1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጅጅጋ አምስት ሰዎች ተገለዋል፤ መከላከያ ገብቷል

ሰኞ፣ ሐምሌ 30 2010

በጅጅጋ የሶማሌ ልዩ ኃይል አባላት በተኮሱት ጥይት አምስት ሰዎች መገደላቸውን እማኞች ተናገሩ፤ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማዋ ገብቷል። ባንኮች፣ አብያተ-ክርስቲያናት እና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተዘርፈዋል። ከጅጅጋ እስከ ደገሐቡር የዘለቀውን ቀውስ "ሥልጣኔን ከምለቅ ሞት እመርጣለሁ" የሚል አቋም የወለደው መሆኑን መንግሥት ገልጿል

Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

በጅጅጋ ከተማ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች በተኮሱት ጥይት አምስት ሰዎች መገደላቸውን የአይን እማኞች ተናገሩ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ ጀምሮ ከተማዋን መቆጣጠሩንም ተናግረዋል። በጅጅጋ ከተማ በሚገኘው የሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ደጃፍ አራት ወጣቶች፤ ቀበሌ 06 ተብሎ በሚጠራው ክፍል አንድ ሌላ የ16 አመት ልጅ መገደላቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል። የአይን እማኙ የክልሉ ልዩ ኃይል ታጣቂዎች ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ "ፊት ለፊት ሰው" ላይ መተኮሳቸውን ተናግረዋል።  ሌላ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ የጅጅጋ ነዋሪ በዛሬው ዕለት ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሱ ጥይቶች የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውን እንደሰሙ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የጅጅጋ ነዋሪዎች እንደሚሉት ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማ ገብቶ በክልሉ ልዩ ኃይል ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን መቆጣጠር ጀምሯል። የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ወደ ከተማዋ ሲገቡ "ግጭት ነበር፤ ከተማዋ በተኩስ ተናውጣ ነበር" ሲሉ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል። የጅጅጋው ነዋሪ "ህዝቡ ከቤተ-ክርስቲያን ወጥቶ እየጨፈረ ነው። እልል እያለ ነው። እነሱ ሊገቡ ሲሉ ከ30 ደቂቃ በፊት እየወጡ ነበር" ሲሉ ስለ ከተማዋ ድባብ አስረድተዋል። 

ማምሻውን የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሕመድ ሽዴ ክልሉ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ወደ ክልሉ ገብቶ ሰላም እንዲያስከብር መታዘዙን ተናግረዋል። አቶ አሕመድ "የክልሉ ሕብረተሰብ የሚጠይቃቸው የሰብዓዊ መብት እና የዴሞክራሲ መብት ጥሰቶች እና በጣም ከፍተኛ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ የጸጥታ ችግሩን የማባባስ ስራ ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል" ሲሉ ተናግረዋል። ኃላፊው "የዜጎች የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይሻሻሉ፤ የፍቅር የአንድነት እና የመደመር አገራዊ ማሻሻያ በእኛም ክልል ተግባራዊ ይሁን ብለው በተንቀሳቀሱ የአገር ሽማግሌዎች እና የህዝብ ተወካዮች ላይ ከፍተኛ ወከባ እና ጉዳት ለማድረስ ሰፋፊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል" ብለዋል። አቶ አሕመድ በመግለጫቸው በክልሉ ታይተዋል ላሏቸው ችግሮች ተጠያቂ የሆኑ ባለሥልጣናትን በስም አልጠቀሱም። በጅጅጋ ተቀስቅሶ ደገሐቡር እና ቀብሪ ደሐርን ወደ መሳሰሉ ከተሞች የተስፋፋው ግጭት መነሾ"ሥልጣንን ልቀቅ ተብያለሁ በማለት ሥልጣኔን ከምለቅ ሞት እመርጣለሁ በማለት ሰፋፊ ቅስቀሳዎችን በክልሉ በማድረግ ክልሉ ወደ ግርግር የማድረግ ሥራ በጥቂት የአመራር ቡድን ሲካሔድ ቆይቷል። ያለ ክልሉ ነዋሪዎች ፈቃድ እና ይሁንታ ክልሉን አስገነጥላለሁ በማለት ከፍተኛ ውዥንብር እና ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ አስነዋሪ ተግባር ሲፈፀም ቆይቷል" ሲሉ አክለዋል።

የክልሉ ልዩ ኃይልመንገዶችን በመዝጋት ሕገ-መንግሥታዊ የሆነውን የዜጎች የመንቀሳቀስ ነፃነት በከፍተኛ ደረጃ መገደቡንም አቶ አሕመድ ጠቅሰዋል። ከጅጅጋ ወደ ሐረር እና ወደ ጅቡቲ የሚያመሩ መንገዶች ከተዘጉት መካከል እንደሚገኙበት አቶ አሕመድ በምሳሌነት አንስተዋል።  ንፁሐን ዜጎች መገደላቸውን፣ መዘረፋቸውን እና የአካል ጉዳት እንደ ደረሰባቸውም አቶ አሕመድ አስረድተዋል። ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ጅጅጋን ጨምሮ የክልሉን ከተሞች ባወከው አለመረጋጋት ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉ ግን አልተናገሩም። የማኅበራዊ አገልግሎት መሥጫ ተቋማት ፤ ባንኮችን ጨምሮ የገንዘብ እና የሐይማኖት ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን እና ዝርፊያ መፈፀሙን አክለዋል። አቶ አሕመድ ለድርጊቱ ተጠያቂዎቹ "ጥቂት የአመራር አባላት እና እነርሱ ያደራጇቸው የወጣቶች ቡድን" እንደሆኑ ገልጸዋል። ኃላፊው የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አብዲ መሐመድ ዑመርን አንድም ጊዜ አልጠቀሱም። 

ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን እና እሁድ ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በከተማዋ ከታየው ጥቃት፤ ዝርፊያ እና አለመረጋጋት ለመሸሽ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና አብያተ-ክርስቲያን ተሸሽገው የነበሩ ነዋሪዎች መውጣት መጀመራቸውን በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ የግብርና ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከትናንት በስቲያ በተቀሰቀሰው ኹከት እና አለመረጋጋት ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ፤ ድብደባ እና እንግልት ተፈጽሟል፤ አብያተ-ክርስቲያን ተቃጥለዋል፤ ሱቆች እና መኖሪያ ቤቶችም ተዘርፈዋል።

በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በክልሉ የሚገኙ ዜጎች ደኅንነት አስግቶናል ሲሉ ዛሬ አደባባይ ወጥተዋል። የሰልፉ ተሳታፊዎች ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ መከላከያ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አካባቢዎች አቅንተው ሥጋታቸውን ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ የክልሉ ተወላጆች እንዲሁም  "በሶማሌ ክልል የወገኖቼ መከራ ያሳስበኛል" ያሉ ተካፍለውበታል። ከተሳታፊዎች አንዷ የሆኑት የህግ ባለሙያዋ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ከበደ " ሰልፉ የተካሔደው በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ወገኖቻችን የሚሞቱበት፣ ቤት ንብረታቸው የሚዘረፍበት እና ሴቶች እና ሕፃናት እየተደፈሩ ያሉበትን ሁኔታ ለመንግሥት የድረሱላቸው ጥሪ ለማሰማት ነው። እሱም ውጤታማ ነበረ። በአሁን ሰዓት ወደ ከተማው መከላከያ ገብቶ እየተረጋጋ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW