ማሕደረ ዜና፣ 2023 አብይት ፖለቲካዊ እዉነቶች ቅኝት ክፍል II
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2016
አብዛኛዉ ዓለም ዘመኑን በግሪጎሪያኑ የዘመን ቀመር አሰላም-አላሳለ አዲስ ዓለም አለ።ትናንት ለዛሬ አጥቢያ።የዘመን መለወጫዉ ፌስታ፣ የመልካም ምኞት መግለጫ፣ ፀሎት፣ የርችት ተኮሱም ከየከተሞቹ ተንቆረቆረ። ከትናንት እኩለሌት በኋላ አምና በምንለዉ 2023 ከተከናወኑ አበይት የዓለም ፖለቲካዊ እዉነቶችን የመጀመሪያዉ ክፍል ሳምንት ቃኝተናል።ዛሬ ሁለተኛና የመጨረሻዉን ክፍል በአጫጭሩ ዳስሰን ዓመቱን ለነበር ዝክር እንሰናበተዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
አዲስ ዓመት-2024 ርችት ተተኮሰ።ለተመቸዉ መጠጥ፣ ሙዚቃ፣ ዳንኪራዉ ፈሰሰ-ቀለጠም።የኃይማኖት አባቶች፣ የሐገራት መሪዎችና የፖለቲከኞች የመልካም ምኞት መግለጫም በየመገናኛ ዘዴዉ ሲሰራጭ ዋለ-ዛሬ። ትናንት እኩለ ሌት ብራንደንቡርግ ቶር-በርሊን በነበረዉ ድግስ ላይ ከተከፋሉት ጀርመናዉያን አንዷ ኒኮለ በትሊንግ ግን «ዓለም አሁን ያለችበት ሁኔታ ጥሩ ዓይደለም» ይላሉ።
«ተስፋዬ፣ በርግጥ ዓለም የበለጠ ሰላም እንዲሰፍንባት ነዉ።ምክንያቱም ነገሮች አሁን ያሉበት ጥሩ አይደለም።በዚሕ መንገድ መቀጠል የለበትም።» ጋዛ ግን ከግዛቲቱ ነዋሪ አንዷ እናት ፋይዛ አል ዚናቲይ እንዳሉት ሐዘን፣ሰቆቃ፣ ዋይታ-ለቅሶ እንጂ የአዲስ ዓመት ፌስታ አታዉቅም።
«ልጄ፣አማቼ እና በጣም ብዙ ዉድ ሰዎችን አጥቻለሁ።አዲሱን ዓመት እንዴት ልቀበለዉ እችላለሁ።በ2024 የሟቾቹን መቀብር ለማየት፣ከፍርስራሽ ሥር እስከሬናቸዉን ለማዉጣት ወደ አካባቢዬ መመለስ ነዉ የምመኘዉ።ስላሉበት ሁኔታ ምንም የምናዉቀዉ ነገር የለም።መቀብራቸዉ ያለበትንም ሆነ መቀበር አለመቀበራቸዉንም እናዉቅም።በቤቶቻችን ፍርስራሽ ላይ ዳግም ለመገናኘት እመኛለሁ።»
የእስራኤል ጦር ዓመቱ መጀመሪያ ወር ጥር 27 (2023) ጀኒን፣ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በሚኖሩ ፍልስጤማዉያን ላይ በተከታታይ ያደረሰዉ ጥቃት ሚያዚያ 5 እየሩሳሌም ደረሰ።
የእስራኤል የፀጥታ ኃይላት በሙስሊሞቹ ቅዱስ ወር ረመዳን፣ የሙስሊሞቹን 3ኛ ቅዱስ ስፍራ አል-አቅሳ መስጊድን ረግጠዉ ለሶላት የታደሙ ፍልስጤማዉያንን ይደበድቡ እያፈሱ ያስሩ ያዙ።የፀጥታ ኃይላቱ ሽማግሌ፣ ካዋቂ፣ ሴት ከወንድ ሳይለዩ መደብደብ፣ ማንገላታት፣ ማዳፋት ማሰራቸዉ ያዉ 75 ዓመታት እንደተለመደዉ ከዕለታት የመገናኛ ዘዴዎች ርዕስነት ባለፍ እስካሁን ተመዝዞ የማያልቅ መዘዝ ያመጣል ብሎ የገመተ ታዛቢ በርግጥ አልነበረም።
ጥቅምት ሰባት።እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ «የአል-አቅሳ ጎርፍ ባለዉ ዘመቻዉ ደቡባዊ እስራኤልን ካየር፣ከምድር፤ ከባሕር ወርሮ 1139 ሰዎች ገደለ።የእስራኤል ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ከሟቾቹ 373ቱ ወታደሮች፣71ዱ የዉጪ ሐገር ዜጎች ናቸዉ።
ሐማስ በዚሕ ጥቃቱ 250 የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎችንም አግቶ ነበር።የእስራኤል መሪዎች የሀማስን ጥቃት ለመበቀል ሰዓታት አልወሰደባቸዉም።የሐገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት «የሰዉ አዉሬዎች» ያሏቸዉን ለማጥፋት ጦራቸዉ ጋዛ ሰርጥ ላይ የሚያዘንበዉ የቦምብ፣ ሚሳዬል፣ መድፍ አዳፍኔ አረር አልበቃቸዉም።ያን ሕዝብበምግብ፣ዉኃና መድሐኒት ዕቀባ ይገርፉት ያዙ።
«ጋዛ ላይ ሙሉ ከበባ ጥለናል።ኤሌክትሪክ የለም።ምግብ የለም።ዉኃ የለም።ጋዝ የለም።ሁሉም ነገር ይቆለፋል።የምንዋጋዉ ከሰብአዊ አዉሬዎች ጋር ነዉ።እርምጃችንም በዚሕ ልክ ነዉ።»
ሕዳር 22 ሐማስና እስራኤል በቀጠር ዋና ሸምጋይነት ላጭር ጊዜ ተኩስ ለማቆምና የታጋችና እስረኞች ልዉዉጥ ለማድረግ ተስማሙ።የቀጠር ባለስልጣናት ያኔ እንዳሉት ተኩስ አቁሙ ከህዳር 24 ጀምሮ ለ4 ቀናት የሚጸና ነበር።
ተኩስ አቁሙ ለተጨማሪ 2 ቀናት ተራዝሞ ጋዛ በጥቅሉ ለ6 ቀናት ፋታ አገኘች።ሰላማዊዉ ሰዉ የርዳታ እሕል ዉኃ ሲቃመስ፣ ሐማስ ምናልባት መሽሎክሎኪያ፣ የእስራኤል ጦር የጎደለዉን ቦምብ ሚሳዬል ከዩናይትድ ስቴትስ ለመዛቅ ሁለቱም ታጋች-እስረኞቻቸዉን ለማስለቀቅ ተጠቀሙበት።
ሐማስ ካገታቸዉ የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎች ከአንድ መቶ በላይ ሲለቅ እስራኤል ባንፃሩ ከ250 በላይ ፍልስጤማዉያን እስረኞችን ለቀቀች። የእስረኛ-ታጋቾች ታሪክ፣ የየቤተሰቦቻቸዉ ደስታ-ፌስታ ተተርኮ ሳያበቃ ጋዛ ትነፍር ሕዝቧ ይረግፍ፣ይቆስል፣ ይሰደድ ገባ።አስከሬን፣ ቁስለኛ፣ ስደተኛ ከመቁጠር ባለፍ ሕይወት ለማዳን ምንም ያልተከረዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ያቺን የድሆች ሰርጥ «መቃብር« አሏት።
የጋዛ እልቂት መዘዝ የሊባኖሱን ሺአ ሚሊሺያ ሒዝቡላሕን፣ የኢራቅ የተለያዩ አማፂዎችን የመሳሰሉ ኃይላትን በእስራኤልና በዩናይትድ ስቴትስ ይዞታና ጥቅሞች ላይ ለጥቃት ሲያነሳሳ የየመን ሁቲዎች ደግሞ በቀይ ባሕር ላይ ወደና ከእስራኤል የሚቀዝፉ መርከቦችን በሚሳዬልና ድሮን ይመቱ ያዙ።
ዩናይትድ ስቴትስም ቀይ ባሕር ላይ ከጦርነቱ በቀጥታ ተሞጀረች።ዓመቱ ለፍፃሜዉ ሲጓዝ ትናንት የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሶስት የየመን ሁቲዎች ጀልባዎችን መምታቱን ሁቴዎች አስታዉቀዋል።የሁቲዉ ቃል አቀባይ ብርጌድር ጄኔራል ያሕያ ሳርዒ እንዳሉት ባሕር ኃይላቸዉ የአሜሪካ ጠላቱን ጥቃት መክቶ ሌላ መርከብ ደብድቧል። «በሌላ በኩልና በፈጣሪ ፈቃድ፣ የየመን ጦር ኃይል ተገቢዉን የባሕር ኃይል ሚሳዬል በመተኮስ መርስክ ሐንግዡ በተባለ የኮንቴይነር መጫኛ መርከብ ላይ ወታደራዊ ርምጃ ወስዷል።መርከቡ በኃይል ወደተያዘዉ የፍልስጤም ግዛት የሚቀዝፍ ነበር።»
ብዙዎች እንደፈሩት የጋዛዉ እልቂት አካባቢዉን እያተራመሰ ነዉ።ለዓለም ሰላም፣ ለዲሞክራሲና ፍትሕ መከበር ቆመናል የሚሉት ዩናይትድ ስቴትስ፣ምዕራብ አዉሮጳና ተባባሪዎቻቸዉ በቀጥታ፣ የአረብና የምስራቅ ኃያላን በተዘዋዋሪ ከትርምሱ ተዘፍቀዉ ይዳክራሉ።
የእስራኤል ጦር ጋዛ ላይ በከፈተዉ ጥቃት፣ የፍልስጤም ባለስልጣናት እንዳሉት 22 ሺሕ ሰላማዊ ፍልስጤማዉያንን፣ ከአንድ መቶ በላይ ጋዜጠኛና የመገናኛ ዘዴ ሰራተኞችን፣ከ300 በላይ ሐኪሞች፣የአምቡላንስ ሰራተኞችና ረዳቶቻቸዉን፣ 142 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞችን ፈጅቷል።56 ሺሕ ሕዝብ አቁስሏል።1.9 ሚሊዮን አፈናቅሏል።እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የእግረኛ ዉጊያ መክፈቷን ካስታወቀች ከጥቅምት 31 ወዲሕ 168 ወታደሮችዋ መገደላቸዉን አስታዉቃለች።
የዓለም ሕግና ሥርዓትን የማስከበሩ ጥያቄ፣ የሰላማዊ በተለይም የሕፃናት፣ የሴቶችና የአቅመ ደካሞችን ሕይወት የመጠበቁ ግዴታ፣ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ካላቸዉ ከዋሽግተን፣ ከለንደን፣ ከፓሪስ፣ ከቤጂንግም ሆነ ከሞስኮ እስካሁን አልተሰማም።የተሰማዉ ባለፈዉ አርብ ከወደ ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ እንጂ።ደቡብ አፍሪቃ የእስራኤልን የኃይል ርምጃ መቃወም፣ ማዉገዝ፣ ኋላም መክሰሷ ደምቆ የተዘገበበት 2023 ለኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የግጭት፣ የምርጫ፣ ዉዝግብ ነበር።
ከ120 የሚበልጡ የኮንጎ አማፂያንን ለመዉጋት ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዩጋንዳና ብሩንዲ በሺ የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸዉን ወደ ምሥራቅ ኮንጎ አዘመቱ።መጋቢት 4 አንድ መቶ የብሩንዲ ወታደሮች ኪቩ ሰፈሩ።በአራተኛዉ ቆን እዚያዉ ኪቩ ዉስጥ አማፂያን 40 ሰላማዊ ሰዎች ገደሉ።
ታሕሳስ 20፣ ኮንጎ፣ ግጭት፣ ግድያ፣ ጎርፍና በሽታ ግራ ቀኝ እያላጋትም ቢሆን ምርጫ አደረገች።የምርጫ ሂደትና ዉጤቱ በተቃዋሚዎች ዘንድ የቀሰቀሰዉ ቁጣ በሚንተከተክበት መሐል የሐገሪቱ ገለልተኛ አስመራጭ ኮሚሽን የበላይ ዴኒስ ካዲማ ዉጤቱን አወጁ።
«በጊዚያዊዉ የምርጫ ዉጤት መሰረት 13 ሚሊዮን 215 ሺሕ 366 ድምፅ ወይም 73.24 ከመቶ ድምፅ ያገኙት ዕጩ ቁጥር 20፣ አንቶን ሼሴኬዲ ናቸዉ።»
ለፕሬዝደት ሼሴኬዲ የአዲስ ዓመት የሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣን ልዩ ስጦታ ሆነ።ታሕሳስ 31 ነበር። አፍሪቃዊቱ ሁለተኛ ሰፊ ሐገር ኮንጎ በግጭት፣ ጦርነት ዉዝግብ፣የተፈጥሮ መቅሰፍት መሐል መሪዎቿን ከመምረጧ ከወራት በፊት በሕዝብ ቁጥር፣ በነዳጅ ዘይት ሐብትም ከጥቁር አፍሪቃ አንደኛይቱ ሐገር ናይጄሪያ መሪዋን መርጣ ነበር።የካቲት 25።የቀድሞዉ የሌጎስ ክፍለ-ግዛት አገረ ገዢ ቺነቡ ቦላ ቲንቡስ አሸነፉ። «የAPC (እጩ) ቺነቡ ቦላ ሐመድ የሕጉን መመዘኛዎች በማሟላታቸዉ የምርጫዉ አሸናፊና ተመራጭ ናቸዉ።»
ፕሬዝደንት ቲንቡስ ቃለ መሐላ መፈፅመዉ የሐገራቸዉንም የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ መሐበረሰብም (ECOWAS)ንም የመሪነት ስልጣን በቅጡ ሳይደላደሉበት የኒዤር የጦር መኮንኖች የሐገሪቱን ፕሬዝደንት መሐመድ ባዞማን ከስልጣን አስወገዱ።የወታደራዊዉ ሁንታ መሪ ጄኔራል አብዱረሕማን ቺያኒ እንዳሉት የጦሩ አላማ ሰላም ማስከበር ነዉ።
«ኒዤሪያዉያን ሆይ፣ ዉድ ጓዶች ባለፈዉ ሮብ ሰኔ 26 2023፣ የእናት ሐገር አስከባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት (CNSP) የመከላከያ ኃይላት 7ኛዉን የሪፐብሊክ ሥርዓት አስወግዷል።የCNSP እርምጃ ዋና መነሻ የዉድ ሐገራችን ደሕንነት ማስከበር ብቻ ነዉ።»
አዲሱ የናጄሪያ ፕሬዝደት የሚመሩት ኤኮዋስ ኒጀርን በጦር ኃይል እስከመዉረር እንደሚደርስ አስጠንቅቆ ነበር።ማስጠንቀቂያ-ዛቻዉ አየር ላይ ሲንከባለል፣ በ2020 ማሊ ላይ የተጀመረዉ መፈንቅለ መንግስት ጊኒን፣ ቡርኪናፋሶን፣ሱዳንን፣ ኒዤርን አዳርሶ ነሐሴ ላይ ለ50 ዓመታት ሊቨርቢል ጋቦን ላይ የተተከለዉን የዑመር ቦንጎንና የልጃቸዉን የዓሊ ቦንጎን አገዛዝ ገረሰሰዉ።
መፈንቅለ መንግስት የተደረገባቸዉ አብዛኞቹ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ሐገራት በየሐገራቸዉ የሰፈረዉ የፈረንሳይ፣ የአዉሮጳና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወታደሮች እንዲወጡ አዘዙ።ወታደሩም ተግተልትሎ ወጣ።
የየሐገሩ ወታደራዊ ገዢዎች የወደፊት ርምጃ፣ የምዕራባዉያን ብቀላ፣ ሩሲያዎች በየሐገራቱ እግራቸዉን ለመትከል የሚያደርጉት ሙከራ እንዳነጋገረ፣ የሱዳን የጦር ጄኔራሎች ሚያዚያ 15 ካርቱም ላይ የገጠሙት ዉጊያ እንዳገረረ፣ ምዕራባዉያን የተዘፈቀበት የጋዛና የዩክሬን ጦርነት እንዳስተዛዘብ ዓለም ያዉ ለዓመት ግብሩ አዲስ ዓመት አለ።መልካም አዲስ ዓመት።
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር