1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ ከ5-8 ሰዎችን ገደለ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13 2016

የህክምና ስራ እያከናወኑ ያሉ ባለሙያ በሽታው እንዳይስፋፋና ተጨማሪ ጉዳት በህብረተሰቡ ላይ እንዳያደርስ የመከላከልና የህክምና ስራ እያከናወኑ ቢሆንም የበሽታው ስርጭት በሌሎች ቀበሌዎች በፍጥነት እየተዛመተ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኮሌራ አማጭ ባክቴርያ
የኮሌራ አማጭ ባክቴርያምስል Dr.Gary Gaugler/OKAPIA/picture-alliance

ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ ከ5-8 ሰዎችን ገደለ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሐረሰብ አስተዳደር ሳህላ ሰየምት ወረዳኮሌራ መሰል በሽታ ከ5 እስከ 8 የሚደርሱ ሰዎችን ሲገድል ከ260 በላ የሚሆኑት ደግሞ በበሽታው መጠቃታቸውን የወረዳው አስተዳደርና የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል።በሽታው በወረዳው በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ መሆኑንም ባለሙያዎች አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሳህላ ሰየምት ወረዳ ከሰኔ 24 /2016 ዓ.ም ጀምሮ “ኮሌራ መሰል” የተባለ ወረርሽኝ ተከስቶ ህይወት ማጥፋቱን ነዋሪዎችና የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት አመልክተዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት በሽታው የተከሰተው ሰኔ 19/2016  ዓ.ም በአካባቢው የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለውን ጎርፍ ተከትሎ ህብረተሰቡ ንፀህናው ያልተጠበቀ ውሀ ከወንዝ ከጠጣ በኋላ ነው፡፡

በሽታው ሰኔ 24/2016  ዓ.ም  መሐሪት በተባለው የወረዳው ቀበሌ ተከስቷል፡፡ በሽታው በትውከትና በተቅማጥ መልክ ሰዎችን አዳክሞ ለሞት የሚያደርስ ቢሆንም እስከ አሁን በምርመራ ተረጋግጦ ምንነቱ እንዳልታወቀ የጤና በለሙያዎች አስረድተዋል፡፡ 
የነዋሪዎች አስተያየት
አንድ የሳህላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪ የበሽታውን ባህሪ በተመለከተ ለዶቼ ቬሌ አንደተናገሩት የበሽታው ምንነት እስካሁን በግልፅ አልታወቀም፣ ሆኖም የጤና ባለሙያዎች በደፈናው “የውሀ ወለድ በሽታ ነው፡፡” ማለታቸውን መስማታቸውን ገልጠዋል፡፡ ታማሚዎቹ ደም የተቀላቀለበት ተቅማጥና ተውከት እንደሚታይባቸውም አስረድተዋል፣ በሽታው እንዳይስፋፋ የጤና ባለሙያዎች ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የበሽታው ስርጭት ግን ወደ ሌሎች የወረዳው ቀበሌዎች እየተሰራጨ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሌላ በህክምና ላይ ያሉና በወረዳው በአንደኛው ቀበሌ የህክምና ስራ እያከናወኑ ያሉ ባለሙያበሽታው እንዳይስፋፋና ተጨማሪ ጉዳት በህብረተሰቡ ላይ እንዳያደርስ የመከላከልና የህክምና ስራ እያከናወኑ ቢሆንም የበሽታው ስርጭት በሌሎች ቀበሌዎች በፍጥነት እየተዛመተ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የወረዳው ባለስልጣናት አስተያየት
የሳህላ ሰየምት ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የሚዲያ ልማት ቡድን መሪ አቶ ጋሻው ቸኮለ በበሽታው ተይዘው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 8 መድረሱንና፣ በሽታውም በወረዳ ደረጃ እንደተሰራጨ ነው ያመለከቱት፣ የበሽታው ምንነት ባይታወቅም ባለሙያዎች ግን ህሙማንን ለመታደግ እየሰሩ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

የሰቖጣ ከተማ በከፊልምስል Alemnew Mekonnen/DW


የሳህላ ሰየምት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ብሩ ጉዳዩን አስመልክተው ለዶይቼ ቬሌ እንዳሉት የተከሰተው በሽታ ወደ ወረዳው ቀበሌዎች በፍጥነት እየተዛመተ ነው፣ የመከላከሉ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ የጤና ኮሚቴ ተቋቁሞ ችግሩ እንዳይሰፋ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ አንደሆነ አስረድተዋል፣ ሁኔታው ከባድ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሲሳይ ሰዎች በብዛት ታመዋል፣ ሞትም አስከትሏል ነው ያሉት፡፡ “ከሰኔ 24/2016 ዓ ም ጀምሮ 8 ሰዎች ሞተዋል፣ 262 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘዋል፡፡”  ብለዋል፡፡
በሽታው መጀመሪያ ላይ “መሀሪት” በተባለው ቀበሌ እንደተከሰተ የገለጡት ዋና አስተዳዳሪው አሁን በሽታው ወደ ወረዳው ቀበሌዎች በመስፋፋት  “ቢላዛ፣ ፍነዋ፣ ግብረሰላም፣ አጥላ ቀበሌዎችና መሻ ከተማ ላይ ተሰራጭቷል” ብለዋል፡፡
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምላሽ
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አሰፋ ነጋሽ የበሽታው ምንነት በግልፅ እንዳልታወቀ ጠቁመው፣ ሆኖም ናሙናዎች ለምርመራ መላካቸውን ተናግረዋል፡፡ ለጊዜው ለአጣዳፊ ተቅማትና ተውከት የሚሰጠውን ህክምና እየሰጡ እንደሆነም አስረድተዋል፣ በደረሳቸው መረጃ መሰረትም እስካሁን 5 ሰዎች በበሽታው መሞታቸውንና262 ሰዎች ደግሞ መታመማቸውን ገልጠዋል፡፡
መምሪያ ኃላፊው አቶ አሰፋ የመከላከልና የህክምና ስራውን በተመለከተ፣ “በአለን አቅም ግብዓቶችን አድርሰናል፣ ልምድ ያላቸውን የህክምና ባለሙያዎችን አሰማርተናል፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ወደቦታው አንቀሳቅሰናል፣ የቤት ለቤት አሰሳና ቅኝት አጠናክረን ቀጥለናል፣ የቤት ለቤት ህክምናም እየሰጠን ነው” ብለዋል፡፡ ዋናው ለበሽታው መነሻ የሆነው ውሀ በመሆኑ ነዋሪው ውሀውን አክሞ እንዲጠቀም የውሀ ማከሚያ ግብአቶች ለህብረተሰቡ መቅረቡንም አስረድተዋል፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ቆላማ አካባቢዎች ደግሞ ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት መስፋፋቱን የብሔረሰብ አስተዳደሩ የጤና ባለሙያዎችና ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW