1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ፥የሕወሓትና ኤርትራ ንግግር፥የ12ኛ ክፍል አነጋጋሪ ውጤት

ዓርብ፣ መስከረም 3 2017

ማይክ ሐመር ከጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና ከጌታቸው ረዳ ጋርፊት ለፊት መነጋራቸው፤ አቶ ጌታቸው ዱባይ ውስጥ ከኤርትራ መሪዎች ጋ ተገናኙ መባሉ እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አስደንጋጭ ውጤት ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል ። ሙሉ ዝግጅቱን በድምፅ አለያም በጽሑፍ መከታተል ይቻላል ።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፊርማ
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፊርማ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዥር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ከትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ ጋር ሲጨባበጡምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

የምስራቅ አፍሪቃ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ጋ ፊት ለፊት ተነጋግረዋል ። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት ጌታቸው ረዳ ዱባይ ውስጥ ከኤርትራ ልዑክ ጋር መወያየታቸውን የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር)ይፋ አድርገዋል ።  ኢትዮጵያ ውስጥ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሲሆን በ1 ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አላለፈም መባሉ በርካቶችን አስደንግጧል ። በሦስቱም ጉዳዮች ላይ አስተያየቶችን አሰባስበናል ።

ማይክ ሐመር እና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ

መስከረም 1 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት  የዩናይትድ ስቴትስ የምስራቅ አፍሪቃ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር  ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ጋ ፊት ለፊት መነጋገራቸው ይፋ ተገልጧል ።  ማይክ ሐመር እና ጄኔራል ጻድቃን ጎን ለጎን ቆመው የሚታዩበት ፎቶ በተያያዘበት የኤምባሲው አጠር ያለ የፌስቡክ መልእክት፦  የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ በአፋጣኝ የመተግበሩ እጅግ አስፈላጊነት ላይ ሁለቱ መስማማታቸው ተጠቅሷል ።

«አማራን በማግለል፤ የአማራን ጥቅም አሳልፎ የሰጠው የነ ሕወሓት ስምምነት አሁን አማራ ክልል ለተከሰተው ጦርነት መንስኤ ነው » ሲሉ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት ሠንደቅ እንዳውቅ የተባሉ በፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ። 

ማይክ ሐመር እስከ ፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ እንደሚቆዩ ተገልጧል ። ልዩ ልዑኩ በኢትዮጵያ ቆይታቸዉ፦ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋርም እንደሚወያዩ ተጠቅሷል ።  በአማራ ክልል የሚካሄደዉን ጦርነት፤ ብሎም በኦሮሚያ ክልል የሚታየዉን አመጽ በዉይይት ለማስቆም ጥረት ያደርጋሉም ተብሏል ። ዋሴ ጌታ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ከሁሉም በላይ ተፈናቃይ ማሕበረብ ወደ ቀየዉ መመለስ በኣስቸካይ መፈፀም ያለበት ችግር ነዉ ምክንያቱም በራብ በህመም ወዘተ እሚሰቃይና እሚሞት ያለ ሰዉ ጥቂት አይደለም የመኖር መብት ይከበርለት» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል ። 

የጊዜ ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ በሚል የፌስቡክ ስም ተጠቃሚ፦ «ያው መጣም አልመጣም ምዕራባውያን የራሳቸውን ጥቅም ያስቀድማሉ እኛ ነን እንጅ ወይ ድንቁርና አይሉ ወይ ዕወቀት አይሉ ወደ ነዱበት እየተነዳን እርስ በርሳችን እየተገዳደልን ፈጣሪ ይድረስልን» ብለዋል ። የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከሰፈሩ በርካታ መልእክቶች መካከል ብዙዎች የፕሪቶሪያው ስምምነት በአፋጣኝ እንዲተገበር ጠይቀዋል ።

ጨርቆስ ወልደ ጊዮርጊስ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ በፌስቡክ ለአምባሳደሩ በእንግሊዝኛ ጥያቄ አቅርበዋል ። «የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር ዐቢይ አህመድ ላይ ጫና ማሳደር አለበት ያን ሲሆን ብቻ ነው ዘላቂ ሰላም በትግራይ፤ በኢትዮጵያ እና በአካባቢው ማምጣት የሚቻለው» ሲሉም መልእክታቸውን አስፍረዋል ። አምባሳደሩ በትግራይ ክልል ፍትሕ እንዲነግስ መጣራቸውን በመግለጥ ብዙዎች አድንቀዋል ።

እዛው የኤምባሲው ገጽ ላይ ከሰፈረው መልእክት ስር ጴጥሮስ ኤም ባንጃው የተባሉ ተጠቃሚ እንዲህ ሲሉ ይጠይቃሉ ። «ለምን ይሆን ማይክ ሐመር ለሕወሓት የሚያደሉት እና የሚሠሩት? በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችም እኮ ሰዎች እየሞቱ ነው ስለዚያ አለሰሙም እንዴ ሲሉ በእንግሊዝኛ ጠይቀዋል ። ሌሎችም በአማራ ክልል ስለሚፈጸመው ግድያ አምባሳደሩ ችላ ለምን አሉ ሲሉ ጠይቀዋል ።

አምባሳደሩ ሐሙስ መስከረም 2 ቀን፤፣ 2017 ዓም ደግሞ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት ጌታቸው ረዳ ጋር ፊት ለፊት መወያየታቸው ተገልጧል ። አቶ ጌታቸው ከአምባሳደሩ ጎን ቆመው የተነሱትን ፎቶግራፍ በማያያዝ በትዊተር ገጻቸው ላይ መልእክታቸውን በእንግሊዝኛ አስፍረዋል ። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት  የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተልእኮውን በ«በተቻለ ፍጥነት» እንዲያሳካ  ቁርጠኛ መሆኑን አምባሳደሩ እንዳረጋገጡላቸው   ገልጠዋል ። እዮስያስ አረጋይ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «እንደተለመደው ከእሳቸው ጋር መነጋገሩ ጥሩ ሊመስል ይችላል ግን ተግባራዊ አይደለም» ብለዋል ። የስምምነቱ ተግባራዊነት መዘግየት አንዳች የሚያመላክት ነገር እንዳለው በመጥቀስም «አንዳች በምሥጢር የታቀደ ነገር አለ» ሲሉ ጥርጣሬያቸውን አክለዋል ።  400 ግድም የጦር ምርኮኞች መለቀቃቸውን በመጥቀስ በርካቶች «ለምን» ሲሉ ጥያቄ አንስተዋል ። የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)በአዲስ ዓመት መልእክታቸው እስረኞቹ መለቀቃቸውን በመቃወም በትግርኛ የተናገሩትን በማጣቀስ ። እስረኞቹ በሰኔ ወር የተለቀቁ ሆናቸውም ቀደም ሲል ተዘግቧል ።

አምባሳደር ማይክ ሐመር  ኢትዮጵያ መገኘታቸውን በመጥቀስ «ምን ይሠራል ሲሉ ይጠይቃሉ ሙሉክ ሊም በሚል የፌስቡክ ስም ተጠቃሚ ። «ችግራችንን ለማወሳሰብ ነው እንደገና በአጭሩ ጥያቄ አስፍረው ይሰናበታሉ ። እኛም ወደ ቀጣዮቹ ጉዳዮች እንሻገር ።

የጌታቸው ረዳ እና የኤርትራ ልዑክ በዱባይ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት ጌታቸው ረዳ ዱባይ ውስጥ ከኤርትራ መሪዎች ጋር መወያየታቸውን የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ከሰሞኑ ይፋ አድርገዋል ። ደብረፅዮን ቦታና ቀን ሳይጠቁሙ በዱባይ ከመጀመርያው ስብሰባ በኋላ ከኤርትራ መሪዎች ጋር ቀጣይ ስብሰባዎች መደረጉንም አመልክተዋል ።

 «ጥሩ ነው ሁሉም ባላንጣዎች ይወያዩ » ይላሉ ጌታቸው መኩሪያ በፌስቡክ ። «ምስራቅ አፍሪካ ሰላም ያስፈልገዋል » ይህን ያሉት ደግሞ ኤልያስ ኤልያስ ናቸው በዛው በፌስቡክ ።

ዶክተር ደብረፅዮን፦ ከኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ተካሄደ ያሉት ውይይት በሕወሓት ሥራ አስፈጻሚና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዕውቅና መሆኑንም ገልጠዋል ። «ሕወሓት ከውጭ ኃይል ጋር(ኤርትራ) ሊወጋን ነው እያለ ሲሳደብ የነበር የብልፄ ደጋፊ / ሚንስትሩ ፈቅዶላቸው መሆኑን ሲሰማ አሁን ምን ሊል ነው ማራ ታሪኩን በደም ፃፊ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ አስተያየት ነው ።

የበረራው ራስ ዳምጤ በሚል ስም የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ወክሎ ዱባይ በመሄድ ውይይቱን ያደረገው ጌታቸው ራሱ ነው በማለት ደፂ የራሱን ምስክርነት ሰጥቷል ይሄን ደግሞ ለአብይ አህመድም አሳውቀን ይሁንታውን ሰጥቶናል ሲል ጨምሯል» በማለት ጽፈዋል ። «ጌታቸው እና ደፂ አንዱ ሌላኛው የሚመራውን ቡድን  ከኤርትራ ጋር እያሴረ ነው » ሲሉም አክለዋል።  ጨርቦሌ በሚል የትዊተር ስም ሌላ ተጠቃሚ፦ «ከሻብያ ጋር ወስልተናል» የሚል አጠር ያለ ጽሑፍፋቸውን በሳቅ በሚያነቡ ምስሎች አያይዘዋል ።

አምላኩ ከፍ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፦ «ክልሎች ከሃገራት ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ማድረግ ይችላሉ ማለት ነውሲሉ ይጠይቃሉ ። «በዚህ ዙሪያ ሕጉ ምን ይላል የሚል ጥያቄም አስፍረዋል ። «ደሃውን ጨርሳችሁ ትገባበዛላችሁ» ያሉት ደግሞ ሮቤራ ሒንሳርሙ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ።

እምባዬ መኮንን፦ «ውይይቱ ሰላም የሚያመጣ ከሆነ በጣም ጠቃሚ እና የዘመናት ጥያቄያችን ነው » ብለዋል ። «ሰላም ለሰው ዘር በሙሉ» ያሉት ደግሞ ምንሊክ አዛዥ ናቸው በፌስቡክ ።

አስደንጋጩ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት

በኢትዮጵያ የአዲስ ዓመት መዳረሻ የወጣ ሌላ ዜና በርካቶችን አስደንግጧል ።  ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው ያለፉ ተማሪዎች 5.4 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸዉ  መባሉ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል ። «ያሳዝናል» አሉ ዳታ ይደግ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በአጭር መልእክታቸው ። ባለ አምስት ሆሄያት ቃላቸውን በአራት ተከታታይ ትእምርተ አንክሮ አጋነው ። ቃሉን ደገሙት ማንደፍሮ መስፍን የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ያሳዝናል»  ሲሉ ። «ይህ የትምህርት ጥራት ሳይሆን ትውልድን ከትምህርት ማጥራት ነው » አስተያየቱ የዳግም ጉልማ ነው ።

«አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አራት ወይንም ስድስት ዓመት ዩኒቨርስቲ አቃጥለህ ወጥተህም ሥራ የማታገኝ ከሆነ፣ ወይንም የምታገኘው ሥራ የእለት ጉርስህን የማይችልልህ ከሆነ የውጤት አለመምጣት ሊያስጨንቅ አይገባም ልል አሰብኩና ተውኩት » ይላሉ ጃራ ቦሩ በፌስቡክ ።

ሳሚ በላይ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ይኼ ነገር ለሦስተኛ ጊዜ ተደጋገመ ማለት፤ የተማሪው ድክመት ሳይሆን የት/ሚሩ ነው። ምክንያቱም ተማሪውን በሚገባ አላስተማረውም ወይም አላዘጋጀውም» ብለዋል ።

«አስደንጋጭ ዜና ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት» ሲሉ በእንግሊዝኛ ትዊተር ላይ የጻፉት ሙሐመድ ቡሊ ናቸው ።ግዛቸው አጥናፉ፦ «ከትምህርት ፖሊሲው» ብለዋል ለችግሩ መንስዔ መልስ ሲሰጡ ። ባዩ ገብሩ ያክላሉ፦ «የወላጆች ድርሻሰ ሲሉ ። «ሌላ ሀገር ቢሆን ሚኒስትሩ በራሳቸው ፈቃድ ሥራ ይለቁ ነበረ» አሉ ደጉ ተሾመ ተስፋዬ በፌስቡክ ።

የትምህርት ሚንስትር ፕሮፊሰር  ብርኃኑ ነጋ በ2016 ለፈተና ከተቀመጡት 684,205  ተማሪዎች መካከል 34 409 የሚሆኑት ተማሪዎች  ብቻ ማለፋቸውን በአዲስ ዓመት መዳረሻ ይፋ አድርገዋል ።  በሀገር አቀፍ ደረጃ  1363 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ የተሳናቸው ናቸዉ ተብሏል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW