1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሩት ቫይስ፣ የፀረ-ሴማዊነት፤ የፀረ-አፓርታይድ፤ የሰብዓዊ መብቶች ታጋይ እና ደራሲ

ሐሙስ፣ መስከረም 15 2018

ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በ 101 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፤ ጀርመናዊትዋ አይሁዳዊት ጋዜጠኛ ደራሲ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሩት ቫይስ፤ የሆሎኮስትን ስቃይ እና በደቡብ አፍሪቃ በአፓርታይድ ስር ካጋጠማቸው ልምዶች ለሰዎች ሁሉ ዘላቂ ትምህርትን የቀረፁ ለጥቁር ህዝቦች መብት የቆሙ ሰዉ ነበሩ።

Ruth Weiss Aktivistin und Schriftstellerin
ምስል፦ DW

ሩት ቫይስ፣ የፀረ-ሴማዊነት፤ የፀረ-አፓርታይድ፤ የሰብዓዊ መብቶች ታጋይ እና ደራሲ

This browser does not support the audio element.

ባለፈዉ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም/ 05.09.2025 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አይሁዳዊቷ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሩት ቫይስ  አፓርታይድን በደቡብ አፍሪቃ ፣ ስደት ሳሉ በከፊል በሌሎች ሃገራትም ታግለዋል። ጋዜጠኛ ሩት ቫይስ ጥላቻ እና ዘረኝነትን በመቃወም በርካታ ጽሑፎችን ያስነበቡም ናቸዉ። 

ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በ 101 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፤ ጀርመናዊትዋ አይሁዳዊት ጋዜጠኛ ደራሲ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሩት ቫይስ "በህይወት በኖሩበት ዘመን ሁሉ በናዚ ጀርመን የአይሁዶችን ጭፍጨፋ ማለት የሆሎኮስትን ስቃይ እና በደቡብ አፍሪቃ በአፓርታይድ ስር ካጋጠማቸው ልምዶች ለሰዎች ሁሉ ዘላቂ ትምህርትን የቀረፁ፤ ሲሉ ነበር የጀርመን የባህል ሚኒስትር ቮልፍራም ቫይመር ስለ ሩት ቫይስ ምስክርነት የሰጡት።

በሩት-ቫይስ የተሰየመዉ ማህበር ባልደረባ አኒ ክሮፕፍ፤ የሩት ቫይስ የህይወት ታሪክ የመቻቻል እና የሰብዓዊነት መልእክትን ለማስተላለፍ እንደ ማነሻሻነት ያገለግላል ሲሉ ተናግረዋል።

«ሩት ቫይስን በተለያዩ ጊዜያት እና ሁኔታዉች እናዉቃቸዋለን። ሁሉ ሰዉ በመጀመርያ ትዉዉቅ የሚማርኩ ሰዉ ነበሩ።  በተለይ ከሰዎች ጋር ባላቸዉ አቀራረብ እና ንግግራቸዉ በጣም ማራኪ ነበሩ። በህይወት ዘመናቸዉ እኛንም እንድንሳተፍ ፈቅደዉልናል። በእንከን የለሹ የማስታወስ ችሎታቸዉ እና ትክክለኛ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጉዳይ ትንታኔያቸዉ ዛሬም እናደንቃቸዋለን። ሃሳባቸዉን በነፃነት እና ያለምንም እንከን መናገር ይችሉ ስለነበር፤ በጣም እንደነቅ ነበር። ጥሩ ቀልድ አዋቂ ስለነበሩም እንገረም ነበር። ትምህርታዊ፣ ቀስቃሽ፣ ልብ የሚኑኩና እና ጊዜ የማይሽራቸው መጽሐፎቻቸዉ ትልቅ ቱሩፋት ናቸው»

ደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበርግ 1936 | ሩት ቫይስ እና እህቷ ማርጎትምስል፦ Basel Afrika Bibliographien/Ruth Weiss Gesellschaft

ሩት ቫይስ እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሳቸዉ የታሪክ ተፈላጊ ምስክርም ነበሩ። ልምዳቸዉን አካፍለዋል፤ ህይወታቸዉ በተለያዩ ተሞክሮዎች የበለፀገም ነበር። በልጅነት እድምያቸዉ ሩት ሎዌንታል በሚል ይጠሩ የነበሩት ሩት ቫይስ፤ ከጀርመናዉያን አይሁድ ወላጆች በጎርጎረሳዉያኑ ሐምሌ 26 ቀን 1924 ዓ.ም በፍራንክፈርት አቅራብያ በሚገኘዉ ፉርት ከተማ ዉስጥ ተወለዱ። የጀርመን ናዚ አገዛዝ ወደ ስልጣን ሲመጣ የሩት ቤተሰቦች በኑረምበርግ ከተማ ይኖሩ ነበር። የናዚ አገዛዝ በአይሁድ ሁሉ ላይ ጥላቻ እንዳለዉ በፍጥነት የተረዱት የሩት አባት ሥራቸዉን ትተዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1933 ወደ ደቡብ አፍሪቃ ተሰደዱ። በመለጠቅ የሩት እናት ከሦስት ዓመታት በኋላ በ 1936 ከሁለቱ ሴት ልጆቻቸዉ ጋር ባለቤታቸዉን ተከትለዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ አቀኑ።

ሽሽት ወደ ደቡብ አፍሪቃ

የዚያን ጊዜ የአስራ ሁለት ዓመቷ ታዳጊ ልጅ ሩት ጆሃንስበርግ በሚገኘዉ፤ ነጮች በሚሰሩበት መንደር ዉስጥ ተፈላጊ እንዳልነበረች እና እንኳን ደህና መጣሽልን፤ እንዳልተባለች ወድያዉ ተገነዘበች። ታዳጊዋ ሩት ከጅምሩ፤ በደቡብ አፍሪቃ የነጭ ፋሺስቶች ጸረ ሴማዊነት እና በጥቁሮች ላይ የሚደርሰው አረመኔያዊ ዘረኝነት ገጥሟታል። በጀርመን የናዚ መንግሥት እና በደቡብ አፍሪቃ የአፓርታይድ ስርአትን ገና ከልጅነታቸዉ የተጋፈጡት ሩት ቫይስ፤ ለሰብአዊ መብት መከበር ያላቸዉን ቁርጠኝነት ቀርጾታል። ለረጅም ዓመታት በበርሊን ነዋሪ የሆኑት ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ፤ ሩት ቫይስ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ እና ጋዜጠኛ መሆናቸዉን ነግረዉናል።

ሩት በደቡብ አፍሪቃ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ካጠናቀቁ በኋላ፤ በአንድ የሕግ ድርጅት ውስጥ አገልግለዋል፤ ይሁንና አፓርታይድ ወጣትዋን አይሁዳዊት ሴት፤ አልተቀበላትም። ሩት በአንድ የባህል ማህበር ውስጥ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸዉ ሰዎች ጋር መገናኘት ሲጀምሩ ቆየት ብሎ ጋዜጠኛዉን እና ዉኃ አጣጭ የሆናቸዉን ባለቤታቸዉን ተዋወቁ። ሩት በጋዜጠኛ ባለቤታቸዉ ስም፤ ከዝያን ጊዜ ጀምሮ   በአዉሮጳ ለሚገኙ ሚዲያዎች ስለ አፓርታይድ ግፍ መጻፍ ጀመሩ። 

ዙርያ ገብ አመለካከትን ማፅናት

ዓለም ምን መሆን እንዳለባት የማትረዳ ከሆነ፤ በጋዜጠኝነት ሞያ መስራት አትችልም ሲሉ ሩት ቫይስ፤ ደጋግመዉ ይናገራሉ። በዚህም አለመለካከትን ማስፋት ቀኝ ግራዉን ማጤን እንደሚያስፈግ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። መንግሥታዊ ያልሆነዉ ድንበር የለሹ ጋዜጠኞች ድርጅት (RSF)ባልደረባ ካትሪና ቫይስ የአይሁዳዊትዋ ጋዜጠኛ የመንፈስ ጥንካሪ ለብዙዎች ተምሳሌ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

ኔልሰን ማንዴላ ፤ የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚዳንት ምስል፦ Kim Ludbrook/EPA//picture alliance/dpa

«እኛ ድንበር የለሽ ጋዜጠኞች በዓለም ዙሪያ ያሉ የሚዲያ ባለሙያዎች የሩት ቫይስን የጋዜጠኝነት ድፍረት እና ታማኝነት እንደ አርአያ መውሰዳቸዉን ይቀጥላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ሩት በዘመኑ ይታይ የነበረዉ የዘረኝነት፣ አፓርታይድ እና ፀረ-ሴማዊነት ሁኔታ ምስክር እንደመሆናቸዉ፤ ብሎም ሁልጊዜም ፍትህን እና ሰብአዊ መብቶችን በዋናነት የሚያስቀምጡ በጣም የበለፀገ የጋዜጠኝነት ውርስ ትተዉ ያለፉ ናቸዉ።»

የጀርመን አፍሪቃ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡሺ ኢድ “የሩት ቫይስ ሞትን ተከትሎ፣ ሩት ቫይስ የአፍሪቃ ቅን ወዳጅን ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ ኃላፊነት እንድንወስድ እና ከታሪክ እንድንማር የሚያስገነዝበንን የሞራል ደጋፊን ነዉ ያጣነዉ”  ሲሉ ተናግረዋል።

ሩት ቫይ ትዳራቸዉ ሳይሳካ ከፍቺ በኋላ በጎርጎረሳዉያኑ 1960 በጋዜጠኝነት ስራቸዉን ሙሉ በሙሉ ቀጠሉ። ሩት ቫይስ በኤኮኖሚ ጉዳይ ዘገባቸዉ ታዋቂ ሆኑ፤ ከዚህ ሌላ በፖለቲካ ነክ ዘገባቸዉ፣ በዛምቢያ እና በአሁኗ ዚምባብዌ ለነበሩት የነፃነት እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪቃ ይደረግ ለነበረው የፀረ-አፓርታይድ ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።  

በጎርጎረሳዉያኑ 1963 ሩት ቫይስ ወደ እስር ከመጋዛቸዉ በፊት ቃለ-መጠይቅ ካደረጉላቸዉ ታዋቂ አፍሪቃዉያን መካከል፤ የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ፣የዛምቢያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ እና የደቡብ አፍሪቃዉ የነፃነት ጀግና ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ፤በርካታ የአፍሪቃ የነፃነት ንቅናቄ ግለሰቦችን አነጋግረዋል፤ ግንኙነትም ነበራቸዉ። 

የደቡብ አፍሪቃዉ የአፓርታይድ አገዛዝ አብዛኛዉን የጥቁር ህዝብ አፍኖቆይቷል- ምስሉ ከ1994 ምርጫ በፊት የማንዴላ ANC ታርቲ በምርጫ እንዳሸነፈ የነበረዉን ሁኔታ ያሳያልምስል፦ ALEXANDER JOE/AFP/Getty Images

ከራስ ወዳድነት ነፃ "አፍሪቃን አዋቂነት"

ሩት ዌይስ ከ 2020 ጀምሮ በውጭ አገር የፔን ጀርመንኛ ተናጋሪ ደራሲያን ማዕከል፤ የክብር ፕሬዝዳንት ሆነዉም አገልግለዋል። ሩት “ስለ አፍሪቃ በጥልቀት የሚያዉቁ”፣ “ለሌሎች ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች የእውቀት ምንጭ ነበሩ” ሲሉ የፔን ዋና ፀሐፊ ሄልጋ ድሩክስ ለDW ተናግረዋል ።  

"ሩት ለሌሎች ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች የእውቀት ምንጭም ነበሩ። በውጭ አገር የጀርመንኛ ተናጋሪ ደራሲያን የፔን ማዕከል ሩት ቫይስ የክብር ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ እድሉን በማግኘታችን ኩራት ይሰማናል። እጅግ ማራኪ እና በዓለም የታወቁ  ታላቅ ሰዉ ነበሩ። ለሰዎች ባላቸዉ ጉጉትነት፣ ቅንነት፣ በቀልዳቸዉ እና በትህትናቸዉ ይታወቃሉ።"

ሩት ቫይስ ከራስ ወዳድነት ነፃ የነበሩ ሰዎችን አጋዥ የነበሩ ሲሉ ፔን የተባለዉ በጀርመን የደራስያን ማህበር አባል እና የአልፍሬድ ኬር ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ዲቦራ ቪዬቶር ኢንግላንደር እንዲሁ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

«ሩት የራሳቸዉን ችግር መፍታት ብቻ ሳይሆን፤በደቡብ አፍሪቃ ካሉ ጥቁር ህዝቦች ጎን በመቆም ለመታገል የሞከሩም ነበሩ።»

እንደጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር  በ 1966 ሩት ቫይስ፤ከአፍሪቃ አህጉር ወጥተዉ ወደ ለንደን ተጓዙ። በለንደን ዘ-ጋርድያን በተባለዉ ጋዜጣ ላይ ጨምሮ በተለያዩ ህትመቶች ላይ ጽፈዋል። እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር ከ 1975 እስከ 1978 በጀርመን ኮሎኝ ይገኝ በነበረዉ፤ በዶቼ ቬለ ሬድዮ ጣብያ DW በአፍሪቃ  ክፍል ውስጥ አገልግለዋል። በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 1980 ዚምባብዌ ከቅኝ ግዛት መዉጣትዋን ተከትሎ ወደ ሃራሬ ለሥራ ተጉዘዉ ነበር።

እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር  በ 2005 "በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ የተመረጡ  1,000 የሰላም ሴቶች" መካከል አንዷ በመሆን ለኖቤልየሰላም ሽልማት ታጭተዋል። ከ 2010 ጀምሮ በጀርመን አሻፍንቡርግ ከተማ ዉስጥ የሚገኝ፤ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ በስማቸዉ ተሰይሟል።  ኬፕ ታውን ዉስጥ የሚገኝ የአይሁድ ሙዚየም  በጎርጎረሳዉያኑ 2014፤ ስለሳቸዉ አዉደ ርዕይ በመዘርጋት አክብሯቸዋል። "የእኔ እህት ሳራ" የተሰኘዉ እና ስለአፓርታይድ አገዛዝ የጻፉት መጽሐፍ፤ በጀርመን ትምህርት ቤቶች የስነ-ፅሑፍ ማስተማርያ ሆንዋል። በጎርጎረሳዉያኑ 2014 ፣ የጀርመን ፌዴራል መንግሥት፤ አንደኛ ደረጃየክብር ኒሻን ተሸላሚም ነበሩ። በ 2023 የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ የክብር ሽልማትን እንዲሁም በ 2024 የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ፤ የክብር ሽልማትን ዳግም ተቀብለዋል።

ጀርመን ቦሁም ከተማ | ደራሲና እና ጋዜጠኛ | ሩት ቫይስምስል፦ Andreas Keuchel/dpa/picture alliance

ሩት ቫይስ በመጨረሻዎቹ ዓመታት የኖሩት ከወንድ ልጃቸዉ እና ከቤተሰቡ ጋር ዴንማርክ ዉስጥ ነዉ።  ሩት ቫይስ በእርጅና ዘመናቸዉ በሥነ-ጽሑፋቸዉ ቀጥለዉ ነበር። የሩት የመጨረሻ ድርሰት በግርድፉ "ማስታወስ ማለት መደራደር" የሚል  ትርጉምን የያዘ ሲሆን በጎርጎረሳዉያኑ ነሐሴ 2025 ለህትመት የበቃ ነዉ።  በውስጡ በመካከለኛው ምስራቅ ስላለው የግጭት መባባስ በማያሻማ ሁኔታ ሃሳባቸዉን ያስቀመጡበት መሆኑ ተዘግቧል።  "ሁለቱም ፤ አይሁዶች እና አረብ-ፍልስጤም ህዝቦች፤ በፍልስጤም የመኖር መብት አላቸው" "በእያንዳንዱ ተጨማሪ ሞት የሚያድገው ጥላቻ፤ ለሁለቱም ህዝቦች አሳዛኝ ሁኔታን ያራዝመዋል ሲሉ ጽፈዋል። ሩት ቫይስ በመካከለኛዉ ምስራቅ የሚታየዉ ግጭት በመጨረሻ መፍትሄ እንደሚያገኝ እንደሚያምኑ እና በጭራሽ ተስፋ እንደማይቆርጡም አክለዉ ጽፈዋል። ይሁንና ይህ ምኞታቸዉ መሳካት አለመሳካቱን፤ለማየት አልታደሉም።

እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር  በ 2023 ፣ ሩት ቫይስ የሬድዮ ጣብያችን በሚገኝበት በሰሜን ራይን ዌስትፋሊያ ግዛት ፓርላማ ውስጥ“ዘረኝነት ፣ ፀረ-ሴማዊነት ድንበር እንደማያውቁ ተምሬያለሁ ፣ ይህን በሁሉም ዘርፍ መታገል አለብን ሲሉ የሆሎኮስት መታሰብያ እለት ተናግረዋል። 

ኒኮላስ ፊሸር / ማርቲና ሽዊኮቭስኪ

አዜብ ታደሰ / ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW