1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምዕራብ ጎንደር ዉስጥ የሰዎች መታገት ያሳደረዉ ስጋት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 17 2016

«--ከመኪናው ውስጥ የነበሩ 3 ያህል ሴቶች ሲቀሩ ሌሎች እንደታገቱ ናቸው፣ ታህሳስ 14 ደግሞ ሚካኤል ከሚባል ቤተክርስቲያን ከ10 ዓመት በታች የሆኑ 13 ህፃናት ተማሪዎች ታግተው ማህበረ ስላሴ ወደሚባል ጫካ ተወስደዋልዋል፣ ጉዳዩን መልክ ከማስያዝ አንፃር የመንግስት ድክመት አለ---»

የመተማ ወረዳ ጽሕፈት ቤት
የመተማ ወረዳ ጽ/ቤት ማስታወቂያምስል Alemnew Mekonnen

ምዕራብ ጎንደር ዉስጥ የሰዎች መታገት ያሳደረዉ ስጋት

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን  መተማ ወረዳ ዉስጥ በተደጋጋሚ ሰዎች መታገታቸዉ የአካባቢዉን ሕዝብ እንቅስቃሴ እየዋከ፣ ለከፍተኛ ስጋት መዳረጉንም የአካባቢው ነዋሪዎችና ፖለቲከኞች አስታወቁ።ሰሞኑን በአተለያዩ ቀናትና አካባቢዎች ከ30 የሚበልጡ ሰዎች በታጣቂዎች ታግተዋል።ነዋሪዎቹ እንዳሉት ከታጋቾቹ 6ቱለአጋቾች ቤዛ ከፍለው ተለቅቀዋል።የዞኑ አስተዳደር ስለ እገታዉ ከነዋሪዎች ጋር እየተወያየ መሆኑንና ታጋቾቹን ለማስለቀቅ እየጣረ መሆኑን አስታዉቋል።

እገታ በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎንደር

ታህሳስ 9፣ 11፣ 14 እና 15/2016 ዓ ም በዞኑ መተማ  ወረዳ ልዩ ሰማቸው መቃ ሌንጫ፣ ኩመር አውላላ፣ ባህር ኩርኩርና ጅረን ውሀ በተባሉ ቦታዎች ኃይል በታከለባቸው እርምጃዎች ከ36 የማያንሱ ሰዎች ባልታወቁ ታጣቂዎች ታግተዋል፡፡አንድ የአካባቢው ነዋሪ እገታዎችን በተመለከተ  ለዶይቼ ቬሌ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

“ዜጎች እየታገቱና በጥይት እየተመቱ ነው ያሉ፣ ሰሞኑን (ታህሳስ 15) ኩመር አውላላ ከሚባል አካባቢ መቃን ቀበሌ  ጅረን ውሀ የምትባል አካባቢ ታግተው ጫካ እንደሄዱ ናቸው፣ ጠቅላላ ከ10 በላይ  የሚሆኑ ከመኪናው ውስጥ የነበሩ 3 ያህል ሴቶች ሲቀሩ ሌሎች እንደታገቱ ናቸው፣ ታህሳስ 14 ደግሞ ሚካኤል ከሚባል ቤተክርስቲያን  ከ10 ዓመት በታች የሆኑ  13 ህፃናት ተማሪዎች ታግተው  ማህበረ ስላሴ ወደሚባል ጫካ ተወስደዋልዋል፣ ጉዳዩን መልክ ከማስያዝ አንፃር የመንግስት ድክመት አለ፣ የወረዳና የአካባቢ ሚሊሺያ ተግባሩን እየተወጣ አይደልም፡፡”

የቅማንት ዴሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳለአምላክ ስመኝም እገታዎች በተደጋጋሚ በወረዳው መፈፀማቸውን ተናግረዋል፡፡

ምዕራብ ኮንደርና መተማምስል DW/Alemenew Mekonnen

 

( “...ታህሳስ 15) ጅረን ውሀ ከሚባለው አካባቢ ነው፣ ከዞኑ ማዕከል ገንዳ ውሀ ተነስቶ ወደ ጎንደር ሰዎችን አሳፍሮ ይሄድ የነበረ የህዝብ ትራንስፖርት “አባዱላ” መኪና  ላይ ነው እገታ የተፈፀመው፣ አንድ አባዱላ የሚጭነው እስከ 16 ሰዎችን ነው ፣ መኪናዎቹ ሙሉ ሰው ካልያዙ ከመናከሪያ አይወጡም፣ መውጫም ስለማይሰጣቸው መኪናው ሙሉ ነው ብለን ነው የምናስበው፣ ታህሳስ 9ም ሁለት ወጣቶች በሞተር ብስክሌት ከመቃ ተነስተው ወደ  ሌንጫ ሲሄዱ ታግተዋል፣ ታህሳስ 11 ደግሞ አውላላ ከሚባለው አካባቢ “አይሩፍ”  በሚባል የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ላይ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው ሁለት ተሳፋሪዎችን ካቆሰሉ በኋላ 6ቱን አግተዋል፣ ታህሳስ 14 ባህር ኩርኩር ከሚባለው ቦታ ላይ ሚካኤል ቤተክርስቲያን  13 የቆፐ ተማሪዎች ታግተው ተወስደዋል፡፡ ” ብለዋል፡፡

ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚደረግ ጥረት

የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ሞገስ በአካባቢው እየታየ ያለውን የሰዎች እገታለመከላከልና የታገቱንም ለማስለቀቅ ከማህበረሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡

“ባለፉት 2 እና 3 ወራት በተሻለ ተንቀሳቅሰናል፣  ሰሞኑን የተፈፀመ እገታ አለ፣  አኩሻራና መቃ በሚባሉ አካባቢዎች ነው እገታ የተፈፀመው፣ ከሐይመኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ውይይቶች ተካሂደዋል፣ የራሳችን አቅጣጫም አስቀምጠናል፣ በተጨባጭ በነዚህ 2 እና 3 ቀናት ውስጥ የታገቱትን እናስለቅቃለን፡፡” ነው ያሉት፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቁ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ያለውን ተግባር አብራርተዋል፡፡

ከህብረተሰቡ ጋር ሰፋ ያለ ውይይት እየተደረገ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ቢክስ፣ ችግሩን በዛላቂነት ለመፍታትም የፀጥታ ኃይሉን የማደራጀት፣ መስመሩን በቋሚ ጥበቃ፣ በቅኝት፣ ማሕበረሰቡን በማሳተፍ ይሰራል ሁለቱም የአካባቢው አስተዳዳዳሪዎች የታጋቾችን ቁጥር በተመለከተ ወደፊት ግልፅ እናደርጋለን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመተማ ወረዳ በከፊልምስል Alemnew Mekonnen

ዛሬ ከቦታው የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ታህሳስ 11 ቀን በአንድ የህዝብ ማመላለሻ ተሳፍረው ሲጓዙ ታግተው የነበሩት 6 ታጋቾችና ታህሳስ 9 በሞተር ብስክሌት ሲጓዙ ታግተው የነበሩ ሌሎች ሁለት ወጣቶች ገንዘብ ከፍለው መለቀቃቸውን የቅማንት ዴሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ሳለአምላክ አረጋግጠዋል፡፡

ቀሪ 28 ያህል ታጋቾች ግን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 17/2016 ዓ ም ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ ወደቤታቸው እንዳልተመለሱ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለፁት፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ አጋቾቹ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የሚሰሩ የትኛውንም ማህበረሰብ የማይወክሉ ናቸው፡፡

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW