1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ጎረቤቶችን ያፋጠጠው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ምርጫ

Eshete Bekele
ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2016

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት ከ2009 ጀምሮ ከያዙት ሥልጣን በሚቀጥለው ዓመት ይለቃሉ። የኮሚሽኑ ቀጣይ ሊቀ-መንበር አስራ አራት ሀገራት ከሚገኙበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ይመረጣል። እስካሁን ከሦስት የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ዕጩዎች ለአፍሪካ ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል።

የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ፣ የሶማሊያዋ ፋውዚያ ይሱፍ አደም እና የጅቡቲው ማሕሙድ አሊ ይሱፍ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት የመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀዋል።
የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ፣ የሶማሊያዋ ፋውዚያ ይሱፍ አደም እና የጅቡቲው ማሕሙድ አሊ ይሱፍ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት የመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ ጎረቤቶችን ያፋጠጠው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ምርጫ

This browser does not support the audio element.

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማትን ለመተካት የወጠኑ ዕጩዎች በመጪው ግንቦት በይፋ የምረጡኝ ዘመቻ ይጀምራሉ። እስካሁን የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ፣ የሶማሊያዋ ፋውዚያ ይሱፍ አደም እና የጅቡቲው ማሕሙድ አሊ ይሱፍ ለሊቀ-መንበርነቱ የመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀዋል። ሦስቱም ዕጩዎች የየመንግሥታቶቻቸው ድጋፍ አላቸው። 

ሙሳ ፋኪን የሚተካው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር አስራ አራት አባል ሀገራት ካሉት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና እንዲመረጥ የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ባለፈው መጋቢት ወስኗል። ምክር ቤቱ መጋቢት 6 ቀን 2016 ይፋ ያደረገው መግለጫ ዕጩ ማቅረብ የሚችሉት ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና ሀገራት ብቻ እንደሚሆኑ ይጠቁማል።

ኢትዮጵያ የኅብረቱ መቀመጫ እንደመሆኗ ለኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ማስመረጥ ስለማትችል ውድድሩ ዕጩ በሚያቀርቡ በአስራ ሦስት ሀገራት መካከል ይሆናል። በሰሜን አፍሪካ የሚገኙ ሀገራት ለምክትል ሊቀ-መንበር ዕጩ የሚያቀርቡ ሲሆን የተቀሩት ሦሰት ክፍለ አኅጉሮች ማለትም ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ አፍሪካ ለስድስት የኮሚሽነር ቦታዎች ይወዳደራሉ። 

በጥር 2009 በሰባት ዙር በተካሔደ ድምጽ አሰጣጥ ሙሳ ፋኪ ማኅማት ሊቀ-መንበር ሆነው የተመረጡት የኬንያዋ አሚና መሐመድን አሸንፈው ነበር። ማሕማት ከሦስት ዓመታት በፊት ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ድጋሚ የተመረጡ ሲሆን የሥራ ዘመናቸው በ2017 ይጠናቀቃል። የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር የአፍሪካ ኅብረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ሕጋዊ ተወካይ እና ዋና የገንዘብ ተቆጣጣሪ በመሆኑ ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት ነው።

ከመጀመሪያው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር አልፋ ኦማር ኮናሬ ጋር በቅርበት የሠሩት ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማት አምባሳደር ተፈራ ሻውል “ጽህፈት ቤቱን በአጠቃላይ የሚያካሒደው የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ነው። ኮሚሽነሮቹን የሚያዘው እሱ ነው። የአፍሪካ ኅብረትን ወክሎ በኒው ዮርክ፣ በጄኔቫ እና በየሀገሩ የሚቀመጠውን የሚመርጠው እና የሚሾመው እሱ ነው” ሲሉ ትልቅ ሥልጣን እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“መሪዎች በመግባባት ነው ዕጩ የሚያቀርቡት” የሚሉት አምባሳደር ተፈራ ከዕጩዎች መካከል “ሁሉ ሰው የማይቃወመው፣ ሁሉም ሰው ሊደግፈው የሚችል ሰው በስብዕናው፣ በአገልግሎቱ በዓለም አቀፍ አበርክቶው” እንደሚመረጥ አስረድተዋል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽኑን በሊቀ-መንበርነት ለመመራት በትምህርት ረገድ ያስቀመጣቸው መስፈርቶች አሉ።

ዕጩዎች ቢያንስ በሕግ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ ኤኮኖሚክስ፣ ዲፕሎማሲ፣ ቢዝነስ አስተዳደር፣ ፖለቲካ ሳይንስ እና ማኅበራዊ ሳይንስ በመሳሰሉ ዘርፎች ከታወቀ ተቋም የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው መሆን ይገባቸዋል። በተጠቀሱት የትምህርት ዘርፎች ዶክትሬት (Ph.D.) ያለው ዕጩ የተሻለ ዕድል እንደሚኖረው የአፍሪካ ኅብረት መስፈርት ያሳያል።

ባለፉት 22 ገደማ ዓመታት ለጥቂት ወራት ያገለገሉት የአይቮሪ ኮስት ዲፕሎማት አማራ ኤሴይ’ን ጨምሮ አምስት ሊቃነ-መናብርት ኮሚሽኑን መርተዋል። የማሊው አልፋ ኦማር ኮናሬ ምዕራብ አፍሪካን፣ የጋቦኑ ዤን ፒንግ ማዕከላዊ አፍሪካን፣ ደቡብ አፍሪካዊቷ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ደቡባዊ አፍሪካን፣ የቻዱ ሙሳ ፋኪ ማሕማት ማዕከላዊ አፍሪካን የወከሉ ናቸው። እስካሁን ድረስ ሰሜን አፍሪካ እና ምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናዎች የአዲስ አበባው መንበር አልደረሳቸውም።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር በሕዝብ ብዛት፣ በኤኮኖሚ እና በጂዖፖለቲካ “ትልልቅ ከሚባሉት ሀገራት ውጪ መሆን አለበት” የሚል ያልተጻፈ ሕግ እንደነበር በቻታም ሐውስ ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አቤል አባተ ይናገራሉ። ይኸ “የሥራ አስፈጻሚውን ሥራ ላለማክበድ፤ በሌሎች ሀገራት መካከል ያለውን ዕይታ እና ተዓማኒነት ላለመሸርሸር፤ ሥራ አስፈጻሚው ለወከለው ሀገር ሊወግን ይችላል የሚለውን ሥጋት ለመቅረፍ” ሲባል የሚደረግ ነበር።

ሙሳ ፋኪ ማኅማት በሚቀጥለው ዓመት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት ሥልጣናቸው ይጠናቀቃል። ምስል John Thys/AFP

ደቡብ አፍሪካ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ሀገራት ተቃውሞ ቢገጥማትም ድላሚኒ ዙማን ለማስመረጥ ባደረገችው “ከፍተኛ ውትወታ እና ዘመቻ” ምክንያት “ብዙዎቹ ያልተጻፉት ሕጎች ተሸርሽረዋል፤ አንዳንዶቹ ተቀልብሰዋል” የሚሉት ዶክተር አቤል “ማን ዕጩ ሆኖ ይቅረብ? ማን የማሸነፍ ዕድል ይኖረዋል? ማን የሁሉን ተዓማኒነት መግዛት ይችላል” በሚሉ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውይቶች ቀርተው “ግልጽ የሆነ በሁሉ ሀገራት መካከል የሚታይ ፉክክር” መፈጠሩን አስረድተዋል።

እስካሁን በይፋ ለመወዳደር ፍላጎታቸውን ካሳወቁ ሦስት ዕጩዎች የኬንያው የተቃውሞ ፖለቲካ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ቀዳሚ ናቸው። የ79 ዓመቱ ጉምቱ ፖለቲከኛ በተደጋጋሚ ለኬንያ ፕሬዝደንትነት ተወዳድረው ባይሳካላቸውም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለአምስት ዓመታት ገደማ ሠርተዋል። የፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት ለኦዲንጋ ድጋፉን ሰጥቷል።

በተለይ ፕሬዝደንት ሩቶ ባላንጣቸው ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት ሲወዳደሩ መደገፋቸው በእርግጥ በሀገራቸው ፖለቲካ ትልቅ ለውጥ አድርገው የቆጠሩት ቢኖሩም ከኦዲንጋ ይልቅ ኡኹሩ ኬንያታን ቢያጩ ይሻል ነበር የሚሉም አልጠፉም። ኦዲንጋ ከተመረጡ ግን ዊሊያም ሩቶ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን በሚደረገው ምርጫ የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍ እንደሚል የፖለቲካ ተንታኞች ያምናሉ።

“ይኸ ማለት ያለቀለት ያበቃለት ነገር ነው ብዬ አላምንም” የሚሉት ዶክተር አቤል ግን “የሌሎች ሀገሮች አሰላለፍ፣ የሌሎች ሀገሮች አተያይ፣ የኬንያ የውስጥ ፖለቲካ ብዙ የራሱ እንድምታ ይኖረዋል” ሲሉ ተናግረዋል። ተሳክቶላቸው ኦዲንጋ ለአዲስ አበባው ወንበር ከበቁ ለ40 ዓመታት ከነገሱበት የኬንያ ፖለቲካ ገለል ብለው አኅጉራዊ ኃላፊነት ከትከሻቸው ይወድቃል።

ባለፈው የካቲት 7 ቀን 2016 ዕጩነታቸውን ይፋ ሲያደርጉ “የአፍሪካ መሪዎች አገልግሎቴን ከፈለጉ እኔ ዝግጁ ነኝ” ያሉት ኦዲንጋ “ዛሬ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት ለመወዳደር ዝግጁ መሆኔ በይፋ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ጄኔራል” እያሉ በቀደመ ወታደራዊ ማዕረጋቸው የሚጠሯቸውን የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ድጋፍ ያገኙት ኦዲንጋ “ወዳጄ የእኔ አምባሳደር በመሆን በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎችን እንዲያግባባልኝ እጠይቃለሁ” ብለው ነበር።

የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት ጥሩ ዕጩ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። ምስል Getty Images

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት እንዲቋጭ የኅብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሆነው ከፍ ያለ ሚና የተጫወቱት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ “ወዳጄ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት በቀላሉ ጥሩ ዕጩ እንደሚሆን ምንም ጥርጣሬ የለኝም” ይበሉ እንጂ ጉዳዩ  በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ፍላጎት እንደሚወሰን የናይጄሪያው ጉምቱ ፖለቲከኛ አላጡትም።

“በእርግጥ ይህ በምሥራቅ አፍሪካ ያሉ መሪዎቻችን አመለካከት፣ ስሜት እና አቋም ላይ የሚወሰን ይሆናል። ከዚያ በኋላ ቀጠናው ዕጩ ካቀረበ የተቀረው አኅጉር ይቀበላል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከራይላ ኦዲንጋ በኋላ ዕጩነታቸውን ይፋ ያደረጉት የሶማሊያ ምክር ቤት አባል የሆኑት ፋውዚያ ይሱፍ አደም ናቸው። በሶማሌላንድ የተወለዱት ፋውዚያ የአባታቸውን ፈለግ ተከትለው ሶማሊያን በዲፕሎማትነት አገልግለዋል። መቀመጫውን በአዲስ አበባ ባደረገው የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ የኤኮኖሚ ኮሚሽን ጭምር ባልደረባ ነበሩ። 

በተለያዩ ጊዜያት ሶማሌላንድ እና ሶማሊያን በፕሬዝደንትነት ለመምራት ምርጫ ተወዳድረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ነገር ግን ወንዶች በነገሱበት የሶማሊያ ፖለቲካ የመጀመሪያዋ ሴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመሆን የበቁ ፖለቲከኛ ናቸው። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትም ሠርተዋል።

የፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ መንግሥት የፋውዚያ ይሱፍ አደምን ዕጩነት ደግፏል። ፋውዚያ ቢመረጡ በአፍሪካ ሀገሮች መካከል አንድነትን ለማበረታታት ፍላጎት አላቸው። መልካም አስተዳደር እና ተጠያቂነት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር፣ የሕዝብ ተሳትፎን ማሳደግ እና ሰብአዊ መብቶችን መጠበቅ ዋንኛ ጉዳዮቻቸው እንደሚሆኑ ፋውዚያ በኤክስ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። ፋውዚያ “ድሕነት፣ ግጭት፣ የከባቢ አየር ለውጥ እና የእኩልነት መጥፋት” የመሳሰሉ የአፍሪካ ችግሮችን ለመፍታት በኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት ላቅ ያለ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ገልጸዋል። 

ሦስተኛው ዕጩ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማሕሙድ አሊ ይሱፍ ናቸው። የ58 ዓመቱ ዲፕሎማት ትንሺቱን ስልታዊ ሀገር በውጭ ጉዳይ እና ዓለም ቀፍ ትብብር ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ ሁለት አስርት ዓመታት ሊሞላቸው እየተቃረበ ነው። ማሕሙድ አሊ ይሱፍ ለአራት ዓመታት ገደማ በግብጽ የጅቡቲ አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል።

ዕጩነታቸውን ይፋ ያደረገው የፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ መንግሥት የአኅጉራዊውን ድርጅት “መግቢያ መውጪያ ጠንቅቀው የሚያውቁ የበሰሉ ዲፕሎማት” በማለት ገልጿቸዋል። ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዘኛ እና አረብኛ ቋንቋዎች የሚናገሩት ማሕሙድ አሊ ይሱፍ የአፍሪካን “ፍላጎት እና ጥቅም ማሟላት የሚችል ሁሉም አቅም” እንዳላቸው የጅቡቲ መንግሥት ዕጩነታቸውን ይፋ ባደረገበት መግለጫ አስታውቋል።

ከኬንያ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ በተጨማሪ ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ክፍለ አኅጉር አባል ሀገራት ዕጩዎቻቸውን እስከ ግንቦት ወር ማቅረብ ይችላሉ። የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝደንት ጃካያ ክክዌቴ በዕጩነት ሊቀርቡ ይችላሉ ተብለው ከሚጠበቁ ታዋቂ ፖለቲከኞች መካከል ስማቸው በቀዳሚነት የሚነሳ ነው።

የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝደንት ጃካያ ኪክዌቴን ጨምሮ ከምሥራቅ አፍሪካ ክፍለ አኅጉር ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት ተጨማሪ ዕጩዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ምስል dapd

አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ተፈራ ሻውል “ሶማሌ ደካማ ስለሆነች፣ ማዳጋስካር ጠንካራ ስለሆነች አይደለም ዕጩዎቹ የሚቀርቡት። እነዚህ ሁለቱም ሀገሮች ዕኩል የአባልነት ደረጃ አላቸው። ሁሉም ሀገር እኩል ዕጩ የማቅረብ መብት አለው። በዲፕሎማሲም በውትወታም ይሰራበታል። ነገር ግን አንድ ሰው ሶማሊያዊ በመሆኑ አይቀርም፤ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ አይመረጥም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ለአራት ዓመታት የአፍሪካ ኅብረትን የሚመራው ቀጣይ ሊቀ-መንበር ምርጫ በየካቲት 2017 ገደማ ይካሔዳል። እስካሁን ፍላጎታቸውን ያሳወቁት ሦስት ዕጩዎች የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ዜጎች ናቸው። ውድድሩ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ዕጩዎች መካከል ብቻ የሚደረግ ቢሆንም የሶማሊያ እና የጅቡቲ ውሳኔ በክፍለ አኅጉሩ ሥምምነት አለመኖሩን ጥቆማ ሰጥቷል።

ዶክተር አቤል አባተ “በአፍሪካ ኅብረት ደረጃ ብዙ ጊዜ ሀገራት አዎንታዊ የሆነ አተያይ ያላቸው ሥጋት ሊያመጡ አይችሉም የሚባሉ ዕጩዎች ላይ ነው” ሲሉ ይናገራሉ። “ብዙ ጊዜ ትልቅ ሚና የነበራቸው፤ በአካባቢያቸው ትልቅ ተጽዕኖ ያሳረፉ፤ በፖለቲካ ጉዳዮቻቸው ከፍተኛ የሆኑ ሥራዎችን የሠሩ አንዳንዶቹ አከራካሪ ውርስ (legacy) ያላቸውን ከሒደቱ በአንድም ይሆን በሌላ የማግለል ሁኔታ ይስተዋል ነበረ” የሚሉት የቻታም ሐውስ ባልደረባ የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ እና የጅቡቲው ማሕሙድ አሊ ይሱፍ በሀገራቸውም ይሁን በአካባቢው ፖለቲካ ለረዥም ዓመታት ትልቅ ሚና የነበራቸው በመሆናቸው ይስማማሉ።

ይሁንና ዶክተር አቤል የዕጩዎቹ ልምዶች “በአካባቢው ሀገራት እንደ ጸጋ ይታያሉ? ወይስ እንደ ሥጋት ሊቆጠሩ ይችላሉ? የሚለው ወደፊት በደንብ መታየት” አለበት የሚል አቋም አላቸው። የሁለቱ ፖለቲከኞች “የሕይወት፣ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ልምድ በአንዳንድ ሀገሮች እንደ ትልቅ እሴት ሊታይ” ቢችልም “የጸጥታ፣ የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የቅቡልነት” ችግር ባለባቸው ዘንድ “ሥጋት ሊያሳድር” እንደሚችል ዶክተር አቤል ተናግረዋል።

በኬንያ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ዕጩዎች መካከል የሚደረገውን ፉክክር የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የቀድሞ ቃል አቀባይ ኑር ማሕሙድ ሼይክ በኢጋድ ቀጠና ተፈጠረ ለሚሉት “ዴሞክራሲያዊ ብስለት ምስክር” አድርገው ያቀርቡታል።

የአፍሪካ መሪዎች ለአራት ዓመታት ኮሚሽኑን የሚመራውን ቀጣይ ሊቀ-መንበር በየካቲት 2017 ይመርጣሉምስል Shadi Hatem/APA Images/ZUMAPRESS/picture alliance

“ጤናማ ፉክክር በዓለም አቀፍ መድረክ የፍሪካ አኅጉርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ብቁ” ሊቀ-መንበር ለመምረጥ ያስችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ኑር ማሕሙድ ሼይክ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ይሁንና በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እና ውጤታማ አመራርን ለማሳካት ውድድሩ “በገንቢ የውይይት እና የትብብር ማዕቀፍ” ሊሆን እንደሚገባ ይመኛሉ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ እንዳለ ንጉሴ እንደሚሉት ግን በቀጠናው ሦስቱ ሀገሮች ዕኩል ተሰሚነት የላቸውም። “ከሦስቱ ካወዳደርን ኬንያ የበለጠ ተሰሚ ነች” የሚሉት አቶ እንዳለ “ከጎረቤት ሀገሮች አንጻር ስናወዳድር ሶማሊያ ገና ሰብሰብ ብላ የፌድራል መንግሥቷን ጥንካሬ እያሳየች አይደለችም። በጎረቤት ሀገራት፣ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ዕርዳታ ያለች ሀገር ነች። ጅቡቲ በአንጻራዊ መልኩ ሰላም ብትሆንም ተሰሟነቱ ግን ከኬንያ ዕኩል ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም” ሲሉ ተናግረዋል።

ራይላ ኦዲንጋ የምረጡኝ ዘመቻቸውን በይፋ ሲጀምሩ በቀዳሚነት ወደ አዲስ አበባ ጎራ እንደሚሉ ይጠበቃል። አኅጉራዊ የምረጡኝ ዘመቻቸውን የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ያግዟቸዋል። የሶማሊያዋ ፋውዚያ ይሱፍ አደም እና የጅቡቲው ማሕሙድ አሊ ይሱፍም ሆኑ ሀገሮቻቸው ምን አይነት መንገድ እንደሚከተሉ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

“ሀገራቱ እነዚህን ዕጩዎች ለማስመረጥ የሚሔዱባቸው ዘመቻዎች፤ የሚያደርጓቸው ውይይቶች እና ውሎች ምን ዓይነት ይሆናሉ? የሚለውን አጓጊ ያደርገዋል” የሚሉት ዶክተር አቤል አባተ “አንዳንድ የምርጫ ሒደቶች በራሱ የሌላውን ዕጩ በማንኳሰስ፣ በማጥላላት ላይ ሊመሠረት ስለሚችል፣ እነዚህ ደግሞ በሀገራት ጭምር የተደገፉ ዕጩዎች ከሆኑ አሁን ያለው የሻከረ ግንኙነት የበለጠ እንዳይሻክር ያሰጋል” ሲሉ አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW