1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ጀመረች

ሐሙስ፣ የካቲት 17 2014

የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሚትሮ ኩሌባ "ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ጀምራለች" ብለዋል። ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ "ለወታደራዊ ተልዕኮ" መዘጋጀቷን ቀደም ብለው ተናግረው ነበር። የጸጥታ ጥበቃ ካሜራዎች ከክሬሚያ የሩሲያ ጦር ተሽከርካሪዎች ወደ ዩክሬን በሰልፍ ሲሻገሩ አሳይተዋል።

Ostukraine Militärfahrzeuge bei Donetsk
ምስል Alexander Ermochenko/REUTERS

የሩሲያ ወታደሮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ዩክሬን መግባታቸውን የአገሪቱ የድንበር ጥበቃ ኃይል አስታወቀ። ታንኮችን ጨምሮ በርካታ የሩሲያ ከባድ መሣሪዎች በክሬሚያ እና ሌሎች የሰሜን ዩክሬን ግዛቶች ድንበር ማቋረጣቸውን የዩክሬን የድንበር ጥበቃ ኃይል ዛሬ ሐሙስ ይፋ አድርጓል። ሩሲያ ክሬሚያን በኃይል ከዩክሬን የገነጠለችው ከስምንት አመታት ገደማ በፊት ነበር። የዩክሬን የድንበር ጥበቃ ኃይል አገሪቱ ከክሬሚያ በምትዋሰንበት አካባቢ አንድ አባሉ መገደሉን አረጋግጧል።

የጸጥታ ጥበቃ ካሜራዎች ከክሬሚያ የሩሲያ ጦር ተሽከርካሪዎች ወደ ዩክሬን በሰልፍ ሲሻገሩ አሳይተዋል። የሩሲያ ወታደሮች ዛሬ ሐሙስ በዩክሬን ላይ ሰፊ ጥቃት መጀመራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። 

ኪየቭ፣ ኻርኪይ እና ኦዴሳን በመሳሰሉ የዩክሬን ከተሞች ከባድ ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን የዓለም መሪዎች "የከፋ ጉዳት ያስከትላል" ያሉት ወረራ መጀመሩን እየተቃወሙ ነው።  የዩክሬን ዜጎች ከአንዳንድ ከተሞች መሸሽ እንደጀመሩ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።  በዘገባው መሠረት የሩሲያ ጦር የዩክሬን የአየር መቃወሚያዎች እና አየር ኃይል በሰዓታት ውስጥ ከጥቅም ውጪ አድርጊያለሁ ብሏል። 

ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለገጠማቸው ውግዘት፣ ማዕቀብ እና ዛቻ ቁብ ያልሰጡት የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሌሎች አገሮችን ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራ "አይታችሁት የማታውቁትን ዳፋ ያስከትላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ የዩክሬን ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች ላይ እንዳነጣጠረች የገለጹት የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በአገሪቱ ወታደራዊ ሕግ ደንግገዋል። መቼ እንደሆነ በግልጽ ባይነገራቸውም ሩሲያ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል ከዚህ ቀደም ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የዩክሬን ዜጎች በመኖሪያ ቤታቸው እንዲቆዩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። 

የጀርመኑ መራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልስ "ሩሲያ በዩክሬን ላይ የሰነዘረችው ጥቃት በግልጽ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥስ ነው። ምንም አሳማኝ ምክንያት የለውም" ብለዋል። የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት የወሰደውን እርምጃ "ግድ የለሽ" በማለት የነቀፉት ሾልስ ከዩክሬን እና ከሕዝቦቿ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን የሩሲያን እርምጃ አውግዘው የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን መንግሥት ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ፑቲን "የደም መፋሰስን መንገድ መርጠዋል" ብለዋል። 

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ቃል ገብተዋል። የሩሲያው ፕሬዝደንት በአገራቸው የቴሌቭዥን ጣቢያ ባደረጉት ንግግር ጥቃቱ በምሥራቃዊ ዩክሬን የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው የሚል ማመካኛ አቅርበዋል። አሜሪካ የሩሲያው ፕሬዝደንት ዩክሬንን ለመውረር እንዲህ አይነት ምክንያት እንደሚያቀርቡ አስቀድማ አስጠንቅቃ ነበር። 

ፑቲን ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ኔቶ አባል እንዳትሆን እንዲሁም የጸጥታ ማረጋገጫ እንዲሰጡ ሩሲያ ያቀረበችውን ጥያቄ አሜሪካ እና አጋሮቿ ቸል ብለዋል ሲሉ ከሰዋል።
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW