1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ማሕደረ ዜና፣ የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫና የዕጩዎቹ የዉጪ መርሕ

ሰኞ፣ ጥቅምት 18 2017

ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ ቢመረጡ መስተዳድራቸዉ እስካሁን ከሚከተለዉ መርሕ መሠረታዊ የሚባል ለዉጥ ማምጣታቸዉ ብዙዎችን ያጠራጥራል።ትራምፕ ግን የዩክሬን-ሩሲያን ጦርነት ባንድ ቀን ለማስቆም ዝተዋል።ለእስራኤል ከእስካሁኑ የበለጠ ድጋፍ ለመስጠት፣ ኢራንን ለማበርከክ ዝተዋል።ከተመረጡ።

በዘንድሮዉ ምርጫ ከሚፎካከሩት ሁለት ፖለቲከኞች አሸናፊዉን አስቀድሞ ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል
ከግራ ወደ ቀኝ።የሪፐብሊካኖቹ ዕጩ ፕሬዝደንትና የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ምክትል ፕሬዝደንትና የዴሞክራቶቼ ዕጩ ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ ምስል Jim WATSON and Brendan Smialowski/AFP

ማሕደረ ዜና፣ የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫና የዕጩዎቹ የዉጪ መርሕ

This browser does not support the audio element.

 

አሜሪካ የነገ ሳምንት ማክሰኞ ትመርጣለች።ግን ማንን? ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስን ወይስ ።የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን።ሁለቱ አንገት ላንገት ይተናነቃሉ።

 የዓለም ኃያል፣ ሐብታሚቱ ሐገር የምርጫ ዉጤት ብዙዎች እንደሚያምኑበት በዓለም ፖለቲካ፣ኤኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋል።እንዴት፣ ለምን ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ። 

የዩናይትድ ስቴትስ ተፅዕኖ በዓለም   

ዩክሬንና ሩሲያ እየተዋጉ ነዉ።ዩክሬንን በማስታጠቅ ሩሲያን በመቅጣት-ማሳጣት አሜሪካን የሚስተካከል የለም።ጋዛና ሊባኖስ ይወድማሉ፣ የመንና ሶሪያ አልፎ አልፎም ቢሆን ይደበደባሉ፣ እስራኤልና ኢራን ይቆራቆሳሉ፣የእስራኤል አስታጣቂ፣የገንዘብ ዲፕሎማሲ ደጋፊ የጋዛዉን ሐማስ፣ የሊባኖሱን ሒዝቡላሕ፣ የየመኑን ሑቲ፣ የደማስቆ ቴሕራን  ገዢዎችን ቀጪ፣አዉጋዥ አልፎአልፎም ደብዳቢ-ደግሞም በተቃራኒዉ የሁሉም «ሸምጋይ»ም አሜሪካ ናት።

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኢትዮጵያ የሌሎችም የአፍሪቃ ሐገራት ተቀናቃኝ ኃይላት አስታራቂ አለያም ከየተፋላሚዎቹ አንዱን ደጋፊ ናት-አሜሪካ።ከሳሕል እስከ ካላሐሪ በረሐ የሸመቁ ደፈጣ ተዋጊዎች  ኒዤርን አሸበሩ ሞዛምቢክን ሸማቂዎቹን ቀድሞ አዉጋዥ፣በአሸባሪነት ወንጃይ ተጠቂዎቹን ደጋፊ አሜሪካ ናት።

በቻይና-ፊሊፒንስ ጠብ፣ በኮሪያዎች ፍጥጫ፣ በሐይቲ ምስቅልቅል፣ በቬኑዙዌላ ዉዝግብ፣ በሜክሲኮ፣ ኮሎምቢያ፣ የፀረ-አደንዛዥ ዕፅ ዘመቻ፣ በአርጀንቲና የምጣኔ ሐብት ቀዉስ ሁሉምጋ አሜሪካ አለች።አሜሪካ ባለችበት ሁሉ አዉሮጶች ይከተላሉ።

የዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ርዳታ፣ ዲፕሎማሲ፣ ሽምግልና ፍርድ ቤት ሥም፣ሥራ ሠራተኞቻቸዉ የዓለም ይባል-ይሆንም ይሆናል ምግባር ዉሳኔዎቻቸዉ ግን ከአሜሪካ ፍቃድና ይሁንታ ዉጪ ነዉ ብሎ የሚያምን ካለ እሱ በርግጥ የዋሕ ነዉ።

ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻ ላይ።ትራምፕ የሩሲያና የዩክሬንን ጦርነት በ24 ሰዓታት ዉስጥ ለማስቆም ፣በርካታ ስደተኞችንም ከአሜሪካ ለማባረር እየፎከሩ ነዉምስል Evan Vucci/AP Photo/picture alliance

ሌላዉ ቀርቶ አሜሪካ አባል ያልሆነችበት የዓለም የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ICC ምርመራ፣ክስ፣ብይን በዋሽግተኖች ጥቅምና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነዉ።የዚችን ሐገር በዉጤቱም የዓለምን አብዛኛ የፖለቲካ-ምጣኔ ሐብት ሒደት ቢያንስ ለ4 ዓመት በዋነናነት የሚዘዉረዉ ፖለቲካኛ በመጪዉ ሳምንት ማክሰኞ ይመረጣል።የዋሽግተኑ ወኪላችን አበበ ፈለቀ መራጩ እየተዘጋጀ ነዉ ይላል ዝግጅቱ ግን የተጣበበ ነዉ-እንደ አበበ።

የዕጩዎች ፉክክርና ተቀራራቢነቱ

«እየተዘጋጀን ነዉ።ምንም እንኳን ግራ አጋቢና የተጣበበ ቢሆንም እየተዘጋጀን ነዉ።(ጥያቄ፣ ምኑ ነዉ የተጣበበዉ፣ የእጩዎቹ ልዩነት?» አዎ ልዩነታቸዉ በጣም ተቀራራቢ ነዉ።መጠይቆች እንደሚያመለክቱት ሁለቱም 48 ከመቶ ላይ ናቸዉ።»

በዴምክራቶቹ ፓርቲ ዕጩ በምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስና በሪፐብሊካኖቹ ዕጩ በቀድሞዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል ያለዉ ልዩነት በጣም ጠባብ ነዉ።የሕዝብ አስተያየት ካሰባሰቡ መገናኛ ዘዴዎች አንዳዶቹ ሐሪስ ባይደንን 48 ለ47 ከመቶ በሆነ ድምፅ ይመራሉ ይላሉ።ሌሎቹ ደግሞ አበባ እንዳለዉ ሁለቱን 48 ከመቶ እኩል ናቸዉ ባዮች ናቸዉ።ሁለቱም ግን ለየደጋፊዎቻቸዉ እናሸንፋለን ይላሉ።ካሜላ ሐሪስ ፊላደልፊያ።

«የሐገራችን የጉዞ አቅጣጫና አመራሩን የሚወስነዉ ሥልጣን በሕዝቡ እጅ ነዉ።----ዘጠኝ ቀን።እያሸነፍን ነዉ።እናሸንፋለን።--በዚሕ ሂደት ማሕበረሰብ እንገነባለን።ተግባባን።ማሕበረሰብ መገንባት ።ሁላችንም ይሕን እንጋራለን።ባለፉት ዓመታት ሥለዚሕ ጉዳይ ብዙ ተብሏል።የትራምፕ ዘመን በሚባለዉ ጊዜ ሰዎች አንዱ በሌላዉ ላይ እንዲጠቋቆም፣ እንዲከፋፈል ሙከራ ሲደረግ ነበር።»

ዶናልድ ትራምፕ ኒዮርክ።ትናንት።

«ይሕ የአሜሪካ ወርቃ ዘመን ነዉ።በፍጥነት ይሆናል።በጣም ፈጥኖ ይደረጋል።የተጋረጡብን ችግሮች በሙሉ ይቃለላሉ።አሁን ግን የሐገራችን እጣፈንታ በናንተ ዕጅ ነዉ።በሚቀጥለዉ ሳምንት ማክሰኞ ለካሜላ ሐሪስ ማሳየት አለባችሁ።በጣም መጥፎ ምግባር ፈፅመሻል።ያ ለማጣ ጆ ባይደን በጣም መጥፎ ምግባር ሠርቷል፣ ሐገራችንን አበላሽተዋል ማለት አለባችሁ።ከእንግዲሕ አንቀበለዉም።ካሜላ ተባረሻል።ጥፊ ከዚሕ።ተባርረሻል።»

ዴሞክራሲ።ቃሉን ግሪኮች ፈጥረዉት፣ ምግባሩን ራሳቸዉ ግሪኮች ጀምረዉት ሌሎች አዳብረዉታል።የዘመኑ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መለኪያ ግን ዩናይትድ ስቴትስ ናት።የዛሬ አራት ዓመት በግሪጎሪያኑ 2020 የተደረገዉን ምርጫ  ተጭበርብሯል ያሉት የያኔዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዉጤቱን አልተቀበሉትም።

የዲሞክራቶቹ ዕጩናምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ (ከግራ) እና የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ በምርጫ ዘመቻ ላይ ምስል Paul Sancya/AP/picture alliance

የዲሞክራሲ አብነቲቱ ሐገር ዴሞክራሲዊነት ሥጋት

የትራምፕን ዉንጀላ የሚጋሩ ደጋፊዎቻቸዉ ጥር 6፣2021 የዩናይትድ ስቴትስን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አብነትን ካፒቶል ሒልን ወርረዉ የሰዉ ነብስ እስከ መጥፋት ያደረሰ ረብሻ መቀስቀሳቸዉ የአሜሪካንን ዴምክራሲያዊ ሥርዓት እንዴትነት አጠያያቂ አድርጎታል።የማክ ኮርትኔይ ተቋም ለዴሞክራሲ የተባለዉ የዩናይትድ ስቴትስ አጥኚ ተቋም የበላይ ኃላፊ ማይክል ቤርክማን እንዳሉት ጥር 6 በአሜሪካ ዴሞክራሲ ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል።

«ጥር ስድስት የሆነዉና ከተፎካካሪዎቹ አንደኛዉ ወገን የምርጫዉን ዉጤት አልቀበልም ማለቱ በዴሞክራሲ ላይ ከፍተኛ ጥፋት አስከትሏል።ምክንያቱም የምርጫ ዉጤት መቀበል ለዴሞክራሲ በጣም መሠረታዊ ጉዳይ ነዉና።»

ሥጋቱ አሁንም እንዳለ ነዉ።ባሁኑ ምርጫ ከሁለቱ ዕጩዎች ግልፅ አሸናፊ አለመታወቁ ብዙዎች እንደሚሉት የዛሬ አራት ዓመቱን ዓይነት ጥርጣሬ ዉንጀላና ምናልባትም ብጥብጥና ሊያስከትል ይችላል።የአሜሪካ ዴሞክራሲም እንደገና ለጥያቄ ይጋለጣል።አበበ ፈለቀ።

«ያሰጋል።በመጀመሪያ ደረጃ አሁን ባለዉ የመጠይቅ ዉጤት ከቀጠለ ዉጤቱ የዚያኑ ዕለት አይታወቅም የሚል ፍራቻ ነዉ ያለዉ።ምክንያቱም ይኸ ሜሊንግ ባለት  የሚባለዉ እስከሚቆጠር ድረስ ዕለታት አይደለም ሳምንትም 15 ቀናትም ሊያስፈልግ ይችላል።-----ሁለተኛዉ ትልቁ ሥጋት ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ከተሸነፉ ምርጫዉ እንደገና ጥርጣሬ ዉስጥ ይገባል የሚል ስጋት አለ።ምክንያቱም ዶናልድ ትራምፕ ከወዲሁ ጥርጣሬ ሥራ እየሰሩ ነዉ----»

 

ልዩነታቸዉ

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ሁለቱ ዕጩዎች የሐገር ዉስጥ ምጣኔ ሐብትን፤ ወንጀል መቀነስን፣ የሥራ ዕድል መፍጠርን በተመለከተ የሚከተሉት መርሕ ተቀራራቢ ነዉ።በዉጪ መርሐቸዉ ግን ልዩነት እንዳላቸዉ በሰፊዉ ይነገራል።ብዙዎች እንደሚሉት ካሜላ ሐሪስ ሌሎችን አሳታፊ ወይም ሁሉን አካታች ዓይነት መርሕ ሲከተሉ ትራምፕ ግን ከዚሕ ቀደም እንደሚታወቁበት መነሻ መድረሻቸዉ አሜሪካና የአሜሪካ ጥቅም ብቻ ነዉ።«የተናጥል» ወይም «የብቻ» መርሕ።እንደገና አበበ።

«ካማላ ሐሪስና ዴሞክራቶቹ ከኔቶም ይሁን ከሌሎች ጋር ተባብሮ የመስራትን መርሕ ይከተላሉ።ዶናልድ ትራምፕ ግን ሌላዉ ምን አገባዉ---»  

ዩናይትድ ስቴትስ በጆ ባይደን አስተዳደር  ለእስራኤልና ለዩክሬን ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር የሚያወጣ ጦር መሳሪያ ታስታጥቃለች።ሐማስ፣ ሒዝቡላሕ፣ ሁቲ ይባሉ ኢራን ወይም ሌላ የእስራኤል ጠላቶች የአሜሪካም ጠላቶች ናቸዉ።

ከዩክሬን ጋር የምትዋጋዉ ሩሲያ፣ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የተፋጠቸዉ ሰሜን ኮሪያ፣ ወይም በምጣኔ ሐብት አሜሪካን የምትፎካከረዉ ቻይናም ለአሜሪካ እንደጠላት የሚቆጠሩ ናቸዉ።

ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ ቢመረጡ መስተዳድራቸዉ እስካሁን ከሚከተለዉ መርሕ መሠረታዊ የሚባል ለዉጥ ማምጣታቸዉ ብዙዎችን ያጠራጥራል።ትራምፕ ግን የዩክሬን-ሩሲያን ጦርነት ባንድ ቀን ለማስቆም ዝተዋል።ለእስራኤል ከእስካሁኑ የበለጠ ድጋፍ ለመስጠት፣ ኢራንን ለማበርከክ ዝተዋል።ከተመረጡ።

«ይኩሬንን በተመለከተ ካማላ ሐሪስ፣ የጆ ባይደን መስተዳድር የሚያደርገዉን መቀጠል ይፈልጋሉ።አሜሪካ   ለዩክሬን ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ወታደራዊ ድጋፍ መስጠት አለባት፣ ራሽያ ላይ የተጠናከረና ሁሉን አቀፍ ምዕቀቡ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸዉ፣ እንዲያዉም የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ዘለንስኪን ጦርነቱን ማስቆም ነበረባቸዉ ይላሉ።የቭላድሚር ፑቲንም አድናቂ ናቸዉ።ከጠመረጥኩ ጦርነቱን በ24 ሰዓታት ዉስጥ አስቆማለሁ ብለዋልም-----»

 ትራምፕ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ዩናይትድ ስቴትስን ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስነዉን ድንበር በግንብ ማሳጠር ጀምረዉ ነበር።ጆ ባይደን ሥልጣን ሲይዙ ግንባታዉን አቋርጠዉታል።አሁን የባይደን ምክትል ካማላ ሐሪስ እንዳሉት የአሜሪካ ምክር ቤት ከተስማማበት የአጥሩ ግንባታ መቀጠሉን ይደግፋሉ።

የዴሞክራቶቹ ፓርቲ ዕጩ ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ የባይደን አስተዳደር ከሚከተለዉ መርሕ ብዙም የተለየ መርሕ እንደሌላቸዉ በሰፊዉ ይታመናልምስል Jacquelyn Martin/picture alliance/AP

የዲሞክራቱ ፓርቲ ዕጩ ለወትሮዉ ፓርቲያቸዉ የሚቃወመዉን አለቃቸዉም ያስቆሙትን ድንበርን በግንብ የማጠር እርምጃን ሲደግፉ ትራምፕ አንድ ርምጃ ቀደሟቸዉ። ሕገ-ወጥ ያሏቸዉን የዉጪ ስደተኞች ጠራርገዉ ለማስወጣት እየዛቱ ነዉ ሰዉዬዉ።

አማራጭ ያጣዉ መራጭ ሕዝብ

  የጆ ባይደን አስተዳደር የጋዛ ሕዝብን እልቂት፣ ሥቃይና ሰቆቃ ባለማስቆሙ በቅርቡ ደግሞ ሊባኖስ ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃትና ግድያ ቸል በማለቱ ከአረብ፣ሙስሊም፣ ከአብዛኞቹ ጥቁር አሜሪካዉያንም ከፍተኛ ተቃዉሞ ገጥሞታል።የባይደር አስተዳደር፣ የአሜሪካ የፀጥታ ኃይላትና ቱጃሮች የጋዛዉን እልቂት በመቃወም እዚያዉ አሜሪካ ዉስጥ በየዩኒቨርስቲዉ የተደረጉ አድማና ሰልፈኞችን አፍነዋል ተብለዉ ይወቀሳሉም።

ለወትሮዉ በአብዛኛዉ የዴሞክራቶቹ ፓርቲ ደጋፊ የነበረዉ የአረብ፣ሙስሊም፣ ጥቁርና ቅይጥ ዝርያ ያለዉ አሜሪካዊ ለዴሞክራቶቹም፣ ለሪፐብሊካኖቹም ዕጩዎች ድምፁን ላለመስጠት እያቅማማ ነዉ።እንደ አብዛኛዉ የዉጪ ዝርያ ያለዉ አሜሪካዊ ሁሉ ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያንምከዴሞክራቲኩ ፓርቲ ጋር ጥብቅ ትስስር አላቸዉ።ባሁኑ ምርጫ ግን አበበ ፈለቀ እንደታዘበዉ በርካታ ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን ወደ ሪፐብሊካኖች ያዘነበሉ መስለዋል።  

«በተለምዶ የዴሞክራቶቹ ደጋፊዎች ነን።ባብዛኛዉ አሁን ግን አንዱ የሰማሁትና  ወሳኝ ነዉ የሚባለዉ ዴሞክራቶች ከፆታ ሕግ ጋር በተያያዘ፣ በትምሕርት ቤት፣ የተለያዩ ጾታ ዉሳኔን በተመለከተ በካሊኩረም----ምብቶች እንዲከበሩ የተለያዩ የፆታ ደንቦች እንዲካተቱ ዴሞክራቶቹ ሥላደረጉ፣ ልጆቻዉ ላይ ስለተመጣ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሪፐብሊካን የማድላት----»   

እና አሜሪካ በመጪዉ ማክሰኞ ትመርጣለች።የልዕለ ኃያሊቱ ሐገር ጉዞም ሮብ ይለያል።

ነጋሽ መሐመድ 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW