ እስከ ከሜድትራንያን ባሕር፣ ከአደን ባሕረ ሰላጤ እስከ የመን ጠፍ ምድር፣ ከሊቢያ ማጎሪያ ሰፈሮች እስከ ደቡባዊ አፍሪቃ ሐገራት ጫካና ወህኒቤት በሚያልቀዉ ኢትዮጵያዊ ወጣት ላይ የምያንማሩ ግፍ መታከሉ በርግጥ አሳዛኝ፣ቅስም ሰባሪም ነዉ።ለወላጅ፣ ዘመድ ወዳጆች ደግሞ ጥልቅ ሰቀቀን።
የምያንማር ወታደራዊ መንግሥትያደራጃቸዉ ሚሊሻያዎች በታይላንድ ትብብር 7 ሺሕ የሚሆኑ ሰለቦችን ከየማሰቃያዉ ሠፈር (ካምፕ) አዉጥተዉ ወደ ታይላድ አሻግረዋል።ብዙዎቹ መንግስታት ታይላድ የገቡትንም እዚያዉ ምያንማር የቀሩትንም ዜጎቻቸዉ ሲያስወጡ ኢትዮጵያዉኑ ግን በየጦር ሠፈሩ እንደበተኑ መሆናቸዉን የወጣቶቹ ቤተሰቦች ይናገራሉ።ባለፈዉ ሮብም ደገሙት።
ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ከ20 የሚበልጡ መንግስታት ዜጎቻቸዉን ወደየሐገራቸዉ መልሰዋል፣ ወይም እየመለሱ ነዉ።ኢትዮጵያዉያኑ ግን እዚያዉ ናቸዉ።ኢትዮጵያ የጦርነት፣የግጭት፣የእገታ፣የግድያ፣የተሰዳጅ መከረኞች ምድር።ያቺ ጥንታዊ፣የአፍሪቃ የነፃነት ቀንዲል፣ የቅኝ ገዢዎች መዋረጃ፣ የሐይማነተኞች ሐገር ለዘመኑ ትዉልድ የእልቂት፣ፍጅት፣የጥፋት ስቃይ ሰቆቃ ምድር የሆነችበት ምክንያት በርግጥ ብዙ አሳሳቢ አነጋጋሪ ምናልባትም ለፈጣን ርምጃ የሚያነሳሳ በሆነ ነበር።ግን ብዙዎች ዘግናኙን ግፍ ሰቆቃ ብዙ ሥለሰሙት ለመዱት።ወይም ሌላ ምክንያት ይኖራቸዋል።
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የበላይ ሐላፊ ያሬድ ኃይለማርያም እንደሚሉት ግን ዋናዉ ምክንያት ከ30 ዓመት በላይ የተነዛ፣ የተሰበከ፣የተሰረባት ጎሳኝነት ነዉ።
«ሰዎች በማንነታቸዉ ብቻ ተለይተዉ መንገድ እንዳያልፉ ይከለከላሉ።በማንነታቸዉ ብቻ ተለይተዉ ሴቶች ይደፈራሉ።በማንነታቸዉ ብቻ ተለይተዉ ንብረታቸዉ ይወድማል።ታፍነዉ ገንዘብ ይጠየቅባቸዋል።በጣም አሰቃቂም፣አስነዋሪም የሚባሉ የወንጀል ባሕሪዎች እየጎሉ የመጡት የዚሕ ላለፉት 4 አስርተ ዓመታት ያበቀልነዉ፣ ያሳደግነዉ ብሔር ተኮር የሆነዉ ፅንፍ የያዘዉ ፖለቲካ ወደ ግጭት ሲቀየር ያመጣዉ ነዉ።»
የብሬዥኔቭ ጥያቄ፣የመንግስቱ ሳቅ
የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ኮሎኔል መንግሥቱ ሐይለማርያም እንደፃፉት የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረትን ለሁለተኛ ጊዜ ለመጎብኘት ወደ ሞስኮ የሔዱት ኃምሌ 1969 ነበር።የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጦርነት፣የኢትዮጵያ መንግስትና የኤርትራ አማፅያን ዉጊያ፣ የኢትዮጵያ መንግስትና የኢዲዮ፣ የታሕት የሌሎች አማፂያን ዉጊያ ሐገሪቱን በየአቅጣጫዉ በሚያነድበት፣ ነጭና ቀይ ሽብር ከተሞችን በሚያተራምስበት በዚያን ወቅት ወደ ሞስኮ ሲሄዱ ከያዙት ሰነድ አንዱ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ካርታ ነበር።
ካርታዉ ኮሎኔል መንግሥቱ እንዳሉት «ፀረ-አንድነትና ፀረ አብዮት ድርጅቶች የሚቆጣጠሩበትና ሽብር የሚያካሒዱበትን አካባቢን የሚያሳይ ቀለም ተቀብቷል።» ስራ ሠለበዛብኝ ካርታዉን እስከዚያ ጊዜ ድረስ አለየሁትም ነበር» ፃፉ መንግስቴ።
ኮሎኔል መንግሥቱ ለሶቭየት ሕብረቱ ኮሚንስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ለሊዮንድ ብሬዥኔቭና ለሌሎች ባለሥልጣናት ካርታዉን ገልጠዉ ገለፃና ማብራሪያቸዉን ቀጠሉ።«ብሬዥኔቭ በገለፃዬ መካከል ጣልቃ ገብተዉ «ጓድ መንግሥቱ ወደ ሌላዉ ገለፃዎ ከመሔድዎ በፊት፣ ልጠይቅዎት የምፈልገዉ ነገር አለኝ ካሉ በኋላ ለመሆኑ አብዮተ የመጣለት ሕዝብ፣አብዮታዊዉ የመከላከያ ሠራዊትና አብዮታዊዉ መንግስት የትነዉ ያሉት?» ብለዉ ሲጠይቁኝ እዚያ የተሰበስበነዉ በሙሉ እኔም ጭምር በሳቅ አወካን» እያሉ ቀጠሉ መንግሥቱ።
ኮሎኔል መንግሥቱ እንዳሉት ካርታዉ አብዛኛዉን የኢትዮጵያ ግዛት በመንግስት ጠላቶች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ የሚያሳይ የተጋነነ ነበር።
ጠላቶቹ አረመኔ፣ ጨፍጫፊ፣ ፋሺስት፣ ጦረኛ፣ እያሉ ያወገዙ፣ የወነጀሉ፣ ያመፁ፣ ሕዝብ ያሳመፁበት፣ ለ17 ዓመታት የወጉት የኮሎኔል መንግስቱ ወታደራዊ ሾሊስታዊ መንግሥት ከተወገደ እነሆ ዘንድሮ ግንቦት 34 ዓመቱ።
ዘንድሮስ ኢትዮጵያ ሰዉ የማይዘረፍ፣የማይገደል፣የማይታገት፣የማይሰደድ፣ የማይፈናቀል፣ የማይራብ፣የማይጠቃ፣ የማይጋጭበት፣ ግዛትዋ የትኛዉ ይሆን? አዲስ አበባ ላይ የሚወራዉ የልማት፣ዕድገት፣ ብልፅናዋ ትሩፋትስ ከአብዛኛ ሕዝቧ የተሰወረበት ሚስጥርስ ምን ይሆን?እንደገና አቶ ያሬድ።
«ያለዉ የኤኮኖሚ መዋዠቅና የኑሮ ዉድነት የብዙ ዜጎችን ሕይወት ፈተና ላይ ጥሏል።በዚያ ላይ የዚሕ የኮሪዶር ልማት፣ የከተሞች ፕሮጀክቶች በጠቅላል ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰዉ ተኮር ዓይደለም።ልማቱ ሲሰራ እዚያ ላሉት ዜጎች የት እናስቀምጣቸዉ? ምን ዓይነት አመቺ ሁኔታ እንፍጠርላቸዉ? የሚሉ ነገሮች አብረዉ አይጠኑም።
ስደትን እንደ አማራጭ ያየዉ ወጣትም በየደረሰበት ይሞታል ወይም ይሰቃያል።ሰብሳቢ፣ጠያቂ፣ተከታታይ የለዉም።የተደራረበዉ መከራ ማብቂያ አለዉ ይሆን?
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ