1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩሲያ ተቀጣ፣ ለዩክሬኖች ምን ረባ?

ሰኞ፣ ሚያዝያ 3 2014

የተቦዳደሱ ሕንፃዎች፣የነደዱ፣ የተሰባበሩ፣ የተመነቃቀሩ የቤት ቁሳቁሶች፣ የተጨረማመቱ መኪኖች፣የተፈረካከሱ ባቡር ጣቢያዎች፣ ፋብሪካዎች፣ የነደዱ ታንክ-መድፍ፣የጦር ተሽከርካሪዎች-ከሁሉም በላይ የተዘረረ አስከሬን፣ የተኮማተረ የሰዉ አካል፣የኪየቭ፣የኻሪኪቭ፣የኸርሰን፣የማርዮፖል፣ የቡቻን የሌሎችም የዩክሬን ከተሞች ገፅታ።የዩክሬን ሕዝብ ምፅዓት።

Ukraine Kiew | Boris Johnson trifft Wolodymyr Selenskyi
ምስል Ukrainian Presidential Press Service/REUTERS

የዩክሬን ጦርነት ሒደቱና መዘዙ

This browser does not support the audio element.


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ብሔራዊ የፀጥታ አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ትናንት እንዳሉት የሩሲያ ጦር የዩክሬን ሰላማዊ ዜጎችን እንደሚገድል የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ጦርነቱ ከመጀመሩበፊት ያዉቁ ነበር።የጦርነቱ ሰበብ-ምክንያትም ዩክሬን፣ ዩንያትድ ስቴትስ የምትመራዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ትሆን አትሁን የሚለዉ ዉዝግብ መሆኑ ግልፅ ነዉ።የልዕለ ኃያልቲ ሐገር መሪዎች ሕዝብ እንደሚያልቅ እያወቁ ዩክሬንን አሳልፈዉ ሰጡ ማለት ይሆን?አናዉቅም።የኃይማኖት አባቶች ግን ካንገትም ሆነ ካንጀት ዛሬም ለሰላም ይፀልያሉ።ይማፀናሉም።የትልቅ ማሕበራት መሪዎች በደስታ ይፍነከነካሉ፣-ያስጨበጭባሉም።መንግስታት ጦር መሳሪያ ያግዛሉ።የዩክሬን ሕዝብ ይገደላል። ይሰደዳል። ዩክሬን ትወድማለች። እስከ መቼ? 
                                     
በቅርብ ዓመታት ፋሉጃሕ፣ ካንዳሐር፣ሲርት፣ አሌፖ፣ ሁዴይዳሕ እንዲያ ነበሩ።ናቸዉም።የዩክሬን ከተማ መንደሮች የጠፉ ቀዳሚዎቻቸዉን ለመብለጥ እሽቅድምድም የገጠሙ መስለዋል።የተቦዳደሱ ሕንፃዎች፣የነደዱ፣ የተሰባበሩ፣ የተመነቃቀሩ የቤት ቁሳቁሶች፣ የተጨረማመቱ መኪኖች፣የተፈረካከሱ ባቡር ጣቢያዎች፣ ፋብሪካዎች፣ የነደዱ ታንክ-መድፍ፣የጦር ተሽከርካሪዎች-ከሁሉም በላይ የተዘረረ አስከሬን፣ የተኮማተረ የሰዉ አካል፣የኪየቭ፣የኻሪኪቭ፣የኸርሰን፣የማርዮፖል፣ የቡቻን የሌሎችም የዩክሬን ከተሞች ገፅታ።የዩክሬን ሕዝብ ምፅዓት።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የፀጥታ አማካሪ ጃክ ሱሊቫን «ዘግናኝ» አሉት የዩክሬን ዜጋን ሞት፣ከተሞችን የጥፋት ገፅታ-ትናንት።«አስደንጋጭ»ም።ግን አልተደነቁም።የሆነዉ እንደሚሆን ያዉቁት ነበርና።
                       
«ከቡቻ እና ከሌሎች ከተሞች የተሰራጩና ያየናቸዉ ምስሎች አሳዛኝ፣ዘግናኝ፣በጣም አስደንጋጭ ናቸዉ።ግን አያስደንቁም።እኛ፣ እንደዕዉነቱ ከሆነ፣ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የሩሲያ መንግስት ባለስልጣናት ወረራዉን የሚቃወሙ የዩክሬን ሰላማዊ ዜጎችን ለማጥቃት ማቀዳቸዉን የሚጠቁሙ የስለላ መረጃዎችን ገና ጦርነቱ ሳይጀመር ይፋ አድርገናል፤ አቅርበናል።»
የፕሬዝደንት ፑቲኗ ሩሲያ፣ ምዕራቦች እንደሚሉት ዩክሬንን መዉረሯ ትልቅ ጥፋት፣ ሰላማዊ ሰዎችን ማስገደል፣ማሰቃየት፣ማፈናቀል-ማስደዷ በመረጃ ከተረጋገጠ ወንጀል መሆኑ በርግጥ አያጠያይቅም።አጠያያቂዉ ሩሲያ ዩክሬንን ለምን ወረረች? ወይም የተባለዉን ወንጀል ለምን አደረሰች?ደግሞስ ወንጀሉን እንደምትፈፅም አስቀድመዉ የሚያዉቁት የዋሽግተን፣ለንደን-ብራስልስ ተባባሪዎችና ተከታዮቻቸዉ የዩክሬንን ሕዝብ ለምን «ጭዳ» አደረጉት የተባለ እንደሆን ነዉ።
አመክንዮ አመክንዮ የሚሆነዉ-ለአመክኖዉያን ነዉ የሚሉ አሉ።እሳቸዉም ያዉ ከልብም ይሁን ከአፍ እንደ መንፈሳዊ መሪ ወግ ፀሎት፣ምሕላ፣ ተማፅኖን ነዉ ያሰሙን።የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ።
«የጠመንጃዉ አፈሙዝ ይዘቅዘቅ።የፋሲካ ተኩስ አቁም ይጀመር።ግን ተጨማሪ ጦር መሳሪያ እንዳይሰጥና አዲስ ዉጊያ እንዳይጀመር።አይሆንም! ለሰዎች ደሕንነት ሲባል፣ የተወሰነ መስዋዕትነት በሚጠይቅ እዉነተኛ ድርድር አማካይነት ሰላም የሚያሰፍን ተኩስ አቁም መሆን አለበት።እንደ ዕዉነቱ ከሆነ በፍርስራሽ ክምር ላይ ባንዲራ መስቀል እንዴት ድል ይሆናል።»
የዋሽግተን፣ለንደን፣ ብራስልስ-ኪየቭ ተባባሪዎችና የሞስኮ ጠላቶቻቸዉ የሰላም ጥሪዉን የሚሰማ ጆሮ ያላቸዉ  አይመስልም።ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የጠመንጃዉ ላንቃ እንዲዘጋ በጠየቁበት ዕለት ትናንት ከዋሽግተን የተሰማዉ አሜሪካኖች ጦርነቱን ለማራዘም መቁረጣቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ።የፕሬዝደንት ጆ ባይደን ብሔራዊ የፀጥታ አማካሪ ጃክ ሱሊቫን እንዳሉት ሐገራቸዉ ዩክሬኖች የሚፈልጉትን ጦር መሳሪያ ታስታጥቃለች።
«ዩክሬን ሩሲያን እንድትመታ፣ ሩሲያዎች እነዚሕ ወንጀሎችን ለመፈፀም ተጨማሪ ከተሞችን እንዳይዙ ለማስቆም ዩክሬኖች የሚያስፈልጋቸዉን ጦር መሳሪያ እንሰጣለን።የሩሲያን ኤኮኖሚ ለመጭመቅ፣በፕሬዝደንት ፑቲን ላይ ግፊቱን ለማጠናከር፣ በክሬምሊንና በሩሲያ መንግስት ላይ ወጪዉን ለማናር አበክረን እንሰራለን።»
ባለፈዉ አርብ ርዕሠ-ከተማ ኪየቭንና ቡቻን  ጨምሮ ጦርነቱ ያወደማቸዉን የዩክሬን ከተሞችን የጎበኙት የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ግን ያዩትን ጥፋት ለጋዜጠኞች ለመዘርዘር ቋንቋ አልበቃቸዉም።«ሔዳችሁ እዩት» አሉ-የ74 ዓመቱ ዲፕሎማት።
 «ያየነዉን ዓይተን ተመልሰን።እና እኛ በዕዉነት----ኪየቭ መሔድ ትችላላችሁ፣ በተቻላችሁ መጠን ኪየቭ ሒዱና እራሳችሁ እዩት።»
ቦሬል የሚገኙበትን የአዉሮጳ ሕብረት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የመሩት የሕብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላይን ዩክሬን የሕብረታቸዉ አባል መሆን የምትችልበትን ሰነድ ለሐገሪቱ ፕሬዝደንት ለቮሎድሚየር ዘለንስኪ አስረክበዋል።
ያቺ የአዉሮጳ-እስያ ሥልጣኔዎች መጋጠሚያዊቱ ሐገር ግዛቶችዋ ከ2014 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)እየተሸራረፉባት ነዉ።ዜጎችዋ ከመገደል-መሰደድ መፈናቀል፣ መሸማቀቅ ፋታ ሳያገኙ ዘንድሮ ሺዎች እየተገደሉ፣ ሚሊዮኖች እየተፈናቀሉ፣ እየተሰደዱባትም ነዉ።
በወር ከ15 ቀኑ ጦርነት 1800 ሰላማዊ ዩክሬናዊ ተገድሏል።2500 አካሉ ጎድሏል።የወታደሩን የሟች-ቁስለኛ ቁጥር በትክክል የተናገረ የለም።4.5 የሚሊዮን  ሕዝቧ ተሰድዷል።ወደ 6 ሚሊዮን ያሕሉ ተፈናቅሏል።ዉብ፣ ዘመናይ ከተሞችዋ ወድመዋል።ጥንታዊ ቅርሶችዋ፣ ወደቦችዋ፣ ፋብሪካዎችዋ፣ እርሻዎችዋ ነድደዋል።አብዛኛ ወጣቷ ተመንጃ አንግቦ በየምሽጉ አድፍጧል።የዓለም ባንክ እንዳስታወቀዉ ከዩክሬን ኤኮኖሚ ግማሹ ወድሟል።

ምስል Janis Laizans/REUTERS
ምስል Efrem Lukatsky/AP Photo/picture alliance

የአዉሮጳ ሕብረት አባል የምትሆነዉ፣ መሆኑ ይቅር፣ አባል ለመሆን የምትዘጋጀዉ ዩክሬን የትኛዋ ትሆን?ፎን ዴር ላይን ግን ልዩ ስጦታዉን ለዜሌንስኪ ባስረከቡ ማግስት ደስተኛነታቸዉን አልሸሸጉም።የደስታቸዉ ምንጭ የወደመችዉን ሐገር መጎብኘታቸዉ፣ የወደመችዉ ሐገር-ሐገር የመሆኗ ተስፋ አይደለም። 
የደስታቸዉ ምንጭ የሞስኮ-ዋሽግተን-ለንደን ብራስልሶች ጠብ ለሚያወድማት ዩክሬን ርዳታ መገኘቱ ነዉ።ምናልባት የርዳታዉ ብዛት ክሬምሊኖችን ያበሽቅ ይሆናል የሚለዉ ግምት ሊሆንም ይችላል።
«ዓለም በስተመጨረሻዉ 9.1 ቢሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብቷል።ከዚሕ በተጨማሪ፣ ቆይ፣ ቆይ ከአዉሮጳ የልማትና የዳግም ግንባታ ባንክ ጋር የሚሰራዉ ኮሚሽን ለዩክሬን ተፈናቃዮች አንድ ቢሊዮን ተጨማሪ (ርዳታ) ሰጥቷል።ይሕ ድንቅ ነዉ።10.1 ቢሊዮን ዩሮ፣ ይሕን በዶላር ካላችሁት ከዚሕም የበለጠ ነዉ።»
ለሌሎች ግን  የርዳታዉ መጠን የወድመቱን ልክ መስካሪ ነዉ።ሞስኮዎች ባንፃሩ ጦራቸዉ የጣለዉን ግድይ ይቆጥራሉ።የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ  ጄኔራል ኢጎር ኮናሼንኮቭ ዛሬ እንዳስታወቁት ጦራቸዉ በስም ካልጠቀሱት የአዉሮጳ ሐገር ለዩክሬን ጦር የተላከ የዓየር መቃወሚያ  መሳሪያን አዉድሟል።
                                    
«ዕሁድ ሚያዚያ 10 ከባሕር ላይ በተተከሰ ኢላማ መቺ ሚሳዬል ድኒፕሮ ደቡባዊ መዳረሻ ተደብቆ የነበረ፣ ካንድ የአዉሮጳ ሐገር ለኪየቭ ሥርዓት የተላከ S 300 ከምድር ወደ ዓየር ተምዘግዛጊ ሚሳዬል መተኮሻ ባታሊዮን ተደምስሷል።አራት S-300 ማወንጨፊያዎችና እስከ 25 የሚደርሱ የዩክሬን ወታደሮችም ተመትተዋል።»
የምዕራባዉያን በተለይም የብሪታንያና የዩንይትድ ስቴትስ ወታደራዊ የስለላ ተቆማት የሩሲያ ጦር  ከዩክሬን ጠላቶቹ ከፍተኛ አፀፋ እንደገጠመዉ በየጊዜዉ ይዘግባሉ።ይሁንና ከዓመታት በፊት ኢራቅ ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ ስለመታጠቋ፣ አምና ይሔኔ ደግሞ ታሊባን ካቡልን ሊቆጣጠር ስለሚችልበት ጊዜ  ከለንደን-ዋሽግተን የተነገረዉንና የሆነዉን እዉነት ተቃርኖ ስፋት ያልዘነጋ   የመረጃ-ፕሮፓጋንዳዉን ልዩነት ለማጤን እየተገደደ ነዉ።
የመረጃ-ፕሮፓጋንዳዉ ልዩነት ቢያደናግርም ምዕራባዉያን መንግስታት ዩክሬንን የሚረዱትን ያክል ሩሲያን ማግለልና መቅጣታቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚየር ዜለንስኪ ግን እስካሁን የተሰጣቸዉ ድጋፍ፣እስካሁን በሩሲያ ላይ የተጣለዉ እቀባና የተወሰደዉ ርምጃ አላረካቸዉም።ተጨማሪ እየጠየቁ ነዉ።«ጊዜ የለም» ይላሉ።
            
«ዩክሬን ጊዜ የላትም።አምባገነን አዉሮጳ ዉስጥ ሰላምን ሊያስጠብቅ  የሚችል ነገርን ሁሉ ሲወር ነፃነት ጊዜ ሊሰጥ አይችልም።አፋጣኝ ርምጃ መወሰድ አለበት።በመርሕ ላይ የተመሰረተ ርምጃ መወሰድ አለበት።ሁሉም የዴሞክራሲ ኃይሎች፣ ሁሉም የሰለጠነዉ ዓለም  የነዳጅ ዘይት ማዕቀብ መጣል የመጀመሪያዉ ርምጃቸዉ ሊሆን ይገባል።ሩሲያ የሚሰማት ያኔ ነዉ።ያኔ  ሰላም  ለሰላም መከራከሪያ፣ ትርጉም የለሹን ጥቃታቸዉን ማስቆሚያም ይሆናል።»
የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ዛሬ ሉክሰምበርግ ዉስጥ እየተነጋገሩ ነዉ።የንግግራቸዉ ዉጤት ለዚሕ ዝግጅት አልደረሰንልንም።የነዳጅ ዘይት ማዕቀብ ይጣል የሚለዉ ሐሳብ ግን በአባል ሐገራት ዘንድ ልዩነትን ፈጥሯል።አዉሮጳ በቀን 450 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ነዳጅ ዘይት ከሩሲያ ትገዛለች።
ብዙ ሳይታሰብ ዛሬ ሞስኮን የጎበኙት የኦስትሪያዉ መራሔ-መንግስት ካርል ኔሐመር ግን ከሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ቀጥተኛ፣ ግልፅና ከባድ» ያሉትን ዉይይት ማድረጋቸዉን አስታዉቀዋል።የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲሕ አንድ የምዕራብ አዉሮጳ ሐገር መሪ ሞስኮን ሲጎበኝ ኔሐመር የመጀመሪያዉ ናቸዉ።

ምስል Metin Aktas/AA/picture alliance
ምስል Mikhail Klimentyev/Stefanie Loos/AFP

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ


 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW