1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ ግንቦት፣ 1983 ለዉጥና የኢትዮጵያ ለዉጦች ክሽፈት

ሰኞ፣ ግንቦት 19 2016

ኢትዮጵያ የለዉጥ ሐገር ናት።ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ጀምሮ በ1933 ትልቅ ለወጥ አድርጋ ነበር።በ1953 የለዉጥ ሙከራ ተደርጎባት ነበር።በ1966፣ በ1983፣ በ2010 ለዉጥ አድርጋለች።ለየሥርዓት ለዉጡ መምጣት ሺዎች ምናልባትም መቶ ሺዎች አልቀዋል።ሁሉም ለዉጥ ግን ከሽፏል።ለምን?

በ1997ቱ ምርጫ ወቅት አዲስ አበባ አደባባይ ከወጡ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ጥቂቶቹ
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ደጋፊዎች ሰልፍ። አዲስ አበባ-1997ምስል Reuters/Tiksa Negeri

ማሕደረ ዜና፣ የግንቦት 1983 ለዉጥና የኢትዮጵያ ለዉጦች ክሽፈት

This browser does not support the audio element.


ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ባለታሪክ ሐገር ናት።የረጅም ጊዜ የአመፅ፣ የግጭት፣ የጦርነት የተደጋጋሚ ለዉጥም ሐገር ናት።በዚያ ዘመንም ከቅርብ ጊዜ ታሪኳ፣ከአመፅ፣ ጦርነት ለዉጦችዋ አንዷ ሆነ።
«ጀግናዉ የኢሐአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረዉን ራዲዮ ጣቢያ----ተቆጣጥሮታል።ግንቦት 20፣1983 ዓመተ ምሕረት።»

ነገ 33 ዓመቱ። የጦርነቱ ፍፃሜ፣የፍፃሜዉ ማግስት ግጭት፣ጦርነትና የኢትዮጵያ ጉዞ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

የቀድሞዉ የኢሕአፓ ታጋይ፣ከኢሕአዲግ አባል ድርጅቶች የአንዱ የኢሕዴን መስራችና የመጀመሪያ አስተባባሪ አቶ ያሬድ ጥበቡ ልዩ ግን የግል ትዝታ አላቸዉ። 
                         
«ያን ጊዜ እንግዲህ የዋሽግተን ዲሲ ነዋሪ ነበርኩ።ብታምንም ባታምንም ለሠርግ እየተዘጋጀሁ ነበር።ከሶስት ሳምንት በኋላ ሠርጌ እየመጣ ነበር።»

ያንዱ ዘመን አመፅ-ጦርነት ፍፃሜ የሌላዉ ጅምር

 

የዚያን ቀን የሆነዉ ግን ጌታቸዉ ጀቤሳ በሚል የትግል ሥም ይጠሩ የነበሩት ያሬድ ጥበቡና ብዙ፣ ምናልባትም ሚሊዮን ብጤዎቻቸዉ የተሳተፉበት፣ ሺዎች ጓዶቻቸዉ ያለቁበት፣ የዚያ ዘመን አመፅ፣ግጭት፣ ጦርነት ማብቂያ፣ የ17 ዘመኑ የደርግ ሥርዓት ፍፃሜ፣ የአዲስ ሥርዓት ጅምር፣ ተስፋ ግን ደግሞ የሌላ አመፅ ጅምርም ነበር።ቅይጥ እዉነት።
«ያሁኔታ ነበር። ግን ከዚያ ጋር የዋሽግተን ከተማ ደግሞ በጣም በፀረ ኢሕአዴግ ማለት ይቻላል ግን በዋናነት በፀረ ሕወሓት ሰልፎች---ኢድሐቅ  የሚባል ነበር ሰፊ የሆነ የተቃዉሞ ሰልፎች የሚካሔዱበትም ወቅት ነበር።»  

ያኔ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ዉስጥ ለነበሩት ለኋላዉ ዕዉቅ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ለአቶ ልደቱ አያሌዉና ለብዙ የዕድሜ አቻዎቻቸዉም ለዉጡ የአንዱ ግጭት፣ ጦርነት፣ አመፅ ፍፃሜ በመሆኑ እፎይታ-የዚያኑ ያክል የእስከዚያ ዘመኑን የኢትዮጵያን ሰሜናዊ ግዛት ኤርትራን የገነጠለ፣ ሰፊ፣ ትልቂቱን ሐገርና ወደብ አልባ ያደረገ በመሆኑ ቁጭትን የቀየጠ ነበር።«የተደባለቀ ስሜት» ይሉታል አቶ ልደቱ።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አርማ

«ባንድ በኩል የደርግ መንግስትን እንጠላ ነበር።በጣም ከፍተኛ የሆነ ግድያ ነዉ የነበረዉ።በተለይ እኔ የነበርኩበት አካባቢ የጦርነት ቀጠና ነበረ።ጦርነት ያልተለዉ አካባቢ ነበር።( ዛሬም አልተለየዉም።)--- ግን ያም ሆኖ በጣም የሚቆጠቁጠንና ልንቀበለዉ በፍፁም የማንችለዉ ጉዳይ ነበር።ከኢሕአዴግ ጋር ተያይዞ---የኤርትራ የመገንጠል ጉዳይ---»
ግንቦት 20ና ከዚያ በኋላ ብዙ የተወራ፣ የተሰበከ፣ የተዘመረለት ሠላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልፅግና ብዙ አልቀጠለም።አዲሶቹ ገዢዎችም የደረግ-ኢሰፓ ርዝራዦች፣ የኢሕአፓ፣ የመኢሶን ትምክሕተኞች፣ የኦነግ ጠባቦች፣ የኢትሐድ አሸባሪዎች ከሚሏቸዉ ኃይላት ጋር ይላተሙ ገቡ።ሕወሐት ኢሕአዴጎች ለነፃነቷ ሕይወት፣ ደም አጥንታቸዉን የገበሩላት ኤርትራ፣ከየትኛዉም ዓለም ቀድመዉ ነፃነቷን በይፋ ያወጁላት ኤርትራ፣ ሕወሓት ኢሕአዴጎች ለሚመሯት ኢትዮጵያ ከጥብቅ ወዳጅነት ወደ ጠላትነት ለመቀየር ከስምንት ዓመት በላይ አልጠበቀችም።የቀድሞዉ የኢትዮጵያ መሪ መለስ ዜናዊ ባንድ ወቅት «ጅል»-ያሉት አዲስ ጦርነት ተቀጣጠለ።

ጅሉ ወይም የጅሎቹ ጦርነትና ምጣኔ ሐብት

 

«ኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ነፃ ከወጣች በኋላ (ነፃ መዉጣት የኤርትራ ሕዝብ ፍላጎት በመሆኑ እኔም ደግፌዋለሁ።ከዚያ በኋላ በድንበር፣ በምጣኔ ሐብት ግንኙነት፣ ባሕር መጠቀምን በተመለከ፣ ምክንያቱም ኤርትራ ነፃ ከወጣች በኋላ እኛ ወደብ አልባ በመሆናችን እነዚሕ የመሳሰሉ ብዙ ችግሮች ነበሩብን።እነዚሕ ችግሮች ከ1990 እስከ 1992 በፍፁም መሆን ወደሌለበት የጅል ጦርነት አስገቡን።»

«ጅሉ» ጦርነቱም ሆነ ጦረኞቹ በትንሽ ግምት ከሁለቱም ወገን መቶ ሺዎች አልቀዉበታል።ያቺ በጦርነት ኖራ፣ ከጦርነት የምትማገደዉ ጥንታዊት ሐገርም ከቀድሞ ክፍለ-ሐገሯ ጋር ለትዉልድ በቀጠለ ግጭት፣ቁርቁስ፣ ሽኩቻ፣የእጅ አዙር ጦርነት ተዘፈቀች።ያም ሆኖ 27ቱ የኢሕአዲግ  ዘመን በምጣኔ ሐብቱ ረገድ መሻሻል ማድረጉን ብዙዎች ይመሰክራሉ።አቶ ያሬድም።
«የረካሁባቸዉ አንዳድ ነገሮች አሉ።ለምሳሌ በኤኮኖሚዉ መስክ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያስመዘገባቸዉ ነገሮች እምደግፋቸዉና መቀጠል ነበረበት ብዬ የማስባቸዉ ይኽ ወደ 28 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ከድሕነት አረንቋ መለቃቁ፣ 2500 ሰዎች መልታይ ሚሊየነርስ የሆኑበት፣ ሚድል ክላሱ የሰፋበት---» 

ግን የምጣኔ ሐብቱ እድገት ፅኑ፣ ነፃና ገለልተኛ መሠረት ሥላልነበረዉ እንዳጀማመሩ አልቀጠለም።እንዲያዉም ተንታኞች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከምስራቅ ሶማሊያ እስከ ሰሜን ትግራይ ጫፍ ጦርነት፣ ግጭት፣ የጎሳ መገዳደል፣ አመፅ፣ ሁከት፣ ጭቆና እመቃ ተንሠራፍቶባት፣ ዕዳ የዉጪ ዕዳ እያናጠረባት «አደገች» መባሉ  ግንጥል ጌጥ ብጤ ነበር።አቶ ልደቱ አያሌዉ እንደሚሉት ደግሞ ኢሕአዴጎች አደጋዉን እያዩ ለሕዝቡ ዳቦ እናቅርብ ማለታቸዉ ለኢትዮጵያ የተከረዉ የለም።
 

የቀድሞዉ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ምሥልምስል AP

«አደጋዉ እየታየ።የዲሞክራሲ አለመኖር የሚያመጣዉ ጣጣ፣ ቅራኔዉ እየሰፋ እየሔደ እያዩት።ሐገሪቱ ከመረጋጋት ይልቅ ወደ ብጥብጥ የማምራት አዝማሚያ ዉስጥ እየገባች እንደሆነ እያዩ ቆም ብለዉ ራሳቸዉን መጠየቅና ማረም አልቻሉም።እና ሕዝቡ ዳቦ ካቀረብንለት፣ ምግብ፣ መጠለያ ካቀረብንለት ዴሞክራሲ ጥያቄዉ ሊሆን አይችልም የሚል አስተሳሰብ ዉስጥ ነዉ የነበሩት።»
ጣጣዉ አልቀረም።ሕወሐት መራሹ የኢሕአዴግ ሥርዓት በ27ኛ ዓመቱ በሕዝብ ትግል ተወገደ።መጋቢት በ2010።የያኔዉ ኦሕዴድ መራሹ ሁለተኛዉ የኢሕአዴግ ወይም የኋላዉ የብልፅግና ሥርዓት በየዘመኑ እንደሚደረገዉ  ለዉጥ ሁሉ ከብዙዎች ጠንካራ ድጋፍ አግኝቶ ነበር። የአዉሮጳ-አሜሪካ ፖለቲከኞችም ለዉጡን አድቀዉ፣አወድሰዉ፣ መሪዎቹን በሽልማት አንበሻብሸዉም ነበር።ኢትዮጵያ ግን እንደለመደችዉ ከግጭት፣ጦርነት፣ሁከት፣ ድሕነት፣ ረሐብ አዙሪት አልወጣችም።እንዲያዉም አንዳዶች እንደሚሉት የኢትዮጵያዉያን እልቂት፣ረሐብ፣ ሥደት መፈናቀል ባሰ እንጂ አልቀነሰም።

ለዉጦችና ክሽፈታቸዉ


ኢትዮጵያ የለዉጥ ሐገር ናት።ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ጀምሮ በ1933 ትልቅ ለወጥ አድርጋ ነበር።በ1953 የለዉጥ ሙከራ ተደርጎባት ነበር።በ1966፣ በ1983፣ በ2010 ለዉጥ አድርጋለች።ለየሥርዓት ለዉጡ መምጣት ሺዎች ምናልባትም መቶ ሺዎች አልቀዋል።ሁሉም ለዉጥ ግን ከሽፏል።ለምን? አቶ ያሬድ ሁለት ምክንያቶች ይጠቅሳሉ።
«አንድ ዜግነቱን ከምር መቀበል ያቃተዉ ሕዝብ ያለን መሆኑ ነዉ የሚመስለኝ።ቀስ በቀስ ለብቱ እየታገለ የተለያዩ ለዉጦች እያመጣና እነዚያን የተዳመሩ ለዉጦች ወደ አጠቃላይ አገራዊ  ለዉጥ የሚያመጡበትን ዕድል እየፈጠረ የሚሔድ አገር ወይም ሕዝብ ስለሌለን ይመስለኛል።ያን አይነት ለብቱ ቀናኢ የሆነ የሲቪል ማሕበረሰብና ኢንስቲቲዉት ሥለሌለን ይመስለኛል።-----ባንድ በኩል እምናየዉ ምንድነዉ አገሪቱ ያፈራቻቸዉ ምሁራን በነዚሕ ታሪካዊ ወቅቶች ላይ የሚከስሙበትም አደጋ ጭምር ነበር።»
አቶ ልደቱ ሶስት ምክንያት ይጠቅሳሉ።
«ሰሞኑን የፃፍኩት አንድ ወረቀት ላይ ለምንድነዉ ችግራችን የበለጠ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እየተወሳሰበ የመጣዉ የሚለዉን ለመመለስ ሞክሬያለሁ።ሶስት ምክንያቶች ናቸዉ ያሉት።አንዱ የአመራር ችግር ነዉ።በንጉሱ ጊዜ የተማሩ ሰዎች ነበሩ----»
ኢትዮጵያ የነጆሞ ኬንያታን የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል፣የዚምባቡዌ፣ የናሚቢያ፣ የደቡብ አፍሪቃ ዜጎችን የመብት እኩልነት ፍልሚያን ደግፋለች።ማንዴላን አሰልጥናለች።ጆሽዋ ንኮሞ፣ ሮበርት ሙጋቤ፣ ሳም ንዮማን፣ ጆን ጋራንግን  ረድታለች፣ ቡድናቸዉን አስታጥቃለች።

ዛሬ የአፍሪቃ የሠላም ደሴት፣ የዕድገት ብልፅግና አብነት፣ የፍትሕ፣ ዲሞክራሲ ሥርዓት ምሳሌዎች ግን አንድም ደቡብ አፍሪቃ፣ ሁለትም ኬንያ፣ ሶስትም ናሚቢያ እንጂ ኢትዮጵያ አይደለች።የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚጭሩትን ጦርነት አብራጅ-ሸምጋዮች፣ የኢትዮጵያ ስደተኞችን አስተናጋጆችም ፕሪቶሪያና ናይሮቢ እንጂ ኢትዮጵያዉያን ራሳቸዉ አይደሉም።
ሰሞኑን በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የምትዘዋወር አንዲት ደብዳቤ በአቶ ያሬድ ጥበቡ በኩል ትናንት ደርሳኝ አነበብኳት።በዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞዉ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሐኑ ድንቄ ከ55 ዓመት በፊት ለአፄ ኃይለ ሥላሴ እንደፃፏት የተጠቀሰችዉ ደብዳቤ አምባሳደሩ ከቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ጋር በተነሱት ፎቶ ታጅባለች።«ግንቦት 25፣ 1957 ነዉ የተፃፈችዉ» ይላል የደብዳቤዋ ማስተዋወቂያ።
«ባሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ማሕበራዊ ሕይወት የሚታየዉን ምሬትና ግፍ፣ የፍትሕም መጓደል---»እያለች ትጀምርና---ይሕ ሁኔታ የሚታረምበትን በኅብረት ለመስራት ባንሞክር ታላቅ ብጥብጥ እንደሚያስከትልብን ከታሪክ መማር ካልቻል ---» እያለች ትቀጥላለች።

ከ1983 ወዲሕ ከተደረጉ ከተደጋጋሚዎቹ ጦርነቶች የአንዱ መዘዝ።ለጦር መሳሪያ የዋለ የሕዝብ ገንዘብ ይጋያል፣ሕዝብ ይሰደዳል።ምስል GIULIA PARAVICINI/REUTERS

የኢትዮጵያ ብዙዎቹ እንሚስማሙበት ሕዝቧ ለመብቱ ለመታገል የሚሸማቀቅባት፣ ፖለቲከኞችዋ ከዉይይት-ምክክር ይልቅ ግጭት፤ ጦርነት፣ መገዳደልን የሚመርጡባት፣ በለስ ቀንቷቸዉ ቤተ መንግስት የተቆጣጠሩ ኃይላት ተቃዋሚዋሚ ወይም ተፎካካሪያቸዉን በጥይት፣ መካሪዎቻቸዉን በልምጭ፣ ሕዝባቸዉን በጦርነት፣ ረሐብ፣ድሕነት የሚገርፉባት ሐገር ነበረች። አሁንም ቁልቁል ማደጓ ነዉ ቁጭቱ።

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW