1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስአፍሪቃ

ማይቻርጅ ፤ዲጅታል የፖወር ባንክ ኪራይ በአዲስ አበባ

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 2 2017

በጉዞ ላይ ወይም በሌሎች የስራ አጋጣሚዎች መንገድ ላይ እያሉ የተንቀሳቃሽ ስልከዎ ባትሪ ጨርሶ በድንገት ዘግቶበዎት ያውቃል? በአደጉ ሀገራት ያለ ሰው እገዛ ዲጅታል በሆነ መንገድ የሚከናወን የፖወር ባንክ ኪራይ መፍትሄ ይሰጣል። ይህ ዲጅታል መፍትሄ በቅርቡ በኢትዮጵያም ተጀምሯል።

.ማይቻርጅ ዲጅታል የፓወር ባንክ ኪራይ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የሚሰጥ አገልግሎት ነው።
ማይቻርጅ ዲጅታል የፓወር ባንክ ኪራይ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የሚሰጥ አገልግሎት ነው።ምስል፦ Privat

ማይቻርጅ፤ ዲጅታል የፖወር ባንክ ኪራይ በአዲስ አበባ

This browser does not support the audio element.

 እንደ ተንቀሳቃሽ  ስልኮች እና ታብሌቶች  ያሉ ዲጅታል መሳሪያዎች በአሁኑ ወቅት ለትምህርት፣ለግብይት፣ ለገንዘብ ዝውውር እና ለመረጃ ተደራሽነት  በአጠቃላይ ለሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ህይወት አስፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል።

ለእነዚህ ተንቀሳቃሽ ዲጅታል መሳሪያዎች አስተማማኝ  የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ በመሆን የሚያገለግሉት ተንቀሳቁሽ   የሀይል  ምንጮች  ወይም  ፓወር ባንኮችም በዚያው መጠን አገልግሎታቸው እና ተፈላጊነታቸው እያደገ መጥቷል። በተለይ አስተማማኝ የኤለክትሪክ ኃይል በሌላቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገራት የኤለክትሪክ አቅርቦት ውስንነት ተግዳሮቶችን ይቀርፋሉ። ይህንን በመገንዘብ ይመስላል ማይቻርጅ የተባለ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ በአዲስ አበባ ከተማ ዲጅታል በሆነ መንገድ ፓወር ባንክ ማከራየት ጀምሯል። የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ናሆም ሰለሞን እንደሚሉት አገልግሎቱ የተጀመረው እያደገ የመጣውን የተንቀሳቃሽ ስልክ  አገልግሎት ታሳቢ በማድረግ ነው።

የአገልግሎቱ አጀማመር

«ኢትዮጵያ ውስጥ ዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 የሚባለው የመንግስት መርሃግብር በተለይ በአዲስ አበባ በግልፅ ይታያል።የትምህርት ስርዓቶች፣የክፍያ፣ስራዎች ፣የመንግስት አንዳንድ ቦታዎች ነዳጅ እንቅዳ ብንል ሁሉም ነገር ዶጅታል እየተቀየረ ነው የመጣው።ምን አስተዋልን ሁላችንም ስልካችን ላይ የምናጠፋው ጊዜ ከመቸውም ጊዜ በላይ ከፍ ማለቱን አስተውለናል።» ብለዋል። በተጨማሪም አዲስ አበባ ውስጥ የተሰራ አንድ ጥናት ሰዎች ከአራት ስዓት በላይ በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ እንደሚያሳልፉ ማሳየቱን ጠቁመው፤ስልካችን ላይ ይህን ያህል ጊዜ የምናሳልፍ ከሆነ የስልክ ባትሪም በዚያው መጠን ዝቅተኛ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው በሚል፤ አገልግሎቱን ለመጀመር ሌላው ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።

አቶ ናሆም ሰለሞን፤የማይ ቻርጅ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚምስል፦ Privat

ባለፈው ግንቦት  ወር 2017 ዓ/ም የተጀመረው ይህ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ከ80 በላይ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች አሉት። በእነዚህ ጣቢያዎችም ዲጅታል በሆነ መንገድ ያለ ሰው እገዛ የኃይል ባንኮችን ስምንት ሺህ ለሚጠጉ ለተጠቃሚዎች እያደረሰ ይገኛል።አገልግሎቱን ለማግኘትም የማይ ቻርጅን የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ በመጠቀም የመጀመሪያው ርምጃ መሆኑን አቶ ናሆም ያስረዳሉ።

አገልግሎቱ እንዴት ነው የሚሰራው

«ስለዚህ አፕሊኬሽኑን ለመጠቀም በመጀመሪያ ከ«ፕሌይ ስቶር»  ወይም ከ«አፕስቶር» ላይ «ማይ ቻርጅ» (mycharge) ብለ በመሀሉ «ስፔስ» ሳናደርግ «ሰርች» እናደርጋለን። ከዚያ ከመተግበሪያውን እናወርዳለን።ለመመዝገብ የስልክ ቁጥር እና ኢሜል ይጠይቀናል። ከዚያ የስልክ ቁጥር እና ኢሜል በማስገባት እንመዘገባለን።ከዚያ የአንድ ጊዜ «ፓስወርድ»

ወይም የእኛነታችን መለያ በስልክ ቁጥራችን ይላካል።ይህን ስናገባ የማይ ቻርጅን መተግበሪያ መጠቀም እንችላለን።»በማለት በመተግበሪው ለመመዝገብ ያለውን ሂደት አብራርተዋል።«ለመጠቀም ደግሞ በቀላሉ መተግበሪያው የማይቻርጅ ጣቢያዎች ያሉበትን ቦታ ያሳያል።«ሰርች» የሚለውን ቁልፍ በመጫንም በአቅራቢያው ያለውን ጣቢያ ለይቶ ያሳያል። ጣቢያው ጋ በመሄድም «ስካን« የሚል አማራጭን በመንካት ፓወር ባንኩን «አውቶማቲካሊ »ይሰጠዋል።» በማለት አሰራሩን አብራርተዋል።

አገልግሎቱን ለማግኘት ማይቻርጅ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያን መጠቀም ያስፈልጋል።ምስል፦ Privat

በዚህ መንገድ ተጠቃሚዎች የተከራዩትን  የኃይል ባንክ ( ፓወር ባንክ) በ 72 ሰዓታት ውስጥ በአቅርራቢያቸው በሚገኝ ማንኛውም ጣቢያ መመለስ ይችላሉ ።ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ላማግኘት  ገንዘብ  ማስያስ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ መሳሪያውን ሲመልሱ በመያዣነት ያስቀመጡትን ብር ለመመለስ የሚያስችል ምንም አይነት የሰው እገዛ የማይፈልግ ዲጅታል አሰራርም አለው።

የአገልግሎቱ ጠቀሜታ

ይህ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የሚሰራ ሲሆን፤በከተማዋ የራሳቸው ፓወር ባንክ ላላቸው ተጠቃሚዎች ሳይቀር፤ በኤለክትሪክ መቋረጥ ሳቢያ ለሚገጥማቸው ችግር መፍትሄ እየሰጠ መሆኑን ሃላፊው ገልፀዋል።ማህደር ታምራት ከነዚህ መካከል አንዷ ነች። ዲጅታል ግብይት እና ይዘት ፈጠራ ላይ እንደምትሰራ የምትገልፀው ማህደር፤ ይህ አገልግሎት በስራዋ ያጋጥማት የነበረውን ችግር እንዳቃለላት ትገልጻለች።

«ማይቻርጅ የሚለውን አፕሊኬሽን «ፕሌይ ስቶር» ላይ ወይም «አፕስቶር» ላይ አለ።«ማይ ቻርጅ» (mycharge) ብለው በመሀሉ «ስፔስ» ሳያደርጉ ቢፈልጉት ያገኙታል።እንዴት ነው አጠቃቀሙ ለሚለው በቀላሉ አንድ ሰው ስልኩ ባትሪ ሲቀንስበት የ«ማይ ቻርጅ» መተግበሪያን ይከፍታል። መተግበሪያውን ሲከፍትም  ከተማችን ላይ የከፈትናቸው የኛ ጣቢያዎች አሉ።» ካሉ በኃላ፤ መተግበሪያውን በመጠቀም በቅርብ የሚገኘውን ጣቢያ በመለየት እና ወደ ጣቢያው በመሄድ «ኪው አር«  የሚባለውን ኮድ በመጠቀም ፓወር ባንኩን መወሰድ እንደሚቻል አብራርተዋል።

ፓወር ባንኩን ከየጣቢያዎቹ መከራየትየሚቻለው ይዲጅታል በሆነ መንገድ «ኪው አር« የሚባለውን ኮድ በመጠቀም ነው።.ምስል፦ Privat

በአጠቃላይ አገልግሎቱ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያን፣ የተጠቃሚ ምዝገባን ፣ትክክለኛ ቦታ መፈለግን፣  ክፍያ መፈፀምን ፣መሳሪያውን መውሰድ እና መመለስን ያጠቃልላል።አቶ ናሆም እንደሚሉት ይህንን አገልግሎት ምቹ ለማድረግ የማይ ቻርጅ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ በእንግሊዘኛ፣ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በትግርኛ እንዲሰራ ተደርጎ የተዘጋጄ ነው።ከዚህ በተጨማሪ በአገልግሎት ወቅት ተጠቃሚዎች ችግር ከገጠማቸው እርዳታ ለመስጠት የጥሪ ማዕከል መዘጋጄቱንም ተናግረዋል።

በየጣቢያዎቹ የሚቀመጡት ፓወር ባንኮች 40 የሚደርሱ ሲሆን እያንዳንዳቸው ሁለት ስማርት ስልኮችን ሙሉ ለሙሉ መሙላት አቅም ያላቸው ናቸው።በእያንዳንዱ ጣቢያ እስከ 25 ኢንች የሚደርሱ ዲጂታል ስክሪኖች  ያሉት በመሆኑ ለማስታወቂያ አዲስ እድል ይሰጣል።በዚህም ከአገልግሎት ከተጠቃሚዎቹ ባሻገር ፓወር ባንኮቹ የሚቀመጡባቸው ቦታዎች ባለቤቶችም  ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

በመላው ኢትዮጵያ አገልግሎቱን የማስፋት ዕቅድ

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የፓወር ባንክ ኪራይ ገንዘብ ቆጣቢ፣ ቀጣይነት ያለው ፣ምቹ እና በመተግበሪያዎች አማካንነት በቀላሉ ተደራሽ በመሆኑ በዓለም ላይ እያደገ ያለ ዘርፍ ነው።ከዚህ አንፃር በጎርጎሪያኑ 2030 ዓ/ም 21,27 ቢሊዮን ዶላር የገበያ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ማይ ቻርጅም አገልግሎቱን  ከአዲስ አበባ ከተማ ባሻገር ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች የማስፋፋት እቅድ እንዳለው አቶ ናሆም ገልፀዋል።ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በአፍሪቃ ሀገራት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ፍላጎት መኖሩን የገለጹት ሀላፊው፤ ከዚያ በፊት ግን የቴክኖሎጂ ኩባንያው በኢትጵያ የኤለክትሪክ መኪናዎችን እና ብስክሌቶችን መሙላት የሚችሉ የሀይል ባንኮችን ለማቅረብ እንደሚፈልግ አቶ ናሆም ሰለሞን አመልክተዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጥነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW