ሩሲያ በዶኔትስክ እና ኼርሶን ግዛቶች በፈጸመችው ድብደባ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን
እሑድ፣ ሐምሌ 27 2017
ሩሲያ በዩክሬን ቁጥጥር ሥር በሚገኙት የዶኔትስክ እና ኼርሶን ግዛቶች በሣምንቱ መገባደጃ በፈጸመችው ድብደባ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ዛሬ እሁድ አስታወቁ። በዴኔትስክ ግዛት በሚገኙ ከተሞች በተፈጸሙ ድብደባዎች አምስት ሰዎች ተገድለው ሌሎች 11 መጎዳታቸውን የግዛቲቱ ባለሥልጣናት እንደተናገሩ የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በኼርሶን ሁለት ሰዎች ሲሞቱ 10 ቆስለዋል።
በዩክሬን ቁጥጥር ሥር የምትገኘው የኼርሶን ከተማ ዛሬ ማለዳም በሩሲያ መደብደቧን ባለሥልጣናት ገልጸዋል። ትላንት ቅዳሜ በከተማዋ በተፈጸሙ ጥቃቶች የመኪና ድልድይ፣ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧምቧ እና በርካታ ተሽከርካሪዎች አውድመዋል።
በደቡባዊ ዩክሬን በምትገኘው ማይኮላይቭ ከተማ በሚገኝ የመኖሪያ አካባቢ ሩሲያ በሚሳይል በፈጸመችው ጥቃት ሰባት ሰዎች እንደተጎዱ የግዛቲቱ የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት አስታውቋል።
በተያያዘ ዜና፦ ከጥቁር ባሕር አጠገብ በምትገኘው የሩሲያ ሶቺ ከተማ አጠገብ ከሚገኝ የነዳጅ ማደያ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ በዩክሬን የድሮኖች ጥቃት የተቀሰቀሰ እንደሆነ የሩሲያ ባለሥልጣናት ወንጅለዋል። የክራንስኖዳር ግዛት አገረ ገዢ ቬኒያሚን ኮንድሪያቴቭ በቴሌግራም በጻፉት መልዕክት ቃጠሎው የድሮን ስባሪ በነዳጅ ማጠራቀሚያ ላይ በመውደቁ የተቀሰቀሰ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በቃጠሎው ሳቢያ የሩሲያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ሶቺ ከሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ የሚደረጉ በረራዎችን በጊዜያዊነት አግዶ ነበር። በዚያው በሩሲያ ቮሮኔዝህ ግዛት በተፈጸመ ሌላ የዩክሬን የድሮን ጥቃት አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በሩሲያ እና በጥቁር ባሕር ሰማይ ላይ ለጥቃት የተወነጨፉ 93 ድሮኖች ማክሸፉን ገልጿል።