1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፤ የኢትዮ-ሶማሊያ ዉዝግብ፣ የአፍሪቃ ቀንድ ተጨማሪ ሥጋት

ሰኞ፣ ሰኔ 17 2016

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሥምምነት ከተፈራረመች ወዲሕ ሶማሊያ ከግብፅ፣ ከኤርትራና የከቱርክ ጋር የነበራትን ግንኙነት አጠናክራለች።ሶስቱ ሐገራት ከሶማሊያ ጋር የነበራቸዉን ግንኙነት ያጠናከሩበት ምክንያት ለየቅል፣ አንዳዴም ያንዱ ምክንያት ከሌለኛዉ የሚቃረን፣ የግንኙነት ደረጃዉም የተለያየ ነዉ።

ሶማሊያ ዉስጥ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2007 ጀምሮ በሺሕ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሠፍረዋል
ሶማሊያ የሠፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት አካል የሆነዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት በከፊልምስል AMISOM

ማሕደረ ዜና፤ የኢትዮ-ሶማሊያ ዉዝግብ፣ የአፍሪቃ ቀንድ ተጨማሪ ሥጋት

This browser does not support the audio element.


አዉሮጶች ከተመሰጉበት የጋዛ እልቂት፣ የዩክሬን ጥፋት ፋታ የኳስ ድል እያማጡ በጎል ግብ ይገላገላሉ።ያዉ ላፍታ።አይሲስ የሚባለዉ አሸባሪ ቡድን መሪ ሶማሊያ ገብቷል መባሉ የአሜሪካኖችን ጠጉር አቁሞ የመን-ሁቲዎች ላይ የደገኑትን ሚሳየል ወደ ፑንትላንድ አዙረዉ ዳአዳርን ያነዳሉ።ሱዳኖች የጦርነት አመድ-ክሳያቸዉን እያሰጡ የተፈናቃይ፣ረሐብተኛቸዉን ቁጥር ያሰላሉ።ኢትዮጵያ ዘንድሮም እንዳምናዉ በግጭት ማጥ ትዳክራለች።ሶማሊያ የፀጥታዉ ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ለሞቃዲሾዎች የብሥራት ጭላንጭል ፈንጥቋል።ይሁንና የሞቃዲሾ መሪዎች የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ከሐገራቸዉ የሚወጣበት ጊዜ እንዲዘገይ እየተማፀኑ፣የኢትዮጵያ ወታደሮች ግን እንዲወጡ ከማሳባቸዉ ጋር መቃረኑ ብሥራቱን በሥጋት ጋርዶታል።የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነት፣ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ተልዕኮ፣ የሶማሊያ ተቃራኒ አቋም፣ የምዕራባዉያን ዘመቻና የአፍሪቃ ቀንድ ትርምስ ብዙዎችን ብዙ ጊዜ አነጋግሯል።ለኛም የዛሬ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ ላፍታ  አብራችሁኝ ቆዩ።

የአፍሪቃ ቀንድ የግጭት-ትርምስ ቀጠና

የአፍሪቃ ቀንድ ሠላም ሆኖ አያዉቅም።ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ ብሶበታል።የአካባቢዉ ትልቅ፣የብዙ ሕዝብ መኖሪያ፣የአፍሪቃ ነፃነት ተምሳሌይቱ ሐገር ኢትዮጵያ ካንዱ ጦርነት እፎይ ሳትል በሌላ ግጭት ደሐ ሕዝቧ እየተገደለ፣ እየተፈናቀለ፣ የደሐ ጥሪቷ እያወደመባት ነዉ።ሁለተኛይቱ ትልቅ ሐገር ሱዳን ነፃ ከወጣች ጀምሮ ሰላም ሠፍኖባት አያዉቅም።ዘንድሮም ሺዎች እያለቁ፣ ሚሊዮኖች እየተሰደዱ እየተራቡባት ነዉ።ጦርነት

ሶማሊያ ከ1991 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እንደ አንድ ሐገር የሚመራት ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የላትም።ኤርትራ በየግጭት ጦርነቱ ከመሞጀር ሌላ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ በቅርቡ እንዳሉት ለሠላም፣ ልማት ዕድገት የሚታትር መንግስት አታዉቅም።ደቡብ ሱዳን ከሰላማዊ ሐገረ-መንግስት ዛሬም ብዙ እንደራቀች ነዉ።ማንቀረ ጅቡቲ? ወይስ ኬንያ? በርግጥ ሙሉ በሙሉ ሠላም ናቸዉ ይሆን? ብቻ፣ የአዲስ አበባዉ የሲቪል ሠርቪስ ዩኒቨርስቲ መምሕርና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ እንደሚሉት የአፍሪቃ ቀንድ በግጭት ከሚተራመሱ የዓለም አካባቢዎች አንደኛዉ ወይም ሁለተኛዉ ነዉ።ምክንያትም ይጠቅሳሉ።
                     
«የአፍሪቃ ቀንድ እንግዲሕ ከዓለማችን የግጭት ቀጠናዎች በቁጥር አንድ ወይም ሁለት ደረጃ የሚቀመጥ ነዉ።ምክንያቱም የአፍሪቃ ቀንድ ከቀይ ባሕር አቀማመጥ ጋር ተያይዞ----ዉስጣዊ ግጭቶች እንዳሉ ሆነዉ የዉጪ ኃይሎች ጥቅማቸዉን ለማስከበር የሚያደርጉት ፉክክር አካባቢዉ ሠላም ሆኖ እንዳይቆይ አድርጎታል የሚል ሐሳብ ነዉ ያለኝ።»  
የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰዒድም የአፍሪቃ ቀንድ ጦርነት፣ግጭትና ትርምስ ተለይቶት እንደማያዉቅ እርግጠኛ ናቸዉ።ለግጭት፣ ጦርነት ሽኩቻዉ «መሠረታዊ» ያሏቸዉን ሁለት ምክንያቶች ይጠቅሳሉም።ቅኝ ግዛትና አምባገነናዊ ገዢዎች።
«የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች ቅኝ ግዛቱን የመሠረቱት የነበረዉን የድሮ አስተዳደር አፍርሰዉ ነበር። ከነፃነት በኋላ  ግን የተመሠረቱት አስተዳደሮች እንደ ቅኝ ግዛቱ ከነበረ ናቹራል አልነበረም።ከቅኝ ግዛት በፊት ወደነበረዉ መመለስ ደግሞ አይመችም።ያደረጉት ምንድነዉ የነበረዉን የቅኝ ግዛት አስተዳደር እንዳለ ወርሰዉ መቀጠል ነዉ።በዚሕ ምክንያት እነዚሕ ሐገሮች ደካማ በመሆናቸዉ የሌላ ጣልቃ ገብነት ያስተናግዳሉ።»

ሶማሊያ የሠፈረዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት ባልደረቦች አሰሳ ከሚያደርጉባቸዉ አካባቢዎች አንዱምስል Luis Tato/AFP/Getty Images

ኃይል፣ ሐብታም መንግሥታት ጣልቃ ለመግባት በየዘመኑ የሚደረድሩት ምክንያት ሞልቶ ተርፏቸዉ።አብዛኞቹ ምክንያቶች በየአብዛኛ ሕዛባቸዉ ተቀባይነት የሌላቸዉ ገዢዎች የሚያመቻቿቸዉ ናቸዉ። ።ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ በኋላ እርዳታ በማቀበል፣የባሕር ላይ ወንበዴዎችንና አሸባሪዎችን በመዋጋት ሰበብ አካባቢዉን ላይ እንደተጣበቁ ነዉ።በቅርቡ ደግሞ የየመንን ጦርነት፣ የሑቲዎችን ጥቃት፣ የሱዳንን የርስበርስ ጦርነት ተተግነዉ ነባሮቹ በአካባቢዉ የሠፈረ ጦራቸዉን እያጠናከሩ፣ ሩሲያን የመሳሰሉት ደግሞ አዲስ ጦር ለማስፈር እያደቡ  ነዉ።
የኢትዮጵያና ዓለም አቀፍ ዕዉቅና የሌለዉ የሶማሊላንድ መንግስታት ባለፈዉ ጥር መጀመሪያ ላይ የተፈራረሙት የወደብና የጦር ሠፈር የመግባቢያ ሥምምነት ደግሞ ወትሮም ያልሰከነዉን ጠብና ሽኩቻ እያናረዉ ነዉ።

የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ስምምነት፣ የተጨማሪ ሥጋት ምንጭ

የመግባቢያ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት እንደተባለዉ ባንድ ወር ጊዜ አይደለም ዛሬም በስድስተኛ ወሩ ማብቂያ ገቢር አልሆነም።ይሁንና የሶማሊያ ፌደራዊ መንግሥትንና የኢትዮጵያን ግንኙነት ለማበላሸት ከበቂ በላይ ነዉ።ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደርእየጣረች፣ ግብፅን ከመሳሰሉ ከኢትዮጵያ ጋር የተቃቃሩ መንግስታትን ድጋፍ እያሰባሰበች ነዉ።አቶ አብዱረሕማን እንደሚሉት ኢትዮጵያ መጠንቀቅ ነበረባት።
«ኢትዮጵያ የአፍሪቃ ሐገራትን የግዛት ሉዓላዊነት የምታከብር ሐገር እንደሆነች ይታወቃል።ከአፍሪቃ ቀንድ፣ ከአፍሪቃም ትላልቅ ሐገራት አንዷ ናት።የአፍሪቃ ሕብረት መቀመጫም የሚገኘዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ።ይህ ሁሉ ያላት ሐገር የአፍሪቃ አንድነትን ቻርተር፣ የዓለም ሕግን ጥሳ ከሶማሊላንድ ጋር መስማማቷ በሶማሊያ ላይ አግሬሽን ፈፅማለች ማለት ነዉ።እና የሶማሊያ ቀጣ የሚጠበቅ ነዉ።»

የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት እስካሁን ከወሰዱት እርምጃ በተጨማሪ ሶማሊያ የሠፈረዉ የኢትዮያ ሠራዊት ከሐገራቸዉ እንዲወጣ እስከማሳሰብ ደርሰዋል።የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያ የሠፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (ATMIS በምሕፃሩ) አካል ሆኖ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት  ከዚሕ ቀደም ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት በሙሉ እስከ መጪዉ ታሕሳስ ድረስ ከሶማሊያ ለቅቆ ይወጣል ወይም በአዲስ ተልዕኮና ባነስተኛ ሠራዊት ይተካል።
 

የአሸባብ ታጣቂዎች እንደሆኑ የሚታመኑ ኃይላት ሶማሊያ በሠፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ላይ ከሰነዘሩት ጥቃት አንዱምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab

የሶማሊያ መሪዎች የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሐገራቸዉ እንዲወጣ  እየገፋፉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ግን ከሶማሊያ የሚወጣበት ጊዜ እንዲዘገይ እየጠየቁ ነዉ።ሮይተርስ ዜና አገልግሎት  ባለፈዉ ሳምንት እንደዘገበዉ በመጪዉ መስከረም ከሶማሊያ እንዲወጣ የታቀደዉ 4000 ሠራዊት የሚወጣበት ጊዜ እንዲዘገይ የሶማሊያ መንግስት በደብዳቤ ጠይቋል።
ዶክተር ሙከረም አንድ የሶማሊያ ባለሥልጣንን ጠቅሰዉ እዳሉት የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ ቢወጣ ኢትዮጵያ አትጎዳም፣ ሶማሊያም አትጠቀምም አሸባብ እንጂ።
                          
«በተለይ የጁባላንዱ ምክትል ፕሬዝደንት እንዳሉት የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ እንዲወጣ የሶማሊያ ባለሥልጣናት መገፋፋታቸዉ ለሶማሊያ አይጠቅምም።ኢትዮጵያን አይጎዳም።የሚጠቅመዉ ካለ ፅንፈኞችን (አሸባብን ነዉ)።»

አዳዲስ ወዳጅ ፍለጋ የምትባትለዉ ሶማሊያ

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሥምምነት ከተፈራረመች ወዲሕ ሶማሊያ ከግብፅ፣ ከኤርትራና የከቱርክ ጋር የነበራትን ግንኙነት አጠናክራለች።ሶስቱ ሐገራት ከሶማሊያ ጋር የነበራቸዉን ግንኙነት ያጠናከሩበት ምክንያት ለየቅል፣ አንዳዴም ያንዱ ምክንያት ከሌለኛዉ የሚቃረን፣ የግንኙነት ደረጃዉም የተለያየ ነዉ።ይሁንና የአፍሪቃ ቀንድና የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጉዳይ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰዒድ እንደሚሉት ሶማሊያ አዳዲስ ያፈራቻቸዉ ወይም በጣም የተጠጋቻቸዉ ወዳጆችዋ የኢትዮጵያ ሠራዊት በተለይ-የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ባጠቃላይ ከሶማሊያ ቢወጣ ሊፈጠር የሚችለዉን የፀጥታ ክፍተት ለመድፈን ይጠቅሟታል።

«እንግዲሕ እየተጠበቀ ነዉ፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ ሊወጣ እንደሚችል።ምናልባት የሌላዉም አፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ያን ያሕል አስፈላጊ ላይሆን ይችላል።ምክንያቱም የሶማሊያ መንግስት ከቱርክ፣ ከግብፅና ከኤርትራም ጋር ጥሩ ግንኙነት እየመሠረተ፣ ሠራዊት የማሰልጠን ስምምነት እያደረገ ነዉ።ሥለዚሕ (የሶማሊያ መሪዎች) ዕድል ከተሰጣቸዉ፣ ፋታ ከተሰጣቸዉ ሕብረተሰቡ ከተቀበላቸዉ አሸባብን ይሁን ሌሎች አሸባሪዎችን ለማሸነፍና ሠላም የመፍጠር ዕድሎች ትላልቅ ሊሆኑ ይችላሉ።»

ዶክተር ሙከረም እንደሚያምኑት ግን ቱርክ ከሶማሊያ ጋር ካላት የምጣኔ ሐብት ግንኙነት ያልተናነሰ ከኢትዮጵያም ጋር አላት።በዚሕም ምክንያት በአዲስ አበባና ሞቃዲሾ መካከል የተነሳዉን ጠብ ለማርገብ ምናልባት ከመሸምገል ያለፈ ላንዱ ወይም ለሌላዉ መወገንዋ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ። 
ይሕ በቀር የቱርክ ይሁን የሌሎቹ ሐገራት ሠራዊት ቀርቶ ከእንግዲሕ የሚሠለጥነዉ የሶማሊያ ሠራዊት እንኳን ዉጊያ ያጠነከረዉን የኢትዮጵያን ወይም የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊትን ተልዕኮ ይተካል የሚለዉን ሐሳብም ዶክተር ሙከረም  አይቀበሉትም።የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ሶማሊያ የሠፈረዉ ከ2007 ጀምሮ ነዉ።17 ዓመቱ።በዚሕ ግዜ ዉስጥ ከአሸባሪዎች ጋር ሲዋጋ ሕይወት እየገበረ ያዳበረዉ ልምድ በቀላሉ የሚተካ አይሆንም እንደ-ዶክተር ሙከረም።
                             
«(ሌሎች ኃይሎች) ወደ ሶማሊያ መጥተዉ ሠላም የማስከበር ዘመቻዉ ላይ ዉጤት ያመጣሉ የሚል ግምት የለኝም።----አሁን ያለዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ይሁን የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ላለፉት 20፣ አሥራ ምናምን አመታት ዱር፣ ገደሉን፣ ቀማኛ ሌባዉን---ያዉቁታል።»

ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ የመግባቢያ ሠነዱን በፈረሙበት ወቅትምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

 

ኢትዮጵያ፣ የሁለት ጠላቶች የጋራ ጠላት ሐገር

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ከሞቃዲሾ መሪዎች እኩል አሸባብም ተቃዉሞታል።የአሸባብ መሪዎች በቅርቡ ባሰራጩት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስትን ርምጃ «የመስቀል ጦረኞች ወረራ» ተቀፅላ በማለት አዉግዘዉታል።ቡድኑ ኢትዮጵያን ለመበቀል ዝቷልም።እንደገና ዶክተር ሙከረም።

«እራሳቸዉን አል ሸባብ አል ሐረካቱል ሙጃሒዲን ነዉ የሚሉት።የአዓብይ አሕመድን ያሁኑን ሥምምነት ሶማሊያ ላይ የታወጀ የመስቀል ጦርነት እርምጃ ነዉ ብለዉ ያወጡት መግለጫ---»
እስካሁን ከመግባቢያነት ያላለፈዉ የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ስምምነት የሶማሊያ መንግስትንና ቀንደኛ ጠላቱን አል ሸባብን እንደ ጥሩ ወዳጅ አንድ አቋም ማስያዙ ለብዙዎች አስገራሚ ነዉ-የሆነዉ።

ከአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ጋር ላለፉት 17 ዓመታት ከሚዋጋዉ የአሸባብ ኃይል በከፊልምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance

ያምድር ግን ለጠብ፣ፍቅር፣ ለግጭት-ድርድር፣ ለመወዳጀት መጣጠላላት ፍርርቅ በርግጥ እንግዳ አይደለም።ባለፈዉ ወር ሌላም ታከለበት። ISIS በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የዓለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን መሪ አቡ ሐፍስ አል ሐሺሚ አል ቁሬይሺ ከሶሪያ በየመን አቋርጠዉ ሶማሊያ መግባታቸዉ ተወርቷል።ወሬዉ እዉነት ሐሰትነቱ በዉል አልተረጋገጠም።
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ግን ባለፈዉ ግንቦት ማብቂያ ሶማሊያ ዉስጥ የሸመቁ ያላቸዉን የISIS ተዋጊዎችን ካየር መደብደቡን አስታዉቋል።የጦሩ አዛዦች እንዳሉት ጦራቸዉ ከቦሳሳሶ 80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ዳአዳር አካባቢ ላይ በከፈተዉ ጥቃት ኢላማ ካደረጋቸዉ ሰዎች አንዱ በሶማሊያ የአይ ሲስ መሪ አብዱቃድር ሙእሚን  ናቸዉ።

ሶማሊያ ከመጪዉ ጥር ጀምሮ ለ2 ዓመት የሚቆየዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ተመርጣለች።በጦርነት፣ ሽብር፣ ግጭትና ዉዝግብ ለምትዳክረዉi ሐገር ብልጭ ያለ ተስፋ ነዉ።ተስፋዉ ይለመልም  ይሆን?ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW