1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 23 2009

ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ተጨዋቾች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማሊ አቻው ተሸንፎ ከማጣሪያው ውጪ ሆኗል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች መሪው ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ ጥሏል።  ማንቸስተር ዩናይትድ ነጥብ ሲጋራ፤ አርሰናል አሸንፏል።

Schottland Glasgow - Mike Towell im Boxkampf gegen Danny Little
ምስል Getty Images/M. Runnacles

ስፖርት 03.10.2016

This browser does not support the audio element.

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዘንድሮ ኮሎኝ  ከአጀማመሩ ድል እየቀናው ነው። ከኃያሉ ባየር ሙይንሽን እና ከዋነኛ ተፎካካሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በስፔን ላሊጋ ዋነኞቹ ቡድኖች ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ተጨማሪ ዘገባ ይኖረናል። 

ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ተጨዋቾች ከሚሳተፉበት የአፍሪቃ የእግር ኳስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡድን ተሰናብቷል።  በሚቀጥለው ዓመት ማዳጋስካር ውስጥ ለሚኪያሄደው ጨዋታ የሦስተኛ ዙር ማጣሪያውን ትናንት ከማሊ ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ቡድን የተሸነፈው 2 ለ1 ነው። የኢትዮጵያ ቡድን ቀደም ሲል ከሜዳው ውጪ 2 ለ0 መሸነፉ ይታወሳል። 4 ለ1 በሆነ አጠቃላይ ውጤት የማሊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል። 

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ትናንት ቶትንሐም ሆትስፐር በድንቅ የጨዋታ ስልት በደረጃ ሠንጠረዡ መሪ የሆነው ማንቸስተር ሲቲን 2 ለ0 አሸንፏል። በእርግጥም በጨዋታው ቶትንሐሞች ልቀው ተገኝተዋል። ቶትንሐም የትናንቱን ጨዋታ ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ከሩስያ ረዥም ጉዞ መልስ ያከናወነው ጨዋታ በመሆኑ ደግሞ የቡድኑ ጥንካሬ እና ጽናት ታይቶበታል። ቶትንሐም ባለፈው ማክሰኞ ከሩስያው ሲ ኤስ ኬ ኤ ጋር ባደረገው ጨዋታ 1 ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፎ መምጣቱ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ቶትንሐም በሻምፒዮንስ ሊጉም ሆነ በፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል።  

ምስል Getty Images/A. Livesey

ቀደም ሲል በደረጃ ሰንጠረዡ የሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው ሊቨርፑል ከትናንት በስትያ ስዋንሲ ሲቲን 2 ለ1 ማሸነፍ ችሏል። ሆኖም ደረጃውን ትናንት በርንሌይን 1 ለምንም ለረታው አርሰናል አስረክቦ ወደ አራተኛነት ዝቅ ብሏል። በ7 ጨዋታዎች 16 ነጥብ ከሰበሰበው አርሰናል ጋር የሊቨርፑል የአንድ ግብ ልዩነት ብቻ ነው ያለው። 

በ4 ነጥብ ብቻ ተወስኖ ከታች 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ስዋንሲ ሲቲ በሜዳው በመሸነፉ አሰልጣኝ ፍራንሴስኮ ጉዊዶሊን ከቡድኑ መሰናበታቸው ዛሬ ተገልጧል። በሳቸው ፈንታ ቡድኑ የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩትን ቦብ ብራድሌይን መተካቱን ይፋ አድርጓል።  በፕሬሚየር ሊጉ አስቶን ቪላም አሰልጣኙን አሰናብቷል።

አስቶን ቪላ ሮቤርቶ ዲ ማቴዎን ከሥራ ያሰናበተው የቡድኑ አጀማመር ደካማ በመሆኑ እንደሆነ አስታውቋል። ከአራት ዓመታት በፊት ከቸልሲ ጋር ሆነው የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ ያነሱት ጣሊያናዊ አሠልጣኝን አስቶን ቪላ «አጀማመራቸው የሚያበሳጭ» በማለት ነው ያሰናበተው። ማንቸስተ።ር ዩናይትድ ከስቶክ ሲቲ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ሌስተር እና ሳውዝሐምፕተን ያደረጉት ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል። ቅዳሜ ዕለት ቸልሲ ሁል ሲቲን 2 ለ0 አሸንፏል። 

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቮልፍስቡርግ ከማይንትስ ጋር ትናንት ያለምንም ግብ ተለያይቷል።  ሻልከ ቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅን በሰፊ ልዩነት 4 ለ0 አሸንፏል። የቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አጥቂ እጥቂ አንድሬ ሐኅን  ቡድኑ ከመጀመሪያው ይልቅ በሁለተኛው አጋማሽ አቋሙ ደኅና እንደነር ተናግሯል።  

«ጥሩ አልነበርንም። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልተጫወትንም።  በሁለተኛው አጋማሽ ብዙ ተበልጠን ጭራሽ የፍጹም ቅጣት ምት ተሰጠብን።  ከዚያ በኋላ ተጋጣሚያችን የበላይ ሆኖ ተዳክመናል። የመከላከል ስልታችን ጠፍቶ ግብ ተቆጥሮብናል»

ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Meissner

በእርግጥ  ሻልከ ያገኛት የፍጹም ቅጣት ምት ለቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኆዎች አጨቃጫቂ ነበረች። ኤሪክ ማክሲም ቾፖሞቲንግ ወደ ፍጽም ቅጣት ምት ክልል ከገባ በኋላ ከኋላ ተጠልፏል በሚል ነው ፍጹም ቅጣት ምቱ የተሰጠው። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ፍጹም ቅጣት ምቱ ተገቢ አይደለም ብሏል። ሆኖም 52ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘችዋን ፍጹም ቅጣት ምት ጥፋት የተሠራበት ተጨዋች ከመረብ አሳርፏታል።  ሁለተኛውን ግብ በ56ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው በ22,5 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ በዝውውር ወደ ቡድኑ የመጣው ብሬል ኤምቦሎ ነው። ግቧ ለብሬልበቡንደስ ሊጋ ታሪኩ የመጀመሪያው ሆና ተመዝግባለታለች። አንዳንዶች ለብሬል ኤምቦሎ የወጣው ወጪ ተገቢ አይደለም ሲሉ ሲተቹ ነበር። በ58ኛው ደቂቃ ሦስተኛዋን ግብ ያስቆጠረው ሊዮን ግሮቴስካ ነው። ስዊትዘርላንዳዊው አጥቂ  ብሬል ኤምቦሎ ተከላካዮችን እና ግብ ጠባቂውን በማለፍ ለራሱ ሁለተኛውን ለቡድኑ አራተኛውን ግብ በማስቆጠር ይቀርብበት የነበረውን ትችት ዋጋ አሳጥቶታል። 

ቮልፍስቡርግ ትናንት ከማይንትስ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ዘንድሮ ከቮልፍስቡርግ ጋር ለአምስት ጊዜያት ተሰልፎ አንድም ግብ ማስቆጠር አልቻለም። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ማሪዮ ጎሜዝ። ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ 29 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው የ31 ዓመቱ አጥቂ ለአዲሱ ቡድኑ እስካሁን አንድም ግብ ማስቆጠር አልቻለችም። በተለይ በትናንቱ ውጤት አጥቂው እጅግ ተበሳጭቷል። 

ምስል picture-alliance/dpa/R. Wittek

«ደጋፊዎቻችን ብቻ አይደሉም የተበሳጩት እኛም በሽቀናል። ዛሬ እንቅስቃሴያችን የሚደንቅ ነበር። ምን ማለት እችላለሁ? እጅግ ከፍተኛ በደል ነው፤ አደገኛ በደል፤ ኳሷ እኮ መስመሩን አላለፈችም ነበር። ዛሬ የምናሸንፈውን ጨዋታ ነው ከእጃችን የተነጠቅነው።»

በ7,8 ሚሊዮን ዩሮ ከጣሊያኑ ፊዮሬንቲና ቡድን ሐምሌ ወር ላይ ወደ ቮልፍስቡርግ የመጣው አጥቂ ቮልፍስቡርግ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ እንዲመለስ ምኞቱ እንደሆነ ገልጧል። 

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት ሪያል ማድሪድ ከአይበር ጋር ተጋጥሞ አንድ እኩል ወጥቷል። ሪያል ማድሪድ በተከታታይ ግጥሚያዎች ነጥብ ሲጋራ  የትናንቱ አራተኛ ጊዜው ነው። ባርሴሎና በሴልታቪጎ 4 ለ3 ተሸንፏል። ሁኔታው ለአትሌቲኮ ማድሪድ የተመቸ ሆኗል። በተመሳሳይ 15 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ አትሌቲኮ ማድሪድ ከሪያል ማድሪድ በልጦ አንደኛ መሆን ችሏል። በሴቪላ በአድ ነጥብ  የሚበለጠው ባርሴሎና 13 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ምስል picture alliance/AP Photo/J. Meyer

የመኪና ሽቅድምድ

በማሌዢያ ግራንድ ፕሪ መኪና ሽቅድምድም ትናንት የሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ዳንኤል ሪካርዶ አንደኛ ወጥቷል። ኒኮ ሮዝበርግ ማክስ ፈርሽታፐንን ተከትሎ በሦስተናነት አጠናቋል።  በአጠቃላይ ድምር ግን ኒኮ 288 ነጥብ ሰብስቦ ይመራል። በ265 አጠቃላይ ነጥብ የሚከተለው የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት በ16ኛው ዙር ላይ በሞተር ብልሽት  ውድድሩን ለማቋረጥ ተገዷል። 

የአፍሪቃ እግርኳስ ኮንፌደሬሽን

የአፍሪቃ እግርኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንቶች ሥልጣን እንዲገደብ ወስኗል። ድርጅቱ ዛሬ ካይሮ ግብፅ በተካሄደ ልዩ ጉባኤ ላይ እንዳስታወቀው እስከ ዛሬ ገደብ ያልነበረው የፕሬዝዳንቶች ሥልጣን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2017 ምርጫ በኋላ  በሦስት የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመኖች እንደሚገደብ አስታውቋል። ድርጅቱን ላለፉት 28 ዓመታት የመሩት የ70 ዓመቱ ካሜሩናዊው ኢሳ ሃያቱ ለሌላ የሥልጣን ዘመን ይወዳደሩ አይወዳደሩ ገና አልታወቀም ። ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የስፖርት አዋቂ አቶ ይደነቃቸው ተሰማ ኮንፈዴሬሽኑን ለ16 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት መርተው ነበር  ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW