ማሕደረ ዜና፣ 2023 አብይት ፖለቲካዊ ሁነቶ፤ ክፍል I
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2016
ማስታወቂያ
የግሪጎሪያኑ 2023 ኢትዮጵያ ዉስጥ ጠላቶች የተወዳጁበት፣ ወዳጆች ጠላት የሆኑበት፤ ጠላቶች እየተደራደሩ ዉጊያ የቀጠሉበት አሳዛኝ ትርዒት የተፈራረቀበት፣የተቀረዉ አፍሪቃ ጦርነትን ከምርጫ፣ መፈንቅለ መንግስትን ከሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ያሰባጠረ ሐቅ ያረበበት ዓመት ነበር።የዋሽግተን፣ ብራስልስ-ለንደን-ኪቭ ተሻራኪዎች ከሞስኮ ጠላቶቻቸዉ ጋር የገጠሙት ጦርነት አሸናፊና ተሸናፊ ያልተለየበት፤ የዋሽግተን ቴሕራኖች የከረረ ጠላትነት የእስረኞች ልዉዉጥ ፋታ የታየበት።የደቡብ አሜሪካዋ ትልቅ፣ሰፊ፣ ሐብታም ሐገር ብራዚል እንደ እግር ኳስ ፌስታዋ ሁሉ በአመፅ-ሥርዓተ አልበኞች የዓለም አርዕስት የሆነችበት ዘመን ነበር።የእስራኤል መሪዎች «የሰዉ አዉሬ» ያሏቸዉን ፍልስጤሞችን በአሜሪካኖች ቦምብ-ሚሳዬል ጥይት የፈጁበት፣ የአሜሪካ-አዉሮጳ መሪዎች በግልፅ፣ የአረብ ታዛዦቻቸዉ በሥዉር ግድያ፣ ግፍ እመቃዉን የደገፉበት፣ የዓለምን ሰላም ያስከብራል የሚባለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዋሽግተኖች ይሁንታ ፈቃድን ካላገኘ ለተቀሩት አባላቱ «ሽባነቱ» የተረጋገጠበት ዓመትም ነበር። 2023። ስድስት ቀን ቀረዉ። አብይት ፖለቲካዊ ሁነቶችን ባጫጭሩ ቃኝተን እንሰናበተዉ። የመጀመሪያዉን ክፍል እነሆ።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ