1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተወሰኑ የሩሲያ ባንኮች ስዊፍት ከተባለ የባንኮች የክፍያ መፈጸሚያ ሥርዓት ሊታገዱ ነው

እሑድ፣ የካቲት 20 2014

የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እና ብሪታኒያ የተወሰኑ የሩሲያ ባንኮችን ስዊፍት ከተባለው ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ሊያግዱ ነው። ምዕራባውያኑ የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ በውጭ አገራት ተቀማጭ ገንዘብ እንዳያንቀሳቅስ ለማድረግ ጭምር አቅደዋል። 

Zahlungsdienstleister SWIFT
ምስል Chris Helgren/REUTERS

የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እና ብሪታኒያ የተወሰኑ የሩሲያ ባንኮችን ስዊፍት ከተባለው ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ለማገድ ተስማሙ። በጉዳዩ ላይ የቡድን ሰባት አባል አገራት መሪዎች ከስምምነት መድረሳቸውን በዛሬው ዕለት አስታውቀዋል። በፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት በኩል ይፋ የሆነው የቡድን ሰባት አባል አገራት መግለጫ እርምጃው የትኞቹ የሩሲያ ባንኮችን እንደሚመለከት በግልጽ ያለው ነገር የለም። 

በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ስዊፍት ተብሎ የሚጠራው የዓለም አቀፍ ባንኮች የግንኙነት ሥርዓት ደህንነቱ የተጠበቀ የመልዕክት መለዋወጫ መንገድ ሲሆን ድንበር ተሻጋሪ ክፍያዎች በፍጥነት የሚፈጸሙበት፣ ዓለም አቀፍ ንግድን የሚያመቻች ነው። 

ከ50 ገደማ አመታት በፊት ሥራ ላይ የዋለው እና መቀመጫውን በቤልጅየም ያደረገው ይኸው ሥርዓት በመላው ዓለም ከ11,000 በላይ ለሚሆኑ ባንኮች እና የገንዘብ ተቋማት የገንዘብ ዝውውርን ያመቻቻል። 

አሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት የሚወስዱት እርምጃ የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ በውጭ አገራት ተቀማጭ ገንዘብ እንዳያንቀሳቅስ መገደብን የሚጨምር ሲሆን በመጪዎቹ ቀናት ገቢራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። 

ነዳጅ፣ ብረት እና እህልን ጨምሮ ምዕራባውያኑ በጣሏቸው አዳዲስ ማዕቀቦች ሳቢያ የሩሲያ የወጪ ንግድ ብርቱ ችግር ውስጥ እንደሚገባ ተንታኞች ይናገራሉ። ዳፋው ግን በሩሲያ ብቻ የሚወሰን አይሆንም። በማዕቀቦቹ ምክንያት በዓለም ገበያ የዋጋ ጭማሪ እና ንረት ሊከሰት እንደሚችል ነጋዴዎች እና ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ። 

ሩሲያ በዓለም የነዳጅ ምርት 10 በመቶ ድርሻ አላት። ከአውሮፓ የጋዝ ፍጆታ 40 በመቶው የሩሲያ ምርት ነው። ሩሲያ በዓለም ቀዳሚ የእህል እና የማዳበሪያ አምራች ጭምር ናት። አገሪቱ ከፓላድየም እና ኒኬል ቀዳሚ አምራቾች አንዷ ስትሆን የከሰል ድንጋይ እና ብረት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ሶስተኛ በእንጨት ምርት ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW