ማሕደረ ዜና፣ የግብፅ መፈንቅለ መንግሥት 10ኛ ዓመት
ሰኞ፣ ሰኔ 26 2015
የግብፅን የመከላከያ ሚንስትርነት ሥልጣንን ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹመት ጋር ደርበዉ የያዙት ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ ከታሕሳስ 2012 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ያዉጠነጠኑት ሴራ ሁሉ በሚፈልጉት መንገድና ባቀዱት ጊዜ ተሳክቷል።የዚያን ቀን የመጨረሻዉን አፈረጡት። ሐምሌ 3፣ 2013።
«ፕሬዝደንቱ የተሰጣቸዉ የ48 ሰዓታት ገደብ ከማለቁ በፊት ትናንት ማታ ባደረጉት ንግግር የሕዝቡን ጥያቄ እንዲቀበሉ እና እንዲያረጋግጡ የቀረበላቸዉን አማራጭ አልተቀበሉትም።»
መፈንቅለ መንግስት።መቶዎች የተገደሉበት፣10 ሺዎች የተገረፉ፣የተደበደቡ፣ የታሰሩበት ሚሊዮኖች የጮኹለት፣ አረብ አፍሪቃ ለአብነቱ የቋመጠለት የፍትሕ፣የእኩልነት፣ የዴሞክራሲ ተስፋ ተቀጨ።ዛሬ 10 ዓመቱ።ላፍታ እንዘክረዉ።
ከቱኒዚያ የተሻገረዉ የግብፅ ሕዝባዊ አመፅ የፕሬዝደንት ሆስኒ ሙባረክን አስተዳደር የካቲት 11፣ 2011 ላይ ገርስሶ ሲያስወገድ፣ የቀድሞዉን የአየር ኃይል ማርሻልና አስተዳደራቸዉን ብቻ ሳይሆን ከ1952 ጀምሮ ካይሮ ላይ የተተከለዉን ወታደራዊ ሥርዓትና የዉጪ አቃፊ-ደጋፊዎቹን ጭምር ከግብፅ ፖለቲካዊ ጨዋታ ዉጪ የማድረጉ አብነት ነበር።
ከሙባረክ መወገድ በኋላ የግብፅ የጦር መኮንኖች አንዴ በሽግግር መንግስት ስም፣ ሌላ ጊዜ ሰላምና ፀጥታ እስኪረጋጋ በሚል ሰበብ ጦር ኃይሉ ሥልጣኑን እንደያዘ እንዲቀጥል መጣራቸዉ አልቀረም።አብዛኛዉ ሙከራ በተለይ ቴሕሪር አደባባይን ሙጥኝ ባለዉ ተቃዉሞ ሰልፈኛ ሲከሽፍ የጦር መኮንኖቹ የመጨረሻ አማራጭ ያደረጉት የቀድሞዉን የዓየር ኃይል ጄኔራልና ጠቅላይ ሚንስትር አሕመድ መሐመድ ሻፊቅ ዘኪን በ2012ቱ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እንዲወዳደሩ ማድረግ ነበር።አደረጉት።ግን ተሸነፉ።
ግብፅ ቦረቀች።የአፍሪቃ፣ የአረብ፣ የእስያ ሕዝብ ከግብፅ አብነት ለመማር አቆበቆበ።የግብፅ የጦር ጄኔራሎች ግን ደነገጡ-ተበሳጩም።ምርጫዉ በርግጥ በረጅም ጊዜዉ የግብፅ ታሪክ የመጀመሪያዉ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነበር።ይሁንና እስልምና ኃይማኖትን ከፖለቲካ የቀየጠዉ እስላማዊ ወድማማቾች የነፃነትና የፍትሕ ፓርቲ ባለዉ የፖለቲካ ማሕበር በኩል የስልታዊቱን አረብ-አፍሪቃዊት ሐገር ፖለቲካ መቆጣጠሩ ለዉጪዎቹ በብዙ ምክንያት የደስታም-የሥጋትም ምልክት ነበር።
የአንካራ፣ የቀጠር፣ የቴሕራን፣ የቱኒዚያና የብጤዎቻቸዉ ሐገራት መንግስታት ከድል አድራጊዎቹ ጋር ለመቆም አላመነቱም።ፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲ የመሪነቱን ሥልጣን እንደያዙ የገቡት ቃል ግን ከደጋፊዎቻቸዉ ይልቅ ለተቃዋሚዎቻቸዉ በጣሙን ለምዕራቡ ኃያላንና ለአረብ ተከታዮቻቸዉ ማረጋገጪያ ብጤ ነበር።
«ከናንተ ጋር ሆኜ አዲሲቱን ግብፅን ለመገንባት ወስኛለሁ።በዘመናዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት የሚመራ መንግስት እንመሰርታለን።ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በሙሉ እናከብራለን።በመላዉ ዓለም ሰላም ለማስፈን እንጥራለን።»
ምዕራቦች በጣሙን ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ግን የመካከለኛዉ ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ ቲሞቲይ ካላዳስ በቀደም እንዳሉት አርቀዉ አለማሰባቸዉ ከሚያስከትለዉ መዘዝ መማር አይፈልጉም።
«በመሰረቱ ምዕራባዉያን መንግስታት አቀራረባቸዉ የአጭር ጊዜ ከመሆኑ ስሕተት ሁል ጊዜ አይማሩም።ስለዚሕ የሚደርሰዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት ቸል ብለዉ መረጋጋት እንዲኖር በሚል (የወሰዱት ርምጃ) ብዙም መረጋጋት አላመጣም።»
በ1952 ኮሎኔል ገማል አብድናስር የመሯቸዉ የግብፅ የጦር መኮንኖች የንጉስ ፋርቁን መንግስት ለማስወገድ ሲያሴሩ የዋሽግተን-ለንደን ድጋፍ አልተለያቸዉም ነበር።
መፈንቅለ መንግስቱ ብሪታንያ በግብፅና በተቀረዉ የዓረብ ዓለም የነበራትን የቅኝ ገዢ የበላይነት ነቅሎ የዩናይትድ ስቴትስን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መሰል ሥርዓት ከማስፈን ባለፍ ለግብፅ ሕዝብ፤ ላካባቢዉ ሰላምም ሆነ፣ ለአንግሎ አሜሪካኖች የረጅም ጊዜ ጥቅም ብዙም የፈየደዉ አልነበረም።
ግን የፖለቲካ ተንታኝ ካላዳስ እንዳሉት ምዕራቦች ካለፈዉ ስሕተት አልተማሩም።በየዘመኑ የሚዘምሩ፣ ለየራሰቸዉ የሚመርጡት፣ ለየሐገሩ የሚመክሩ የሚያስትምሩት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ካይሮ ላይ ብልጭ ማለቱ አልጣማቸዉም። የአዲሱን ፕሬዝደንት ቃልም አላመኑትም።
ሕዳር 2012 አዲሱ ሕገ መንግስት ሲፀድቅ የተፈጠረዉ ዉዝግብ የግብፅ የጦር ጄኔራሎችን-ከሐገሬዉ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የቴል አቪቭ፣ ዋሽግተን፣ ለንደን የሥለላ-የፖለቲካ ዘዋሪዎችን ከሪያድ -አቡዳቢ ነገስታት ጋር ባንድ አሰለፈ።
ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የመሐመድ ሙርሲ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን በ2018 ሚድል ኢስት አይ ለተባለ አምደ-መረብ እንደነገሩት ማርሻል አል ሲሲ ከታሕሳስ 2012 ጀምሮ በየሳምቱ ሐሙስ ማታ ወደ ግብፅ ባሕር ኃይል መኮንኖች መዝናኛ ክበብ ይሄዱ ነበር።
ማርሻሉ ወደ መኮንኖቹ ክበብ የሚሔዱት እንደ ሙስሊሞቹ ወግ ለ«ለይለተን ጁመዓ» ፀሎት አልነበረም። ከሌሎች የጦር መኮንኖችና ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ለመነጋገር እንጂ።አል ሲሲ ባሕር ኃይል መኮንኖች ክበበብ ዉስጥ መሐመድ አልበረዳይና አምር ሙሳን ከመሳሰሉ ዕዉቅ ፖለቲከኞች ጋር በተደጋጋሚ መነጋገራቸዉን ፕሬዝደንት ሙርሲ ያዉቃሉ።
ይሁንና ሙርሲ የሚያዉቁትን ለአል ሲሲ ከመንገራቸዉ በፊት ራሳቸዉ አል ሲሲ «ከተቃዋሚዎች ጋር የተፈጠረዉን ልዩነት ለማስወገድ እየጣርኩ ነዉ» አሏቸዉ።የዋሑ ፕሮፌሰር የማርሻላቸዉን ቃል አልጠረጠሩም ወይም እንደዘበት አለፉት።
በፊልድ ማርሻሉ ጉትጎታና ዋስትና የተበረታቱ የሚመስሉት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን አዲሱን ሐገ መንግስትና ፕሬዝደንቱን በመቃወም ተሕሪር አደባባይን ያጨናንቁት ያዙ።የተቃዋሚዎቹ መጠናከር ያሳሰባቸዉ የሙርሲ ደጋፊዎች ዘግየት ብለዉም ቢሆን ዓመቱ አጋማሽ ላይ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ወሰኑ።
ይሁንና ጦር ሠራዊቱ ተሕሪር አደባባይ በተቃዋሚ ሰልፈኞች ተይዟል በሚል ሰበብ የሙርሲ ደጋፊዎች ራብአና ነሐዳ በተባሉ መለስተኛ አደባባዮች እንዲወሰኑ አደረገ።ሰኔ 23፣2013 ማርሻል አል ሲሲ ሙርሲንና ደጋፊዎቻቸዉን የሚነቅፍ አሰራጩ።አል ሲሲ የግብፅ ጦር ኃይልን የሚነካ ወይም የሚያጠቃ ማንኛዉንም ወገን ጦሩ እንደማይታገስ ያስጠነቀቁበት ንግግር የሙርሲ ዘመን ማብቃቱን ጠቋሚ ነበር።
የዚያኑ ቀን የቤተ መንግስቱ ልዩ ጠበቃ ጦር አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ዘኪ «ለፕሬዝደንቱ ደሕንነት» በሚል ሰበብ ሙርሲ ከኢትሐዲያ ቤተ-መንግስት ወደ ልዩ ጥበቃዉ ጦር ዋና ማዘዢያ እንዲዛወሩ አዘዙ።
ጄኔራል ዘኪ የአል ሲሲ ቀኝ ዕጅ እንደነበሩ የሙርሲ ደጋፊዎች ያወቁት ነገሩ ሁሉ ካበቃ በኋላ ነበር።
ፊልድ ማርሻል አልሲሲ በ1992 ብሪታንያ፣ በ2006ና ሌላ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የከፍተኛ የጦር አዛዥነት ኮርስ ተከታትለዋል።በሪያድ የግብፅ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ሆነዉ ሰርተዋል።ከሶስቱም መንግስታት ወይም የስለላ ተቋማት ጋር በቀላሉ ለመገናኘት ይችላሉ።
የአል ሲሲ ሴራ፣የሙርሲ ተቃዋሚዎች ሰልፍና ጥቃት በተጠናከረበት መሐል የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ ለፕሬዝደንት ሙርሲ ደዉለዉ «ጠንካራ ዉሳኔ ይወስኑ» የሚል አሻሚ መልዕክት ነገሯቸዉ።ሰኔ 30 ነበር።
ሙርሲ የኦባማን የግድምድሞሽ መልዕክት ሚስጥር ለመፍታት ሲያብሰለስሉ፣በግብፅ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር አነ ፓቴርሰን ከሙርሲ የዉጪ ግንኙነት አማካሪ ጋር ባደረጉት ዉይይት «የሚቃወማችሁ ህዝብ ቁጥር የፈለገዉን ያክል ቢበዛም» አሏቸዉ «መልዕክታችሁ ማነጣጠር ያለበት ለአል ሲሲ እንጂ ለሕዝቡ መሆን የለበትም» አከሉ።
ከሰኔ 30 እስከ ኃምሌ 3 በነበረዉ ጊዜ የኖርዌ አምባሳደር፣ የብሪታንያ ዲፕሎማት፣የአረብ መልዕክተኞች ሙርሲና ረዳቶቻቸዉ ቢሮ ሲመላለሱ፣ አል ሲሲ ዝግጅታቸዉን አጠናቀቁ።እና በቴሌቪዝን ብቅ ብለዉ መፈንቅለ መንግስቱን አወጁ።
አል ሲሲ መፈንቅለ መንግስቱን ሲያዉጂ የግብፅ ሕዝብ ለመረጣቸዉ ፕሬዝደንት ደሕንነት መጨነቃቸዉን ከሳምንት በፊት ሲናገሩ የነበሩት ጄኔራል መሐመድ ዘኪ በሕዝብ የተመረጡትን መሪ ሙርሲና ረዳቶቻቸዉን አሰሩ።
አል ሲሲ መፈንቅለ መንግስቱን ባወጁበት መልዕክታቸዉ የሚያዙት ጦርና የፀጥታ ኃይል የግብፅን ህዝብ ሰላም፣ነፃነትና ደሕንነት፣ በሰላማዊ መንገድ የሚያደርገዉን ተቃዉሞም እንደሚያከብር ቃል ገብተዉ ነበር።ቃላቸዉ ግን ከቃል አላለፈም።መፈንቅለ መንግስቱን የተቃዋሙ በሺ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ባደባባይ አስገደሉ።አሳሰሩ።አስደፈሩም።የሙስሊም ወድማማቾች ማሕበርና የመሪዎቹን ሐብት ንብረት፣ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሳይቀር ተወረሰ ወይም ተዘጋ።
የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት አል ሲሲ ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ በመቶ የሚቆጠሩ ደብዛቸዉ ጠፍቷል።በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ታስረዋል።የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ ነፃ መገናኛ ዘዴ ብሎ ነገር በአል ሲሲዋ ግብፅ «ሐራም» ነዉ።መሐመድ ሙርሲም ወሕኒ ቤት እንደማቀቁ ሞቱ።
ዩናይትድ ስቴትስ መፈንቅለ መንግሥቱን «መፈንቅለ መንግሥት» ለማለት እንኳን አልፈቀደችም። የአፍሪቃ ሕብረት፣ ቱርክና ኢራንን የመሳሰሉ ሐገራት ወግዘትም ከሳምንታት «ጫጫታ» ባለፍ ያመጣዉ ዉጤት የለም።ማርሻሉ በ2018 በተደረገዉ ምርጫ ብቻቸዉን ተወዳድረዉ በ97 ከመቶ ድምፅ ማሸነፋቸዉ ተነግሯል።የአረብ-ምዕራባዉያን መንግስታት ምርጥ ወዳጃም ናቸዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ