1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሞሮኮ ምዕራብ ሰሐራን ለመቆጣጠር ለረዥም ዓመታት የተከተለችው ስልት እየሰራ ነው

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 18 2016

ሞሮኮ በምዕራብ ሰሐራ ግዛት ላይ የምታነሳውን የይገባኛል ጥያቄ በመደገፍ ፈረንሳይ ለንጉሥ መሐመድ 5ኛ መንግሥት ከፍ ያለ ውለታ ውላለች። በምላሹ ፈረንሳይ ወደ አውሮፓ መጓዝ የሚፈልጉ ስደተኞችን ሞሮኮ እንድትቆጣጠር ትሻለች። የፈረንሳይ የአቋም ለውጥ ለሰሐራ ሰዎች የነጻነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በሞሮኮ እና አልጄሪያ ውዝግብ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል

የፖሊሳሪዮ ግንባር
ሞሮኮ የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳበት የምዕራብ ሰሐራ ግዛት ሰዎች ለነጻነት በሚታገለው እና በአልጄሪያ በሚደገፈው የፖሊሳሪዮ ግንባር ይወከላሉ። ምስል Guidoum Fateh/AP/picture alliance

ሞሮኮ ምዕራብ ሰሐራን ለመቆጣጠር ለረዥም ዓመታት የተከተለችው ስልት እየሰራ ነው

This browser does not support the audio element.

ለሞሮኮው ንጉሥ መሐመድ አምስተኛ ዓመት ይኸ በጋ ወቅት በታሪክ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ሊሆን ይችል ይሆናል። ለአምስት አስርት ዓመታት ከሞሮኮ በስተደቡብ የምትገኘው የምዕራብ ሰሐራ ግዛት አሁን ሊያበቃ የሚችል የግጭት ማዕከል ሆና ቆይታለች።

በፎስፌት የበለጸገው እና ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኘው ግዛት 160,000 ገደማ የሳሐራዊ ሰዎች መኖሪያ ነው። ከግዛቲቱ ስፔን በጎርጎሪዮሱ 1975 ለቃ ከወጣች ወዲህ የሀገሬው ሰዎች ሉዓላዊ ሀገር ለመመስረት ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የሳሐራዊ ሰዎች በአልጄሪያ በሚደገፈው ፖሊሳሪዮ ግምባር ይወከላሉ። የራባት መንግሥት ግን ግዛቲቱ የሞሮኮ አካል ነች የሚል አቋም አለው።

በዚህ ምክንያት በተፈጠረ የረዥም ጊዜ ውዝግብ ሞሮኮ እና አልጄሪያ በተደጋጋሚ ተጋጭተዋል። ሁለቱ ሀገሮች ግንኙነታቸውን ከአራት ዓመታት ገደማ በፊት አቋርጠዋል። አልጄሪያ የፖሊሳሪዮ ግንባርን ትደግፍ እንጂ ግዛቲቱን የመቆጣጠር ፍላጎት የላትም።

በአውሮጳ ደጃፍ በሞሮኮዋ ናዶር የሚገኙ ስደተኞች ይዞታ

ባለፉት ዓመታት ሞሮኮ በግዛቲቱ ላይ የምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ ድጋፍ እያገኘ ሔዷል። በአሁኑ በጋ ደግሞ ፈረንሳይ በጉዳዩ ላይ ስትከተል የቆየችውን ዲፕሎማሲያዊ አቋም ቀይራለች።

የ61 ዓመቱ ንጉሥ መሐመድ 5ኛ ሥልጣን የያዙበት 25ኛ ዓመት ሲከበር ከፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ የተቀበሉት “የእንኳን ደስ ያለዎ” ደብዳቤ ሞሮኮ ለምዕራብ ሰሐራ ግዛት ያላትን ዕቅድ ፈረንሳይ እንደምትደግፍ አብስሯቸዋል።

የ61 ዓመቱ ንጉሥ መሐመድ 5ኛ ሥልጣን የያዙበት 25ኛ ዓመት ሲከበር ከፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ የተቀበሉት “የእንኳን ደስ ያለዎ” ደብዳቤ ሞሮኮ ለምዕራብ ሰሐራ ግዛት ያላትን ዕቅድ ፈረንሳይ እንደምትደግፍ አብስሯቸዋል።ምስል Moroccan Royal Palace/AFP

የራባት መንግሥት በጎርጎሪዮሱ 2007 ያቀረበው ምክረ-ሐሳብ በግዛቲቱ ራስ ገዝ የፖለቲካ ተቋማት ማቋቋም፣ በአትላንቲክ ውያኖስ ዳርቻ ወደብ መገንባትን ጨምሮ ኤኮኖሚያዊ ዕድገትን ማፋጠንን የሚያካትት ነው። ነገር ግን ሞሮኮ የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያ እና የመገበያያ ገንዘብን ትቆጣጠራለች።

መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የአትላንቲክ ካውንስል ተመራማሪ ሳራሕ ዛይሚ “ፈረንሳይ እና ስፔን የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች በመሆናቸው የምዕራብ ሰሐራን ግጭት ሊፈታ የሚችል እጅግ በጣም ትዕምርታዊ የሆነ ውሳኔ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

በአሜሪካ የሰላም ኢንስቲትዩት የሰሜን አፍሪካ መርሐ-ግብር ዳይሬክተር ቶማስ ሒል በዚህ ወር በጻፉት የግል አስተያየት የምዕራብ ሰሐራ ግጭት “አበቃ” ብለዋል። ሒል የሰሐራዊ ሰዎች የነጻነት እንቅስቃሴ ያለው አማራጭ በሞሮኮ ሥር የምዕራብ ሰሐራዊ ግዛት የሚኖራትን አንዳች ሉዓላዊ አስተዳደር መቀበል ብቻ ነው የሚል አቋም አላቸው። 

የፈረንሳይ “የእንካ ለእንካ ፖለቲካ”

ምዕራብ ሰሐራዊ የሞሮኮ ግዛት ናት የሚል ዕውቅና በመስጠት ፈረንሳይ ብቸኛዋ ሀገር አይደለችም። ስፔን ከሁለት ዓመታት በፊት ቀደም ብላ ተመሣሣይ እርምጃ ወስዳለች። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ ሳሉ ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ስትጀምር አሜሪካ በልዋጩ የራባትን ንጉሣዊ መንግሥት የሚያረካ አቋም ወስዳለች።

የመካከለኛው ምሥራቅ፣ በርካታ የአፍሪካ እና የላቲን አሜሪካ ሀገራትም ምዕራብ ሰሐራ የሞሮኮ አካል ናት ብለው እውቅና ሰጥተዋል። የዛኑ ያክል ግን በርካታ ሀገራት የፖሊሳሪዮ ግንባር እና የሳሐራዊ ሰዎች ለነጻነት ለሚያደርጉት ትግል ድጋፍ ይሰጣሉ። ይሁንና ይኸኛው ድጋፍ እየተቀዛቀዘ ነው።

የምዕራብ ሰሐራ ግዛት ጉዳይ ለረዥም ዓመታት በሞሮኮ እና በአልጄሪያ መካከል ብርቱ መቃቃር ፈጥሮ የዘለቀ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ለሞሮኮም ሆነ ለፖሊሳሪዮ ግንባር አቋሞች እውቅና አይሰጥም። ድርጅቱ የሳሐራዊ ሰዎችን እጣ-ፈንታ ለመወሰን በተባበሩት መንግሥታት የሚመራ ሕዝበ-ውሳኔ እንዲካሔድ ይደግፋል። ስፔን እና ፈረንሳይ አቋማቸውን ቢቀይሩም በርካታ የአውሮፓ ሀገራትም ጉዳዩ በሕዝበ-ውሳኔ እንዲቋጭ ይሻሉ።

መቀመጫውን በለንደን ያደረገው አዙር ስትራቴጂ የጂዖ ፖለቲካ እና ደሕንነት ጉዳዮች ዳይሬክተር አሊስ ጋወር “የማክሮ እርምጃ ያለምንም ጥርጣሬ የእንካ ለእንካ ፖለቲካ አካል ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምዕራብ ሰሐራ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚፈልጉ ስደተኞች ዋንኛ መነሻ መሆን በመጀመሯ ንጉሥ መሐመድ 5ኛ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ፈረንሳይ ትሻለች።

ከሊቢያ የሚመለሱት አፍሪቃውያን ስደተኞች

ከዚህ በተጨማሪ ፈረንሳይ በጦርነት የተዘፈቁት ሊቢያ እና ሱዳን በሚገኙበት የሳሕል ቀጠና የኃይል ክፍተት እንዲፈጠር አትሻም። “የሞሮኮን ንጉሣዊ መንግሥት ተቀባይነት ከፍ ለማድረግ ፍላጎትም አለ። ሩሲያ እና ኢራን በጎረቤት አልጄሪያ ያላቸው ተጽዕኖ በማደጉ እና በሳሕል ቀጠና በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የሞሮኮ መንግሥት የተቀባይነት ቀውስ ውስጥ ተዘፍቋል” ሲሉ ጋወር ተናግረዋል።

የአልጄሪያ ፖለቲካዊ ጫና

የፈረንሳይ ውሳኔ ግን አልጄሪያን ምዕራባውያኑ ወደ ማይሹት የሩሲያ እና ኢራን ጥምረት የበለጠ ሊገፋ እንደሚችል የአትላንቲክ ካውንስል ባልደረባ የሆኑት ዛይሚ ይሰጋሉ። “ከቀዝቃዛው ጦርነት ድንበሮች ጀርባ የተደረገው የአሰላለፍ ለውጥ በመስከረም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚጠብቀው የአልጄሪያ መንግሥት የአጸፋ እርምጃ እንዲወስድ አስገድዶ ቀጠናውን ሊያተራምስ ይችላል” የሚሉት ሳራሕ ዛይሚ “አልጄሪያን ወደ ሩሲያ እና ኢራን ጥምረት እቅፍ ሊገፋ፤ ወደ አውሮፓ የሚፈሰው ጋዝ ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ላለፉት 50 ዓመታት በአልጄሪያ መጠለያ ካምፖች የሚኖሩ 173,600 የሰሐራዊ ስደተኞች ራስ ገዝ ግዛት መመሥረት እንደ አንድ አማራጭ ያስባሉ።ምስል Noe Falk Nielsen/NurPhoto/picture alliance

አልጄሪያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ዘይነ ላብዲን ጊቡሊ የፖሊሳሪዮ “የፖሊሳሪዮ ግንባር አማራጮች እየተወሰኑ በመሔዳቸው የማይመጣ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ወታደራዊ ዘመቻውን ማጠናከር ተገቢ እና የበለጠ ጠቃሚ ነው ብሎ የሚወስንበት ወቅት ላይ መድረሳችን በጣም ግልጽ ነው” የሚል አቋም አላቸው።

ቁጣ የቀሰቀሰው በሜሊላ የአፍሪቃውያን ስደተኞች ሞት

ይሁንና ሰሐራዊ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው “የፖሊሳሪዮ ግንባር በሞሮኮ በኃይል የተያዘው የምዕራብ ሰሐራን ሁኔታ መፍታት የሳሐራዊ ሰዎችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚያረጋግጡ የዓለም አቀፍ ሕጋዊ ውሳኔዎች ጥብቅ ትግበራ እንደሚፈልግ አረጋግጧል።”  

ላለፉት 50 ዓመታት በአልጄሪያ መጠለያ ካምፖች የሚኖሩ 173,600 የሰሐራዊ ስደተኞች ራስ ገዝ ግዛት መመሥረት እንደ አንድ አማራጭ ያስባሉ። አልጄሪያ በበኩሏ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዋን አጠናክራለች። በፓሪስ የነበሩት የአልጄሪያ አምባሳደር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የታዘዙ ሲሆን ፈረንሳይ በግዳጅ እየጠረነፈች የምትመልሳቸውን አልጄሪያውያን ስደተኞችም አልቀበልም ብላለች።

አልጄሪያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ዘይነ ላብዲን እንደሚሉት ይኸ ፈረንሳይ ሞሮኮን በመደገፏ የተሰጠ የአጸፋ እርምጃ ነው። “የምዕራብ ሰሐራ ሁኔታ ከአልጄሪያ ባለሥልጣናት የብሔራዊ ደሕንነት ብያኔ፣ የድንበሮች፣ የጂዖፖለቲካ ሁኔታዎች እና የፖሊሳሪዮ ትግል ተቀጥላ ነው”  ሲሉ አስረድተዋል።

ጀኒፈር ሖሌይስ/እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW