ማሕደረ ዜና፣ የዶናልድ ትራምፕና የኤለን መስክ ጠብ ወዴት ያመራ ይሆን?
ሰኞ፣ ሰኔ 2 2017
2021 ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የታተመዉ ታይም መፅሔት «ባለርዕይ፣የመድረክ ሰዉ፣ጥቅል ልምድን የሚቃረን፣ ተናዳፊ» ይላቸዋል ኤለን መስክን።መፅሔቱ ለኤለን መስክ «የዓመቱ ምርጥ ሰዉ» ማዕረግን በቸረበት በዚሕ ዕትሙ «ዓለማችንን ዳግም እየቀረፀ ነዉ።» ብሏቸዋልም። የዓለም አንደኛ ሐብታም፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ኤሎን መስክ፣ ከዓለም ትልቅ ፖለቲከኛ፣ ልማዳዊዉ ነጋዊና ሐብታም፣ዶናልድ ትራምፕ ጋር ሰሞኑን የገጠሙት ጠብ፣ መስክ ዓለምን «ዳግም የመቅረፅ» ፍላጎት-ጥረታቸዉ አካል ይሆን? ሆነም አልሆነ ሁለቱ ዝሆኖች እንደ ቅርብ ወዳጅ ገቢር ያደረጉት ፀረ-የዉጪ ተወላጆች ደንብ የአሜሪካ ዕዉቅ ዩኒቨርስቲዎችን እያንገዳገደ፣ ልጅን-ከወላጆች እየነጣጠለ፣ ትላልቅ ከተሞቿን እያተራመሰ ነዉ።ሰሞኑን እንደ ጠላት የገጠሙት እሰጥ-አገባ ደግሞ የኃያል፣ ሐብታም፣ትልቂቱን ሐገር የፖለቲካ-ምጣኔ ሐብት-ቴክኖሎጂን ጉዞ እንዴትነት እያጠ,ያየቀ ነዉ።ላፍታ እንዴት ለምን እንበል።
የዓለም ኃያል-ሐብታም ሐገርን «ከሁሉ ለማስቀደም»ባንድ ያበሩት የአሜሪካ ኃያል ፖለቲከኛ፣ ቀዳሚ ሐብታም፣ ምጡቅ የቴክኖሎጂ አዋቂዎች የቀየሱት የቀረጥ፣የወጪ ቁጠባ፣ የስደተኞችና ሌሎች መርሕ-ሕጎች የዓለምን የጋራ ማሕበርን፣ ሕግን፣ፍርድ ቤቶችን፣የንግድ ዉልን፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ሥምምነትን እየመነቃቀሩ፣ የአሜሪካን ትላልቅ ዩኒቨርስቲዎች እያሽመደመደ፤ የዘመናት ታዛዥ ወዳጆቿን ሳይቀር ቂም እያስቋጠሩ ነዉ።
ካለፈዉ አርብ ጀምሮ ደግሞ ሎሳንጀለ፣ ኒዮርክና መሰል የአሜሪካ ትላልቅ ከተሞች የፀረ-ስደተኞችን ሕግ በሚቃወሙ ሰልፈኞችና በፀጥታ ኃይላት መካከል በተነሳ ግጭት፣ በርችት፣ አስለቃሽ ጢስ እየታጠኑ ነዉ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም የሰልፈኛዉን ለማመቅ በተለይ ሎሳንጀልስ ከተማ የብሔራዊ ዘብ ጦር ማዝመታቸዉን ከካልፎርኒያ አገረገዢ ጭምር ተቃዉሞ ገጥሞተናል።ሰልፉንም ወደ ሁከትና አመፅ ለዉጦታል።
«እዚህ የመጣነዉ የቤተሰቦቻችን አባላት እንዲለያዩ መገደዳቸዉን ለመቃወም ነዉ።ፍትሕ እንፈልጋለን።(ብሔራዊ ዘቦች) ነገሩን እያባባሱት ነዉ።የራሳችንን መንግሥት እንዳናምን እያደረጉ ነዉ።እኛ ላይ ምናምኑን እየወረሩብን ነዉ።ጥሩ ሥፍራ አይደለም።»
የዋሽግተን ወኪላችን አበበ ፈለቀ እንደሚለዉ የእስካሁኑ ሰልፍ ለትራምፕ መስተዳድር ትልቅ ፖለቲካዊ ተቃዉሞ ነዉ።
«እነኚሕ ኒዮርክ፣ ዋሽግተን ሎሳንጀለስና የመሳሰሉት ሳንክቹዋሪ ሲቲስ ይባላሉ።ምን ለማለት ነዉ ሕጋቸዉና ደንባቸዉ ከዉጪ ለሚመጡ ሰዎች ድጋፍ ያለዉ---እዚያም ያለዉ ሕብረተሰብ አክራሪ አይደለም፣ (ከስደተኞቹ) ጋር የተዛመደ፣ የተጋባ፣ በዚሕ አይነት ፍልስፍና ዉስጥ ያለ ነዉ---ፖለቲካሊ ትልቅ ሪዝዝታንስ ነዉ---»
ኤለን መስክና የዶናልድ ትራም ጠብ
የቢሊየነሩ ኤለን መስክ አመፅስ፣ ለዶናልድ ትራምፕ መስተዳድር ትልቅ ፈተና ይሆን-ይሆን? መሆን አለመሆኑ ለጊዜ ሒደት የሚተዉ ነዉ።ከአምና ኃምሌ ጀምሮ «ሞት ይለየን» አይነት ጥብቅ ወዳጆች ይመስሉ የበሩት ዶናልድ ትራምፕና ኤለን መስክ በርግጥ ተጣልተዋል።
ሁለቱ ዝሆኖች የገጠሙት የመገናኛ ዘዴ ጦርነት በጣሙን የቃላት አጠቃቀመቻዉ ግን የዓለም መሪ-ቱጃሮችን ባሕሪና ስብዕና እያሳየ ነዉ።።የጠቡን መነሻ አበበ ፈለቀ «በይፋ የተነገረና ያልተነገረ» ይለዋል። ካልተነገረዉ ግን ካጠቃላዩ እንጀምር።
«ባጠቃላይ እዚሕ አገር ምን ይባላል ከትራምፕ ጋር የሚሰራ ሰዉ ሼልፍ ላይፍ አለዉ ይባላል።ይሕ ማለት ምንድነዉ ለምሳሌ ሱቁ ዉስጥ የተደረደረ እንቁላል ወይም ሌላ ነገር የሚያገለግልበት ጊዜ አለ።---ከትራምፕ ጋር ሆነሕ ዘላቂ የሆነ ግንኙነት ይኖረኛል ማለት እትችልም።»
ኤለን መስክ-ምጡቁ አዕምሮ
«የ3 ዓመት ሕፃን እያለ ጀምሮ የኔ ትንሹ ምጡቅ ልጅ ነበር» ይላሉ፤ የኤለን እናት ማዬ መስክ።«ባለ ምጡቅ አዕምሮዉ ልጅ (Genius Boy) እንለዉ ነበር።» አከሉ ወይዘሮ መስክ።ትንሹ ባለምጡቅ አዕምሮ በ12 ዓመቱ (ተጫዋጮች፣ የአስፈሪ እንግዳ ፍጥሮች መርከቦች የሚደበድቡበትን) Blastar የተባለዉን የኮምፒዉተር መጫዎቻ ፈጥሮ በ500 ዶላር ሸጠ።
ከደቡብ አፍሪቃ- ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ-ካናዳ፣ እንደገና ዩናይትድ ስቴትስ እየተፈናጠረ ትምሕርቱን እየቀሰመ፣የOnline (ኢንተርኔት) መስመርን ይዋኝበት ያዘ።በ17 ዓመቱ የተነሳዉ ፎቶ ግራፍ እናቱ ላይ በባርኔጣ ላይ ባርኔጣ ደርቧል፣ የሱሪዉን ግርጌ ሽቅብ ሸቅቆ ጉልበቱ ላይ አድርሷል።«ካናዳ አጎቴ እርሻ ዉስጥ» ይላል የፎቶዉ ማብራሪያ።
ያ ፈጣን፣ ቅብዝብዝ፣ ችኮ፣ ችኩል ግን ሥልታዊ፣ ብልሕ ወጣት ከ1990ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ-ኢንተርኔቱን እንደ አጎቱ ማሳ እያረሰ፣ እንደራረበዉ ባርኔጣ በፈጠራ ላይ ፈጠራ እየደራረበ፣ ሽቅብ እንደሸቀቀዉ ሱሪዉ ገንዘብ ይከምር፣ ኩባንዮችን ይኮለኩል ያዘ።ፔይፓል፣ ዚፕ2፣ ሶላርሲቲ፣ ቴስላ፣ኦፕን ኤ አይ፣ ስፔስ ኤክስ፣ቦሪንግ ካምፓኒ፣ኖየር ሊንክ---»
የሁለቱ ዝሆነች ጠላት-ወዳጅ-ጠላትነት
መስክ፣ በ2016 ኖየር ሊንክን ፈጥሮ ሲያስመርቅ የ25 ዓመትታላቁ ዶናልድ ትራምፕ ንግዱንም፣ ድለላዉንም፣ የቴሌቪዥን ትርዒቱንም፣ የፍርድቤት ሙግት፣ ክርክሩንም ብለዉት፣ ብለዉት ፖለቲካዉን ተቀይጠዉ ነበር።ዉልደት፣እድገት፣የሕይወት ጉዞ፣ፍላጎት፣ የሕብት ምንጭ ሲለያያቸዉ ሐብት-ብልጠት የሚያመሳስላቸዉ ሁለቱ ኃይለኞች የሩቅ-ለሩቅ ትዉቃቸዉ ግን ተቃራኒ አቋማቸዉ የጎላዉም ያኔ ነበር። በ2016።
ቢሊየነርኑ መስክ ትራምፕን «ለፕሬዝደንትነት ተገቢዉ ሰዉ ዓይደለም» በማለት ተቃወሙ።የአሜሪካ ሕዝብ ግን ትራምፕን መረጠ።የመስክ እናት በልጅነቱ ያሉትን ዶናልድ ትራምፕ በ2020 ደገሙት።
«ከታላላቅ ጂኒዮሶቻችን አንዱ ነዉ» አሉ ትራምፕ፣ትራምፕ በ2021ዱ ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ግን መስክን «ሌላ ቡልሺት» አሉት «ጅል» ብንለዉ ያስኬዳል።የመስክ አፀፋ ለስለስ ያለ ግን ለሞገደኛዉ አዛዉንት ቆጥቋጭ ነበር።«ሰዉዬዉን አልጠላዉም» አሉ-መስክ «ነገር ግን ትራምፕ ባርኔጣዉን ሰቅሎ ወደ ፀሐይ መግቢያ የሚቀዝፍበት ሰዓት አሁን ነዉ።» አከሉ መስክ።
ምክንያቱ አስተዳደግ፣ ዕዉቀት፣ ሐብት፣ በየተሰለፉበት መስክ ያገኙት ዉጤት፣ ከሰዉ የሚጎርፍላቸዉ አንድናቆት ሌላም ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።ሁለቱም ግን በድል፣ዉጤታቸዉ የሚመፃደቁ፣ ማን አሕሎኝ ባዮች፣ እብሪተኛና ሞገደኛ ናቸዉ።ሁለት አዉራ ዶሮ አንድ ቆጥ ላይ አይሰፍርም።
አምና ሐምሌ ትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻ ሲያደርጉ የአንድ ጆሯቸዉን ጫፍ የቀነጠበችዉ ጥይት ግን ሁለቱን ኃይለኞች አቀራረበች።በትራምፕ ላይ የተቃጣዉ የግድያ ሙከራ እንደተሰማ መስክ ለትራምፕ ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገቡ።የዓለም አንደኛ ቱጃር ትራምፕንና ትራምፕ የሚመሩት የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ እንደራሴዎችን ለመደገፍ ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ፣ኩባንያ፣ጊዜያቸዉን ያጎርፉት ያዙ።
ሹመት-ሽረት፣ ጠብና ስድድብ
መስክ የጠበቁት ይሟላ አይሟላ አይታወቅም።ትራምፕ ግን ቱጃሩን የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ኤለን መስክን የመንግስት ዉጤማነትን ይከታተላል የተባለዉ መስሪያ ቤት ኃላፊ አድርገዉ ሾሟቸዉ።መስክ 5 ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ USAID፣ VOAና ሌሎች ዉጪ ያበዛሉ የተባሉ የአሜሪካ ድርጅቶችን እንዲዘጉ፣ወይም እንዲሸጋሸጉ በማድረጉ ሒደት ትልቅ ሚና ተጫዉተዋል።
በቅርቡ ግን ሥልጣን ለቀዉ ከትራም ጋር እሰጥ አገባ ለመግጠማቸዉ በይፋ የሰጡት ምክንያት «ወጪ ይቀነስ» በሚባልበት ባሁኑ ወቅት የትራምፕ መስተዳድር ከ3.8 ትሪሊዮን በላይ ዶላር በጀት መጠየቁን ነዉ።ብዙዎች ግን የበጀት መብዛት የጠቡ ትንሹ ሰበብ እንጂ መሠረታዊዉ ምክንያት ብዙ ምናልባትም ዉስብስብ ነዉ ባይ ናቸዉ።አንዱ ጥቅም ነዉ።
መስክ ለቴክኖሎጂ የቀረበዉን የNASAን የበላይ ኃላፊነት ተመኝተዉ ነበር ይባላል።ትራምፕ ግን አላደረጉም።ሌለኛዉ ባሕሪ ነዉ።ሁለቱም እብሪተኛ ናቸዉ።ሁለቱም ሞገደኛ ናቸዉ።ሁለቱም ማን አሕሎኝ ባይ ናቸዉ።ሁለት አዉራ ዶሮ አንድ ቆጥ ላይ አይሰፍርም።
መስክ ከትራምፕ ጋር መዘላለፍ-መሰዳደብ ከጀመሩ በኋላ ባንድ ቀን ዉስጥ ብቻ ከ34 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አጥተዋል።የ400 ቢሊዮን ዶላሩ ቱጃር ግን እስካሁን አልተገዳገዱም።ትራም የአሜሪካ መንግሥት የጠፈር፣ የጦርና የሳተላይት ቴክኖሎጂን ከመስክ ኩባንያ ለመግዛት የተዋዋለዉን ኮንትራት እሰርዛለሁ እስከማለት ደርሰዋል።መስክ ባንፃሩ ኋላ ቢሰርዝትም የትራፕን የወሲብ ቅሌትን ለማጋለጥ ዝተዋል።ተቃዋሚ ፓርቲን ሊደግፉ ወይም አዲስ ፓርቲ ሊመሰርቱ ይችላሉም ይባላል።
በዚሕም ብሎ በዚያ የሁለቱ ኃይለኞች ጠብ የአሜሪካ ፖለቲካዊ ኤኮኖሚያዊ ጉዞን እንዳያወለካክፈዉ አስግቷል።መስክ በ2021 በሰጡት ቃለ መጠይቅ «በአምስት ዓመት ዉስጥ ማርስ ላይ ካለረፍን፣ በጣም እደነቃለሁ» ብለዉ ነበር።ማርስ ላይ ሰዉ ማሳረፍ-አለማሳረፋቸዉ ወይም መደነቅ አለመደነቃቸዉን ለማሳየት ከእንግዲሕ አንድ-ዓመት ከመንፍቅ አላቸዉ።ዋይት ሐዉስ ግን ገብተዉ፣ ሽማግሌዉን፣ ቀኝ አክራሪ ትልቅ መሪን አደናብረዉ ባምስተኛ ወሩ ወጥተዋል።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ