1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ምርጫው ፉክክር የሚታይበት አይሆንም»

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ሰኔ 11 2013

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅትታችንም ሰኞ ዕለት በሚካሄደው የኢትዮጵያ  6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ላይ ትኩረቱን አድርጓል። ለ DW አስተያየታቸውን ያካፈሉን የዝግጅታችን ተከታታዮች እንደሚሉት ከሆነ « የምርጫ ውጤት አስቀድሞ የለየ» ነው። ለዚህ ምክንያት የሚሉትን እና በሚኖሩበት አካባቢ ሰሞኑን የነበረውን የምርጫ ድባብ አጠያይቀናል።

Äthiopien NEBE-Wahlunterlagen-Display
ምስል Solomon Muchie / DW

«ምርጫው ፉክክር የሚታይበት አይሆንም»

This browser does not support the audio element.

እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሆነ ከ 37 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በ 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ለመሳተፍ ተመዝግቧል። መካሻ - በአዲስ አበባ አቅራቢያ የሚኖር ወጣት ነው። ሰኞ ዕለት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተደረጉት ምርጫዎች ብዙም የሚለየው ነገር የለም ባይ ነው። « የኢትዮጵያ ምርጫን ሳይመረጥ ማን እንደሚመረጥ ህዝቡ ያወቀው ነው። እዚህ ውጪ ወጥተው የሚጨፍሩ ፓርቲዎች በሙሉ አንድ አይነት እህትማማች ፓርቲዎች ናቸው። » የምርጫው ውጤት ግልፅ ስለሆነ መምረጥ አያስፈልገኝም ብሎ የደመደመው መካሻ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ነው የሚል እምነትም የለውም። ለዚህ በምሳሌነት የሚያቀርበው ደግሞ የምርጫ ዘመቻ ቅስቀሳውን ነው። « ከቤታችን በሌሊት እየመጡ ውጡ ነው የሚሉን። መጥሪያ እየሰጡን። እኔን ብቻ ምረጡ ማለት የግዴታ ምርጫ ነው።»መካሻ ይህን ሁለት ቀናት ትንሽ ዕረፍት አግኝቷል። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ረቡዕ ዕለት ይፋ እንዳደረገው ምርጫው ሊካሄድ አራት ቀን ሲቀረው ያለው ጊዜ የጥምና ወቅት ነው። በነዚህ ቀናት የፓለቲካ ፓርቲዎች «ማንኛውም አይነት የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አይፈቀድላቸውም»፡፡ ይህም ቤት ለቤት ይደረግ የነበረውን የምርጫ ቅስቀሳ ያካትታል። 
ከመዲና አዲስ አበባ 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የአማራ ክልል ፣ ሸዋ ሮቢት ከተማ ሰኞ ዕለት ምርጫ አይካሄድም። እንደሚታወቀው በዚህ አካባቢ በተደጋጋሚ የፀጥታ ችግሮች ነበሩ። የከተማው ነዋሪ የሆነችው ወጣት ሃይማኖት ሰኞ ዕለት ምርጫ አለመካሄዱን በሁለት ከፍላ ነው የምታየው። « ውሳኔው በከፊል ሲታይ አግባብነት አለው። ገና አሁን ነው እየተረጋጋን ያለነው። በግማሽ ሲታይ ደግሞ አልደግፈውም። ምክንያቱም መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ምርጫው ከሁሉም ኢትዮጵያውያኖች እኩል መምረጥ እንድንችል ማድረግ ይገባው ነበር።
ምንም እንኳን ሸዋሮቢት ሰኞ ዕለት ምርጫ የማይካሄድባት ብቸኛዋ የኢትዮጵያ ከተማ ባትሆንም፤ ለሃይማኖት እና መሰል ጎደኞቿ ለየት ያለ ስሜት ፈጥሮባቸዋል። ምርጫው ቢካሄድ ኖሮ ግን የወጣቱ ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ሐይማኖት ትናገራለች።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ እንዳደረገው ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ ሰኔ 14 ምርጫ በማይደረግባቸዉ በተወሰኑ የአማራ፣ የኦሮምያ ፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፤ እና ደቡብ ክልል ከተሞች እንዲሁም በሐረሪና በሶማሊያ ክልሎች ምርጫው ጳግሜ 1 ቀን 2013 ዓም ይካሄዳል ። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገራዊ ምርጫ በሳምንታት ልዩነት በተለያየ ስፍራ ሲካሄድ የዘንድሮዉ ምርጫ የመጀሪያው ይሆናል። 
ሌላው ከዶይቸ ቬለ ስርጭት ተከታታዮች መካከል ደውለን ያገኘነው ወጣት ጎጃም አካባቢ እንደሚኖር የነገረን ደረጀ ነው። ሰኞ ዕለት ድምፁን ይሰጣል። የምርጫውን ውጤት በሚመለከት ግን አስቀድሞ ርግጠኛ ሆኗል።  « የራስሽን ነገር ትሞክሪያለሽ። ዞሮ ዞሮ ግን ገዢው ፓርቲ እንደሚያሸንፍ ይታወቃል። አፍሪቃ ውስጥ አይደል እንዴ ያለነው?» ደረጀ ገዢው ፓርቲ ያሸንፋል የሚል ዕምነት ይኑረው እንጂ የዘንድሮው ምርጫ በሀገሪቱ ከዚህ ቀደም  ከተካሄዱ ምርጫዎች የተሻለ እንደሚሆን ያምናል። ውጤቱም የተጋነነ አይሆንም ባይ ነው። « የተወሰነ ዲሞክራሲ ይጨመርበታል የሚል እምነት አለኝ።»
መስፍን የደሴ ከተማ ነዋሪ ነው። እሱም በሚኖርበት አካባቢ ያለው የምርጫ ድባብ «ብዙም የተለየ ነገር ታይቶበታል የሚያስብል አይደለም» ይላል። « ወጣቱ ብዙ ካርድ አልወሰደም። እንደሚመስለኝ በየቦታው በተፈረው ነገር ወጣቱ ቅሬታ አለበት። ሌላው ደግሞ ምርጫ ምንም ፋይዳ የለውም በሚል አመለካከት ነው»  መስፍን በ97 ዓ ም በተካሄደው ምርጫ ድምፅ ሰጥቷል። በአሁኑ ምርጫ ግን ላለመምረጥ ወስኗል። የመራጭ ካርድም አልወሰደም። መስፍን እስካሁን የነበረውን የምርጫ ሂደት « እስካሁን ሰላማዊ የሚባል ነው »ይላል።  « ወደፊት ከምርጫ በኋላ የሚመጣው ግን አይታወቅም» ውጤቱንም አስቀድሞ የሚታወቅ ስለሆነ ብዙም የሚደንቀን ነገር የለም የሚል እምነት አለው። 
ወጣት አስያ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት። በምርጫው ላይ እምነት ስለሌላት ላለመምረጥ እና « ከዳር ሆና ለመታዘብ» መወሰኗን ነው የነገረችን። « ትክክለኛ እና ፍትኃዊ ምርጫ ይደረጋል ብዬ ስለማላምን ለመምረጥ አላሰብኩም።» የጎንደር ከተማ ነዋሪ እንደሆነ የነገረን ጀማል በአንፃሩ ሰኞ ዕለት ድምፁን ለመስጠት ወስኗል። በሚኖርባት አካባቢ የተለያዩ የምርጫ ዘመቻዎችንም ታዝቤያለሁ ይላል።  «ሰው የተለያየ አመለካከት አለው። ካርድ ያወጣም ፣ያላወጣም አለ።» ይላል።
ሌላው በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት አስተያየቱን ያካፈለን ወጣት በኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ አቅራቢያ ነዋሪ ነኝ ያለን ዮናስ ነው። እንደ ወጣቱ ከሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ የሚባሉ የሉም «አንድ ፓርቲ ነው ያለው ለማለት ይቻላል። አብዛኛው  ተፎካካሪዎች ታስረው ነው ያሉት» ፣የምርጫ ካርድ ያወጣውም «ተገድጄ ነው» ይላል።  « ድብደባ ስለነበር ነው ያወጣሁት። መንገድ ላይ ፖሊሶች ነበሩ። ዘይት ለመግዛት እና ለታክሲ ቲኬት ለመቁረጥ የምርጫ ካርድ ይጠየቅ ነበር» ይላል።

ምስል National Election Board of Ethiopia
ምስል Yohannes Gebreegiziabher/DW

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW