የሩዋንዳ ፖለቲካ ሰብአዊ መብቶች እና የስደተኞች ጉዳይ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 13 2016
አንድ ታዋቂ የጀርመን ፖለቲከኛ ሰሞኑን ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያቀረቡት ሐሳብ ዳግም በአፍሪቃን አህጉር ላይ ትኩረት እንዲደረግ አድርጓል። የሩዋንዳዉ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና በሩዋንዳ የሚገኙ ስደተኞች ጉዳይ ምን ይመስል ይሆን። ጀርመናዊዉ ፖለቲከኛ እና የተቃዋሚዎ የክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ አባል የንስ ሽፓን በያዝነዉ ታህሳስ ወር በሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ፣ ብሪታንያ ካቀረበችው ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ሞዴል ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ሃሳብ አቅርበዋል።
በዚህ ሳምንት ሩዋንዳን የጎበኙት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባርቦክ በጉብኝታቸዉ ወቅት የሽፓንን ሐሳብ አንስተዉ «የቂል ሃሳብ» ሲሉ አስረግጠዉ ተቃዉመዉታል። ይሁን እንጂ ተገን ጠያቂዎችን ከባሕር ባሻገር የመላክ ሐሳብ እንዴት ቀልብን እየሳበ መምጣቱን የሚያሳይ ሆንዋል ። ከዚህ ሌላ ሩዋንዳ ራሷን የተገን ጠያቂዎች ዓለም አቀፍ መናኸሪያ በማድረግ ረገድ ስኬታማ እየሆነች መምጣትዋንም ያመላክታል። ስለ ሩዋንዳ መንግስት፣ ኢኮኖሚ፣ የሰብአዊ መብት ይዞታ እና ስለሚከተለዉ የስደተኞች ፖሊሲ ማወቅ ይፈልጋሉ ? ይህን ይመስላል።
የሩዋንዳ መንግስት እና ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ
ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜና የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (RPF) ከጎርጎረሳዉያኑ 1994 ዓ.ም በሃገሪቱ ከተከሰተዉ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ማብቂያ ጀምሮ ትናንሽ ተራሮች በብዛት የሚገኝባትን ለምዋን እና ትንሽዋን ምስራቅ አፍሪቃዊት ሃገር ሩዋንዳን እየገዙ ይገኛሉ። ሀገሪቱ በወረቀት ላይ እንደተቀመጠዉ ባለ ብዙ ፓርቲ እና ዴሞክራሲያዊ ሃገር ነች። የዩናይትድ ስቴትስ የልማት ድርጅት ዩኤስኤአይዲ እንዳስቀመጠው ግን ሩዋንዳ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚባል ነገር የላትም። ካጋሜ ሦስት ምርጫዎችን ድምጽን በማጭበርበረብ እና ማስፈራራት በድል አሸንፌያለሁ ሲሉ በትረ ስልጣኑን ተቆናጠዉ ቀጥለዋል። በጎርጎረሳዉያኑ 2017 በሀገሪቱ የተካሄደዉን ምርጫ 99% ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸዉ በይፋ ተነግሮላቸዋል።
የመብትና ነፃነት ጉዳይ በሩዋንዳ ምን ይመስላል ?
ሩዋንዳ የሰብዓዊ መብቶችን እና ዓለም አቀፍ እና ክልላዊ ህጎችን አጽድቃለች። እነዚህ ህጎች በሀገሪቱ ህገ መንግስት እንደማህለቅ የሰፈሩ ናቸው። ይሁን እንጂ በርካታ ታዛቢዎች እንደሚሉት በሩዋንዳ ከፍርድ ቤት ነፃ የሆኑ ግድያዎች ፣ በመንግሥት እርምጃ የሰዎች መሰወር ብሎም ተቃዋሚዎችን ማሠቃየት እና ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ አሳዉቀዋል። ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት «ሂውማን ራይትስ ዋች» እንደገለፀዉ ሁኔታዉ "በሀገሪቱ ሃሳብን በነጻነት የመናገር ነጻነት በመነፈግ" ሐሳብን የመግለጽና የመቀራረብ ነፃነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። የሚዲያ ነፃነትን በተመለከተ የሩዋንዳ የመገናኛ ብዙኃን ገፅታ በአፍሪቃ ከሚገኙት ሃገራት መካከል እጅግ ያሽቆለቆለ መሆኑን ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ድርጅት ሪፖርተርስ ዊዝ አዉት ቦርደርስ አስታዉቋል። ከቀናት በኋላ በሚጠናቀቀዉ በጎርጎረሳዉያኑ 2023 ሩዋንዳ በፕሬስ ነፃነት መዘርዝር ከ180 ሃገራት መካከል 131ኛ ቦታ ላይ ተቀምጣለች።
የሩዋንዳ ኢኮኖሚ
ፕሬዚዳንት ካጋሜ በጎርጎረሳዉያኑ 1994 ዓ.ም በ100 ቀናት ውስጥ ብቻአንድ ሚሊየን ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱስ በዘር ማጥፋት ዘመቻ ከተጨፈጨፉ በኃላ ነበር የደቀቀ ምጣኔ ሀብት የነበራትን የሩዋንዳን መንበረ ስልጣን የወረሱት። የሩዋንዳ ኢኮኖሚ ዛሬም በግብርና ላይ የተመረኮዘ ነዉ። ይሁንና በተሃድሶ የጎለበተ እዉቀት ያላቸዉ ካጋሜ ሩዋንዳን ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገትና በኑሮ ደረጃ "ከፍተኛ መሻሻል" እንዲኖራት ማድረጋቸዉን የዓለም ባንክ መስክሮላቸዋል።
አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ከጎርጎረሳዊዉ 2000 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ እድገቱ 142% ያሻቀበ ሲሆን በጎርጎረሳዉያኑ 2016-17 በተደረገዉ ጥናት መሰረት ሩዋንዳ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ወደ 52% መቀነሱ ተረጋግጧል። ሀገሪቱ የእናቶችንና የህፃናት ሞትንም በእጅጉ ቀንሳለች። በአሁኑ ወቅት 13 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ያላት ሩዋንዳ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪቃ ሀገራት መካከል ረጅም ዕድሜ የሚኖሩ ህዝቦች የሚገኙባት ሃገራት ዉስጥ ተመድባለች። አፍሪቃ ውስጥ ሙሰኝነት በጣም ቀንሶ ከሚታይባቸዉ አገሮች አንዷ የሆነችው ሩዋንዳ፤ በንግድ ግብይት ከአህጉሪቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ።
ሩዋንዳ በኃያላኑ ምዕራባውያን የምትወደደው ለምንድን ነው?
ሩዋንዳ የተረጋጋችና በሀገሪቱ ሙስና ዝቅተኛ በመሆኑ በየዓመቱ 1 ቢልዮን ዶላር (914 ሚሊዮን ዩሮ) እርዳታን ትቀበላለች። "የልማት እርዳታ እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ መዋሉን ሀገሪቱ ዉስጥ የሚታዩት ንፁህ መንገዶች እና ምርጥ ሥነ ህንጻዎች ምስክር ናቸዉ፤ ይሁንና እና እርዳታዉ ለሰላምና ለደህንነት፣ ለሰብዓዊ መብቶች ምንም ሚና አለመጫወቱ ሚታይ ነዉ" ሲሉ በብሪታንያ ማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የዓለምአቀፍ የፖለቲካ ጥናት ፕሬዚዳንት ቶኒ ሃስትሩፕ ተናግረዋል።
በሩዋንዳ የሚገኙ ስደተኞች ሁኔታ ምን ይመስላል?
ሩዋንዳ ወደ 135,000 የሚጠጉ ስደተኞችን ታስተናግዳለች። በአብዛኞቹ ስደተኞች ከቡሩንዲ እና ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የመጡ ናቸው። እንደ ሌሎች ብዙ አገሮች በሩዋንዳ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ለመኖር አይገደዱም። የመንቀሳቀስ ነፃነት፤ የመሥራት፣ ንብረት የመያዝ፣ የንግድ ድርጅቶችን እና የባንክ ደብተሮችን የመክፈት መብት አላቸው። በሩዋንዳ ዉስጥ የሚኖሩ የስደተኞች ፖሊሲ ምሳሌ መሆኑን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ በያዝነዉ ዓመት ዘገባዉ ጠቅሷል። ያም ሆኖ በሩዋንዳ የሚገኙ ስደተኞች ጭፍን ጥላቻና መድልዎ ይደርስባቸዋል፤ አብዛኞቹ ስደተኞች ድሆች ናቸው። አብዛኞቹ (93%) የሚሆኑት የሚኖሩት በካምፖች ውስጥ ነዉ። ምግብ ለመግዛት በወር እርዳታ በሚሰጣቸዉ 10,000 የሩዋንዳ ፍራንክ ወይም (7.94 የአሜሪካ ዶላር) ተስፋ ያደርጋሉ።
የቡሩንዲ ስደተኛ ኬሊ ኒሙቦና ለDW እንደተናገረው ‹‹በሩዋንዳ ሕይወት አስቸጋሪ ነዉ። በቀን ሁለት ጊዜ ለመብላት አቅሙ የለንም። ሥራ የማግኘት ዕድልም የለንም ›› ሲል ችግሩን ገልጾታል። በሩዋንዳ ከድህነት ሌላ በሀገሪቱ የሚታየዉ የሰብአዊ መብት አያያዝ ለስደተኞች የምትመች እና መኖርያ አገር አያደርጋትም ሲሉ የመብት ድርጅቶች ገልፀዋል። የብሪታንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ባለፈዉ ኅዳር ወር ላይ ባስተላለፈዉ ድንጋጌ በሩዋንዳ ተገን ጠያቂዎች ደህንነታቸዉ ተጠብቆ የሚኖሩባት ሃገር አይደለችም።
ኬት ሃሪሰን
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ