"ሞት፣ ዕዳ እና ዕድል — የኮሮና ጫና በአፍሪካ"
ረቡዕ፣ ሐምሌ 8 2012
በሚቀጥሉት አምስት ወራት ብቻ የአፍሪካ መንግሥታት በኮሮና ወረርሽኝ ጫና እና በነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ምክንያት ከገቢያቸው 45 ቢሊዮን ዶላር ሊያጡ እንደሚችሉ ሦስት ተቋማት ይፋ ያደረጉት አንድ ጥናት ይጠቁማል። የጸጥታ ጥናት ተቋም፣ ጎርደን ቢዝነስ ኢንስቲትዩት እና የፍሬድሪክ ኤስ ፓርደ የጥናት ማዕከል ይፋ ያደረጉት ይኸው ጥናት የአፍሪካ አገሮች የዕዳ ክፍያ እና ወለድ በመገበያያ ገንዘባቸው የመግዛት አቅም መዳከም ሳቢያ በየአመቱ ወደ 40 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መጨመሩን ጠቁሟል።
ምንም እንኳ የአፍሪካ ኤኮኖሚ በሚቀጥሉት ሁለት አስርት አመታት በ130 በመቶ ያድጋል ተብሎ ቢተነበይም ጥናቱ እንደሚያሳየው አህጉሪቱ ከተጠበቀው አኳያ ወደ ኋላ ቀርታለች። ከጎርጎሮሳዊው 2020 እስከ 2040 ባሉት አመታት የአፍሪካ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት በ4.3 በመቶ ብቻ እንደሚገታ ጥናቱ ያሳያል።
የኮሮና ወረርሽኝ 12 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ወደ ከፋ ድህነት ይገፋል። በዚህም በጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም. 26 ሚሊዮን አፍሪካውያን ከድሕነት ወለል በታች ይወድቃሉ። በጥናቱ መሠረት ከአስር አመታት በኋላ በከፋ ድሕነት ውስጥ የሚኖሩ አፍሪካውያን ቁጥር 570 ሚሊዮን ይደርሳል። ኮሮና ግን ይኸን ቁጥር ወደ 631 ሚሊዮን እንዲያሻቅብ ሊገፋው ይችላል።
ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ሲደናቀፍ
የጸጥታ ጥናት ተቋም መሥራች እና የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃኪ ሲልየርስ "የኮሮና ወረርሽኝ በአፍሪካ ከባድ ተፅዕኖ ያሳድራል። በአጭር ጊዜ የሚያስከትለውን የጤና ቀውስ እና የዜጎች ሞት ለመቋቋም ስንታገል የአፍሪካ ኤኮኖሚ ለፈጣን ዕድገት መዋቅራዊ ማሻሻያ የማድረግን አስፈላጊነት ያጎላዋል። በመጨረሻ ከኮሮና ለማገገም የሚያስችለን ብቸኛ መንገድ ይኸ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በሶስት ተቋማት የተጠናቀረውን ጥናት በገንዘብ የደገፈው የጀርመኑ ሐን ዚድል ፋውንዴሽን ሊቀ መንበር እና የአውሮፓ ምክር ቤት አባል የሆኑት ማርኩስ ፌርበር "የኮሮና ወረርሽኝ በአፍሪካ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2030 የሚያሳድረውን የጤና እና የኤኮኖሚ አጠቃላይ ተፅዕኖ የሚተነብየው የመጀመሪያ ጥናት ይፋ የሆነው እጅግ ጠቃሚ በሆነ ወቅት ነው" ሲሉ ፋይዳውን አስረድተዋል። "አፍሪካ በወረርሽኙ የከፋ ጫና ይደርስባታል። ይሁንና የዛኑ ያክል ቀውሱ ለዘላቂ ኤኮኖሚያዊ ሽግግር ዕድል ይሰጣል" ይላሉ ፌርበር።
"ሞት፣ ዕዳ እና ዕድል — የኮሮና ጫና በአፍሪካ" የሚል ርዕስ የተሰጠው ይኸው ጥናት አበዳሪዎች እና ባለወረቶች አኅጉሪቱ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ በፍጥነት እንድታገግም የዕዳ ክፍያ ፋታ እንዲሰጡ አሊያም ጭርሱን የአፍሪካን ብድር እንዲሰርዙ ጠይቋል። በዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ምዘና መካከለኛ የዕዳ ጫና ካለባቸው አገራት ተርታ ትመደብ የነበረችው ኢትዮጵያ ከነበረችበት ያሽቆለቆለችው ከሁለት አመታት ገደማ በፊት ነው። በወቅቱ ድርጅቱ ኢትዮጵያን "የከፋ የዕዳ ጫና ሥጋት" ካለባቸው አገራት ጎራ ቀላቅሏታል። ከሰሐራ በረሐ በታች የሚገኙ አገራትን የዕዳ አስተዳድር እና የምጣኔ ሐብት ይዞታ የፈተሸው የዓለም የገንዘብ ድርጅት የቀጠናው መንግሥታት ለሚሰሯቸው ሥራዎች ብድር ማብዛታቸው ለዕዳ ጫና ዳርጓቸዋል ብሏል።
በዓለም የገንዘብ ድርጅት የአፍሪቃ ቢሮ ዳይሬክተር አበበ አዕምሮ ሥላሴ ባለፈው ወር በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ኮሮና ካሳደረው ጫና ባሻገር የዕዳ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል። ቀድሞም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የዕዳ ጫና ውስጥ ወድቀው እንደነበር የገለጹት አበበ ይኸ ሊባባስ እንደሚችል ተናግረዋል።
አበበ አዕምሮ ሥላሴ "ከኮሮና ቀውስ በፊት በበርካታ አገራት ከስምንት እስከ አስር ባሉ አመታት የተጠራቀመ ዕዳ ጫና አሳድሮ ነበር። በወቅቱ በርካታ አገራት ተጨማሪ ገንዘብ መበደር ወደ ማይችሉበት ደረጃ ተቃርበዋል። በአጭር ጊዜ የሚበደሩትን በመቀነሳቸው እንዲሁም በጀታቸውንም ለማጠናከር በመሞከራቸው የበርካታ አገራት ዕዳ ከአጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠናቸው አኳያ ያለው ምጣኔ እየቀነሰ ይሔዳል የሚል ዕሳቤ ነበር። በዚህ ቀውስ የአገራት ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴ ጫና ውስጥ በመውደቁ ሳቢያ ከሰሐራ በረሐ በታች ለሚገኙ በርካታ የአፍሪካ አገራት ዕዳቸው ከአጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠናቸው አኳያ ያለው ምጣኔ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። ስለዚህ በቀጠናው የኮሮና ወረርሽኝ ከመቀስቀሱ በፊትም ከነበሩት አኳያ በርካታ አገሮች የዕዳ ጫና ውስጥ ይወድቃሉ" ሲሉ አብራርተዋል።
የኮሮና ጡጫ
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት ዜጎች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ እንደ ምግብ የመሰሉ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው የዋጋ ግሽበት ገጥሟቸዋል። ይኸ በተለይ ቀድሞም ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ለነበረ ዜጎች ችግራቸውን የበለጠ የከፋ ያደርገዋል። ለዚህ ሻይ፣ ዳቦ እና በሶ በአዲስ አበባ ጎዳና እየሸጡ ኑሯቸውን የሚገፉት ወይዘሮ ሐድራ በድሩ ኹነኛ ምሳሌ ናቸው። የኮሮና ወረርሽኝ ኢትዮጵያ በገባ በጥቂት ቀናት ልዩነት የመሠረታዊ ግብዓቶች ዋጋ መናሩን የእርሳቸውም ሆነ የደንበኞቻቸው ኑሮ መቀዛቀኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ሐድራ ኑሮ ፈታኝ ከሆነባቸው ኢትዮጵያውያን አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ሐድራ በድሩ ለዶይቼ ቬለ "ሻይ፣ ቡና፣ ብስኩት እና በሶ እያዘጋጀሁ ነበር የምሸጠው። ይሁንና አሁን እህሉ ተወደደ። አንድ ኪሎ አርባ ብር ገባ። ሰውም ብር ስለሌለው እኔም ተውኩት። ሥራ የለም። የልጆቼም አባት ከእኔ ጋር ነው ያለው። የውጪውንም የቤቱንም ወጪ የምሸፍነው እኔው ነኝ" ሲሉ ፈተናቸውን አስረድተዋል።
የኮሮና ሥርጭትን ለመከላከል ገቢራዊ የተደረጉ ክልከላዎች እንዲህ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ዜጎች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። በዩጋንዳዋ ካምፓላ የምትኖረው የሶስት ልጆች እናት ሜሪ ናንዮንጋ "እርዳታ ያስፈልገናል። ምግብ ተወዷል። ድሆች የሚበላ የሚያገኙት ከወዴት ነው?" ስትል የገጠማትን ፈተና ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።
የናንዮንጋ ባለቤት ለሶስት ልጆቹ የዕለት ጉርስ ማቅረብ ተስኖት ጥሎ ጠፍቷል። ልጆቿን ለመመገብ የሙዝ ልጣጭ ስትቀቅል የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ድረ ገፆች ከታየ በኋላ ናንዮንጋ መነጋገሪያ ሆና ነበር። ናንዮንጋ እንደምትለው ከመንግሥት ዕርዳታ ብትጠብቅም ጠብ ያለ ነገር የለም። እናም ልጇቿን የሙዝ ልጣጭ ቀቅሎ ለመመገብ ተገዳለች። እንዲህ አይነቱ የኮሮና ዳፋ በተለይ በኢመደበኛው የኤኮኖሚ ዘርፍ የለት እንጀራቸውን የሚያበስሉ አፍሪካውን ላይ በርትቷል።
"ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ኤኮኖሚ 2020 ዓ.ም. በ3.2 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ሚያዝያ ይቀንሳል ብለን ካሰብንው ይኸ እጥፍ ነው። ካሁን ቀደም ከታየውም የከፋው ነው። የኮሮና ቀውስ ከመከሰቱ በፊት የአኅጉሪቱ ኤኮኖሚያ ያድጋል ብለን ከተነበይንው ሰባት በመቶ ለውጥ ማለት ነው። በተጨባጭ ይኸ ቀውስ እጅግ ተጋላጭ የሆኑ ቤተሰቦች የለት ተለት አኗኗር ላይ የከፋ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ አጠቃላይ አመታዊ ገቢንም ከአመታት በፊት ወደ ነበረበት ወደ ኋላ ይመልሳል" ብለዋል አበበ አዕምሮ ሥላሴ።
የጸጥታ ጥናት ተቋም መሥራች እና የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃኪ ሲልየርስ የአፍሪካ መንግሥታት የኮሮና ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ተገቢ ያሉትን እርምጃ ቢወስዱም ኤኮኖሚያዊው ዳፋ የከፋ እንደሆነ አልጠፋቸውም። "የአፍሪካ መሪዎች መጀመሪያ በቻይና ከዚያ ቀጥሎ በአውሮፓ የተወሰዱ ውሳኔዎችን በምሳሌነት በመከተል ወረርሽኙ የሚስፋፋበትን ፍጥነት ለመግታት የሚያስችል እርምጃ ወስደዋል። አሁን ትልቁ ፈተና ለውሳኔው ኤኮኖሚያዊ ጣጣ መፍትሔ ማበጀቱ ነው። ምክንያቱም በአፍሪካ መቋጫ ለሌው ጊዜ እንቅስቃሴ በመግታት መቆየት አይቻልም" ሲሉ ገልጸዋል።
በዓለም የገንዘብ ድርጅት የአፍሪቃ ቢሮ ዳይሬክተር አበበ አዕምሮ ሥላሴ በዚህ ይስማማሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት ወረርሽኙ ካስከተለው ቀውስ ኤኮኖሚያቸውን ለመታደግ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ያስታወሱት አበበ ይሁንና አሁንም የጎደለ እንዳለ አልዘነጉም።
"አገራት ኤኮኖሚያቸውን ለመደገፍ በፍጥነት እርምጃ ወስደዋል። ይሁንና እነዚህ እርምጃዎች በገቢ መቀነስ እና በበጀት ውስንነት ምክንያት በቂ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የኮሮና ቀውስ ከመቀስቀሱ በፊት ያደገው የአገሮች የዕዳ ጫና አገሮች ለቀውሱ መፍትሔ ለማበጀት የሚያደርጉትን ጥረት አደናቅፏል። እስካሁን ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት ከአጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠናቸው ሶስት በመቶ የሚሆን ከኮሮና በተያያዘ ለሚያስፈልጋቸው በጀት አዘጋጅተዋል። ይኸ አስደናቂ እና እጅግ የሚያስፈልግ ጥረት ነው። ነገር ግን በሌሎች ቅድሚያ በሚሰጧቸው የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ሥራዎች ላይ ጫና አሳድሯል" ሲሉ ጫናውን ገልጸዋል።
"አብዛኞቹ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት እጅጉን ዕገዛ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎቻቸው እርዳታ ማቅረብ አልቻሉም። አብዛኛ ዜጎቻቸው ወረርሽኙን ለመከላከል ተግባራዊ የተደረጉ ገደቦች የከፋ ተፅዕኖ ባሳደሩባቸው እና በኢመደበኛው የኤኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ በሚገኙ የሥራ ዕድሎች የተሰማሩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ለመርዳት የሚያስችሉ የሴፍቲ ኔት መርሐ ግብሮች የሉም። በዚህ ምክንያት በበርካታ አገራት የድሕነት መጠን በዚህ አመት መጨመሩ የተረጋገጠ ነው። የዓለም ባንክ ለምሳሌ በዚህ አመት የድሆች ቁጥር በ20 ሚሊዮን እንደሚጨምር ያስቀመጠው ትንበያ አለ" ብለዋል።
መንግሥታት ያላቸውን ጥሪት ኮሮናን መቋቋም ወደሚያስችሏቸው እርምጃዎች ሲያዞሩ የአፍሪካ የጤና አገልግሎት የበለጠ ተዳክሞ ሌሎች አደገኛ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ሊያሽመደምድ ይችላል። ይኸ ጥናት ወባ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ ሳምባ ነቀርሳ እና የእናቶች ሞት በላይቤሪያ፣ ሴራ ሊዮን እና ጊኒ የኢቦላ ወረርሽኝ በተቀሰቀሰበት በጎርጎሮሳዊው 2014 እና 2016 በርትቶ እንደነበር አስታውሷል። በተመሳሳይ መንግሥታት ጥሪታቸውን ኮሮናን ለመከላከል ወደሚያስችሏቸው የሥራ ዘርፎች ካዞሩ በኤችአይቪ፣ ሳምባ ነቀርሳ እና በወባ በሚቀጥሉት አምስት አመታት የሚሞቱ አፍሪካውያን ቁጥር እስከ 36 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ይኸ ጥናት አስጠንቅቋል።
የተስፋ ጭላንጭል
የጸጥታ ጥናት ተቋም፣ ጎርደን ቢዝነስ ኢንስቲትዩት እና የፍሬድሪክ ኤስ ፓርደ የጥናት ማዕከል ይፋ ያደረጉት እና በ55 ገፆች የተቀነበበው ሰነድ የአፍሪካ መንግሥታት ለኮሮና ወረርሽኝ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ከመፈለግ ባሻገር የረዥም ጊዜ መላ ካበጁ ከኮሮና ቀውስም በኋላ ተስፋ እንዳለ አሳይቷል። ለዚህም አንገብጋቢ የመሠረተ ልማቶች ግንባታ እና የጤና አገልግሎትን ማጠናከር ይገኙበታል። አፍሪካ ከተቀረው ዓለም እጅግ ኋላ የቀረችበትን ኤኮኖሚ ለማሻሻል ከመሪዎቿ እና መንግሥታቱ ከሚከተሉት ፖሊሲ ኹነኛ አመራር እንደምትሻ ጃኪ ሲልየርስ አስገንዝበዋል።
ጃኪ ሲልየርስ የጸጥታ ጥናት ተቋም መሥራች እና የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ "ምክንያቱም የወደፊቱን ካየን በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም መካከለኛ ገቢ ልዩነት እየሰፋ መሔዱን ቀጥሏል። ኮሮና ባይኖርም በአፍሪካ ነገሮች መሻሻል አሳይተዋል። ነገር ግን በሚፈለገው መጠን ፈጣን አይደለም። ስለዚህ ይኸን ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል። ዕድሉ ደግሞ ተገቢ በሆነ አመራር እና ፖሊሲ ላይ ይመሰረታል። የኮሮና ወረርሽኝ የዚህን ሽግግር አስፈላጊነት እንድንገነዘብ አድርጓል" ብለዋል።
"ሞት፣ ዕዳ እና ዕድል — የኮሮና ጫና በአፍሪካ" የሚል ርዕስ የተሰጠው ሰነድም ይሁን ጥናቱን ያከናወኑ ባለሙያዎች ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት ወደ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ሊያደርጉ ለሚችሉት ሽግግር የኮሮና ወረርሽኝ ኹነኛ ዕድል ፈጥሯል ባይ ናቸው። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ይኸ ዓለም አቀፍ ቀውስ ዲጂታላይዜሽን እንዲሁም የዲጂታል ኤኮኖሚ ተግባራዊ የማድረግን አስፈላጊነት አሳይቷል። ጃኪ ሲልየርስ "አፍሪካ ቀድሞም ይኸን ጉዞ ለመጀመር እርምጃ ጀምራ ነበር። አሁን ከሚገኝበት ከዝቅተኛው ደረጃ ጀምረን በፍጥነት ልናሳድገው እንችላለን። በምሥራቅ አፍሪካ ፈጣን መሻሻሎች አይተናል። ነገር ግን እጅግ ማሳደግ ይኖርብናል " ብለዋል።
አቡባከር ጃሎ/እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ