1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥራ በፍቅር ህይወት ውስጥ እንዴት ያለ ሚና ይጫወታል?

ዓርብ፣ ሰኔ 10 2014

አብዛኞቹን ወጣቶች በለጋ ዕድሜያቸው ከሚያሳስቧቸው ጉዳዮች አንዱ ፍቅር ነው። ለመሆኑ የአንድ ሰው ሥራ በፍቅር ህይወት ውስጥ እንዴት ያለ ሚና ይጫወታል? በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት « ሥራ እና የፍቅር ግንኙነትን» በሚመለከት የተወሰኑ የአፍሪቃውያን ወጣቶችን አስተያየት እንሰማለን።

Symbolbild Liebe
ምስል Colourbox

ሥራ በፍቅር ህይወት ውስጥ እንዴት ያለ ሚና ይጫወታል?

This browser does not support the audio element.

 « ከአንድ ፖለቲከኛ ጋር የፍቅር ግንኙነት የምመሰርት ወይም የማገባው በፍፁም አይመስለኝም። ምክንያቱም ይዋሻሉ»  « ባለቤቴ የሞተ ሰው የሚነካ ከሆነ ምን አይነት ስሜት እንዳለው አላውቅም። ከዛ ደግሞ ወደ ቤት መጥቶ እኔን ሊነካኝ? በፍፁም» ይላሉ እነዚህ ሁለት የጋና ወጣቶች።
አንዳንድ የሥራ ዘርፎች በሌሎች ሰዎች ዘንድ ወዲያው እውቅና አግኝተው ዝና እና ከበሬታን ያጎናፅፋሉ። አንዳንድ ሰዎች እንደውም የቢሮ ሥራ ካለው ወይም ካላት ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመር  ለምሳሌ እርሻ ላይ ከሚሠሩ ሰዎች ይልቅ ይበልጥ ያስከብራል ብለው ያምናሉ። ሥራ በፍቅር ህይወት ውስጥ እንዴት ያለ ሚና ይጫወታል? በዚህ ጉዳይ ላይ የዶይቸ ቬለ DW 77 ከመቶው ዝግጅት ጋና ላይ የተወሰኑ ወጣቶችን አወያይቶ ነበር።  ኢፍያ ፤ ለምሳሌ አብራው የምትሆነው ሰው የሙያ ዘርፍ ለእሷ ለምን ወሳኝ እንደሆነ ስታብራራ «ለእኔ በጣም ወሳኝ ነው። የፍቅር ግንኙነት  ወይም ትዳር በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ሰዎች ስላለሽበት ደረጃ ይጠይቃሉ። ስለዚህ ጥሩ የስራ ስም ካለው ሰው ጋር መሆኑን እመርጣለሁ። ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ የሚሰጠውን ደረጃ እንድጠብቅ ያደርገኛል።»
ካርፍሪ ግን በፍቅር ግንኙነት ውስጥ የሚኖረው ኃላፊነት ከሥራ ይበልጣል ይላል።« ሴቶች ብዙውን ጊዜ ሥራ አስኪያጅ፤ ወይም የመስሪያ ቤት ኃላፊ ፤ በቃ የቢሮ ሥራ ያለው አይነት ወንድ ነው የሚፈልጉት፤ ቆንጆ መኪና ያለው። የዚህ ድርጅት ኃላፊ ሚስት ናት እንዲባሉ ነው የሚፈልጉት ። ለእኔ ግን ይህ ያን ያህል ሚና አይጫወትም።»
በርግጥ ሴቶች የሚፈልጉት ካርፍሪ የሚላቸውን አይነት ወንዶች ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?  «ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚሰሩ ረዳት እና ወያላ የመሳሰሉ ሰዎች ጋር በፍፁም አብሬ መሆን አልፈልግም» የምትለው ሜሮን ከዝቅተኛው ገቢ በላይ የሚረብሻት ነገር አለ። « ስነ ሥርዓታቸው ከባድ ነው። በሱስ የተያዙም አሉ። በዛ ምክንያት ነው» ሜሮን በግል ስራ ላይ ከተሰማራ ወንድ ጋር መሆንን ትመርጣለች።
ጋናዊው ሪቻርድ የሴቷ ሥራ ብዙም ሚና አይጫወትም ከሚሉት ነው። « በአንድ ግንኙነት ውስጥ ፍቅር ትልቅ ሚና ይጫወታል። አንድን ሰው የምናፈቅር ከሆነ የእሷ በአንድ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት ትልቅ ሚና አይጫወትም። » ኢፊያ ግን ይህንን ታስተባብላለች። « ሁሉም ፍቅር ፍቅር ይላሉ። ታውቃላችሁ፤ ወንዶች በሥራ ሴቷ እንድትበልጣቸው አይፈልጉም። እንበል እና ሴቷ የአንድ ድርጅት ኃላፊ ብትሆን እና እሱ የሆነ ነገር ላይ ቢሰራ፤ እሷ ኃላፊ ሆና ይላል። በርግጥ ፍቅር ወሳኝ ነው። ነገር ግን የሴቷ ሥራ ብዙም አያሳስበንም ለምን ትላላችሁ። ከምትበልጣችሁ ሴት ጋር መሆን አትፈልጉም። »
የትዳር አጋሩ በመስተንግዶ ወይም ከብዙ ሰዎች ጋር የሚያገናኛት አይነት ሥራ ባይሆን የሚመርጠው ኢትዮጵያዊው ወጣት ዘመኑም «ሴቶቹ የተሻለ ሥራ ሲኖራቸው ወንዶች ለመቀበል ይከብዳቸዋል» የሚባለው እውነት ነው ይላል። « ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ሴቶች በኢኮኖሚ ከወንዶች ዝቅ ያሉ ስለሆኑ ወንዱ የበላይ ቢሆን የተሻለ ነው ብለው ያስባሉ። ይህ ግን ትክክል አይደለም።» ሜሮንም ስህተት በመሆኑ ትስማማለች። ወደፊት አብራው የምትኖረው ሰው « ሥራ ፈቶ አይቀመጥ እንጂ ፤ የምናገኘው ገቢ ለጋራ ስለሆነ አይረብሸኝም» ትላለች። 
በዛብህ ቅርብ ጊዜ ትዳር መስርቷል። ለእሱ የሁለታችንም ስራ « ለየቅል መሆን አለበት» ይላል። « ልዩነቱ ውበት አለው። እኔ አሁን ድርጅት ውስጥ ነው የምሰራው። እሷ ደግሞ የቢሮ ስራ ነው የምትሰራው» በዛብህ እንደሚለው ምንም እንኳን እሱ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሠራ ቢሮ ውስጥ ከምትሰራው ባለቤቱ የበለጠ ገቢ ቢያገኝም በሰዎች ዘንድ ያለው እውቅና ግን ከእሷ የቀነሰ ነው። ጋናዊው ሪቻርድም በምሳሌ የሚያብራራው ይኼን ነው « እንበል እና ባለቤታችሁ ገበሬ ነው። እኛ አፍሪቃውያን ግን ስለ ገበሬዎች ያለን አስተሳሰብ አይገባኝም። ሌላው የዓለማችን ክፍል በሚገባ ተረድተውታል። ገበሬዎች ሀብታም እና ቢሊዮኔሮች ናቸው። ጋና ውስጥ ወይም አፍሪቃ ውስጥ ግን ገበሬ ነኝ ካልካት፤ አለቀልህ። መልሳ አታገኝህም።»
ሴቶች ከወንዶች ይልቅ አብረው ስለሚሆኑት ሰው ይበልጥ ይጨነቃሉ ማለት ነው? ኢፍያ ለምሳሌ በፍፁም አብራው መሆን የማትፈልገው ሰው የሒሳብን ባለሙያ  ወንድ ነው፤ «ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ለምሳሌ በጣም ጥንቁቅ ናቸው። እኔ ደግሞ ሰዎች ብዙ ጥንቁቅ ሲሆኑ አልወድም። መቼ እንደምሞት አናውቅም። ህይወትን ነገ እንደሌለ አድርገን ዛሬን ብቻ እንኑር፣ ሳልጨነቅ መኖር ነው የምፈልገው። ስለዚህ ባጀት ምናምን እያልኩ መጨነቅ አልፈልግም። ሌላው ደግሞ ጋና ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ያለውን የአስክሬን ክፍል እንውሰድ ፣  ባለቤቴ የሞተ ሰው የሚነካ ከሆነ፤ ምን አይነት ስሜት እንዳለው አላውቅም። ከዛ ደግሞ ወደቤት መጥቶ እኔን ሊነካኝ? በፍፁም፤ ስለትዳር ሳስብ ስለራሴ ብቻ አይደለም ወደፊት ስለሚኖሩን ልጆችም አስባለሁ፤ እንደ አዋቂ ከሰዎች የሚመጡ አሉታዊ ነገሮችን መቋቋም ይቻል ይሆናል። ሕፃናት ግን አይችሉም።»
ኢፊያ ሌላም መስፈርት አላት። ከመምህርም ጋር መሆን አትፈልግም። « ረዥም ጊዜ ያስተማረ ወይም ፕሮፌሰር ከሆነ ምናልባት ከግምት አስገባው ይሆናል። ነገር ግን እታች ያለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ ፤ አልፈልግም።

የወጣት ዝምባዊያን አስተያየትስ ምን ይመስላል?
« ባንክ ወይም ወግ እና ስርዓት የሚበዛበት ቦታ ላይ የሚሰራ ሰውን አልፈልግም።  ምክንያቱም ስርዓት ማክበር ብዙ ደስ አይለኝም። ባንክ ውስጥ የሚሰሩ ወንዶች አብዛኛውን ጊዜ ሱፍ ይለብሳሉ። ተራ ጫማም አያደርጉም፤ ስርዓት ያለው  መሆን አለበት። ስለዚህ ባንክ የሚሰራ ወይም ሥራ አስኪያጅ ከሆነ ሰው ጋር ፍቅር አልጀምርም። »
የሒሳን መዝገብ አያያዝ ተማሪ የሆነው ይኼ የዚምባቡዌ ወጣት ደግሞ ፍቅረኛው የእሱ አይነት ተመሳሳይ ሥራ እንድትሠራ አይፈልግም። ይህ ከሆነ ይላል፣« በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ብዙ የባጀት ጉዳይ ይኖራል። ስለዚህ ቢያንስ ትንሽ ሚዛኑን የጠበቀ መሆን ይኖርበታል።» 
ፖለቲከኞችስ?
«  ከአንድ ፖለቲከኛ ጋር የፍቅር ግንኙነት የምመሰርት ወይም የማገባው በፍፁም አይመስለኝም። በዛ ላይ እንደዚህ አይነት ግንኙነት ውስጥ ገብቼ ሳይሳካ ቢቀር ያ ሰው ግልፁን ይነግረኛል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ጥሩ ህይወት እንዲኖራቸው ነው የሚፈልጉት። ብቻ ይዋሻሉ።  »
ሴቶች ጥሩ ሥራ ያለውን ወንድ ብቻ ነው የሚፈልጉት የሚለውን የአንዳንድ ሰዎች አስተሳሰብ የማትጋራው ሌላኛዋ ወጣት ለምሳሌ ለእሷ ለምን የተከበረው የህክምና ባለሙያ ወይም ዶክተር ሙያ ጥያቄ ውስጥ እንደማይገባ ታብራራለች። « ብዙ በሥራ የተጠመዱ ይመስላሉ።  ስለዚህ እንደዚህ አይነት ሥራ ካለው ሰው ጋር አብሬ ብሆን አድካሚ ሊሆን ይችላል።  እረፍት ላይ ሆነው አስቸኳይ ጥሪ ሊደርሳቸው እና ሊሄዱ ይችላል። »
ሰዎች የተሰማሩበት የሥራ መስክ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በፍቅር ህይወታቸው ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው የዛሬው እንግዶቻችን በተለያየ መንገድ ገልፀዋል። ምናልባት በኦንላይን ለሚተዋወቁ ሰዎች ይህንን ፍላጎታቸውን በቀላሉ ሊያሳኩ ይችሉ ይሆናል።  ጓደኛ በሚፈልጉበት ገፅ ላይ ከአጋራቸው የሚፈልጉትን የሥራ መስክ መምረጥ ወይም አስወግደው መፈለግ ይችላሉ። ሥራ በፍቅር ህይወት ውስጥ ምን አይነት ሚና ይጫወታል? የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ርዕስ ነበር። ሳምንት በሌላ ዝግጅት እንገናኝ።

ምስል Reinhard Kurzendörfer/imago

ልደት አበበ 

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW