1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
እምነት

ማራቶን፥ ረሐብ ፥ መስቀልና መውሊድ በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ መስከረም 18 2016

በሳምንቱ መነጋገሪያ የነበሩ ሦስት ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ያሰባሰብንበት የየማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት መሰናዶ ሙሉ ዘገባን በድምፅ አለያም በጽሑፍ ከታች መመልከት ይቻላል ።

የደመራው ሥነስርዓት በመስቀል አደባባይ፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
የመስቀል ዋዜማ ማለትም የደመራው ሥነስርዓት በመስቀል አደባባይ፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያምስል Solomon Muche/DW

የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት አስተያየቶች ስብስብ

This browser does not support the audio element.

ዘንድሮ የመስቀል ዋዜማ ማለትም የደመራው ሥነስርዓት እንዲሁም የነቢዩ መሐመድ ልደት የመውሊድ በዓላት በተመሳሳይ ቀን ተከብረዋል ። በዓላቱ ላይ ስለተስተዋሉ ጉዳዮች የተለያዩ አስተያየቶች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተሰጥተዋል ። በተለይ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል ። ግጭት እና ጦርነት ባዳቀቃቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰዎች በረሐብ እየሞቱ መሆኑ ተዘግቧል ። በዚህ ላይም አስተያየቶችን አሰባስበናል ። ባለፈው ሳምንት በጀርመን ቤርሊን ከተማ የማራቶን የሩጫ ፉክክር የዓለም ክብረወሰንን ሰብራ ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሠፋም የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ዋነኛ ትኩረት ሆና ቆይታለች ።

ሁለት ዐበይት ሃይማኖታዊ በዓላት በአንድ ቀን

በኢትዮጵያ ከትናንት በስትያ ሁለት ዐበይት ሃይማኖታዊ በዓላት በአንድ ቀን ተከብረዋል ።  ሙስሊሞች 1,498ኛው የመውሊድ በዓልን ሲያከብሩ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮችም የመስቀል በዓል ዋዜማ የሆነውን የዳመራ ማብራት ሥርዓት አከናውነዋል ። የሁለቱ እምነቶች በዓል በአንድ ቀን መግጠሙን በተመለከተ ራስ ጥሌ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሰጡት አስተያየት «እናት ኢትዮጵያ የሃይማኖት ስብጥር» ሲሉ ጽፈዋል። 

የመውሊድ በዓል አከባበር በጥንታዊቷ የሐረር ከተማ፤ ኢትዮጵያምስል Mesay Tekelu/DW

ዘላለም ሲሳይ ሞላ ደግሞ፦ «እንኳን አብሮ አደረሠን ዶቸ ቬለዎች ድባቡ ቀዝቃዛ ነው ። ኑሮው ሠማይ ሆኗል » ብለዋል ። 

ሕያብ በሚል ስም የትዊተር ተጠቃሚ፦ «የኔ የምትሉትን በዓላት እና ትውፊት የሰላም እጦት በመፍጠር አስባችሁት ብቻ እንድትውሉ ማድረግ የጨቋኞች ትልም ነው » ብለዋል ። «ይህ ቀን እስኪያልፍ ሁሉን ተቋቁሞ የነበረን ማስቀጠል የብልህ ሕዝብ ምርጫ ነው ። እንኳን ለደመራ እና መውሊድ በዓል አደረሳችሁ!» ሲሉም መልእክታቸውን አስፍረዋል።

ኪም ብራውን  በሚል የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ የሁለቱ እምነቶች በዓል በአንድ ቀን መግጠሙን በማስመልከት አድናቆታቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽሑፋቸው አስፍረዋል ።  «ይደንቃል ይህ በተመሳሳይ ቀን ነው የሆነው» በማለት ያንደረደሩት ጽሑፋቸው «ኢትዮጵያውያን» በሚል የትዊተር ተጠቃሚ የተላለፈ መልእክት ተያይዞበታል። የኢትዮጵያውያን መልእክት «የክርስቲያን እና የሙስሊም ወንድሞች እና እህቶቻችን፦ እንኳን ለብርሃነ-መስቀሉ እና ለመውሊድ በዓል በስላም አደረሳችሁ » በሚል ይነበባል ።  የሙስሊም እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትያን አባቶች በፈገግታ የታጀበ ፎቶግራፍም ተያይዞበታል ።

የመስቀል ዋዜማ ማለትም የደመራው ሥነስርዓት በመስቀል አደባባይ፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያምስል Solomon Muche/DW

የሰንደቁ ጉዳይ

ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ የመስቀል ደመራ በመጣ ቁጥር በርካቶችን ከሚያስቆጡ ጉዳዮች መካከል በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም ሰንደቅ ዓላማን ዐታሳዩን መባሉ ነው ይላሉ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ።

ዘንድሮ ቁጥጥሩ ካማረራቸው መካከል አንዷ ወጣት ራሷን በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጻ የበርካቶችን ምሬት በቀልድ አዋዝታ ያስተላለፈችው መልእክት ብዙዎች ጋር ደርሷል ። የልጅቷ መልእክት በአጭሩ ሲጠቃለል የሚከተለውን ይመስላል ። ምንጊዜም ለመስቀልበዓል ወቅት እንደምናደርገው የሰፈር ልጆች ተሰባስበን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም ሰንደቅ ዓላማ እየሰቀልን ነበር። ፖሊሶች መጥተው አውሩርዱ አሉን፤ አወረድን ። ቀና ብለው ሲመለከቱ ሰማዩ ላይ ቀስተደመና አለ ። «እና እሱንስ እናውርደው በፌዝ መልክ ትጠይቃለች ወጣቷ ። «እሱን ጠይቀው የሰቀለውን» ስትልም ጣቷን ወደ ሰማይ ታመለክታለች፤ በምጸት እየሳቀች ።

ይህን ቪዲዮ በትዊተር ገጻቸው ላይ ካያያዙ ሰዎች መካከል እዮባ በሚል የትዊተር ተጠቃሚ ይገኙበታል ። እሳቸውም አጭር መልእክት አላቸው ።  «እህታችን ትናገራለች፣ የሚመለከተው ይመልስላት ። ብቻ ከትዊተርም ላይም አውርዱ እንዳይባል» ሲል ይነበባል የእዮባ መልእክት ።

ጽዮን የቤቲ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ፦ «ኢትዮጵያ ሀገሬ ሰላምሽ ይብዛ እንኳን አደረሳችሁ ወድ ወገኖቼ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርከን መልካም በአል እወዳችዋለው » ሲሉ ፌስቡክ ላይ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ። «ሰላም ለኢትዮጵያ» የወይንሸት ተሸሞ አጭር መልእክት ነው ። ሰላም ለኢትዮጵያ ።

ረሐብ በኢትዮጵያ ሕይወት እየቀጠፈ ነው

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በተለይም በግጭት እና ጦርነት ያሳለፉ ብሎም አሁንም በግጭት ውስጥ በሚገኙ ክልሎች ክቡር የሰው ልጅ በረሐብ እየተቀጠፈ መሆኑ ተዘግቧል ። ረሐቡ፦ በአማራ፤ በትግራይ፣ በአፋር እንዲሁም በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ሰዎችን ለብርቱ ችግር መዳረጉን ከየአካባቢዎቹ የሚደርሱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መልእክቶች ያመለክታሉ ።

በትግራይ ክልል ሰዎች በረሐብ እየሞቱ ነው ።ከትናንት በስትያ ራሱ (መስከረም 16 ቀን፣ 2016 ዓ.ም) በረሐብ የተነሳ አንዲት በ20ዎቹ መጀመሪያ የምትገኝ ሴት መሞቷን አንድ ተፈናቃይ ለዶይቸ ቬለ (DW)ተናግረዋል ። በትግራይ ክልል በተደረገ ጥናት ከጦርነቱ በኋላ በረሐብ ምክንያት መሞታቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 1,329 መሆኑ ተዘግቧል ። «በጣም ያሳዝናል» የተስፋዬ ዘገዬ አጭር መልእክት ነው ።

ረሐቡ፦ በአማራ፤ በትግራይ፣ በአፋር እንዲሁም በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ብርቱ ችግር መጋረጡን የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መልእክቶች ያመለክታሉምስል Ben Curtis/AP/picture alliance

ሣኅሉ አእምሮ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ፦ «ዋግ ኽምራ እና ሰሜን ጎንደር ሰዎች በረሐብ እያለቁ ነው»  ብለዋል በአማራ ክልል ስላለው የረሐብ አደጋ ሲገልጹ ።  ሀገር ውስጥ ባሉት ተስፋ መቁረጣቸውን በሚገልጽ መልኩም ችግሩን «ለዓለም መንግሥታት ዐሳውቁ» ብለዋል ። በፌስቡክ መልእክታቸው፦ «የወለጋንም ብታዩ ድንቅ ነው» ያሉን ባራና ባሪኡፍ ናቸው ። «በወለጋ የረሐብ ማብቂያው መቼ ነው ሲሉም ይጠይቃሉ ባራና።

አሚን ዶጋ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታያችን በላኩልን አስተያየት ደግሞ፦ አፋር ክልል ውስጥም ረሐብ ብርቱ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል ።«በአፋር ክልል በዞን ሁለት ከፍተኛ ረሀብ እየገባ ነው» ሲሉም ጽፈውልናል ። መሐመድ የተባሉ ሌላኛው አስተያየት ሰጪንም ከዛው ከአፋር ደውለን አነጋግረናል ።

ታንጉት ዳኛው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው፦ «ረሀብ መጥፎ ነው» ሲሉ አጠር ያለ ጽሑፋቸውን ይጀምራሉ ። «ብልጽግናው ቀርቶብን ዛሬን በልተን ማደር ብንችል መልካም ነበር ።»  የመልእክታቸው ማጠቃለያ ነው ። 

የአትሌት ትእግስት አሰፋ የቤርሊን ማራቶን አስደናቂ ድል

2 ሰአት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ ። ብዙዎች አስደማሚ ሲሉ ዘግበውታል ። የአትሌት ትእግስት አሠፋን አዲስ ክብረወሰን ። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሠፋ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በጀርመን ዋና ከተማ ቤርሊን ያስመዘገበችው ድንቅ ውጤት በማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ሰፊ ሽፋን አግኝቷል ። ትእግስት ውድድሩን ያጠናቀቀችበት ሰአት በማራቶን ሩጫ ፉክክር አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል ። በርካቶች አትሌት ትእግስትን ለዚህ አስደናቂ ውጤቷ «ጀግና» ሲሉ አወድሰዋታል ።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሠፋ በቤርሊን ማራቶን ያስመዘገበችው ድል -2 ሰአት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ-አዲስ ክብረወሰንምስል Markus Schreiber/AP/picture alliance

«ሌሎች አትሌቶች ይሮጣሉ፣ ትግስት አሰፋ ትበራለች የትዊተር አስተያየቱ የዐወቀ አብርሃም ነው ። በረከት በቀለ እዛው ትዊተር ላይ በሰጡት አስተያየት፦ «ጊዜው የኢትዮጵያ ነው» ብለዋል ።

ትዝታ አሰፋ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ አጭር መልእክት ደግሞ የብዙዎችን አስተያየት የሚያጠቃልል ይመስላል ። እንዲህ ይነበባል ። «የዓለም ማራቶን በትግስት አሰፋ በጀርመን ተሰባበረ!!!»  እኛም የዛሬውን የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት መሰናዶ በዚሁ እናጠናቅቅ። መልካም ጊዜ።  ጤና ይስጥልን!

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW