1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሥጋት ሆኖ የቀጠለው የኦሞ ወንዝ ሙላት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 9 2017

በኦሞ ወንዝ ሙላትና​​​​​​​ የቱርካና ሀይቅ መስፋፋት በወረዳው ከ81 ሺህ በላይ ሰዎች በአደጋው ውስጥ እንደሚገኙ የዳሰነች ወረዳ መስተዳድር አስታውቋል፡፡አሁን በውሃ ተከበው የሚገኙ ነዋሪዎችን ወደ ደረቃማ ሜዳዎች የማዛወር ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የዳሰነች ወረዳ የአደጋ ሥጋትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሠይድ ገልጸዋል ፡፡

 በዳሰነች ወረዳ የደረሰ የውሃ ማጥለቅለቅ
(ፎቶ ከማህደር) በዳሰነች ወረዳ የደረሰ የውሃ ማጥለቅለቅምስል፦ Dasenech Wereda communication

ሥጋት ሆኖ የቀጠለው የኦሞ ወንዝ ሙላት

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝሙላት ዛሬም ለነዋሪዎች መፈናቀልና ለንብረት ውድመት መንሥዔ እንደሆነ ይገኛል ፡፡  ነዋሪዎች እንደሚሉት ወንዙ ከባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ከፍታውን በመጨመር ከመደበኛ መስመሩ እየወጣ ይገኛል ፡፡ በወረዳው አንድ የቶልታሌ ቀበሌ ነዋሪ ሁኔታውን “ አስጊ “ በማለት ነው ለዶቼ ቬለ የገለጹት ፡፡ እሳቸው የሚኖሩበት ቶልታ ቀበሌን ጨምሮ  በቅርብ የሚያውቋቸው አምስት አጎራባች ቀበሌያት በውሃ መዋጣቸውን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዋ “ውሃው አንዳንድ ቤቶችን በሙሉ ሲያፈርስ ሌሎችን ደግሞ በግማሽ ውጦ ይገኛል ፡፡ሰው ሁሉ አጎበር አንጥፎ ነው ሜዳ ላይ የተኛው ፡፡ በጣም ስቃይ ነው ፡፡ ምንም ተስፋ ያለው ነገር አይመስልም “ ብለዋል ፡፡

በውሃ የተከበበችው ኦሞራቴ

የኦሞ ወንዝ ከመደበኛ መውረጃው በመውጣቱና  የቱርካና ሐይቅ ሞልቶ ወደ ኋላ በመመለሱ አሁን ላይ የዳሰነች ወረዳ የአስተዳደር ከተማ የሆነችው የኦሞራቴ  ነዋሪዎች በውሃ መከበባቸው ሌላው የከተማው ነዋሪ ተናግረዋል ፡፡ የኦሞ ወንዝ የኦሞራቴ ከተማን አቋርጦ የሚያልፍ መሆኑን የተናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች “ አሁን ወንዙ መደበኛ የመውረጃው መስመሩን ሞልቶ ግራና ቀኝ እየፈሰሰ ይገኛል ፡፡ በተጨማሪም በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የቱርካና ሀይቅም በወንዙ ፍሰት በመሙላት ወደ ኋላ እየተመለሰ በከተማዋ ሁለት ኪሎ ሜትር ላይ ደርሷል ፡፡ ሰሞኑን የጀመረው ዝናብ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነና የወንዙ ሙላቱ ከጨመረው ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ትዋጣለች የሚል ሥጋት አለ ፡፡ ነዋሪውም በፍረሃት ውስጥ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

(ፎቶ ከማህደር) በዳሰነች ወረዳ የደረሰ የውሃ ማጥለቅለቅምስል፦ Dasenech Wereda communication

ነዋሪዎችን የመታደጉ ጥረት

በኦሞ ወንዝ ሙላትና የቱርካና ሀይቅ መስፋፋት የተነሳ በወረዳው ከ81 ሺህ በላይ ሰዎች በአደጋው ውስጥ እንደሚገኙ የዳሰነች ወረዳ መስተዳድር አስታውቋል ፡፡ አሁን ላይ በውሃ ተከበው የሚገኙ ነዋሪዎችን ወደ ደረቃማ ሜዳዎች የማዛወር ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የዳሰነች ወረዳ የአደጋ ሥጋትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሠይድ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡ ዋናው ችግር አብዛኛው የወረዳው መሬት በውሃ መያዙ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኡሱማን “ ነገር ግን ባለው ቦታ ላይ ነዋሪውን የማሥፈር ሥራ እየተሠራ ይገኛል ፡፡ ለዚህ ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን  ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የፌዴራል መንግሥት አማካኝነት በቅንጅት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

የኦሞራቴን ከተማን በተመለከተ ውሃው በሁለት ኪሌ ሜትር ርቀት ላይ ከቦ እንደሚገኝ የተናገሩት ሃላፊው “ በከተማው ተመሳሳይ የሕይወት አድንና የጥንቃቄ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል ፡፡ በዘላቂነት ከተማዋን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው “ ብለዋል ፡፡

(ፎቶ ከማህደር)በዳሰነች ወረዳ የደረሰ የውሃ ማጥለቅለቅምስል፦ South Omo Zone Government

ዘላቂ መፍትሄ መቼ ይገኝ ይሆን ?

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ በተደጋጋሚ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ይገኛል ፡፡ የወንዝ ሙላቱ መፍትሄ እንዲበጅለት ለረጅም ጊዜ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ቢቀርቡም እስከአሁን ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ አልቻለም ፡፡ ጉዳዩ በቅርቡ ተካሄዶ በነበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ችግሩ መፍትሄ እንዲሰጠው የአካባቢው ተመራጮች ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በወረዳው በመካሄድ ላይ የሚገኙ የመስኖ ካናል ሥራዎች ሲጠናቀቁ የወንዝ ሙላቱ ችግርም አብሮ ይቀረፋል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW