ማሕደረ ዜና፣ የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት
ሰኞ፣ ጥቅምት 5 2016
የአረብ ሐገራት መሪዎች የአዉሮጳ፣አሜሪካ ዲፕሎማቶችን እያስተናገዱ ይሻኛሉ።የአረብ ወታደር ፍልስጤሞችን የሚደግፉ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ያግዳል።እስራኤልና ምዕራባዉያን መግስታት በአሸባሪነት የፈረጇቸዉ ሐማስና ሒዝቡላሕ ወደ እስራኤል ሮኬት ያወነጭፋሉ።የእስራኤል ጦር ጋዛን ከሰዎች መኖሪያ ግዛትነት ወደ አስከሬን፣ ፍርስራሽ መከመሪያነት እየለወጣት ነዉ።የዓለም ሕዝብ አስከሬን፣ቁስለኛ፣ ታጋችና ተፈናቃይ ያሳላል።ሁለተኛ ሳምንት።
የሁለቱ ደመኞች ቁንፅል ወግ
እሳቸዉ።የስድስተኛ ክፍል አስተማሪያቸዉ ሩት ሩቤንስታይን «ፃፉት» እንደተባለዉ የያኔዉ የእየሩሳሌም አዳጊ ወጣት ትሁት፣ ለመርዳት ዝግጁ፣ ኃላፊነት የሚሰማዉ፣ ቀጠሮ አክባሪ፣ተግባባቢ፣ ቀልደኛ ጎበዝና ንቁና አክባሪ ነበር።እንደ ፖለቲከኛ ግን በርግጥ ሰዉዬዉ ሌላ ናቸዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ነታንያሁ። ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ደግሞ ለጠላታቸዉ ምሕረት የለሽ ።
«ሐማስ ISIS ነዉ።ISIS እንደወደመ ሁሉ ሐማስም ይወድማል።ከመንግስታት ማሕበረሰብ ሊተፋ ይገባል።»
የ1948ቱ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የዓረብ እስራኤል ጦርነት በእስራኤል የበላይነት ቆሟል።እንደ አብዛኛዉ የተማረ እስራኤላዊ ቤተ ሰብ ሁሉ የታሪክ አጥኚዉ የፕሮፌሰር ቤንዚዮን ኔታንያሁ ቤተሰብም የጦርነቱን ድል፣ የአዲሲቱን ሐገር ግንባታ ልፋትና-ፍጥነት እያነሳ ሲጥል 1949 ተገባደደ።
ጊዜዉ ይሮጣል።በጦርነቱ ወቅት ሸሽተዉ ኻን ዩኑስ-ጋዛ ስደተኞች ጣቢያ የሰፈረዉ የፍልስጤም ሕዝብ በዚያች ጠባብ መጠለያ ጣቢያ ታጭቆ ርዳታ ይጠብቃል።አንደ ሁሉም ተፈናቃይ ፍልስጤማዊ የመስሪ ቤተሰብም ምፅዋት ጠባቂ ነዉ።
የመስሪ ቤተ ሰብ ጋዛ ዉስጥ ለዕለት ጉርሱ የለጋሾችን እጅ አንጋጥጦ ሲጠብቅ፣ በድል መልካም ትዝታ፣ በሐገር ግንባታ ርካታ፣ በወደፊቱ ብሩሕ ተስፋ የተመላዉ ለኔታንያሁ ቤተ ሰብ ሁለተኛዉ ወንድ ልጅ ተወለደ።ጥቅምት 21።1949።ቴል አቪቭ።
እሱ።ወጣቱ ቢኒያሚን ዌይንኮት,ቻልተንሐም ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን ሲከታተል ኻን ዩኑስ-ጋዛ የተጠለለዉ የመስሪ ቤተሰብ ወንድ ልጅ ወለደ።ስሙንም መሐመድ ዲያብ ኢብራሒም መስሪ አሉት።
ቢኒያሚን ዩኒቨርስቲ እያማረጠ፣ ከዩናይትድ ስቴስ-እስራኤል እያቀያየረ፣ ከወታደርነት-የንግድ ኩባንያ መሪነት፣ እያለዋወጠ ኖሮ በ1980ዎቹ አጋማሽ ዲፕሎማት ሆኑ።(ከእንግዲሕ አንቱ ናቸዉ)
መሐመድ ባንፃሩ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ዉስጥ ከመንደር መደር እየተዘዋዋወረ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን አጠናቀቀ።ቀልደኛ፣ ሥነጥበብ አፍቃሪ ግን አንዴ የያዘዉን የማይለቅ ይሉታል።ከጋዛ እስላማዊ ዩኒቨርስቲ በፊዝክስ፣ ኬሚስትሪና ባዮሎጂ ተመረቀ።በዩኒቨርስቲ ቆይታዉ ሳይንስ ቢያጠናም፣ የዩኒቨርስቲዉ የመዝናኛ ክበብ ኃላፊ ነበር።
በ1987 ኔታንያሁ በዩናይትድ ስቴትስ የእስራኤል አምባሳደር በነበሩበት ወቅት ፍልስጤሞች የቀሰቀሱት የመጀመሪያዉ ታላቅ አመፅ ወይም ኢንቲፋዳሕ ሲቀጣጠል ወጣቱ መሐመድ አክራሪዉን ደፈጣ ተዋጊ ቡድንሐማስንተቀየጠ።
ወትሮም እድሜ፣ አስተዳገግ፣ ኑሮ፣ እምነት፣አስተሳሰብ ያቃራናቸዉ ሁለቱ ሰዎች አንዳቸዉ ሌላቸዉን ሳያዉቁ የፖለቲካ ደመኛ ጠላቶችም ሆኑ።ኔታንያሁ ዲፕሎማትነቱን፣ የምክር ቤት እንደራሴነቱን፣ ሚንስትርነቱን ተራምደዉ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ርካብ ሲረግጡ የ16 ዓመት ታናሽ ግን ያሁን ቀንደኛ ጠላታቸዉ ኢዘ ዲን አል ቃስም ብርጌድ የተባለዉ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ ሆነ።
ስሙንም መሐመድ ድይፍ ብሎ ቀየረዉ።ሮይተርስ እንደዘገበዉ በ1989 የእስራኤል ፀጥታ አስከባሪዎች ይዘዉ ለ16 ወራት ታስሯል።የእስራኤል ቀንደኛ ጠላት ለዩናይትድ ስቴትስም ከ2000 ጀምሮ አሸባሪ ነዉ።እስራኤል ከሰነዘረችበት የግድያ ሙከራዎች ሰባቴ አምልጧል።ግን አንድ አይኑን አጥቷል።እግሩን ክፉኛ ቆስሏል።ጓደኞቹ፣ ሚስቱ፣ የ7 ወር ሕፃን ልጁና የ3 ዓመት ሴት ልጁ ተገድለዋል።
የ20 ዓመት ጎረምሳ እያለ ከተነሳዉ በስተቀር ፎቶ ግራፍ የለዉም።ተንቀሳቃሽ ስልክ አይዝም።በመገናኛ ዘዴዎች ብዙ አይናገርም።ባለፈዉ ቅዳሜ ግን እንዲሕ አለ።
«በፈጣሪ ርዳታና ብርታት የሚከተለዉን እናስታዉቃለን።በመጀመሪያዉ የአል አቅሳ ጎርፍ ዘመቻ በጠላት ታላሚዎች፣ በአዉሮፕላን ማረፊያዎችና በወታደራዊ ተቋማት ላይ በ20 ደቂቃ ዉስጥ 5 ሺሕ ሮኬቶችና ሚሳዬሎች አወንጭፈናል።ይሕ የዓለም የመጨረሻዉን ግዛትን በኃይል የያዘ፣ የመጨረሻዉን የዘር መድሎ ሥርዓት ለማስወገድ የታላቅ አብዮት ዕለት ነዉ።»
ከእስራኤል በተጨማሪ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና ብሪታንያ በአሸባሪነት የፈረጁት የመሐመድ ደይፍ ቡድን በሚሳዬል፣ በሮኬት፣ በዓየር፤ በባሕርና በምድር ባዘመታቸዉ ተዋጊዎቹ በከፈተዉ ድንገኛ ጥቃት ከ1400 በላይ እስራኤላዉያንና የሌሎች ሐገራት ዜጎች ተገድለዋል።ከ2800 በላይ ቆስለዋል።ከ100 የሚበልጡ ታግተዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዳሉት ድንገተኛዉ ጥቃትና ጥፋት በእስራኤል ታሪክ ታይቶ አያዉቅም።
አፀፋ ዛቻ፣ፉከራዉ ከቴል አቪቭ፣ ከዋሽግተን፣ ከበርሊን፣ ከለንደን፣ከፓሪስና ብራስልስ ሲንቆረቆር የእስራኤል ጦር ጋዛን በቦምብ ሚሳዬል ያነፍራት ያዘ።
የጋዛን ከተማና መንደሮች የአየር ክልልን እንዳሻቸዉ የሚፏልሉበት የእስራኤል የጦር ጄቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት እንደሚሉት መኖሪያ ቤቶች፣ ትምሕርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን ሳይለዩ ያጋዩት ያዙ።
ምዕራባዉ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ረመላሕ ከተማ ዉስጥ ተሽመድምዶ የተቀመጠዉ የፍልስጤም መስተዳድር ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሼታያሕ ዛሬ እንዳሉት እስከ ዛሬ ጧት ድረስ ከ2800 በላይ ፍልስጤማዊ አልቋል።
«ከ2808 በላይ ሰዎች ተሰዉተዋል።11 ሺሕ ቆስለዋል።እነዚሕ እያንዳዳቸዉ የየራሳቸዉ ታሪክ፣ ኑሮ የነበራቸዉ።ታሪክ፣ መፃኤ ሕይወት ያለዉ የሰለጠ ሕዝብ አካል የነበሩ ነበሩ።ግዛቶችን በኃይል የያዙት ሐይላት እንዳሉት ሰብአዊ አዉሬዎች አይደሉም።ሕዝባችን እጅ አይሰጥም።»
የጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ መንግስት ከቦምብ ሚሳዬል ለተረፈዉ የጋዛ ሕዝብ ዉኃ፣ምግብ፣ መድሐኒት እንዳይደርሰዉ አግዷል።ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጠዉ ሕዝብ ደግሞ ወደ ደቡባዊ ግዛቶች እንዲሰደድ የእስራኤል ባለስልጣናት ባለፈዉ ሳምንት አዘዋል።
ዛሬ በአሜሪካኖች ልመና ለጋዛ ዉኃ እንዲደርስ ተፈቅዷል።ምክንያትን ተቀብሎ እዉነትን መናገር የሚያስከትለዉን መዘዝ የሚያዉቁት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎች የአገም ጠቀም መልዕክታቸዉን አላቋረጡም።
ለእስራኤል ተጨማሪ ወታደራዊ ርዳታ የላከችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ጦሯን በመርከብ ሚንስትሮችዋን ባዉሮፕላን ወደ መካከለኛዉ ምስራቅአዝምታለች።የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን የዮርዳኖስ፣የሳዑዲ አረቢያ፣የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የባሕሬን፣ የቀጠርና የግብፅን ገዢዎች አነጋግረዉ ዛሬ ወደ እስራኤል ተመልሰዋል።
የብሊንከንና የሌሎች ምዕራባዉያን መንግስታት ሚንስትሮችና ዲፕሎማቶች ከአንዱ ርዕሰ ከተማ ወደ ሌላዉ የመብረራቸዉ ምክንያት በሐማስና በእስራኤል መካከል ተኩስ አቁም እንዲደረግ ለማግባባት ነዉ የሚል ዘገባ እየተናፈሰ ነዉ።የእስራል ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ዳንኤል ሐጋሪ እንዳሉት ግን ተኩስ አቁም ብሎ ነገር የለም።
«ባሁኑ ወቅት እንዲሕ ዓይነት ተኩስ የማስቆም ጥረት የለም።አዳዲስ መረጃዎችን ለሕዝቡ እናሳዉቃለን።በገዳዩ ድርጅት ሐማስ ላይ የከፈትነዉን ጦርነት እንቀጥላለን። የታገቱና የጠፉ ሰዎችን በሚመለከት የሚለወጥ ነገር ካለ እርምጃዎቹን በሙሉ ለሕዝብ እናሳዉቃለን።»
በእስራኤልና በምዕራባዉያን መንግስታት ሌላዉ በሸባሪነት የተፈረጀዉ የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕ አልፎ አልፎ ከእስራኤል ጦር ጋር ሮኬትና ሚሳዬል ይወራወራል።የእስራኤል ጦር ሐገሪቱን ከሊባኖስ ጋር በሚያዋስነዉ ድንበር አካባቢ በ28 መንደሮች የሚኖሩ እስራላኤላዉያንን ከየአካባቢዉ እያሸሸ ነዉ።
ከሐማስ እስከ ሒዝቡላሕ ያሉ ደፈጣ ተዋጊዎችንም፣ ከደማስቆ እስከ ሰነዓ የሚገኙ ገዢዎችንም ዩናይትድ ስቴትስንና እስራኤል የሚቃወሙትን የመካከለኛዉ ምስራቅ ኃይላትን በሙሉ ትረዳለች የምትባለዉ ኢራን እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስን እያስጠነቀቀች ነዉ።
የኢራን ባለስልጣናት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የከፈተችዉን ድብደባ አጠናክራ ከቀጠለች ባካባቢዉ ያሉ «ፓርቲዎች» ያላቸዉ ኃይላት በሙሉ ጣታቸዉ ቃታ ላይ ነዉ በማለት ትናንት አስጠንቅቀዋል።የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ ዛሬ «ፅዮናዊት» ያሏት እስራኤል ለምትፈፅመዉ ወንጀል ዩናይትድ ስቴትስም መጠየቅ አለባት ብለዋል።
«ፅዮናዊዉ ሥርዓት ለሚፈፅመዉ ወንጀል የአሜሪካ መንግስት ተጠያቂ መሆን አለበት።ፅዮናዊዉ ሥርዓት በሚጨቁነዉ የፍልስጤም ሕዝብ ላይ ለሚያደርሰዉ በደል ያለዉን ከፍተኛ ጉልበት በመጠቀም ሁሉንም ድጋፍ የሚሰጠዉ የአሜሪካ መንግስት ነዉ።የጦር መርከቦችን ወደ አካባቢዉ የባሕር ክልል ማዝመት ጨቋኞች በተጨቋኞች ላይ የሚያደርሱትን (ጭቆና) ከመደገፍ ሌላ፣ ሌላ ትርጉም የለዉም።»
የቃላት እሰጥ አገባ፣ ፉከራ፣ ቀረርቶዉ ቀጥሏል።የምዕራባዉያን ሚንስትሮች በየደረሱበት የአረብ ከተሞች የየሐገሩ ሕዝብ ለፍልስጤም ያለዉን ድጋፍ ባደባባይ ሰልፍ እየገለጠ ነዉ።ታዛቢዎች እንደሚሉት የአረብ ገዢዎች ከታች ሕዝባቸዉ፣ ከላይ የዋሽግተን-ቴል አቪቭ-ብራስልስ-ለንደን ኃይለኞች የሚያደርሱባቸዉን ጫና በዘዴ ለማለፍ ሐማስን «ጫዳ» የሚያደርጉበትን ብልሐት እያዉጠነጠኑ ነዉ።
የዓለም ሕዝብም የጦርነት ግጭት፣ መጠቃቃት፣ መጠላለፉን ትክክለኛ ምክንያት\ ከማሳመሰያዉ ለመለየት ግራ እንደተጋባ አስከሬን፣ ቁስለኛ፣ ታጋች-ስደተኛ ይቆጥራል። ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ