ማሕደረ ዜና፣ የዓለም መሪዎች እየተግባቡ ይሆን ወይስ ግራ እያጋቡ
ሰኞ፣ መስከረም 19 2018
በየአመቱ መስከረም እንደሚሆነዉ ዘንድሮም ለ80ኛ ዓመት ዲፕሎማቶች ቃላት እየሰነጠቁ-ሠፉበት፣ የኃለኞችን ስሜት-ፍላጎት ለማስፈፀም ጠብ ርግፍ አሉበት።ሰላዮች ተመሳጠሩ-ተቧጨቁበት።ጋዜጠኞች፣አስተናጋኞች፣ ደላሎች ተራወጡበት።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ።ኒዮርክ።መሪዎች አወሩ፣ተወቃቀሱ-ተመሰጋገኑ፣ተሸረዳዱበትም።«በጦርነት ዓመድ ላይ የተመሠረተዉ ድርጅት የመጀመሪያ ትልቅ ዉሳኔ የአዉቶም ጦር መሳሪያ ምርትን መቆጣጠርና ማስወገድ ነበር።1945(ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)።ዘንድሮ በ80 ዓመቱም ከጉባኤተኞች ትላልቅ ርዕሥ አንዱ-አቶሚክ ነበር።በ1947 የጠቅላላ ጉባኤዉ አወዛጋቢ ርዕሥ የፍልስጤም-አይሁድ የመንግሥትነት ዕቅድ ነበር።ዘንድሮ በ78ኛ ዓመቱም ትልቁ አወዛጋቢ ርዕሥ ፍልስጤም እስራኤል ጉዳይ ነዉ።ዓለም እየተግባባ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
ዓለም የገጠማት ፈተና በጉተሬሽ እምነት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመስራቾቹ-እስከ ዘንድሮ ተረካቢዎቹ ለ80 ዓመታት እንዳሉት የዓለምን ሠላም በጋራ ለማስከበር የቆመ የዓለም ማሕበር ነዉ።ዓለም ግን ዛሬም ሠላም የላትም።የዓለምን ሁለንተናዊ ሒደት የመዘወር አቅም ያላቸዉ መንግሥታት መሪዎችም ለጋራ ሠላም ከመቆም ይልቅ ለተናጥል ጥቅምና የበላይነት እየተራወጡ ነዉ።የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እንዳሉት ደግሞ የዘንድሮዉ ጠቅላላ ጉባኤ የተደረገዉ ዓለም በጆኦ ፖለቲካ ልዩነት በተከፋፈለችበት፣ ግጭቶች በተስፋፉበት፣ ለሕግ ተጠያቂነት በጠፋበት ወቅት ነዉ።
«የምንሰበበዉ በማዕበል በሚናወጥ፣ አልተርፎም በማይቀዘፍበት ባሕር ላይ (በምንዋኝበት ወቅት) ነዉ።የጂኦ ፖለቲካዊ ልዩነት እየሰፋ፣ ግጭቶች እየበዙ፣ የሕግ ጥሰትና የተጠያቂነት እጦት እየተበረከተ ነዉ።ምድራችን አለቅጥ እየጋለች፣አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንበለ-ቁጥጥር እየተመረቱ፣ መበላለጥ በየሰዓቱ እየደገ፣ብሔራዊ ትብብር እየከሰመ፣ ግፊቶች በእድሜያችን አየተናዉ በማናዉቃዉ ደረጃ እየናሩ ነዉ።»
የዓለም መሪዎች እየተግባቡ ይሆን ወይስ ግራ እያጋቡ
የዓለም ትልቅ ዲፕሎማት አቶኒዮ ጉተሬሽ እና የዓለም ልዕለ ኃያል ሐገር የዩናትድ ስቴትስ መሪ ዶናልድ ትራምፕ ፊት ለፊት ሲገናኙ ይሞጋገሳሉ።ይደናነቃሉም።ባለፈዉ ሳምንት ጉተሬሽ ከትራም ጋር ሲነጋገሩ ትራምፕ ሰላም ለማስፈን የሚያደርጉትን ጥረት አደነቁ።
«በሌላ በኩል ቀና በሆነ መንገድ የምንተባበርባቸዉ ብዙ መስኮች እሉ ብዬ አምናለሁ።በጣም አስፈላጊዉ ነገር ሠላም ማስፈን ነዉ።እርስዎም ሰላምን የዘመነ ሥልጣንዎ ዋና ግብ አድርገዉ መርጠዋል።አመሰግናለሁ።»
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕከጥቂት ሳምንታት በፊት።«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብዙ አቅም አለዉ።ይሁንና ይሕን አቅሙን እየሠራበት አይደለም።በእዉነቱ ለረጅም ጊዜ እየሰራበት አይደለም።ብዙ ተስፋ ነበር ግን እዉነቱን ለመናገር በትክክል እየተመራ አይደለም።»
የጉተሬሽ አፀፋ።
«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለያዩ አካባቢዎች የሠላም ድርድር እንዲደረግ በጣም ብዙ ጠንካራ ጥረቶች ያደርጋል።ይሁንና ካሮትም አርጩሜም የለንም።በጆኦ ፖለቲካ በተከፋፈለችዉ ዓለም ካርቶና አርጩሜ ሥለሌለን በየግጩቱ የሚዋጉ ኃያላትን ሠላም እንዲያስፍኑ ማግባባት ሲባዛ ከባድ ነዉ።ባሁኑ ጊዜ ካሮትና አርጩሜ ያላት ዩናይትድ ስቴትስ ናት።እና ሁለቱ በሚያስፈልግበት ወቅት አቅሙ ያላት ቢያንስ የተወሰኑ የሠላም ሒደቶች ዉጤት እንዲያመጡ ማድረግ ይቻላል።»
እየተግባቡ ይሆን ወይስ ግራ እያጋቡ።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በዘንድሮዉ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ለማድረግ ሲሔዱና ሲናገሩ ያጋጠማቸዉ መሰናክል ደግሞ የትልቂቱን ሐገርና የትልቁን ድርጅት ግራ-አጋቢ ግንኙነት ይበልጥ አወሳስቦታል።ትራምፕ ይጓዙበት የነበረዉ ተሽከርካሪ ደረጃ (ስኬለተር) ድንገት ቆመ።ንግግር ሲያደርጉ ደግሞ ፅሑፋቸዉን የሚያነብቡበት (ተዘዋሪ-አትሮኖስ) teleprompter ተቋረጠ።«ሻጥር» አሉት ሰዉዬዉ።
የኔታንያሁ የድል ብሥራት፣ የአዉሮጶች ተቃርኖ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ መጀመሪያ ካሳለፋቸዉ ትላልቅ ዉሳኔዎች አንዱ ዓለምን ከአቶሚ ጦር መሳሪያ ሥጋት ለማላቀቅ ልዩ ኮሚሽን መሰየም ነዉ።በዘንድሮዉ ጉባኤ በርካታ መሪዎች ከተናገሩበት ጉዳይ አንዱ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሥጋት ነዉ።
በተለይ የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር የእስላማዊቱ ሪፐብሊክ ጠላቶችም ወዳጆችም መነጋገሪያ ነበር።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ባደረጉት ንግግር የእስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይላት ባለፈዉ ሰኔ ባደረጉት ድብደባ ኢራን ኑክሌር ቦምብ ትታጠቃለች የሚለዉን ሥጋት አስወግደዋል።
«ኢራን የኑክሌር የጦር መሳሪያ ከማምረት እንደምንገታት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና እኔ ቃል ገብተን ነበር።ቃላችንን ገቢር አድርገናል።በእስራኤል ላይ የተቃጣዉን የሕልዉና አደጋና በሰለጠነዉ ዓለም ላይ የተቃጣዉን የግድያ ሥጋት አስወግደናል።»
ሰዉዬዉ ከመቸኮላቸዉ የተነሰ «በእስራኤል ላይ» የሚለዉን «በኢራን ላይ» የተቃጣ አደጋ ብለዉት ነበር።ቸኩለዉ አሉት።ፈጥነዉ አረሙት።ኔታንያሁ እስራኤል ከመጥፋት አደጋ፣ ዓለምም ከመገደል ሥጋት ድኗል ቢሉም የለንድን፣ የፓሪስና የበርሊን መሪዎች አልተቀበሉትም። እንደ አሜሪካ ሁሉ የእስራኤል የቅርብ ወዳጆች፣ የኢራን ጠላቶች ፈረንሳይ፣ ብሪታንያና ጀርመን የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ያሰደረዉ ሥጋት አልተወገደም ይላሉ።ወይም የኔታንያሁን ማረጋገጪያ አላመኑትም።በሶስቱ ሐገራት ግፊት የተሰየመዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በኢራን ላይ ዳግም ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንዲጣል ወስኗል።
እነሆ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት አንዲት ሐገር የታጠቀችዉ አቶሚክ ቦምብ ትልቅ ርዕሥ ነበር በ80ኛ ዓመቱ ዘንድሮም ዘጠኝ ሐገራት የታጠቁት አዉዳሚ ጦር መሳሪያ ጥብቅ ወዳጆችን የማያግባባ ወይም ተራዉን ሕዝብ የሚያደናግር ርዕሥ ሆነ።
የትራምፕ አስተዳደርና የአባስ አስተዳደር
እስራኤል እንደ ሐገር እንድትመሠረት ሐሳብ ከቀረበበት ከ1940ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ ሁለንተናዊ ድጋፍ ተለያቷት አያዉቅም።እስራኤል በገጠመቻቸዉ ጦርነቶች፣ በልማትዋ ይሁን ቴክኖሎጂዋ፣ በፖለቲካዋ ይባል በዲፕሎማሲያዋ ዋና ደጋፊዋ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።
የእስራኤልና የአረቦች ወይም የፍልስጤሞች አደራዳሪም ዩናይትድ ስቴትስ ናት።እርግጥ ነዉ ዩናይትድ ስቴትስ የእስራኤል ሙሉ ደጋፊም-የእስራኤልና የጠላቶቿ አስታራቂም የመሆንዋ ተቃርኖ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ባንድ ወቀት እንደፃፉት «ሊሆን የማይቻለዉን እንደሚሆን ማስመሰል» መሆኑ ለብዙዎች የተሰወረ አይደለም።
ይሁንና ከ1947 በኋላ ተዳፍኖ የነበረዉን የሁለት መንግሥታት መፍትሔን ዩናይትድ ስቴትስ በ1990ዎቹ ብልጭ ሥታደርገዉ የፍልስጤሞችን ጨምሮ የዓለም መሪዎች የየጉባኤቸዉ መጀመሪያና መጨረሻ አድርገዉታል።ኦስሎ-ኖርዌ ላይ በተደጋጋሚ ከተደረገ ድርድር በኋላ እስራኤልና የፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት በ1993 ዋሽግተን ላይ የሰላም ዉል ተፈራረሙ።
በሥምምነቱ መሰረት የተመሠረተዉ የፍልስጤም ራስ-ገዝ መስተዳድር መሪዎች በአሜሪካኖችና በምዕራብ አዉሮጶች ይደገፋሉ።ዘንድሮ ግን የትራምፕ አስተዳደር የፍልስጤም ባለሥልጣናት «ለአሜሪካ ፀጠታ ሥለሚያሰጉ» በኒዮርኩ ጉባኤ ላይ እንዳይካፈሉ የመግቢያ ፈቃድ ወይም ቪዛ ከለከላቸዉ።
በልማዱ፣ ረጅም ጊዜ ባስቆጠረዉ ሥምምነትና አሠራርም የዓለም አቀፉ ድርጅት ዋና መቀመጫ ዩናይትድ ስቴትስ ለጉባኤተኞች ቪዛ መከልክል አልነበረባትም።የትራምፕ አስተዳደር ነባሩን ዉል ጥሷል የሚሉ መንግሥታት የዘንድሮዉ የጉባኤ ሥፍራ ከኒዮርክ ወደ ዤኔቭ እንዲዛወር እስከመጠየቅ ደርሰዉም ነበር።የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።
የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስ ከረመላሕ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ግን መስተዳድራቸዉ ከፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ ነዉ።ድቅም አይደል።ግን ሰዉዬዉ 89 ዓመታቸዉ ነዉ።እና አሉት።
«የመስከረም 22ቱ ሥብሰባ ያፀደቀዉን የሠላም ዕቅድ ገቢር ለማድረግ ከፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከፈ,ረንሳይ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከሁሉም ወዳጆቻችን ጋር ተባብረን ለመሥራት ዝግጁ መሆናችንን እናስታዉቃለን።ለፍትሐዊ ሠላምና ለአካባቢዉ አጠቃላይ ትብብር (እንጥራለን)።»
የዓለም አቀፉ ድርጅት የ78 ዓመታት አንድ ርዕሥ
ፍልስጤም ይባል የነበረዉ ግዛት ለሁለት ተገምሶ በሁለቱ ገሚስ አይሁድና አረቦች ሁለት መንግሥታት እንዲመሠርቱ፣ እየሩሳሌም በገለልተኛ ወገን እንዲተዳደር በ1947 የቀረበዉ ዕቅድ የያኔዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሐገራትን ብዙ አወዛግቦ ነበር።ዉዝግቡ አዲሱን ድርጅት እንደ ቀዳሚዉ የመንግሥታት ማሕበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ይበትነዋል የሚል ሥጋት አሳድሮም ነበር።ድርጅቱ አልተበተነም።
ከዉሳኔዉ ግን ገቢር የሆነዉ ገሚሱ ነዉ።እየሩሳሌም እስካሁን ገለልተኛ አስተዳዳሪ የላትም።የፍልስጤም መንግሥትም አልተመሠረተም።78ት ዓመቱ።ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ አዉስትሬሊያ፣ ቤልጂግና ሌሎች መንግሥታት 78 ዓመታት ሲያንገራግሩ ቆይተዉ በጋዛ ጦርነት ሰበብ የየሕዝባቸዉ ግፊት ሲያይልባቸዉ ዘንድሮ ለፍልስጤም የመንግሥትነት እዉቅና ሰጥተዋል።
ምዕራባዉያን መንግሥታት እዉቅና በመስጠታቸዉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ አጥብቀዉ ወቅሰዋቸዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ዓለም ለፍልስጤም የመንግሥትነት እዉቅና ሠጠም አልሰጠ መንግሥታቸዉ የፍልስጤም መንግሥት እንዲመሠረት አይፈቅም።ጋዛ ላይ የሚፈፅመዉ ጥቃትም በኔታንያሁ አገላለፅ «ሐማስን የማጥፋቱ ሥራ እስኪጠናቀቅ ይቀጥላል።»
«የሐማስ መጨረሻዎቹ አባላት፣ የመጨረሻዎቹ ቅሪቶች ጋዛ ከተማ ዉስጥ ተሸሽገዋል።ኃይላቸዉ ክፉኛ ቢዳከምምም፣ ጥቅምት 7 የተፈፀመዉን ግፍ ለመደጋገም በተደጋጋሚ ይዝታሉ።ለዚሕም ነዉ እስራኤል የጀመረችዉን ሥራ ማጠናቀቅ ያለባት።ለዚሕ ነዉ በተቻለ ፍጥነት ለማጠናቀቅ የምንፈልገዉ።»
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግን የጋዛን ጦርነት ለማስቆም መስተዳድራቸዉ ባለ 21 ነጥብ ዕቅድ መንደፉን አሰታዉቀዋል።ኔታንያሁ ሥራዉን ይጨርሳሉ።ትራምፕ የሰላም ተስፋ ይሰጣሉ።ይቃረናሉ።ግን ሁለቱ መሪዎች ዛሬ ይገናኛሉ።የጋዛ እልቂት ቀጠሏል።ግራ የተጋባዉ የዓለም ሕዝብ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርገዉ ሰልፍና ዘመቻም እንቀጠለ ነዉ።ቸር ያሰማኝ።
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ