1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የእስራኤል መጠቃት፣ የጋዛ ጦርነትና ድርድር 2ኛ ዓመት

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ መስከረም 26 2018

በሚንስቴሩ መዘርዝር መሠረት የጋዛዉ ጦርነት እንደ ሐማስ መሪዎች ሁሉ ከጆናታን ሽታንይበርግ-እስከ ቶሞር ግሪንበርግ ያሉ 6 ኮሎኔሎችን፣ 11 ሌትናት ኮሎኔሎችን፣ ከ70 በላይ ሻለቆችን ጨምሮ እስካለፈዉ ሳምንት ድረስ 913 የእስራኤል ወታደሮችን ሕይወት አጥፍቷል

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።ዋሽግተን ዉስጥ ሲወያዩ።መስከረም 29፣ 2025
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።ዋሽግተን ዉስጥ ሲወያዩ።መስከረም 29፣ 2025 ምስል፦ Jonathan Ernst/REUTERS

ማሕደረ ዜና፣ የእስራኤል መጠቃት፣ የጋዛ ጦርነትና ድርድር 2ኛ ዓመት

This browser does not support the audio element.

እሥራኤል ከ1973 ወዲሕ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ ተደፍራለች-ተወርራለች።ጥቅምት 7፣ 2023።ጋዛ ከሰዉ መኖሪያነት ወደ ሕዝብ ማለቂያነት፣ወደ አስከሬን መቀበሪያ-ፍርስራሽ መከመሪያነት ተቀይራለች።ሐማስ ተዳክሟል።እስራኤል በፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ ከብዙዉ ዓለም ጋር ተላትማለች።ነገ ሁለት ዓመታቸዉ።የመጨረሻ ዉጤት ድርድር።የሁለቱ ዓመቱ ጥፋት-ዉድመት፣ የመጨረሻ  ድርድር እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

የሥልታዊ ጠቀሜታ አልባዋ ሠርጥ መከራ

 

በ1956 የስዊዝ ካናል ጦርነት በሚባለዉ ዉጊያ እስራኤል፣ ታላቅዋ ብሪታንያና ፈረንሳይ ግብፅን ሲደበድቡ የእስራኤል ጦር ትንሺቱን የፍልስጤሞች መኖሪያ ሰርጥ ጋዛን ለጥቂት ወራት ተቆጣጥሯት ነበር።በ1967ቱ የዓረብ እስራኤሎች ጦርነት እስራኤል ያቺን መከረኛ ግዛት ዳግም ተቆጣጠረቻት።በ1956ቱ ጦርነት የእስራኤልን 202ኛ ተወርዋሪ ብርጌድ ፣ በ1967ቱ ጦርነት ደግሞ የታንከኛ ክፍለ ጦርን አዘዉ ግብፅን የወጉት አርየል  ሻሮን እንደ ጠቅላይ ሚንስትር እስራኤል ሲመሩ እስራኤል ጋዛን ለቅቃ እንድት ወጣ አዘዙ።ነሐሴ ነበር 2005።ምክንያት፣- የያኔዋ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ እንደዘገበችዉ ጋዛን ለእስራኤል ሥልታዊ ጠቀሚታ የላትም የሚል ነበር

«የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፣ እስራኤል ጋዛን ለዘላለም መቆጣጠር አለባት የሚል ተስፋ ከነበራቸዉ አንዱ ነበርኩ።ነገር ግን አሁን እንደተረዳሁት ከስልት አኳያ አይቻልም።»

እስራኤል የአይሁድ የሠፈራ መንዶሮችን፣ የጦር ሠፈሮችና ተቋማቷን አፈራርሳ ከጋዛ ሠርጥ ወጣች።ቀስ በቀስ ግን የጋዛን የዓየር፣ የምድር፣ የባሕር መገናኛዎችን በሙሉ ዘጋች።ከጋዛ ጋር የሚያዋስናትን ድንበርም በግንብ አጠረች።መዉጪያ መግቢያዋ የተዘጋባት፣ ድንበሯ በኮንክሪት፣ የሰዉን እንቅስቃሴ የሚያነፈንፉ የድምፅና የምሥል መሳሪዎች የታጠረችዉ ጋዛ በ1980ዎቹ ለተመሠረተዉ ሐማስ መጠናከሪነት በቂ ነበረች።

41 ሐገራት በአሸባሪነት የወነጅሉት፣በእስራኤልና በዩናይትድ ስቴትስ በጥብቅ የሚታደነዉ፣ዋሻ ለዋሻ የሚፈናጠረዉ ሐማስ የዛሬ ሁለት ዓመት ደቡባዊ እስራኤን ማጥቃት የቻለበት ሚስጥር ለብዙዎች አጠ,ያያቂ፣ አስደናቂ፣ አደናጋሪም ነዉ።ግን ሆነ።

ግጥም ጥሞሹና የአፀፋዉ ግቦች

የዓረብ በተለይም የግብፅና የሶሪያ ጦር ኃይላት የእስራኤል ጠላታቸዉን ከምዕራብና ከሰሜን ምሥራቅ አቃርጠዉ ድንገት ያጠቁት ጥቅምት 6፣ 1973 ነበር።እስራኤሎች የዮም ኪፑር-አረቦች የረመዳን የሚሉት ጦርነት ድንገት የተጫረበት 50ኛ ዓመት በተዘከረ በማግሥቱ ደቡባዊ እስራኤል ጋየች።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ደጋግመዉ እንዳሉት 1200 ሰዎች ተገደሉ።251 ታገቱ።የእስራኤል ጠንካራ አፀፋ ጋዛን ያንቀረቅባት ያዘ።ዓላማዉ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እንዳሉት ሶስት ነዉ።

«ሶስት ግቦችን ቀይሻለሁ።ሐማስን ማጥፋት።ታጋቾችን ማስለቀቅ።ጋዛ ለእስራኤል እንዳታሰጋ ማረጋገጥ።»

የሐማስ ታጣቂዎች ጥቅምት 7 ቀን 2023 ደቡባዊ እስራኤልን ወርረዉ የገደሏቸዉ ሰዎች መታሰቢያ ምስል፦ Ilia Yefimovich/dpa/picture alliance

ከ1948 ጀምሮ እስራኤል ያልተለያት የአዉሮጳ፣ አሜሪካኖችና የተባባሪዎቻቸዉ ሁለንታናዊ ድጋፍም ለጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ መንግሥት ዕቅድ ገቢራዊነት ይንዠቀዠቅ ያዘ።የኔታንያሁ ግብ አንድ ሐማስን ማጥፋት።በሁለት ዓመቱ ጦርነት የእስራኤል ጦር በሺ የሚቆጠሩ የሐማስ ታጣቂዎችን፣ከእስማኢል ሐኒያሕ እስከ መሐመድ ዳይፍ፣ ከያሕያ ሲንዋር እስከ ታናሽ ወንድሙ መሐመድ ሲንዋር የነበሩ የሐማስ የፖለቲካና የጦር መሪዎችን ገድላለች።

የእስራኤል መንግስት የሐማስ ይሁን የሒዝቡላሕ መሪዎች፣ የኢራን ባለሥልጣናትን ይሁኑ የጦር ጄኔራሎችን በገደለ ቁጥር የዋሽግተን ጥብቅ ወዳጆቹ የፖለቲካ፣ የመረጃ፣ የወታደራዊና የፖለቲካ ድጋፍ ተለይቶት አያዉቅም።

                                    

                 ሐማስ ተዳክሟል፣ የእስራኤል ጦርም ተጎድቷል

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን።ጥቅምት 2024።ዘንድሮ ዓመቱ።ባይደን፣ የሐማስ መሪ መገደል ለዓለም «ያመጣል» ያሉት ሠላምም፣ የእሳቸዉ ኃያል ሥልጣንም የሉም።የእስራኤል መከላከያ ሚንስቴር መግለጫ ግን በቀደም ተሰራጭቷል።በሚንስቴሩ መዘርዝር መሠረት የጋዛዉ ጦርነት እንደ ሐማስ መሪዎች ሁሉ ከጆናታን ሽታንይበርግ-እስከ ቶሞር ግሪንበርግ ያሉ 6 ኮሎኔሎችን፣ 11 ሌትናት ኮሎኔሎችን፣ ከ70 በላይ ሻለቆችን ጨምሮ እስካለፈዉ ሳምንት ድረስ 913 የእስራኤል ወታደሮችን ሕይወት አጥፍቷል።ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል እንደዘገበዉ ከ70 በላይ ፖሊሶችም ተገድለዋል።ነገ ሁለት ዓመቱ የኔትናያሁ ግብ-አንድ ተሳክቶ ይሆን?

«ሐማስ ተዳክሟል»ይላሉ በለንደኑ የኪንግስ ኮሌጅ የጦርነት ጉዳይ አጥኚ ማሪና ሚሮን።

«ደሕና፣ ሐማስ በጋዛ ከተማ ዉስጥ ሥላለዉ ጥንካሬ የተለያዩ ዘገቦች አሉ።ሐማስ ከፍተኛ ወታደራዊ ዉድቀቶች አጋጥመዉታል።ይሁንና አሁንም ዳግም የመደራጀት፣ዕዝና ቁጥጥርን የመጠገን አቅምና ችሎታ አለዉ።»

ግብ-ሁለት-ታጋቾችን ማስለቀቅ

 የጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ግብ ሁለት-ታጋቾችን ማስለቅ ነዉ።ሐማስ ካገታቸዉ የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎች ዉስጥ 148ቱ ተለቅቀዋል።ከነዚሕ ዉስጥ የእስራኤል ጦር በኃይል ያስለቀቃቸዉ 8 ብቻ ናቸዉ።ከተቀሩት 135ቱ የተለቀቀቁት በድርድርና በሺሕ የሚቆጠሩ የፍልስጤም እስረኞችን እስራኤልን ለቅቃ ወይም በልዉዉጥ፣ አምስቱ በሐማስ በጎ ፍቃድ የተለቀቁ ናቸዉ።የኔታንያሁ ግብ ሁለት-ተሳክቶ ይሆን? ሌላ ጥያቄ።

ግብ ሶስት-ጋዛ ለእስራኤል እንዳታሰጋ ማረጋገጥ ወይስ ርሕራሔ ማጣት

ግብ-ሶስት የጋዛ ሰርጥን ለእስራኤል የማታሰጋ ማድረግ።ዘገቦች እንዳመለከቱት ሁለት ዓመት በደፈነዉ ጦርነት እስራኤል ከ85ሺሕ ቶን በሚበልጥ ቦምብ ጋዛን ቀጥቅጣለች።የሚሳዬል፣ ድሮን፣ መድፍ፣ አዳፍኔ፣ ጥይቱን ዉርጅብኝ በዝርዝር ያጠኑት አልነገሩንም።የጋዛ ከተማ-መንደሮች፣ ሆስፒታል-ትምሕርት ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት-መኖሪያ ቤቶች፣ ቤተ-እምነቶች ወድመዋል።

የፍልስጤም ባለሥልጣናት እንደሚሉት በትንሽ ግምት ከ70 ሺሕ በላይ ፍልስጤማዊ አልቋል።ከ170ሺሕ በላይ አካሉ ጎድሏል።እስራኤል ርዳታ እንዳይገባ በማገዷ ብቻ በረሐብ ከ400 በላይ ሰዉ ሞቷል።

የእስራኤል ጦር ከገደላቸዉ ፍልስጤማዉያን ከ20 ሺሕ የሚበልጡት ወደፊት እስራኤል እንዳታሰጋ ተደርጋ የምትሰራዉን ጋዛን ሊረከቡ የሚገባቸዉ ሕፃናት ወይም ልጆች ነበሩ።ብራዚሎች የሚያደርጉት ቢጨንቃቸዉ ሐማስ ለገደላቸዉ 37 እስራኤላዉያን ልጆችና ለ20ሺዉ ፍልስጤማዉያን ሪዮ ዲጄኔሮ ዉስጥ መታሰቢያ አቆሙላቸዉ።

የጋዛ ትልቅ ከተማ ጋዛ ከተማ በጦርነቱ መጀመሪያ ሰሞን በ,እስራኤል ጦር ጥቃት ሥትነድ።ጥቅምት 8 ቀን 2023ምስል፦ Fatima Shbair/AP Photo/picture alliance

መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት የእስራኤል ጦር ከ250 በላይ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ዘዴ ሠራተኞች ገድሏል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ባንድ ጦርነት በርካታ ባልደረቦቹ የተገደሉት ጋዛ ዉስጥ ነዉ።ድርጅቱ እንዳስታወቀዉ ጋዛ ዉስጥ የራሱን ሠራተኞች ጨምሮ ከ543 የርዳታ ሠራተኞች ተገድለዋል።1500 የጤና ባለሙያዎች ተገድለዋል።

በቴል አቪቭ ዩኒቨርስቲ የግጭት መፍትሔና የድርድር ክፍለ-ትምሕርት ሐላፊ ኮሬይ ጊል ሹስተርን «ሰብአዊነት መጥፋቱ ያሳስባል» ይላሉ።

«እስራኤልን በተመለከተ ትልቁ ፍርሐቴ ርሕራሔ ማጣት ነዉ።ሰዎች ለሕፃናት፣ ለሽማግሌዎች ወይም ለሕሙማን እንኳን መራራት አቁመዋል።ምክንያቱም በየትኛዉም ማሕበረሰብ የካንሰር በሽተኛ አለ።መንቀሳቀስ የማይችሉ ሽማግሌዎች አሉ።ልጆች አሉ።በጦርነቱ አቅላቸዉ የተቃወሰ አለ።ለነሱ ጭምር ርሕራሔ የለንም።»

የጋዛዉን ጦርነት በመቃወምና ታጋቾች እንዲለቀቁ በመጠየቅ ቴል አቪብ እስራኤል ዉስጥ በተደጋጋሚ ከሚደረጉ የአደባባይ ሰልፎች አንዱ።ምስል፦ Eyal Warshavsky/SOPA Images/ZUMA/picture alliance

ጭካኔዉ ጠንቷል።ግብ ሶስት መሳካት አለመሳካቱ ግን አይታወቅም።

የምዕራባዉያን የአቋም ሽግሽግ-የትራምፕ ዕቅድ 

የእስራኤል ጦር ዓለም አቀፍ የባሕር ክልል ድረስ እየሔደ ማጥቃቱ የዓለምን ሕዝብ አቋም ለዉጦቷል።ሐቻምና ይሔኔ እስራኤል ስትጠቃ ከእስራኤሎች እኩል አዝኖ ሐማስን ያወገዘዉ የዓለም ሕዝብ ዘንድሮ የእስራኤልን ርምጃ በየአደባባዩ እያወገዘ ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያም ከላሆር እስከ ናይሮቢ፣ ከኒዮርክ እስከ ፓሪስ፣ ከለንደን እስከ ሊዝበን፣ ከቴል አቪቭ እስከ ኩዊቶ (ኤኳዶር) ዓለም ሌላ ርዕሥ አልነበረዉም።

ሕዝባቸዉ በየአደባባዩ የሚያደርገዉ ግፊት የጠናባቸዉ የምዕራብ አዉሮጳ መሪዎች እየተግተለተሉ ለፍልስጤሞች የመንግሥትነት እዉቅና ሰጡ።ኔታንያሁ በሚጭሩት ጦርነት ዘለዉ በመግባት ወይም  ለኔታንያሁ መንግስት ፍፁም ድጋፍ በመስጠታቸዉ ምክንያት አረብ-ሙስሊም እየራቃቸዉ፣ ሕዝብ እየተከፋባቸዉ፣ ከተቀረዉ ዓለምም እየተነጠሉ የመጡት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጥብቅ ወዳጃቸዉን ኔታንያሁን በቅርቡ «በቃሕ» አሉሏቸዉ።ወይም ያሉ መሰሉ።

«ይሕን ጉዳይ እንዳደራጅ የረዱኝን ሐገራት በሙሉ ማመስገኝ እወዳለሁ።ቀጠር፣ ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ግብፅ፣ ዮርዳኖስ እና ሌሎች ብዙ ሐገራት።ብዙ ሰዎች አበክረዉ ጥረዋል።ይሕ ታላቅ ዕለት ነዉ።እንዴት ገቢር እንደሚሆን እናያለን።የመጨረሻዉ ቃል ወደ ተጨባጭ ድርጊት መለወጥ አለበት።

ትራምፕ ያስረቀቁትን ባለ 20 ነጥብ የተኩስ አቁም ዕቅድ እስራኤልም ሐማስም መቀበላቸዉን አስታዉቀዋል።ብዙ ሐገራትም ደግፈዉታል።ዕቅዱ ገቢር ሥለሚሆንበት ሥልት ለመነጋገር የእስራኤል፣ የሐማስ፣ የአረብና የዩናይትድ ስቴትስ ተደራዳሪዎችና አደራዳሪዎች ዛሬ ሻርም-አልሼይኽ-ግብፅ ዉስጥ ተሰብስበዋል።

ቴሕራን-ኢራን ዉስጥ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት የሐማስ ፖለቲካዊ ክንፍ መሪ ኢስማኤል ሐኒያሕ ምስል፦ Iran's Presidency/WANA/REUTERS

የፍልስጤምና የእሥራኤሎች ቂም-ቁርሾ

የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዮሐን ቫደፉልም ድርድሩን በተዘዋዋሪ ለመርዳት ወደ ግብፅ እንደሚጓዙ አስታዉቀዋል።ቫደፉል ዛሬ እንዳሉት የጋዛዉ ጦርነት መቆም አለበት።ፍልስጤማዊዉ የፖለቲካ ሳይንቲስት ኻሊል ሺካኪ እንደሚሉት ግን የትራምፕ ዕቅድ ገቢር ሆነም-አልሆነ የሁለት ዓመቱ ጦርነት ዘመናት ያስቆጠረዉን የፍልስጤምና የእስራኤል ሕዝብን ልዩነት ወደለየለት ጥላቻ አንቻሮታል።

«የሁለት ዓመቱ ጦርነት ፍፁም ጭካኔ የታየበት ነዉ።ሁለቱ ማሕበረሰቦች አንዱ ሌላዉን ያደርገዋል ብሎ ከሚያስበዉ፣ ወይም ከሌላዉ ባሕሪ በመነሳት የሌላዉን ሰዉ መሆን ጭምር ከማይቀበሉበት ደረጃ ደርሰዋል።»

ብቻ የሻርም አል-ሼኹ ጉባኤ ከተሳካ፣ ጋዛ ወደመች፣ ሐማስ ተዳከመ፣ ኔታንያሁ ከሰሩ፣ ትራምፕ አተረፉ ማሰኘቱ አይቀርም።ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW