ምሥራቅ ጀርመን
ማክሰኞ፣ ጥር 29 2010ጀርመንን ከፍሎ የነበረው ግንብ መሰራት የጀመረው በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 1961 ዓም ነበር ። የፈረሰው ደግሞ ህዳር 9 1989 ነው። ግንቡ መፍረስ የጀመረው በተሰራ በ28 ዓመት ከ2 ወር ከ26 ቀናት በኋላ ነው። ግንቡ ከፈረሰ እስከ ትናንት ያለው ጊዜ ሲሰላ ደግሞ ከግንቡ እድሜ ጋር የሚስተካከል ሆኗል። የግንቡ እድሜ እና ከፈረሰ በኋላ የተቆጠረው ዘመን እኩል መሆን እዚህ ጀርመን ትናንት ትውስታን እያጫረ ብዙ አነጋግሯል። ለጀርመን ብቻ ሳይሆን ለዓለም በትልቅ ተምሳሌትነቱ የሚጠቀሰውን ሰላማዊውን የጀርመን ውህደት ያፈጠነው ሳይጠበቅ እና ሳይታሰብ የበርሊን ግንብ መፍረሱ ነበር። ያኔ በስፍራው የሆነውን የመከታተል እድል ከነበራቸው መካከል የኔ ምዕራብ በርሊን ውስጥ ተማሪ የነበሩት አቶ በላይነህ ተሾመ አንዱ ናቸው።
አቶ በላይነህ ጀርመን ሲኖሩ ከ35 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ግንቡ ከመፍረሱ በፊት በሁለቱ ጀርመኖች መካከል የነበረውን ልዩነትም በቅጡ ያውቃሉ። ተማሪ ሳሉ ምሥራቅ ጀርመን በሄዱባቸው አጋጣሚዎች ልዩነቶቹ በግልጽ የሚታዩ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
ዶክተር አየለ ጉግሳም የበርሊን ግንብ ሲፈርስ ተማሪ ነበሩ። እርሳቸው ደግሞ ምሥራቅ በርሊን ውስጥ ነበር የሚኖሩት። ምዕራብ ጀርመንን በጎበኙባቸው አጋጣሚዎች ጎልቶ የሚታይ ልዩነት እንደነበረ ነው የሚናገሩት። ልዩነቱንም የገለጹት የሰማይና የምድር ያህል ነበር ሲሉ ነው።
የጀርመን ውህደት ለጀርመን ኤኮኖሚ መመንደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ልዩ ልዩ መብቶቻቸው ላይ ገደብ ተጥሎባቸው የነበሩ ዜጎች ነጻነት አኝኝተዋል። ውህደቱ እነዚህን እና ሌሎችንም በርካታ ጥቅሞችን ማስገኘቱ ቢታወቅም ቀድሞ በኮምኒስት አስተዳደር ስር ለነበረው ምሥራቅ ጀርመን ግን ተስፋ የተደረገበትን እና የተጠበቀውን ያህል ውጤት አለማስገኘቱ አንዱ ችግር ነው እንደ ዶክተር አየለ ።አቶ በላይነህ እንደሚሉት በዚህ የተነሳ አንዳንድ የምሥራቅ ጀርመን አካባቢዎች አሁንም ድረስ ወደ ኃላ እንደቀሩ ነው።
ይህ ባስከተለው ቅሬታ ምሥራቅ ጀርመኖች መብታቸው እንዳልተጠበቀ በመቁጠር የቀኝ ጽንፈኛ እና የዘረኛ እንቅስቃሴዎች መነኻሪያ ሆነዋልም ይላሉ አቶ በላይነህ ። ቀኝ ጽንፈኞች በምሥራቅ ጀርመን ምክር ቤቶች ውስጥ የሚይዟቸው መቀመጫዎች ቁጥር እያደገ የመምጣቱ ፣ባለፈው መስከረም በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫም «አማራጭ ለጀርመን»የተባለው መጤ ጠል ፓርቲ ብዙ ድምጽ አግኝቶ የጀርመን ምክር ቤት ውስጥ መግባት የመቻሉ ምክንያት በምሥራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ላይ ያደረው የተረስተናል ስሜት ነው እንደ አቶ በላይነህ።
ዶክተር አየለ ደግሞ የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ መጠናከር የጀርመን ችግር ብቻ አይደለም ይላሉ። ያም ሆኖ ከጀርመኖች ውህደት ሌላው ዓለም ብዙ ትምሕርት ሊቀስም ይችላል ይላሉ አቶ በላይነህ ።
ኂሩት መለሰ
ተስፋለም ወልደየስ