1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ ርዳታ፣ ሰልፍና ዲፕሎማሲ

ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2016

ከአሜሪካኖች ግፊት፣ ከተቀረዉ ዓለም ልመና፣ጩኸት፣ ከዓለም አቀፉ ድርጅት ተደጋጋሚ ተማፅኖ በኋላ የተወሰኑት ካሚኖች ወደ ጋዛ እንዲገቡ እስራኤል ፈቀደች።ቅዳሜ።20 ካሚዮን፣ ርዳታዉ ትናንትና ዛሬም ገብቷል።የአል አቅሳ መስዋዕት» ለተባለዉ ሆስፒታል ግን እስከ ትናንት የደረሰ ርዳታ የለም

ጋዛ ሰርጥ ዛሬም ትወድማለች
የእስራኤል ጦር ጥቃት በጋዛ ሰርጥምስል፦ Ariel Schalit/AP/picture allianceIsr

ማሕደረ ዜና፣ ለጋዛ የተላከ ርዳታ፣ ሰልፍና ዲፕሎማሲ

This browser does not support the audio element.

የእስያ-አፍሪቃ፣ የአሜሪካ-አዉሮጳ ሐገራት ሕዝብ የሰላማዊ ሰዎች መገደል፣ መፈናቃል፣ መራብ መጠማት እንዲቆም ባደባባይ ይጠይቃሉ።የአረብ፣ አዉሮጳ-አሜሪካ መሪዎች፣ ሚንስትሮችና ዲፕሎማቶች ካንዱ ሐገር  ርዕሰ-ከተማ ወደ ሌላዉ ይመላለሳሉ።ሲሻቸዉ ደግሞ ይሰበሰባሉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአዉሮጳ ሕብረትና የሌሎች ማሕበራት ተጠሪዎች ከምክንያት ይልቅ በዉጤት ላይ የተንጠለጠለ ተማፅኖ ያሰማሉ።ጋዛ ትወድማለች።እስራኤል ለተጨማሪ ወረራ ተዘጋጅች።ዩናይትድ ስቴትስ ለመካከለኛዉ ምስራቅ ኃያል፣ ጠንካራ ጦር ተጨማሪ ጦር መሳሪያ ታስታጥቃለች-ጦር ኃይል ታዘምታለችም።ሶስተኛ ሳምንት።ግን እስከ መቼ?
                                      
ሲና በረሐ-ግብፅ። ጋዛ ማቋረጪያ አጠገብ።አርብ ። በመቶ የሚቆጠሩ ካሚዮኖች መድሐኒት፣ የሕክምና መሳሪያ፣ምግብ፣ ነዳጅ ወዘተ  ጭነዉ ተደርድረዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ርዳታዉ ለጋዛ ሕዝብ እንዲገባ ኃይለኞችን ተማፀናሉ።

«ከግንቡ በዚሕኛዉ በኩል ዉኃ፣ነዳጅ፣ መድሐኒት፤ ምግብ የጫኑ ብዙ ካሚዮኖች እናያለን።የጫኑት ቁሳቁስ ከግንቡ ማዶ በጣም የሚፈለግ ነዉ።ስለዚሕ እነዚሕ ካሚዮኖች ተራ ካሚዮን አይደሉም።ጋዛ ዉስጥ ላሉ ብዙ ሰዎች እስትፋንስ ማስቀጠያ ናቸዉ።በሕይወትና ሞት መካከል ያሉ መለያ ናቸዉ።እዚሕ ታግደዉ ማየት ለኔ በጣም ግልፅ ያደርገዋል።»

ሰብአዊ ርዳታ የጫኑ ካሚዮኖች ወደ ጋዛ ሰርጥ ሲገቡምስል፦ Mohammed Asad/AP Photo/picture alliance

ከአሜሪካኖች ግፊት፣ ከተቀረዉ ዓለም ልመና፣ጩኸት፣ ከዓለም አቀፉ ድርጅት ተደጋጋሚ  ተማፅኖ በኋላ የተወሰኑት ካሚኖች ወደ ጋዛ እንዲገቡ እስራኤል ፈቀደች።ቅዳሜ።20 ካሚዮን፣ ርዳታዉ ትናንትና ዛሬም ገብቷል።የአል አቅሳ መስዋዕት» ለተባለዉ ሆስፒታል ግን እስከ ትናንት የደረሰ ርዳታ የለም።ሆስፒታሉ ከሚገኝበት ከዴይር አል-ባላሕ-ሰፈር በቅርብ ርቀት የሚገኙ አካባቢዎችን የሚያወድመዉ የቦምብ ሚሳዬል ድምድምታም በቅርብ ርቀት ይሰማል።
ዘጋቢዉ እንዳለዉ ሆስፒታሉ ዉስጥ ሐኪሞች ያለ ወቅታቸዉ የተወለዱ ሕፃናትን ሕይወት ለማትረፍ ይራኮታሉ።የሐኪሞቹ፣ የሆስፒታሉ አስተዳዳሪዎች፣ የወላጅ ወይም የበሽተኞች ጭንቀት ሆስፒታላቸዉ ዳግማዊ አል አሕሊ አረብ እንዳይሆን ብቻ አይደለም።የሕይወት እስትፋሳቸዉ መቀጠል-ያለመቀጠሉ ወሳኝ መሰረቶች መድሐኒት፣ የሕክምና ቁሳቁስ፣ የጄኔሬተር ነዳጅ እየተሟጠጠ መምጣቱ ጭምር እንጂ።የሆስፒታሉ የበላይ ኃላፊ ኢያድ አቡ ዛሕር 

«የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጋቸዉ በሽተኞች፣ አለወቅታቸዉ የተወለዱ ሕፃናት እና ወላዶች {አደጋ ላይ ናቸዉ} ይሕ ሆስፒታል፣ አገልግሎት ሊሰጥ ከሚችለዉ በላይ ብዙ እጥፍ እያገለገለ ነዉ።{በኤሌክትሪክ ኃይል በሚሰራ} ኢንኩቤተር ዉስጥ ያሉ ያለወቅታቸዉ የተወለዱ ሕፃናት በጣም አደገኛ ሁኔታ ዉስጥ ናቸዉ።»
ጉተሬሽ-«የመኖርና መሞት ልዩነት» ያሉትን ርዳታ ከሚጠብቁት ሕፃናት ያንዱ ወይም ያንዷአባት የልጃቸዉን እጣ አንታ ይጠይቃሉ።
«የልጆቹ ሕይወት ያሰጋናል።ልጆቻችን ከተገደሉትና ሕይወታቸዉን ካጡት ስዉዓን ምንም አይሻሉም።ለመላዉ ዓለም የምንለዉ የነዚሕ ልጆች የወደፊት እጣ-ፈንታ ምንድ ነዉ።»

ደካሞች ለዝንተ ዓለም የተጠየቁት-ዛሬ የሚደገም፣ ወደፊትም የሚጠየቅ ግን መልስ ያጣ ጥያቄ።ሰሞኑን ከአማን እስከ ዋሽግተን፣ከጃካርታ እስከ  ለንደን፣ ከብራስልስ እስከ ቤይሩት፣ ከቱኒዝ እስከ በርሊን አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች ለእልቂት፣ፍጅት፣ ጥፋት ምናልባት ለጋዛዉ አባት ስጋት መወገድ፣ አብነቱ የፍልስጤም ነፃ መዉጣት ነዉ ይላሉ።
የብሪታንያዉ ሰልፍ የሐገሪቱ ፖሊስ እንዳረጋገጠዉ ሌሎቹ አካባቢዎች ከተደረጉት ሁሉ እጅግ ደማቅ፣ በቅጡ የደረጃና መቶ ሺዎችን ያስተናገደ ነበር።ብራስልስም ቀጠለ።ከሰልፈኞቹ አንዷ« ሰላማዊ ትግል» ትለዋለች።
«ተቃዉሞን በሰላማዊ መንገድ ለመገለፅ፣ በተለይ ተኩስ አቁም እንዲደረግና በተጨማሪም ዘር ማጥፋት እንዲቆ እርምጃ እንዲወሰድ-ዓለም አቀፍ ርምጃ እንዲወሰድ ለመጠየቅ ነዉ።በዚሕ አስቸጋሪ ወቅት እዚሕ መሰለፍ በጣም አስፈላጊ ነዉ።» 

የእስራኤል ታንኮች ለእግረኛ ወረራ ሲዘጋጅምስል፦ Ohad Zwigenberg/AP/dpa/picture alliance

የእስራኤልና የጀርመን መንግስታት ባለስልጣናት የተካፈሉበት እስራኤል የሚደግፍ ሰልፍደግሞ በርሊን ዉስጥ ተደርጓል።በ10 ሺሕ የሚቆጠር ሰዉ መሳተፉ ተዘግቧል።በሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት 
የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር እንዳሉት «የእስራኤል ሕመም የጀርመንም ሕመም» ነዉ።
«ዉድ የዚሕ ሰልፍ ተሳታፊዎች፤ እስራኤል ላሉና ለመላዉ የሁዲዎች ብቻችሁን አይደላችሁም እንላለን።በዚሕ አስቸጋሪ ወቅት ከጎናችሁ እንቆማለች።ሕመማችሁ ሕመማችን ነዉ።»

የብራስልሷ ተራ ሰልፈኛ «ተኩስ ይቁም» ትላለች።የበርሊኑ ፖለቲከኛ ግን እስራኤልን እንደገፍ።ዓለም በርግጥ ስለ ዓለም ሰላም እየተግባባ ይሆን? 

የጀርመኑ ፕሬዝደንት ቫልተር ሽታይን ማየር በበርሊኑ ሰልፍ ላይ ንግግር ሲያደርጉምስል፦ Sean Gallup/Getty Images

አዉሮጳን ያወደመዉ የተቀረዉን ዓለም ክፉኛ የጎዳዉ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ባበቃ ማግስት  በዩናይትድ ስቴትስ መሪና አስተባባሪነት ዓለም የጋራ ማሕበር የመሠረተዉ እስኪዚያ ዘመን ድረስ የነበሩ እልቂት፣ ፍጅቶች እንዳይደገሙ ነበር።የተባበሩት መንግስታት የተባለዉ ማሕበር  መሠረታዊ ዓላማም የሰዉ ልጅ የየትኛዉም ቀለም ባለቤት ይሁን የማንኛዉም ጎሳ ተወላጅ ወይም የየትኛዉም ኃይማኖት ተከታይ፣ ጠንካራ ይሁን ደካማ፣ በሰላም እኩል እንዲኖር የሚግባባትን ደንብ እንዲያስከብር ነበር።ወይም እኒዲያ ብለዉ ነገሩን።

ሴነ 26፣ 1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሳንፍራንሲስኮ-ዩናይትድ ስቴትስ ላይ የተደረገዉ የድርጅቱ የመጀመሪያ ጉባኤ ሲጠናቀቅ የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን ያስተላለፉት መልዕክትም የዓለም ማሕበረሰብ በተለይ መንግስታት አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር ተከባብረዉ እንዲኖሩ የሚጠይቅ ነበር።
«ጥንካሬያችን ምን ያሕል ከፍተኛ ቢሆንም እንኳ በፈለግነዉ ጊዜ እኛ የፈለግነዉን ነገር እንዳናደርግ እራሳችንን ማቀብ አለብን።ማንኛዉም አንድ ሐገር፣ ማንኛዉም አካባቢያዊ ቡድን ሌላዉን ወገን የሚጎዳ  ነገር የማድረግ ልዩ መብት ማገኝት አይችልም፣ መጠበቅም የለበትም።»

ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ ቬትናም፣ ከካምቦዲያ እስከ ኒካርጓ፣ ከኢራቅ እስከ አፍቃኒሲታን፣ ከሰርቢያ እስከ ሊቢያ፣አሁን ደግሞ ፍልስጤም ግዛት የሆነና የሚሆነዉ በርግጥ የሕዝብን ሰላም፣ የዓለም መንግስታትን የጋራ ጥቅም ለማስከበር ይሆን? 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ለጋዛ ሕዝብ ርዳታ እንዲደርስ ለመማፀን ባለፈዉ ሳምንት ወደ ሲና በረሐ-ግብፅ ከመዉረዳቸዉ ከ3 ቀን በፊት ብራዚል ለጋዛ ሕዝብ ርዳታ ይደርስ ዘንድ «ሰብአዊ ተኩስ አቁም» እንዲደረግ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ አቅርባ ነበር።በምክር ቤቱ ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን ያላት ዩናይትድ ስቴትስ ረቂቅ ደንቡን ዉድቅ አደረገችዉ።
ምክንያት? በድርጅቱ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ወይዘሮ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ለዲፕሎማሲ ቅድሚያ መስጠት አለብን ብለዉ ነገሩን።
«እና ብራዚል ይህ ፅሁፍ እንዲፀድቅላት መፈለጓን እያከበርን፣ ዲፕሎማሲ ዉጤት እንዲያመጣ መፍቀድ አለብን ብለን እናምናለን።በተለይ ዋና ፀሐፊ ጉቴሬሽ፣ፕሬዝደንት ባይደን፣ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ብሊከን ዛሬ እኛ እዚሕ ባቀረብነዉ ጉዳይ ላይ ከአካባቢዉ ኃይላት ጋር ከፍተኛ ድርድር በሚያደርጉበት ወቅት (እዚሕ ማንሳቱ አስፈላጊ አይደለም)

በፍልስጤም ላይ የሚደርሰዉን ግድያ በመቃወም ከተደረጉ ሰልፎችምስል፦ Belga/IMAGO

ጉቴሬሽ የሚመሩት ድርጅት ዋና ዘዋሪ ዩናይትድ ስቴትስ መቃወሟን እያወቁ ሲና በረሐ ድረስ ወርደዉ ርዳታ እንዲደርስ መማፀናቸዉ፣ የዓለም መሪዎች አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር የሚግባቡበትን ልክ ለመረዳት ይከብዳል።
በሳምንቱ ማብቂያ ግብፅ «የሰላም ጉባኤ» ያለችዉን ስብሰባ ካይሮ ላይ አስተናግዳለች።በጉባኤዉ የተካፈሉት የአረብ ሐገራት መሪዎችና የአዉሮጳ ሚንስትሮች የተግባቡበት አንድ ነጥብ ብቻ ነዉ።እስራኤልና በፍልስጤም ሁለት መንግስታት እንዲያቆሙ መጠየቅ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በ1947 ማብቂያ ላይ ያሳለፈዉ ዉሳኔ እስከዚያ ዘመን ድረስ ፍልስጤም ይባል የነበረዉ ግዛት እሁለት ተገምሶ ባንደኛዉ ገሚስ እስራኤል በተቀረዉ አረቦች ወይም ፍልስጤሞች መንግስት እንዲመሰርቱ የሚጠይቅ ነዉ።
እስራኤል ጠንካራ መንግስት መስርታለች።ፍልስጤሞች ግን መንግስት የላቸዉም።ከካይሮ 340 ኪሎ ሜትር ላይ የምተገኘዉን ጋዛን የሚያነፍረዉን የቦም-ሚሳዬል ዝናብ ማስቆም ያቃታቸዉ፣ ያልፈለጉ ወይም የሚደግፉት ወገኖች ድፍን 75 ዓመታት ታኝኮ የተተፋዉን ርዕሰ እንዳዲስ ማስታቸዉ ምናልባት ታዛቢ ዳግም እንዲጠይቅ ይገፋፋዉ ይሆናል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽምስል፦ picture alliance/dpa

በጉባኤዉ ላይ የተካፈሉት የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለጋዛ ሕዝብ ሰብአዊ ርዳታ ማቅረብ እንዲቻል የሰብአዊ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ይፈልጋሉ።

«በግሌ ሰብአዊ ርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባና ማከፋፈል እንዲቻል በግሌ ሰብአዊ ፈታ (ተኩስ አቁም) አስፈላጊ ይመስለኛል።አስቡት።ግማሽ የሚሆነዉ የጋዛ ሕዝብ ከየቤቱ ተፈናቅሏል።»

የአዉሮጳ ሕብረት አንጋፋ ዲፕሎማት ይሕን ሐሳባቸዉን ለካይሮ ጉባተኞች፣ ለዩናይትድ ስቴትስ ወይም ለእስራኤል አቻዎቻቸዉ ነግረዉ ይሆን? አይታወቅም።

የታወቀዉ ጋዛ ዛሬም ለ17ኛ ቀን በእስራኤል ጦር እየወደመች፣ ሕዝቧም ሕፃን ካዋቂ፣ ሴት ከወንድ ሳይለይ እየተገደለ፣ ከሞት ያመለጠዉ በረሐብ፣ዉሐ ጥም፣ በሕክምና መጠለያ እጦት እየተሰቃየ መሆኑ ነዉ።
የፍልስጤም ባለስልጣናት እንዳሉት የእስራኤል ጦር የገደላቸዉ ፍልስጤማዉያን ቁጥር ከ5ሺሕ በልጧል።አብዛኞቹ ሕፃናት፤ሴቶችና አቅመ ደካሞች ናቸዉ።
እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና ብሪታንያ በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ባለፈዉ መስከረም 26 በደቡባዊ እስራኤል ግዛቶች ላይ በከፈተዉ ጥቃት 1400 ሰዎች ገድሏል።ከ200 በላይ አግቷል።
አንዳድ ዘገቦች እንደጠቆሙት ዩናይትድ ስቴትስ ከ1990ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ ከመቶ የሚበልጡ ቡድናትና ድርጅቶችን በአሸባሪነት መዝግባለች።የከፔሩዉ አንፀባራቂ ፈለግ እስከ ዓለም አቀፉ አልቃኢዳ የነበሩ ቡድናት በኃይል ተደፍልቀዋል።ለዋሽግተን ቴል አቪቭ-ብራስልስ ተባባሪዎች የሰሞኑ ቁጥር አንድ አሸባሪ ሐማስ ነዉ።ሐማስ ሲጠፋስ? ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW