«ሥራችንን እየሰራን ትግላችን በሰላማዊ መንገድ እንቀጥላለን» የጤና ባለሙያዎች
ሰኞ፣ ግንቦት 11 2017
የጤና ባለሙያዎች የመጨረሻ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻና የስራ ማቆም አድማ ማስጠንቀቂያኑሮው ከበደን ያሉ የጤና ባለሙያዎች የሚከፈለን ክፍያ ከስራችን እና አሁን በኢትዮጵያ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር የተጣጣመ አይደለም በሚል ከቀናት በፊት የጀመሩት ሰላማዊ ሰልፍ ስራ ወደማቆም ተሸጋግሮ የተለያዩ የጤና ተቋማት የጤና ባለሙያዎች ከስራ ገበታቸው ውጭ ሲሆኑ መንግስትም ወደ ስራቸው እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ከዛሬ ጀምሮም የጤና ባለሙያዎቹ ጥያቄ ስራ በማቆም ይቀጥላል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ደሴ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች የጤና ባለሙያዎቹ ወደ ስራ ቦታቸው ተመልሰው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የጤና ባለሙያዎቹም በስራ ገበታቸው ላይ የተገኙት ተገደው መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ እና ድምፃቸው እንዲቀየር የፈለጉ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
‹‹ኃላፊዎች መጥተው ማስፈራራት አድርገውብናል፤ ስራውን ማቋረጥ እንደሌለብን ከተቋረጠ እርምጃ እንደሚወስዱ ነገሩን ከዚያ በኋላ ስብሰባ አደረጉ፡፡ መቼም በእልክ የሚሆን ነገር የለም፡፡ የጉልበት ስራን በእልክ ልታሰራው ትችላለህ፤ እኛን ግን ተጭነውን ነው እኛ አምነንበት አይደለም ወደ ስራ የተመለስነው፡፡ ›› አንዳንዶቹ የጤና ባለሙያዎች ቀናትን በስር ቤት ማሳለፋቸውን ገልፀው የዞንና የክልል የጤና ቢሮ ኃላፊዎች ለሚፈጠረው የህክምና ችግር ተጠያቂ እንደሚያደርጉን በማስፈራራታቸው ወደ ስራ ልንመለስ ተገደናል ይላሉ፡፡
‹‹ማስፈራሪያና ዛቻ ነበረ ምክንያቱም ስራ ማቆም አይችልም አንድ የጤና ባለሙያ ጥያቄያችሁ ወደ ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ዙሯል፡፤ እናንተ አይደላችሁም የምትጠይቁት፣ የሚል ነበር፤ ሁለተኛ የሰው ህይወት በማጥፋት ወንጀል ትጠየቃላችሁ ብለውናል፡፡ ምክንያቱም ስራ ስታቆሙ የሞተ ሰው ነበረ፡፡ በዚህ የነብስ ማጥፋት ትከሰሳላችሁ፤ ነፍስ ያጠፋ ሰው ደግሞ በዋስ አይወጣም የሚልም ነበረበት፡፡›› የጤና ባለሙያዎች የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ
የጤና ባለሙያዎቹ እያነሳን ያለው ጥያቄ ሰላማዊ እና የተለየ ፍላጎት የማይታይበት የኑሮ ደረጃችንን መሰረት ያደረገ ነው ያሉ ሲሆን አሁን ላይ ግን በጤና ተቋማቶች አካባቢ የፀጥታ ሀይሎችን በማስፈር ጫና እየተደረገብን ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ከዞንም መጥተው ያነጋገሩን አጥጋቢ አይደለም ምላሻቸው፤ ምክንያቱም እኛ አደጋ ላይ ነው ያለነው ዘግተን እንወጣለን ብንል እዚህ መሄድ አንችልም፤ ሆስፒታሉና አድማ ብተና ጎን በጎን ነው ያሉት፡፡››
የአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች ሰብሳቢ አቶ ሻምበል ፋንታየ ለምናነሳው የደመወዝ ጥያቄ ስራችንን እየሰራን በሰላማዊ መንገድ ትግላችንን እንቀጥላለን ያሉ ሲሆን አሁን በእስር ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እንዲለቀቁ እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ስራን በማቆም ስራ የማቆምን አድማ በማድረግ እናቶች ወይም ሌሎች እየሞቱ ባለሙያው ጥቅም እንዲያገኝ የሚል አይነት መንገድ አይደለም፡፡ እየሰራን መስዋዕትነት እየከፈልን መንግስት በተገቢው ጥያቄያችንን ይፍታ የእኛ አቋም ይህ ነው፡፡ ችግሮችን በንግግር እንዲፈቱልን እንፈልጋለን በማሰርና በማሸማቀቅ አይደለም መልስ ማግኘት ያለብን›› የጤና ባለሙያዎች በስራ ቦታቸው በመገኘት ግልጋሎት መስጠት ጀምረዋል ያሉት አቶ ሻምበል ፈንታየ አሁን ጥያቄያችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ ጥረት እናደረጋለን ሲሉ ነው የተናገሩት፡- ‹‹ጥያቄው ይቀጥላል፡፡ አሁንም ጥያቄውን ይዘን እንቀጥላለን መልስ እስከምናገኝ ድረስ ሆኖም ግን ባሙያው አንዲረጋጋ አንድም ባለሙያ ጉዳት እንዲደርስበት አንፈልግም አንዳንድ የታሰሩ ባለሙያዎችም እንዲፈቱ ሰፊ ጥራት እያደረግን ነው፡፡››
ኢሳያስ ገላዉ
ሸዋዩ ለገሠ
አዜብ ታደሰ