1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥራና ደሞወዝ የተከለከሉት የትግራይ ፖሊሶች

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 25 2015

"ወደ ትግል አልተቀላቀላችሁም" በሚል ምክንያት ከስራ ውጭ ተደርገናል ሲሉ በትግራይ የሚገኙ የቀድሞ ፖሊሶች ተናገሩ። እስከ 30 ዓመት በመደበኛ ፖሊስነት ያገለገሉት ፖሊሶች፥ ቋሚ የመንግስት ሰራተኞች ብንሆንም በሕገወጥ መንገድ ተባረናል "ከስራ የታገድንበት ምክንያት ግልፅ አይደለም። ፍንጮች ግን ወደ ትግል አልተቀላቀላችሁም የሚል ነው" ብለዋል።

Äthiopien Tigray Region Polizeipräsidium
ምስል Million H.Silase/DW

"ወደ ትግል አልተቀላቀላችሁም" በሚል ምክንያት ከስራ ውጭ ተደርገናል

This browser does not support the audio element.

"ወደ ትግል አልተቀላቀላችሁም" በሚል ምክንያት ከስራ ውጭ ተደርገናል ሲሉ በትግራይ የሚገኙ የቀድሞ ፖሊሶች ተናገሩ። እስከ 30 ዓመት በመደበኛ ፖሊስነት ያገለገሉ እነዚህ የቀድሞ ፖሊሶች፥ ቋሚ የመንግስት ሰራተኞች ብንሆንም ከሕገወጥ መንገድ ተባረናል ሲሉ ቅሬታቸው ገልፀዋል።

እነዚህ እስከ 30 ዓመት ድረስ በተለያዩ የትግራይ አካባቢ ተመድበው በፖሊስነት ስራ ላይ ተሰማርተው የቆዩ የቀድሞ የትግራይ ፖሊስ አባላት፥ ከስራ እና ደመወዝ ውጭ እንዲሆኑ የተደረጉት ከጦርነቱ ጅማሮ በኃላ ባለው ግዜ መሆኑ ነግረውናል።  ላለፉት ከ30 በላይ ዓመታት በጉሎመኸዳ ወረዳ ዛላምበሳን ከተማ በመደበኛ ፖሊስነት ስራ ተሰማርተው ሕግ በማስከበር ተግባር ላይ መቆየታቸው የገለፁልን ኮማንደር ኪዳነማርያም ካሳ፥ ለዓመታት ከሰራንበት ሙያ አለአግባብ ታግደናል፣ ለምን ብንልም የሚሰማን ጠፍቷል ብለው ያማርራሉ።

"ከስራ የታገድንበት ምክንያት ግልፅ አይደለም። ፍንጮች ግን ወደ ትግል አልተቀላቀላችሁም የሚል ነው" የሚሉት የቀድሞ ፖሊስ ኮማንደር ኪዳነማርያም "ለአቤቱታ ወደሚመለከታቸው አቤት ብንልም የሚሰማን ጠፍቷል" ይላሉ።

ሌላው በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ቢሮ አቤቱታ ሊያቀርቡ ተገኝተው በፀጥታ ሐይሎች ወደ ውስጥ እንደይገቡ ታግደው ካገኘናቸው የቀድሞ ፖሊስ አባላት መካከል የሆነው ረዳት ኢንስፔክተር ፀጋይ ብርሃኑ፥ ለ13 ዓመታት በፖሊስነት ማገልገሉ ይናገራል። "አሁን ላይ ከስራ የታገድነው፥ ወደ ትግል አልተቀላቀላችሁም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ጦር በ2013 ዓ.ም ትግራይ ሲቆጣጠር ተቋቁሞ ከነበረው አስተዳደር ደሞዝ ተቀብላችኋል በሚሉ ምክንያቶች ነው" ይላል ረዳት ኢንስፔክተር ፀጋይ።

ከስራ መታገድ፣ ደሞዝ አለመሰጠት ብቻ ሳይሆን ስራው ለመልቀቅ ፈልገን ጭምር መልቀቅያ ስጡን ብንል የሚሰማን አጥተናል የሚሉት ደግሞ ሌላው በትግራይ ፖሊስ ኮምሽን ላለፉት 15 ዓመታት ያገለገሉት ቅሬታ አቅራቢ ረዳት ኢንስፔክተር ፍስሃየ ተስፋይ በበኩላቸው፣ በዚህ ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንዳለ ጠቁመዋል።

በቅሬታ አቅራቢዎቹ የቀድሞ ፖሊሶች ጉዳይ ዙርያ ከትግራይ ፖሊስ ኮምሽን ምላሽ ለማግኘት ዶቼቬሌ ለቀናት በተደጋጋሚ፥ በስልክና በአካል ሙከራ አድርጓል። በዛሬው ዕለት ያገኘናቸው የትግራይ ፖሊስ ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር ገብረስላሴ በላይ፣ ወደ ስብሰባ እየገቡ መሆኑ በማንሳት ለዝርዝር ጉዳዮች ቃለመጠይቅ መስጠት እንደማይችሉ የነገሩን ሲሆን፣ የቀድሞ ፖሊሶቹ ጉዳይ ግን "እየተመለከትነው ነው" የሚል አጭር የቃል ምላሽ ሰጥተውናል። በጦርነቱ መካከል ባለፈው 2014 ዓመተምህረት በህወሓት ይመራ የነበረው የክልሉ አስተዳደር መደበኛ ፖሊስ መበተኑ እና አዲስ የፖሊስ ሐይል አሰልጥኖ፣ አስመርቆ ወደ ስራ ማስገባቱ ሲገልፅ ነበር።

 

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW