1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችአውሮጳ

ሩሲያ በዩክሬን ኻርካይቭ ከተማ ላይ በፈጸመችው ከባድ ድብደባ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ተገደሉ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 30 2017

በምሥራቃዊ ዩክሬን በምትገኘው ኻርካይቭ ከተማ ላይ ሩሲያ በድሮኖች እና ሚሳይሎች በፈጸመችው ከፍተኛ ጥቃት ቢያንስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ 21 መቁሰላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ። የከተማዋ ከንቲባ ኢሖር ቴሬክሖቭ በኻርካይቭ የለሊቱ ድብደባ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ “እጅግ ከባዱ” መሆኑን ገልጸዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ኻርካይቭ ከተማ በፈጸመችው ከባድ ድብደባ የሚቃ,ጠል ሕንጻ
ሩሲያ በዩክሬን ኻርካይቭ ከተማ በፈጸመችው ከባድ ድብደባ የመኖሪያ ሕንጻዎች እና ቤቶች የወደሙ ሲሆን ቢያንስ ሦስት ሰዎች ተገድለዋልምስል፦ Sofiia Gatilova/REUTERS

በምሥራቃዊ ዩክሬን በምትገኘው ኻርካይቭ ከተማ ላይ ሩሲያ በድሮኖች እና ሚሳይሎች በፈጸመችው ከፍተኛ ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ 21 መቁሰላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ። የከተማዋ ከንቲባ ኢሖር ቴሬክሖቭ በኻርካይቭ የለሊቱ ድብደባ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ “እጅግ ከባዱ” እንደሆነ መግለጻቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ከንቲባው እንዳሉት ድብደባው የመኖሪያ ሕንጻዎች እና ቤቶች አውድሟል።  

ሩሲያ ባለፉት ቀናት በዩክሬን በተደጋጋሚ የፈጸመቻቸው ጥቃቶች ብርታት ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት በቅርቡ ከሰላም ሥምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚለውን ተስፋ አዳክሞታል። 

የዩክሬን አየር ኃይል ሩሲያ ለሊቱን በ215 ሚሳይሎች እና ድሮኖች ጥቃት መፈጸሟን አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል 87 ድሮኖች እና ሰባት ሚሳይሎች ማክሸፉን አየር ኃይሉ ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ የዩክሬን አየር ኃይል ሱ-35 (Su-35) ተብሎ የሚጠራ ተዋጊ የጦር ጀት መትቶ መጣሉን በቴሌግራም በኩል ያሰራጨው መግለጫ ይጠቁማል።

የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲብያሕ ከኻርካይቭ በተጨማሪ በዶኔትስክ፣ ድኒፕሮፔትሮቭስክ፣ ኦዴሳ ግዛቶች እና ቴርኖፒል ከተማ ጥቃቶች መፈጸማቸውን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በጻፉት መልዕክት አስታውቀዋል።

የዩክሬን አየር ኃይል ሱ-35 (Su-35) ተብሎ የሚጠራ ተዋጊ የጦር ጀት መትቶ መጣሉን አስታውቋል። (ምስል ከማሕደር)ምስል፦ Alexander Strela/Zoonar/picture alliance

ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ሩሲያ የምትፈጽመውን ግድያ እና ውድመት ለማቆም በሞስኮ ላይ ከፍ ያለ ጫና ከማሳደር በተጨማሪ ዩክሬንን ለማጠናከር ተጨማሪ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ” ብለዋል።

የሩሲያ አየር ኃይል በዩክሬን ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ያነጣጠሩ ያላቸው ጥቃቶች ረዥም ርቀት በሚወነጨፉ የጦር መሣሪያዎች እና በድሮኖች እንደፈጸመ ዛሬ ቅዳሜ አረጋግጧል። የሩሲያ አየር ኃይል “የጥቃቶቹ ዓላማ ተሳክቷል። የተመረጡት ዒላማዎች በሙሉ ተመትተዋል” ብሏል። በጥቁር ባሕር ላይ አራት የዩክሬን ሰው አልባ ጀልባዎች መውደማቸውን የሩሲያ የዜና አገልግሎቶች የሀገሪቱን መከላከያ ሚኒስቴር ዋቢ በማድረግ ዘግበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሩሲያ ዛሬ ቅዳሜ 36 የዩክሬን ድሮኖች ማትታ መጣሏን አስታውቃለች። በሞስኮ ግዛት ቢያንስ ሁለት ሰዎች በዩክሬን የድሮን ጥቃቶች መቁሰላቸውን የግዛቲቱ አስተዳዳሪ አንድሬ ቮሮብዮቭ ገልጸዋል። የሩሲያ የበረራ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ዶሞዴዶቭ፣ ሼሬሜትዬቮ እና ዡኮቭስኪ አውሮፕላን ማረፊያዎች የበረራ ደሕንነትን ለማረጋገጥ በጊዜያዊነት መዘጋታቸውን አስታውቋል። ይሁንና ከአየር ማረፊያዎቹ የሚደረገው በረራ ዳግም መጀመሩን መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW