ረሃብ አድማ የመታዉ ግብጻዊዉ የማኅህበረሰብ አንቂ
ሰኞ፣ ኅዳር 5 2015
ለግብፅ ዲሞክራሲ መስፈን የሚታገለዉ እና በእስር ላይ የሚገኘዉ አል- አብደል ፋታህ የረሃብ አድማ ማድረግ መቀጠሉን ተከትሎ የግብፅ ባለ ሥልጣናት "በሕክምና ክትትል" ሥር እንዲሆን ማድረጋቸዉ ሰሞኑ ከግብፅ የተሰማ ዜና ነዉ።
በካይሮ በሚገኝ እስር ቤት ተዘግቶበት አምስት ዓመታት የሆነዉ የብሪታኒያ ዜጋ ትዉልደ ግብጻዊዉ የማኅበራዊ አንቂ የአል-አብደል ፋታህ ቤተሰብ፤ ስለ አብደል ፋታህ እንዴትነት፤ ወይህኒ ቤቱን ጠይቀዉ የእስር ቤቱ ባለስልጣናት "የእስረኛዉን ጤንነት ለመጠበቅ ሲባል የህክምና ጣልቃ ገብነት" ተወስዷል የሚል መልስ እንደተሰጧቸዉ ተናግረዋል።
ከግብጻዉያን ግንባር ቀደም የዴሞክራሲ አራማጆች አንዱ የሆነው ትዉልደ ብሪታንያዊው ግብጻዊ አል-አብደል ፋታህ የግብጽ ፖሊሶች በህብረተሰቡ ላይ የሚፈጽሙትን የጭካኔ ድርጊት በፌስቡክ ላይ በመጻፉ "ሐሰተኛ ዜና በማሰራጨት ወንጀል" ተከሶ ዘብጥያ ከተወረወረ አምስት ሆነዉ።
ለወራት የዘለቀዉ የረሃብ አድማ
የ40 ዓመቱ አል-አብደል ፋታህ መታሰሩን በመቃወም እና የታሰረበት ቤት ሁኔታ ሰብዓዊነት የጎደለዉ ሲል ባለፈዉ ሚያዝያ 2 ቀን የጀመረዉ፤ የረሃብ አድማ ለ220 ቀናት ቀጥሎበታል። በግብፅ ቀይ ባህር ዳርቻ በምትገኘዉ ሻርማልሴክ ከተማ ላይ ባለፈዉ እሁድ 27 ኛዉ የተመ የአየር ጥበቃ ጉባዔ ሲጀመር አብደል ፋታህ ውኃ መጠጣት እንዳቆመ ለቤተሰቡ አሳወቀ።
የታሳሪዉ አብደል ፋታህ እህት ሳና ሰይፍ የዓለም መንግሥታት እና የመንግሥታት ተጠሪዎች የዓለም አየር ንብረት ጥበቃ ጉባኤ ወደ ሚያካሂዱባት ወደ ሻርማል ሼክ ከተማ በመጓዝ፤ ከዓለም ወደ ተሰባሰቡት ጋዜጠኞች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በመሄድ የጉዳዩን አሳሳቢነት ይፋ አድርጋለች።
«ወደዚህ የመጣሁት ተጽዕኖ ለማድረግ እና የነገሩን አሳሳቢ መሆኑን ለማስገንዘብ ነዉ ። እሞት አፋፍ ላይ ለሚገኘዉ ወንድሜ ቋሚ ማስታወሻ ለመተዉ ነዉ።»
አብደል ፋታህ በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ.ም ግብፅ ላይ በፈነዳዉ እና የግብፁ የረጅም ዓመታት ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን በገረሰሰዉ በግብጹ የፀደይ አብዮት ላይ ባሳየዉ ከፍተኛ ተሳትፎ ዝናን እና እዉቅናን አትርፋል። ትዉልደ ግብጻዊዉ የዴሞክራሴ አራማጅ ባለፉት አስር ዓመታት አብዛኛዉን ጊዜዉን ያሳለፈዉ እስር ላይ ነዉ። አንዳንድ ግብጻዉያን፤ የንቅናቄ አራማጁ አብደል ፋታህ በመታሰሩም ፤ ግብፅ ወደ አምባገነናዊ አገዛዝ መመለስዋን የሚያመላክት ርምጃ እንደሆን ያምኑበታል።
አብደል ፋታህ ከእስር እንዲለቀቀ ዓለም ያቀረበዉ ጥሪ
አዲሱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ የግብጽ መንግሥት አብደል ፋታህን እንዲፈታ ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተጠሪ ቮልከር ቱርክ እስር ላይ የሚገኘዉ የማኅበረሰብ አንቂ "ህይወት በታላቅ አደጋ ላይ ነው" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ከሰባት ወር ጀምሮ ወንድሜ በረሃብ አድማ ላይ ነዉ የምትለዉ የአብደል ፋታህ እህት ሳና ሰይፍ፤ በቀን ጥቂት ኃይል ሰጭ ምግብ ብቻ እንደሚወስድ ግን በጣም መድከሙን ተናግራለች
«በጣም ፈርቻለሁ። አንብቤ እንደተረዳሁት አንድ ጤናማ ሰው ዉስጥ የፈሳሽ መጠን ለአንድ ሳምንት መቆየት የሚያስችል ነዉ። ነገር ግን የአብደል ፋታህ ሰዉነት ለረጅም ጊዜ ምግብ ስላገኘ ጤናማ አይደለም። በጣም ደካማ ነው እያወራን ያለዉ ስለ ቀናት ወይም ስለ ሰዓታት እንደሆነ ያወቅን አልመሰለኝም። በጣም ፈርቻለሁ ።»
በግብፅዋ ሻርማልሼክ ከተማ የዓለም መንግሥታት እና የመንግሥታት ተጠሪዎችን የሚነቅፉ የማኅበረሰብ አንቂዎች አብደል ፋታህ ነፃ ከእስር ነፃ እንዲሆን፤ እየወተወቱ ነዉ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እንደሚሉት በግብፅ እስከ 60,000 የሚደርሱ የፖለቲካ እስረኞች እስር ቤት ታጉረዋል። የካይሮ መንግስት ግን ይህን ክስ ያስተባብላል። በግብፅ የሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪ ቲራና ሃሰን እንደምትለዉ በግብፅ የሲቪል ማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ፤ እንዲከስም ተደርጓል።
«በአልሲሲ አመራር የሲቪል ማህበረሰቡ ከፍተኛ ውድቀት ነዉ ያጋጠመዉ። ይኸዉም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንቅስቃሴ፣ የአየር ንብረት ተሟጋቾች እና ነፃ ፕሬስ ተሟጋቾች ተግባር አሽቆልቁሏል። ብዙም «ሳንርቅ ባለፈው ሳምንት የሲቪል ኅብረተሰብ ተወካዮች ሰልፍ ለማደራጀት በመሞከራቸው እስር ቤት ተወርዉረዋል።»
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀፍ ውስጥ የሚካተተውና የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት የሚያደርገው 27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለአንድ ሳምንት የሚዘልቅ ይሆናል፡፡
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ