1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደ ዜና፤ የዓለም ወይስ የኃያላን ፍርድ ቤት

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሐምሌ 10 2015

መንበሩን ዘ-ሔግ ኔዘርላንድስ ያደረገዉ ፍርድ ቤት ባሁኑ ወቅት የአንድ መቶ ሐገራት ዜጎች የሆኑ 900 ሰራተኞች አሉት።ኒዮርክ፣ኪንሻሳ፣ ቡኒያ፣ካምፓላ፣ ባንጉይ፣አቢጃን እና ቲቢሊሲ ዉስጥ ሰባት ቅርጫፎች አሉት።170 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ በጀት ተመድቦለታል።ፍርድ ቤቱ 31 ክሶችን እየተመለከተ ነዉ። 40 የእስራት ዋራንቶችን ቆርጦ 21 አሳስሯል።

Den Haag Internationaler Strafgerichtshof 1998
ምስል picture-alliance/dpa/L. Del Castillo

«ፍርድ ቤቱ በአፍሪቃና በደካሞች ላይ ያነጣጠረ ነዉ»

This browser does not support the audio element.


ኃምሌ 17፣ 1998 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሮም።
«የጉባኤዉ ተወካዮቼ፣ ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች መቅጫ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም የተወሰነበትን የሮም ሰነድን እንድትረከቡ እጠይቃለሁ።
የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን።የሰዉ ልጅ ለዘመናት የተመኘዉ፣አዋቂዎች ከ1919 ጀምሮ የለፉለት የጋራ የፍትሕ ተቋም ዕዉን ሆነ።ዛሬ 25 ዓመቱ።የፍርድ ቤቱ ተልዕኮ ተሳክቶ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
ፍልስጤማዊ-አሜሪካዊቱ የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ሽሪን አቡ አክሌሕ ጄኒን-ፍልስጤም ዉስጥ ከተገደለች ከግንቦት 11፣ 2022 ወዲሕ እርስዎ የአልጀዚራ ቴሌቪዥን የእንግሊዝኛ አገልግሎትን የሚከታተሉ ከሆነ ጣቢያዉን በከፈቱ ቁጥር ከስክሪንዎ ግርጌ ከሚነበቡት ፅሑፎች ደጋግሞ የሚነበብ አንድ መልዕክት  አለ።«የዓለም የወንጀለኞች መቅጫ ፍርድ ቤት (ICC) የሽሪን አቡ አክሌሕን ግድያ እንዲያጣራ አልጄዚራ ይጠይቃል» የሚል።
ግዙፉ ዓለም አቀፍ ጣቢያ ጠየቀ-አሳወቀ።ፃፈ-አነበብን።ዓመት ከሁለት ሁለት ወር።ኮፊ አናን የሰዉ ልጅን በሙሉ እንዲያገለግል የተመኙት ፍርድ ቤት ገዳዮችን መክሰስ አይደለም አገዳደላቸዉን ለመመርመር እንኳን አልፈለገም ወይም አልቻለም።
ምዕራባዊ ሱዳን ግዛት ዳርፉር ዉስጥ 87 ሰዎች በጅምላ የተቀበሩበት ጉርጓድ መገኘቱ ባለፈዉ ሮብ በይፋ ተነገረ።የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከሪም ኻን ሁለት ቀን አልቀዩም።መስሪያ ቤታቸዉ  በመላዉ ሱዳን ሶስት ወር ባስቆጠረዉ ጦርነት ተፈፅሟል የተባለዉን የጦር ወንጀል እንደሚመረምር አስታወቁ።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አስቸኳይና ጠንካራ  ርምጃ እንዲወሰድም ተማፀኑ።አርብ።
 «የኔ ትንታኔ፣ፀሎትና ምክር ለአደጋ የተጋለጡትን ሰዎች ለማዳን አስቸኳይና የጋራ ርምጃ መዉሰድ አለብን የሚል ነዉ።በተደጋጋሚ የሚነገረዉ «ሁለተኛ በጭራሽ» የሚለዉ ሐረግ በርግጥ ትርጉም ያለዉ ከሆነ፣ ለ20 ዓመታት ያክል በስጋት፣ ሕመምና በግጭት ቅሪቶች ለተሰቃየዉ ለዳርፉር ሕዝብ አሁን፣እዚሕ የሆነ መልዕክት ሊደርሰዉ ይገባል።»
አላበሉም።ሱዳኖች ባጠቃላይ ዳርፉሮች በተለይ ከእልቂት፣ፍጅት፣ስደት እንግልት የሚያድናቸዉ ይሻሉ።ግን እንኮ ዓለም አቀፉ  ፍርድ ቤት ከተመሰረተ ወዲሕ ከፍልስጤም-እስከ ኮንጎ፣ ከኢራቅ እስከ አፍቃኒስታን፣ ከየመን እስከ ምያንማር (ሮሒንጊያ)፣ከሶሪያ እስከ ሊቢያ፣ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ ሱዳን ሌላም ጋ የሚገኘዉ ሕዝብ ተመሳሳይ ምናልባትም የከፋ እልቂት ግፍ፣በደል ሲዋልበት «ለመላዉ ሰብአዊ ፍጡር የቆመ» የሚባልነት ፍርድ ቤት ምን አደረገ?ምንስ ሞከረ?
ኬንያዊዉ የሕግ ባለሙያና የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጉዳይ አጥኚ አጊና ኦጅዋንግ መልስ ብጤ አላቸዉ
«ፍርድ ቤቱ የምስራቅና የአፍሪቃ ሐገራትን መጨቆኛ፣ አሜሪካኖችንና እስራኤልን የመሳሰሉ ወዳጆችዋን መከላከያ  መሳሪያ ሆኗል።ይሕ የምሥረታ በዓሉ ብዙዎች የዛሬ 25 ዓመት የጠበቁት አይነት እንዳይሆን አድርጎታል።»
ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የሚፈፅሙ ፖለቲከኞችና የጦር መሪዎች የሚዳኙበት ፍርድ ቤት እንዲመሰረት ሐሳቡ በይፋ የመነጨዉ የመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ነበር።በ1919።በ1937 በያኔዉ የመንግስታት ማሕበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) የበላይነት ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች የሚዳኙበት ቋሚ የዓለም ፍርድ ቤት እንዲመሰረት ከሊጉ አባል መንግስታት 13ቱ  ተስማሙ።ግን ስምምነቱ ሳይፀድቅ ዓለም እንደገና ከዘግናኝ ጦርነት ተማገደች።ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት።
ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ለበርካታ ዓመታት ተዘንግቶ፣ ኋላም ሲጓተት ቆይቶ የሩዋንዳዉ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፣ የይጎዝላቪያዉ የጦር ወንጀል ሚሊዮኖችን መፍጀቱ ዓለምን ካስደነገጠ፣ ካነጋገረና ካስተዛዘበ በኋላ የዓለም ወንጀለኞች መቅጫ (ICC) የሚባለዉ ፍርድ ቤት እንዲመሠረት 120 ሐገራት ወሰኑ።ሮም 1998።በርግጥ ለብዙዎች ደስታ፣ ብስራት፣ አናን ያኔ እንዳሉት ትልቅ ተስፋ  ብጤም ነበር።
«ፍርድ ቤቱ ለሚመጣዉ ትዉልድ ሁሉ የሰዉ ልጅን በሙሉ እንዲያገለግል እመኛለሁ።»
በ4ኛ ዓመቱ በ2002 የሮሙን ዉል ከፈረሙት ሐገራት 60ዎቹ ሲያፀድቁት  ፍርድ ቤቱ በይፋ ሥራ ጀመረ።የሮም ስምምነትን በመፈረሙና በማፅደቁ መሐል አንዳድ መንግስታት በተለይም  ሰላም፣ፍትሕና ርትዕትን ለማስፈን ቆሚያለዉ የምትለዉ የዓለም ልዕለ ኃይል ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ የያዘችዉ ተለዋዋጭ አቋም ለብዙዎች ግራ አጋቢ ነበር።
የሮሙ ስምምነት በተፈረመበት ወቅት ሥልጣን ላይ የነበረዉ የፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን መስተዳድር ስምምነቱን ፈረመ።ግን የሐገሪቱ ምክር ቤት ስምምነቱን እንዲያፀድቅለት የክሊተን መስተዳድር አልጠየቀም።
ስምምነቱ በፀደቀበት ወቅት ሥልጣን ላይ የነበረዉ የፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ለፍርድ ቤቱ ዕዉቅና እንደማትሰጥ አስታወቀ።ፕሬዝደንት ቡሽ መስተዳድራቸዉ የፍርድ ቤቱን ሕልዉና ላለመቀበሉ «ምክንያት» ያሉትን ሰበብ አስታዉቀዉ ነበር።
«ዩናይትድ ስቴትስ ሰላም ለማስከበር በመላዉ ዓለም ስለምትጥር ዲፕሎማቶቻችንና ወታደሮቻችን ወደዚሕ ፍርድ ቤት ሊጎተቱ ይችላሉ።ይሕ ለኔ በጣም አሳሳቢ ነዉ።»
ብሩኪንግስ የተባለዉ የዩናይትድ ስቴትስ አጥኚ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ማይክል ኦ ሐንሎን ያኔ እንዳሉት ዩናይትድ ስቴትስ የፍርድ ቤቱን መመስረት ያላፀደቀችበትን ግን  መሪዎችዋ ያልተናገሩት ግልፅ ምክንያት በግልፅ ተናገሩ።
«ዩናይትድ ስቴትስ በጣም ኃይለኛናት፤ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል ትጠቀማለች፤ ኃይልን ለመጠቀም አታመነታም የሚል አስተሳሰብ አለ።(አሜሪካኖችን) የሚያስጨንቀዉ ዩናይትድ ስቴትስን የሚፃረር እንዲሕ ዓይነት አጠቃላይ ዓለም ዓቀፍ የህዝብ አስተያየት እያለ አንድ ፓይለት ትዕዛዝ በመቀበሉ ብቻ እንዲከሰስ የሚፈልግ ዳኛ ወይም አቃቤ ሕግ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዉስጥ ሊኖር ይችላል መባሉ ነዉ።»
ፓይለቱ ትዕዛዝ ፈፃሚ ከሆነ-አዛዦቹ የማይጠየቁበት ምክንያት አለ ይሆን? ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ ፍርድ ቤቱ ከዳርፉር እስከ ኮንጎ ከዩጋንዳ እስከ ሊቢያ ባሉ ግጭትና ጦርነቶች በጦር ወንጀለኝነት የሚጠረጠሩ ሰዎችን ፍርድ ቤቱ እንዲዳኝ ከፍተኛ ተፅዕኖ ታሳድራለች።
የፍርድ ቤቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሱዳን ዉስጥ ተፈፅሟል የተባለዉን ወንጀል እንደሚመረምር ባለፈዉ አርብ ማስታወቁን ለመደገፍ ዩናይትድ ስቴትስን የቀደመ ሐገር የለም።እንዲያዉም የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማቲዉ ሚለር እንዳሉት የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ በሱዳንም ሆነ በሌሎች ሐገራት ወንጀል ለሚፈፅሙ ሁሉ መልዕክት ያስተላልፋል።
ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የቀድሞዉን የሊቢያ መሪ ልጅ ሰይፍ አል ኢስላም ቃዛፊን ከስሷል።የሊቢያን መሪን ጨምር ሺዎችን በገደሉ፣ባስገደሉ፣ ሐገሪቱን እስከ ዛሬ ከተዘፈቀችበት ትርምስ በዶሉት የዉጪ ኃይላት ግን ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ትንፍሽ አላለም። 
ከዩናይትድ ስቴትስ በተጨማሪ በፀታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን ያላቸዉ ሩሲያና ቻይና የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አባላት አይደሉም።ከፀጥታዉ ምክር ቤት አባላት ሌላ ሕንድ፣ እስራኤል፣ ኢራንና ሳዑዲ አረቢያን የመሳሰሉ አካባቢያዊ ኃላንም የፍርድ ቤቱን ህልዉና አልተቀበሉትም።«ድቀት» ይሉታል ኬንያዊዉ የሕግ ባለሙያ።
«የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዋና ዋና አባላት ስምምነቱን አለማፅደቃቸዉ ታላቅ ድቀት ነዉ።በሁለተኛ ደረጃ ምግባራቸዉ የፍርድ ቤቱን ሕግጋት የሚጥሰዉ እስራኤልን የመሳሰሉ አካባቢያዊ ኃያላንም እራሳቸዉን አባል አላደረጉም።ስለዚሕ ዉጤቱ፣ ብዙዎች ፊርማቸዉን ባኖሩበት ወቅት የነበረዉ  (የፍርድ ቤቱ) ዓለምአቀፋዊነት እየከሰመ ሊሔድ ይችላል።» 
ኢትዮጵያም አባል አይደለችም።  
መንበሩን ዘ-ሔግ ኔዘርላንድስ ያደረገዉ ፍርድ ቤት ባሁኑ ወቅት የአንድ መቶ ሐገራት ዜጎች  የሆኑ 900 ሰራተኞች አሉት።ኒዮርክ፣ኪንሻሳ፣ ቡኒያ፣ካምፓላ፣ ባንጉይ፣አቢጃን እና ቲቢሊሲ ዉስጥ ሰባት ቅርጫፎች አሉት።170 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ በጀት ተመድቦለታል።ፍርድ ቤቱ 31 ክሶችን እየተመለከተ ነዉ። 40 የእስራት ዋራንቶችን ቆርጦ 21 አሳስሯል።

ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Corder
ምስል Everett Collection/picture alliance
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከሪም ካሕን ኮንጎን ሲጎበኙምስል Justin Makangara/AA/picture alliance

የቀድሞዉ የሱዳን ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽርን ጨምሮ 16ቱ ተጠርጣሪዎች እስካሁን በመታደን ላይ ናቸዉ።በነገራችን ላይ ሩዋንዳና የዩጎዝላቪያ ዉስጥ የተፈፀሙ ወንጀሎች የመረመሩና በወንጀለኞች ላይ የፈረዱት ችሎቶች በየሐገራቱ የተፈፀሙ ወንጀሎችን ለመመልከት የተመሰረቱ እንጂ ቋሚ ችሎቶች ወይም ፍርድ ቤቶች አይደሉም።
ቋሚዉ ፍርድ ቤት 123 አባል ሐገራት አሉት።አብዛኞቹ የአፍቃ ሐገራት ናቸዉ።33።የእስያ ፓስፊክ ሐገራት 19፣ የምስራቅ አዉሮጳ ሐገራት 18፣ የደቡብ አሜሪካና የፓስፊክ አካባቢ ሐገራት 28፣ የምዕራብ አዉሮጳና የሌሎች የተባሉት ደግሞ 25 ናቸዉ።ፍርድ ቤቱ በሶስት ችሎቶች ካሉት 18 ዳኞች 4ቱ አፍሪቃዉያን ናቸዉ።ይሁንና ዓለም አቀፍ የሚባለዉ ፍርድ ቤት እስካሁን ከፈረደ፤ ከከሰሰ፣ ከመረመረና ሊመረምር ቀጠሮ ከያዘባቸዉ ጉዳዮች፤ከፈረደባቸዉ ተጠያቂዎችና ዋራት ከቆረጠባቸዉ ተጠርጣሪዎች አብዛኞቹ አፍሪቃዉያን ናቸዉ። ይሕ እዉነት ወትሮም የአሜሪካና የተባባሪዎችዋ ጥቅም ማስጠበቂያ የሚባለዉን ፍርድ ቤት «የደካሞች መወንጀያ» የሚያሰኝ ትችትና ወቀሳም አስከትሎበታል።ባንድ ወቅት ደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ ሶስት የአፍሪቃ ሐገራት ከፍርድ ቤቱ አባልነት ለመዉጣት ዝተዉ ነበር።

ምስል Klaus Rainer Krieger/reportandum/IMAGO

የኬንያዉ የሕግ ባለሙያ አጊና ኦጅዋንግ ከአፍሪቃ ተጠርጣሪዎች መሐል እንኳ ጉቦ መስጠት የቻሉ አይከሰሱም ይላሉ።

«እዚያ ፍርድ ቤት ከቀረቡ የአፍሪቃ መሪዎች መካከል አንዳዶቹ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ጉቦ ሰጥተዉ ተለቅቀዋል ይባላል።ጉቦ ፍርድ ቤቱን ሰርስሮ መግባቱን መስማት በጣም የሚያሳምም ነዉ።የኬንያም ሆነ የሌላዉ የአፍሪቃ ሐገራት ህዝብ ይሕ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ጉቦ ለመስጠት በጣም አዳጋች ነዉ ብሎ ያስብ ነበር።እዉነቱ ግን ተቃራኒዉ ነዉ።» 
ፍርድ ቤቱ የጦር ወንጀሎችን፣ ዘር ማጥፋትን፣ በሰዉ ልጅ ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችንና መሰል ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን እየመረመረ፣ በስልጣን ወይም በኃይላቸዉ ምክንያት በየሐገራቸዉ ፍርድ ቤቶች የማይቀርቡ ፖለቲከኞችን፣ የጦር ወይም የታጣቂ ኃይል መሪዎችንና ተባባሪዎቻቸዉን የሚከስና የሚቀጣ ፍርድ ቤት ነዉ።

አንዳድ መንግስታትና ባለስልጣናት የፍርድ ቤቱ አቅም መጠናከር፤፣ የቆመላቸዉ ዓላማዎች መሻሻል አለባቸዉ ይላሉ።ብዙዎቹ እንደሚሉት ግን የአንድ ወገን ፍላጎትና ጥቅም ማስከበሪያነቱ ካልቀረ ደንብ፣ አመራር አሰራሩ መሻሻል ወይም መቀያየሩ የሚያመጣዉ ለዉጥ የለም። ክርክሩ ቀጥሏል፣ ፍርድ ቤቱም 25ኛ ዓመቱን አክብሯል።ለዛሬ ይብቃን።

ነጋሽ መሐመድ 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW