ሩሲያ እና ዩክሬን በአፍሪካ የእጅ አዙር ጦርነት እያካሔዱ ነው?
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 4 2016በመጀመሪያ ታሪኩ ግልጽ ነበር። የቱዋረግ ተዋጊዎች እና ረዳቶቻቸው በማሊ በረሐ ቢጫ እና ሰማያዊ ቀለማት ያሉት የዩክሬን እና የአዛዋድ ነጻ አውጪ ብሔራዊ ንቅናቄ (MLNA) የተባለው ታጣቂ ቡድን ሰንደቅ ዓላማዎች ይዘው ድላቸውን የሚያበስር ፎቶግራፍ ተነሱ።
ዓላማው በርካታ የሩሲያ ቅጥር ወታደሮች እና የማሊ ጦር ሠራዊት አባላት በተገደሉበት የደፈጣ ጥቃት ዩክሬናውያን እንደተሳተፉ መልዕክት ማስተላለፍ ነበር። የዩክሬን ወታደራዊ የስለላ ተቋም ተወካይ ይኸንንው የሚያረጋግጥ መግለጫ አውጥተዋል። ከዚያ ማሊን የሚመራው ወታደራዊ ኹንታ ሀገሪቱ ከዩክሬን ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠ።
ቀረብ ተደርጎ ሲመረመር ጉዳዩ የበለጠ የተወሳሰበ ነበር። የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሊ እርምጃውን ከመውሰዷ በፊት ማረጋገጫ እንድታቀርብ ጠየቀ። በደፈጣው ጥቃት ዩክሬናውያን ተሳትፈዋል መባሉን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞችም አይቀበሉትም።
“ዩክሬን ሚና አላት ብዬ አላምንም” የሚሉት የጀርመን ወግ አጥባቂ ፓርቲ ክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት (CDU) ቅርብ የሆነው የኮነራድ አደንአወር ፋውንዴሽን የሳህል ቀጠና ቢሮ ኃላፊ ኡልፍ ሌሲግ ናቸው። “በሚኑስካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በርካታ የሔሊኮፕተር አብራሪዎቿ ተሳትፈው ስለነበረ ዩክሬን ሰሜናዊ ማሊን ጠንቅቃ ታውቃለች። ነገር ግን ዩክሬን ቀጠናቸውን ጠንቅቀው ለሚያውቁት የቱዋረግ አማጺያን የተለየ ነገር ማቅረብ ትችላለች ብዬ ማሰብ አልችልም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በሳሕል ቀጠና ቀውስ የምትታመሰውን ማሊ ከወታደራዊ ኹንታው ጎን በመወገን ያረጋጋሉ የተባሉት የሩሲያ ቅጥረኞች የደረሰባቸው ጥቃት በሁሉም ወገኖች ተረጋግጧል። በዚህ ውስጥ ዩክሬን የተጫወተችው ግልጽ ያልሆነ ሚና ሩሲያ እና ዩክሬን በአፍሪካ የገጠሙት የእጅ አዙር ጦርነት ምን ያክል ብርቱ ነው? የሚለው ጥያቄ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል።
የቱ ወሬ ማንን ይጠቅማል?
ዩክሬናዊው የጸጥታ ተንታኝ ኤልያ ኩሳ በሰሜናዊ ማሊ ቲንዛዋቴና በተባለ ቦታ በተፈጸመው ጥቃት የሀገራቸው እጅ የለበትም የሚል እምነት አላቸው። የዩክሬን የፊውቸር ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ኩሳ “የሩሲያ መገናኛ ብዙኀን ዜናውን ተቀብለው አዎ ዩክሬናውያን በማሊ አሉ ማለት ጀመሩ። ይህ የአፍሪካ አገሮችን ተመለከታችሁ ዩክሬን መጥፎ ሀገር ነች ብሎ ለማሳመን ለሚያደርጉት ጥረት መከራከሪያ ስለፈጠረላቸው ለእነሱ የተመቻቸ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
ኤልያ ኩሳ እንደሚሉት ሩሲያውያን “ዩክሬን ጥሩ አጋር አይደለችም፤ ሽብርተኝነትን ትደግፋለች” ብሎ ለመወንጀል ተጠቅመውበታል። ከዚህ በተጨማሪ “ቱዋረጎች ራስን በራስ ለማስተዳደር መብታቸው የሚዋጉ ታጣቂዎች ብቻ አይደሉም፤ ዩክሬንን በመሳሰሉ የምዕራቡ ዓለም ደጋፊ ኃይሎች ገንዘብ የሚሰጣቸው እና የሚደገፉ ሽብርተኞች ናቸው” ለማለት እንዳመቻቸው ኩሳ ይከራከራሉ።
“ወታደራዊ ተልዕኮዎቻቸውን የበለጠ ለማስፋት እና በማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ሌሎች አገሮች ለመገኘታቸው መከራከሪያ ይሆናቸዋል” ሲሉ ዩክሬናዊው ተንታኝ አተያያቸውን አስቀምጠዋል።
የሩስያ ቅጥረኛ ወታደሮች በማሊ አማጺያን ብርቱ ጉዳት ደረሰባቸው
በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን በሚገኘው የክዋዙሉ ናታን ዩኒቨርሲቲ የሩሲያ ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢሪና ፊላቶቫ ግን እስካሁን ባለው መረጃ ተንተርሰው ድምዳሜ ላይ መድረስ አይፈልጉም። ነገር ግን ዩክሬን እንደ ተሳታፊ የመታየት ፍላጎት በእርግጠኝነት እንዳላት ይናገራሉ።
“ለአፍሪካ አገሮች ሩሲያውያን ብርቱ እንዳልሆኑ፤ ሊሸነፉ እንደሚችሉ ማሳየት አለባቸው” የሚሉት ኢሪና ፊላቶቫ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች “ሩሲያ ጠንካራ ናት፤ በሁሉም ረገድ ልትረዳን ትችላለች” የሚል አረዳድ እንዳለ መታዘባቸውን ገልጸዋል። “በኃይል የሰለጠኑ የሩሲያ ወታደሮችን የቱዋረግ አማጺያን ይዘው ለመግደል ባደረጉት ዘመቻ ዩክሬን ተሳትፋለች የሚለው ሐሳብ ሩሲያውያን ያን ያህል ብርቱ እንዳልሆኑ፣ እነሱም እንደሚሸነፉ ያሳያል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ከማሊ በስተምሥራቅ የሚደረገው ደም አፋሳሽ ውጊያ በበርካቶች ዘንድ የእጅ አዙር ጦርነት ተደርጎ ይቆጠራል። ከሚያዝ 2015 ጀምሮ በመሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የበላይነቱን ለመያዝ እየተዋጋ ነው። ዩክሬን ከዚህ ቀደም የሩሲያን ወረራ ለመግታት የሎጂስቲክስ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለሰጡት የሱዳን ጦር አዛዥ ጄነራል አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን ባሳየችው ወገንተኝነቷ እንደጸናች ትገኛለች።
ሩሲያ በአንጻሩ በመጀመሪያ በቫግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን እና በሌሎች ኃይሎች ጥበቃ የወርቅ ፍለጋ እንድታካሒድ የፈቀደላትን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ትደግፍ ነበር።
“ሩሲያ በየትኛውም ግጭት አንድን ወገን በዘላቂነት ደግፋ አታውቅም” የሚሉት ኢሪና ፊላቶቫ “ለጥቅሟ ምላሽ የሚሰጣትን እያየች ለሁለቱም የምታደርገውን ድጋፍ ትቀያይራለች” ሲሉ አስረድተዋል። “ማዕከላዊው መንግሥት ሩሲያ የጦር ሠፈር ልትመሠርት የምትፈልግበትን የባሕር ዳርቻ ይቆጣጠራል” የሚሉት ፊላቶቫ በአሁኑ ወቅት ሩሲያ የሱዳንን ማዕከላዊ መንግሥት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።
የሱዳን ጦርነት ጭካኔው ቀዝቀዝ ሳይል ለ16 ወራት የዘለቀበት አንዱ ምክንያት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ግብጽን የመሳሰሉ የቀጠናው ተዋናዮች የሚያቀርቡት የጦር መሣሪያ ነው። ዩክሬናዊው የጸጥታ ተንታኝ ኤልያ ኩሳ “በእኔ አረዳድ ይኸ ለእኛ ትልቅ ትኩረት የምንሰጠው አይደለም። በሱዳን ጦርነት ጥልቅ ተሳትፎ አለን ብዬ አላስብም” ሲሉ ተናግረዋል። “ሀገራችን ሩሲያ በምትገኝባቸው ሀገራት ሁሉ ከፍተኛ ፍላጎት አላት” የሚሉት ኩሳ “ምክንያቱም በጦርነቱ ሳቢያ የሩሲያ በየቦታው መገኘት በርካታ ሰዎችን ማሳሰብ ጀምሯል” በማለት ምክንያቱን አስረድተዋል።
ሱዳን፦ የጦር ኃይል አዛዧ ላይ የተቃጣው የድሮን ጥቃት መዘዝ
ሁለቱ ተቀናቃኞች ግብግብ የገጠሙት ግን ከዩክሬን የጦር አውድማዎች ርቀው ጭምር ነው። ኪየቭ ፖስት የተባለው በእንግሊዘኛ የሚታተም የዩክሬን ጋዜጣ ባለፈው የካቲት አንድ ቪዲዮ አሰራጭቶ ነበር። በዚያ አጭር ቪዲዮ ሦስት ሰዎች ዐይናቸው ተሸፍኖ፣ እጆቻቸው የፊጥኝ ታስረው እና መሬት ተንበርክከው የዩክሬን ልዩ ኃይል አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም በተባሉ ግለሰቦች ሲመረመሩ ይታያል። ከሦስቱ ታሳሪዎች አንዱ የቫግነር ቅጥረኛ ኩባንያ አባል እንደሆነ እና ወደ ሱዳን ያመራው የሀገሪቱን መንግሥት ለመጣል ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው እንደሆነ ይናገራል።
ዩክሬን እና ሩሲያ ከራሳቸው የጦር አውድማ ርቀው እየተፋለሙ ነው? ኢሪና ፊላቶቫ በሱዳን የሚገኙ የዩክሬን እና የሩሲያ ኃይሎች ቁጥር የተመጣጠነ ባለመሆኑ የእጅ አዙር ጦርነት ማለት ይቸግራቸዋል።
“የዩክሬን ልዩ ኃይሎች እና የዩክሬን ወታደራዊ ስለላ ተቋም ሩሲያውያንን በቻሉበት ቦታ ሁሉ እየተዋጉ መሆኑ ግን ግልጽ ነው” የሚሉት ኢሪና ፊላቶቫ “ሩሲያን በአፍሪካ መዋጋቷ ለዩክሬን በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ሩሲያ በአፍሪካ የምትፈልገውን ጂዖፖለቲካዊ የበላይነት ዩክሬንም ትፈልገዋለች” በማለት አብራርተዋል።
የደቡብ አፍሪካው የጸጥታ ጥናት ተቋም መሥራች እና የቦርድ ሊቀመንበር ጃኪ ሲለርስ ግን በአፍሪካ የሚካሔድ የእጅ አዙር ጦርነት ምልክቶች እያዩ ናቸው። በእርሳቸው አባባል ግን የእጅ አዙር ጦርነቱ የሚካሔደው በሩሲያ እና በመላው ምዕራቡ ዓለም መካከል ነው።
“በአፍሪካ እርስ በርስ ገጥመዋል የሚል ዕምነት አለኝ” የሚሉት ሲለርስ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካን የመሳሰሉ ሃገራት ምክር በመለገስ፣ በስለላ እና ምን አልባትም ለወታደራዊ እርምጃ የሚሆን የዒላማ መረጃ ካላቀበሉ እንደሚገረሙ ለዶይቼ ቬለ በጽሁፍ በሰጡት ምላሽ አብራርተዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ሩሲያ እና ምዕራባውያኑ በአፍሪካ የገቡበት ፍጥጫ ወደፊት ለሚመጣው ኃይለኛ ግብግብ ገና ጅማሮ ነው።
ዴቪድ ኢል/እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ