1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማክሮ ከአመጹ በኋላ 'መሰረታዊ መልሶች' ለመስጠት ቃል ገቡ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 2015

ታዳጊው ፈረንሳዊ ናሃል ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ከሞተ በኋላ በፈረንሳይ በተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰዉ ኃይል የቀላቀለ አመጽ የፈረንሳይን አሽመድምዶ ነዉ የከረመዉ። የህዝቡ ቁጣ በመንግስት ላይ ያነጣጠረ ነዉ። ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዛሬ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያገኙ ቃል ገብተዋል። ማክሮ ከ220 በላይ የአካባቢ ከንቲባዎችንም አግኝተዋል።

Paris Macron Treffen mit Bürgermeistern
ምስል፦ Ludovic Marin/AFP/AP/picture alliance

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በአመፅ እየተናጠች ካለችዉ አገራቸዉ በተለይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸዉ  ከ 220 በላይ ከሚሆኑ አካባቢዎች የመጡ ከ 220 በላይ ከንቲባዎችን አግኝተዉ አነጋገሩ። በፈረንሳይ በታየዉ ኃይል የቀላቀለ ተቃዉሞን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ማክሮ ከሥነ-ሞራል  ድጋፍ በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸውን የከተማ አዳራሾችና ሌሎች የሕዝብ ተቋማትን ለመጠገን እርዳታ መስጠት እንደሚፈጉ ፓሪስ የሚገኘዉ መንግሥት ገልጿል። የዛሬ ሳምንት አንድ የፈረንሳይ ፖሊስ ናሄል ኤም የተባለ የ17 ዓመት ወጣት የትራፊክ ቁም ምልክትን ጥሶ ሊያልፍ ሲሞክር በቅርብ ርቀት በጥይት መትቶ ከገደለዉ በኋላ ድርጊቱ ያስቆጣዉ ሕዝብ ለቀናቶች ያካሄደዉ የአደባባይ ሰልፍና አመፅ የሐገሪቱን እንቅስቃሴ አሽመድምዶት ነዉ የከረመዉ። በአብዛኛዉ  ወጣቶች የታደሙበት በዚህ ተቃዉሞ መዲና ፓሪስን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች፤ በየአካባቢዉ የቆሙ መኪኖችን፣ የቁሻሻ ማጠራቀሚያዎችን፣ የመንግስት ተቋማትንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ሰባብሯል፤ አቃጥሏል። ፖሊሶችን በተቀጣጣይ ተወርዋሪ፤ እና በድጋይ ቁሳቁስ ደብድቧል። መዲና ፓሪስ 12 የፖሊስ ጣቢያዎች፤ ተሰባብረዋል አልያም  በእሳት ጋይተዋል። ተቃዉሞዉ ዛሬ መብረዱ ተመልክቷል። 
የፈረንሳይ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ «የመጀመሪያ ደረጃ» ባለዉ ምርመራዉ የ17 ዓመቱን ወጣት የገደለዉ ፖሊስ ጥፋተኛ መሆኑን ማስታወቁ ይታወቃል። የፖሊሱ ጠበቃ ግን ገዳዩ ሆን ብሎ አለመግደሉን በወጣቱ ሞት መፀፀቱንም አስታዉቋል። ናሔል በሚል የመጀመሪያ ስሙ ብቻ በይፋ የሚጠራዉ ወጣት ወላጆች የአልጄሪያ ዝርያ ያላቸዉ ናቸዉ። የሟች ቤተሰቦች እንደሚሉት የፈረንሳይ ባለሥልጣናት፤ ትራፊክ መብራት ላይ አልቆም ያለን፤ ፖሊስ ሊተኩሰበት ይችላል የሚለውን ሕግ መቀየር ይገባቸዋል። ፈረንሳይ በጎርጎረሳዉያኑ 2017 የቀየረችው ሕግ ፖሊስ ኃይል እንዲጠቀም የሚፈቅድ ነው። ተቃዋሚዎች ፖሊስ የትራፊክ ሕግን የሚጥሱ ሰዎችን እየገለደ ያለው በዚህ ሕግ ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ።
 

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW