1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኅብረተ ሰብየመካከለኛው ምሥራቅ

«ወደኋላ የተሳብኩትን ያህል ወደፊት መጥቻለሁ»

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4 2017

ምህረተ ተገኝ በህይወቷ ከባድ የሚባሉ ፈተናዎችን አሳልፋለች። ለተሻለ ህይወት ስትል በቤት ሰራተኛነት ለመስራት ወደ አረብ ሀገርም አቅንታ ነበር። በዚህ መሀል ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈችው ወጣት ዛሬ በሁለት እግሯ መቆም ችላለች። በህይወቷ ስለገጠሟት ትልልቅ ፈተናዎች፣ ከነሱ የተማረችውን እና ለሌሎች የምትመክረው አላት

 Äthiopien I Ex Hausmädchen
ምስል privat

«ወደኋላ የተሳብኩትን ያህል ወደፊት መጥቻለሁ»

This browser does not support the audio element.

ምህረት ተገኝ ገና በ17 አመቷ ነበር ህይወቷን ለመቀየር የወሰነችው እና ወደ አረብ ሀገር የተጓዘችው፤ ጅማ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ምህረት ዛሬ 30 ዓመቷ ነው።  ሌሎች ከህይወት ተሞክሮዋ እንዲማሩ ታሪኳን ለማካፈል  ስለፈቀደች እንግዳችን አድርገናታል። 

ከሀብታም ጋር መዋል ሀብታም መሆን ይመስለኝ ነበር

«ምህረት ህይወትሽን ለማሻሻል ስትይ ገና በልጅነትሽ ወደ አረብ ሀገር ሄደሽ  በቤት ሰራተኝነት ትሰሪ ነበር። እዛም ብዙ ፈተናዎችን ካለፍሽ በኋላ ህይወትሽን አሻሽለሽ እና ገንዘብ አግኝተሽ ነበር። ተመልሰሽ ደግሞ ይህንን ገንዘብ አጥተሻል። ምህረት የብር ሚሊየነር መሆን ችላ ነበር?

«በጊዜው ሚሊየነር ባልሆነም አረብ ሀገር  በሰራሁት ከእድሜ አቻዎቼ የበለጠ ገንዘብ ኖሮኝ ነበር።  ምክንያቱም በሳምንት ውስጥ ሶስት ስራ ነበር የምሰራው። በጊዜው ህይወቴን ይቀይራል የምለውን ያህል ገንዘብ አግኝቻለሁ ብዬ አምናለሁ። ግን ገንዘቡን የተጠቀምኩበት መንገድ ልክ አልነበረም። ገንዘቡን አውል የነበረው ራሴ ላይ ነበር። ስለዚህ ያገኘሁት ገንዘብ እኔን ያጠፋኝ ነበር። ለምሳሌ ውድ የምንላቸው አልባሳትን፣ ጫማዎችን፣ ሽቶዎችን እገዛ ነበር። ከዛ ባለፈ ትላልቅ ቦታዎች እየሄድኩን ከሀብታም ጋር መዋል ሀብታም መሆን ስለሚመስለኝ  ትላልቅ ሆቴሎች ላይ በመብላትም ይሁን በመጠጣት ገንዘቤን አጠፋ ነበር።»


ምህረት ከገንዘብ አያያዝ ጋር በተገናኘ ስህተት ነበር ከምትለው ተምራለች።  ዛሬ « አንድ ሰው ስለሰራ ብቻ ያገኛል የሚለው አመለካከቴ ተቀይሯል። ማስተዋል እና ጥበብም ያስፈልጋል» ባይ ናት።  ሌላው ምህረት ገንዘቧን እንድታጣ ምክንያት ነበር የምትለው  ጥናት ሳታደርግ በተደጋጋሚ ከሌሎች ሰዎች ጋር አብራ የሰራችባቸው ወቅቶች ናቸው። «ከአንዴም ሶስት ጊዜ አብሬያቸው የሰራኋቸው ሰዎች ተጠቅመውብኛል» የምትለው ምህረት ከዚህ የተማረችው ነገር «የሰው ሀሳብ ጥገኛ መሆን የለብንም» የሚል ነው።  «ልክ ያልሆነው ነገር፤  የሚመርጡን ሰዎች እኛ የምንመርጣቸው ሰዎች ሊሆን ይገባል። በሀሳብ በበኃሪ እንደገና ደግሞ ስራውንም በወውደድ ሁለት ወይም ሶስት ሰዎች እኩል የሚግባቡ ሲሆን ስራው የሚያዋጣ እና የሚቀጥል ይመስለኛል። እኔ ጋ ግን ያልተሳካበት የመጀመሪያው ምክንያት መራጭ ሳይሆን ተመራጭ መሆኔ ነው። ለዛ ቦታ እና ለዛ ስራ»!


 ምህረት አረብ ሀገር በነበረችበት ጊዜ ከወላጆቿ ጋር የነበረው ግንኙነቷ ተቋርጦ ነበር። ወደ ሀገሯ ከተመለሰች ጊዜ በኋላ ግን የተፈጠረውን መቀያየም  በይቅርታ ማለፍ ችላለች።  ግን ከመጀመሪያውኑ በቤተሰብ መሀል ጥል ወይም መቀራረን እንዳይፈጠር ውጭ ሀገር የሄዱ ልጆችም ሆኑ ወላጆች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?  « የላኩትን ገንዘብ ስመጣ አላገኘሁትም። ይህ ከቤተሰቦቼ ጋር የመጀመሪያውን ቅራኔ የፈጠረው ነው። አረብ ሀገር ለስራው በጣም ዋጋ እንከፍላለን። የግቢ መጥሪያ ክፍሌ ተደርጎ ነው የምቀሰቀስ የነበረው፤ ቤት ውስጥ ምግብ አለ ማለት እኔ እበላለሁ ማለት አልነበረም።  ያንን ያህል መስዋትነት የከፈልንበት ገንዘብ እዚህ ሲመጣ እኛ እንደምንፈልገው ሳይውል ሲቀር አለመቃረን አይቻልም። ቢያውቁልን ብዬ የምለው እኛ እንደምንልከው ፎቶ፣ እንደወፈርነው ወይም አየሩ እንዳቀላን ተመችቶን እንዳልሆነ ነው። እኛም ደግሞ የሆነውን ነገር አንናገርም። ፎቶዎቻችን የሚናገሩት ምቾታችንን ብቻ ነው። » 

ከሳዑዲ አረቢያ በግዳች የጠረዘቻቸው ኢትዮጵያውን ሀገራቸው ሲገቡምስል JENNY VAUGHAN/AFP

የማህበረሰብ ጫና

ሌላው ፈተና ደግሞ ከማህበረሰብ የሚመጣው ጫና ነው።  አንዲት ህይወቷን ለመቀየር ወደ አረብ ሀገር የሄደች ወጣት ውሏን ጨርሳም ይሁን ነገሮች እንዳሰበችው ሆነው ባለማግኘቷ ውሏን አቋርጣ ወደሀገሯ መመለስ ብትፈልግ ወላጆች መልሰው ሊቀበሏት ይገባል» ትላለች ምህረት፤ «እዛ ያለች አንዲት ልጅ ስትመለስ ለቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤትም ጭምር ነው። ስላመነችበት ብቻ ሳይሆን ከማህበረሰቡ ጋር ተስማምታ ለመኖር ስትል ነው። ይህ ልክ አይደለም ብዬ ነው የማስበው። ሌላው ደግሞ ወላጆች ለእኛ መቆም አለባቸው። ትምጣ ልጄ ከዜሮ መጀመር ትችላለች፣ ሀገርም መቀየር ትችላለች ብለው ማሰብ መቻል አለባቸው። ያኔ እዛ ላሉ ሰዎች ሞራል ነው። ብዙ ጊዜ የዚህ  ሀገር የዘይት እና የበርበሬ ዋጋ ነው የሚነገራቸው። እዚህ መጥታችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ማለት አትምጡ ነው። ስለዚህ ከሁለት ቦታ ነው ተጎጂ የሚሆኑት።» 


መሞትን የተመኘችበት ቀን እንደነበር በግልፅ የምትናገረው ምህረት መንፈሳዊ ህይወት በስመጨረሻ ጥንቃሬ የሰጣት ነገር ስለሆነ የየትኛውም እምነት ተከታዮች መንፈሳዊ ህይወታቸው ላይ ጠንካራ እንዲሆኑ ትመክራለች። 
« ከርሃብ በላይ እንድሞት ያኔ ያስመኘን የነበረው በዙሪያዬ የነበሩ ሰዎች የሚነግሩኝ ነገር ነው።ከዚህ በኋላ ምን ትጠብቂያለሽ? ለመንገድ ጠረጋ እንኳን እድል ካልተሰጠሽ ምን አሰብሽ ? የሚሉ አስተያየቶች። ይኼ ድምፅ የሰይጣን ነው። ሰይጣን ሰዎችን ይጠቀማል። እግዚያብሔርም ሰዎችን ይጠቀማል።»


ምህረት ከፈተናዎቿ ሁሉ ከባድ ጊዜ ነበር የምትለው ያለእቅዷ ያረገዘችበትን ወቅቱ እና ሴት ልጇን ከተገላገለች በኋላ የነበረውን ጊዜ ነው።  የልጇ አባት ማርገዟን ቢያውቅም ምህረትን ያውቃት የነበረው ገንዘብ ባላት ጊዜ ስለነበረ እና እሷም ስላለችበት ሁኔታ ልትነግረው ስላልፈለገች፤ ልጇን ብቻዋን ማሳደግ ከብዷት እንደነበር ትናገራለች። «ልጄ የወራት እድሜ እያለች የወተት መግዣ ስላልነበረኝ፣ ውኃ በስኳር ፤ አጃ ፤ ተልባ ነበር የማጠጣት። ከጋብቻ ውጪ መውለድ ልክ ላይሆን ይችላል። ግን ማስወረድን አልደግፍም። ምክንያትም ልጄን ለመግደል አቅም ካለኝ እናቴንም ለመግደል አቅም አለኝ። ልዩነቱ እናቴን ብገድል መንግሥት ተጠያቂ አድርጎ እታሰራለሁ። ልጄን ብገድል ግን ከእግዚያብሔር ውጪ ማንም አያየኝም እንደማለት ነው። ስህተት ሁለት ጊዜ መደገም የለበትም!

ምህረተ ተገኝ እና ልጇምስል Pixel Photography

ልጅሽን ብቻሽን ነው የምታሳድጊው?

«ልጄ እና አባቷ ይጠያየቃሉ። አሁን ደግሞ የትምህርት ቤት እና አንዳንድ ነገሮች እየከፈለ ይደግፋታል። የእሱ እና እኔ ግንኙነት ለልጅ ብሎ እንዲቀጥል አልፈለኩም። ሁለታችንም ጋር የፍቅር ስሜት ሳይኖር ነው የተረገዘችው እና ለልጃችን ብለን አንድ ላይ ብንኖር አለመግባባት እና አለመዋደዳችንን እያየች ነው የምታድገው፤ ያ ደግሞ እኔ ትናንት ያደኩበት ቤት ነው። ያንን ደግሞ በልጄ መድገም አልፈለኩም።

ህይወቷን ከሚወነጨፍ ቀስት ጋር የምታነፃፅረው ምህረት ወደፊት ለመወንጨፍ መጀመሪያ ቀስቱን ወደኋላ መሳብ እንዳለ ትናገራለች።  ምህረት በአሁኑ ሰዓት አልባሳትን የምትነግድበት ሱቅ ጅማ ከተማ ውስጥ አላት። ደጋግማ ወደ ኋላ መሳብ እና በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈችበት ቀስት ግቡን መቶ ይሆን? 
« አዎ እንደዛ ብዬ አስባለሁ። አሁን የፀፀት ኑሮ ላይ አይደለም ያለሁት። በገንዘብ የሚተመን ሚሊየነር አይደለሁም ግን የሀሳብ ሚሊየነበር አድርጎኛል። ተስፋ አለኝ፤ ለቤተሰቦቼ ለጓደኞቼ ይቅርታ ማድረግ ችያለሁ። ማድረጌን ደግሞ በተግባር ገልጬዋለሁ። ያን ሳስብ ለእኔ ስኬት መንገድ እንጂ መዳረሻ አይደለም። ወደኋላ የተሳብኩትን ያህል ወደፊት መጥቻለሁ።» 
መፅሀፍ መፃፍ አንዱ ህልምሽ ነበር። ይህንንም እያሳካሽ ነው። መፅሀፉ ስለምንድን ነው? ለሌሎችስ መማሪያ ይሆናል?

መፅሀፉ በቃለ መጠይቆች ወይም በሶሻል ሚዲያ ሊነገር አይገባም ያልኳቸውን ሚስጥሮቼን የያዘ ነው። በእኔ ህይወት ውስጥ ልክም የሆነ እንዲሁም ያልሆኑ ነገሮችን የያዘ ነው። ጥንካሬዬን ብቻ ሳይሆን ደካማ ጎኖቼም ተፅፈውበታል። ሰዎች ራሳቸውን እያጠፉ ያሉት በገንዘብ እጦት ብቻ አይደለም። እዛ ላይ የፃፍኳቸው ነገሮች ትውልድ ይጠቀምበታል ብዬ ያሰብኩትን ነገሮች ነው።»
ምህረት ተገኝ መፅሀፉ በወራት እድሜ ውስጥ ለገበያ እንደሚቀርብ ተስፋ አላት።  

ልደት አበበ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
 


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW