1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ መስጊዶች ተቃጠሉ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 11 2012

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በአራት መስጊዶች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ። ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ሁለቱ መስጊዶች በቃጠሎ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን እና ሌሎች ሁለቱ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።

Äthiopien PK Getnet Yirsaw zu Brandstiftungen
ምስል፦ DW/A. Mekonnen

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በአራት መስጊዶች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ። ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ሁለቱ መስጊዶች በቃጠሎ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን እና ሌሎች ሁለቱ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል። ምክር ቤቱ «እየተመረጠ እና እየተፈለገ የሙስሊሙ ሕዝብ ንብረት የሆኑ ሆቴሎች፤ መኖሪያ ቤቶች እና መደብሮች ዘረፋ፤ ውድመት እና ቃጠሎ» ደርሶባቸዋል ብሏል። 
የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒከየሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው ማምሻውን በሰጡት መግለጫ አንዳሉት የክልሉን ሰላም በማይፈልጉ ኃይሎች ባሏቸው ሰዎች በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ የማቃጠል ሙከራ እና በሶስት መስጊዶች ላይ የመቃጠል አደጋ ደርሷል፡፡ የደረሰው ጥቃት መነሻም በከተማዋ የሚገኘው የጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን ላይ የተደረገው የማቃጠል ሙከራ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል። «በከተማው ውስጥ የጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያንን የማቃጠል ሙከራ ነው የተደረገው። ሙከራውን ማክሸፍ ከተቻለ በኋላ ወዲያውኑ ጉዳዩ ሌላ ቅርፅ ይዞ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ግለሰቦች መስጊዶችን ወደማጥቃት ነው የሄዱት። በሶስት መስጊዶች ላይ ጉዳት ደርሷል። አጋጣሚውን በመጠቀምም ስርዓት አልበኛ የሆኑ ቡድኖች ሱቆችን ወደ መዝረፍ እና ማቃጠል ነው የሄዱት በዚህም በርካታ ንብረት ወድሟል። በሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ አደጋ ደርሰዋል።» የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒከየሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት መግለጫውን እስከሚሰጡበት ጊዜ ድረስ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል። አንድ የሞጣ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ DW እንደተናገሩት ከቤተ እምነቶቹ ባሻገር አንድ የመገበያያ አዳራሽ ጭምር መቃጠሉን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሞጣ እና በአካባቢው ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ሥጋቱን ገልጾ «መንግሥት ለዜጎች ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ» ጠይቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትናንት ማምሻውን የደረሰውን አደጋ አውግዘዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ  “በኢትዮጵያ የሀገራችንን የቆየ የሃይማኖቶችን የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል የሚፃረሩ ጽንፈኛ አካሄዶች ቦታ የላቸውም» በማለት አስጠንቅቀዋል።

አቶ ጌትነት ይርሳውምስል፦ DW/A. Mekonnen

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW