1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩዋንዳ፤ ከ 60 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርት ድገሙ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 6 2014

አነስተኛ ዉጤት ያመጡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይደግማሉ ያለዉ የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስቴር፤ በሃገሪቱ ዉስጥ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ቁጥር ተማሪዎች ማለትም ወደ 60 ሺህ ተማሪዎች በየዓመቱ ትምህርታቸዉን እንደደገሙ ገልፆአል።

Ruanda | Schüler und Schülerinnen mit Maske imi Unterricht
ምስል Simon Wohlfahrt / AFP

በሩዋንዳ ከአንደኛና ከሁለተኛ ደረጃ የተዉጣጡ ከ 60,000 በላይ ተማሪዎች በአፈጻጸም ጉድለት በሚል ፈተና መዉደቃቸዉን ተገለፀ። የሃገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎቹ aአነስተና ዉጤት በማምጣታቸዉ ትምህርታቸዉን እንደሚደግሙ ገልፆአል። ተማሪዎቹ የሚማሩበትን ክፍል እንዲደግሙ የተባለዉ  COVID-ወረርሽኝ ባመጣዉ ተፅኖ ነዉ። ቤተሰቦቻቸዉ የተመጣጣን ገቢ ያላቸዉ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን በሬድዮ፤ በቴሌቭዥን እንዲሁም በኢንተርኔት አማካኝነት ይከታተሉ ስለነበር ብዙዎቹ ፈተናን አልወደቁም ። ይሁንና የደሃ ቤተሰብ ልጆች ኢንተርኔት እና ሬድዮን መጠቀም ባለመቻላቸዉ ትምህርታቸዉን አልተከታተሉም። ቢሆንም የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስቴር ይህ ዉሳኔ ሚዛናዊነት ጎደለዉ ስትል በሩዋንዳ የአንድ የግል ትምህርት ቤት አስተማሪ ተናግራለች።

«አንዳንዶቹ ሌሎች የሚማሩትን ለማግኘት ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥኖችና ኢንተርኔት እንኳ አልነበራቸውም።  የሚበሉት ምግብ እንኳ ይምጣ አይምጣ ጭንቀት ላይ ባሉበት ሁኔታ ላይ ተሆኖ ትምህርትን ማጥናት አይቻልም።  በወረርሽኙ ምክንያት ትምህርታቸዉን ለመከለስ በቂ ጊዜም አልነበራቸዉም ። በአጭር ጊዜ ዉስጥ ግን  ሥርዓተ ትምህርቱን መጨረስ ነበረባቸው። እነዚያ ተማሪዎች ግን ደሃ ስለሆኑ ብቻ ትምህርታቸዉን መድገማቸዉ ኢፍትሐዊ ይመስለኛል»

ምንም እንኳን ሩዋንዳውያን የውሳኔውን ምክንያታዊነት ቢረዱም ፣ ብዙዎች ከኮቪድ ወረርሽኝ  ጋር የተከሰቱት ተግዳሮቶች ብቻ ናቸዉ ወይ ብለዉ ዳግም ይጠይቃሉ። ሩዋንዳዊትዋ ጆአን ካዩምባ የሁለት ልጆች እናት እና የህክምና ባለሙያ ናት። ውሳኔው የተማሪዎቹን የአእምሮ ጤንነት ሊጎዳ ይችላል የሚል ስጋት አላት።

ምስል Olympia De Maismont/AFP/Getty Images

«ኮቪድን ተከትሎ ብዙ ነገሮች ተከስተዋል። በጣም አስጨናቂ ጊዜ ነበር። ተማሪዎቹ በሥነ-ልቦና ተጎድተዋል። ተማሪዎች አንድን ክፍል ከመድገም ይልቅ ድጋፍ ቢደረግላቸዉ ይመረጣል። ምክር ይፈልጋሉ።  ተስፋ እንዳለ ሊነገራቸዉ እና ትምህርታቸዉን  እንደሚቀጥሉ ሊደረግ  ይገባል እንጂ ትምህርታቸዉን  መድገም የለባቸውም።  ምክንያቱም ትምህርትን እንዲደግሙ ማድረግ ተስፋ አስቆራጭ ነው። ምናልባትም አንዳንዶቹ በትምህርት ቤት ተመልሰዉ መምጣትና ትምህርታቸዉን መቀጠል ላይፈልጉ ይችላሉ»

ከሃያ ዓመታት በፊት ሩዋንዳ ተማሪዎች በአነስተኛ ዉጤት ምክንያት ትምህርታቸዉን  እንዳያቋርጡ አንድ መመርያ አዉጥታ ነበር፤ ሲሉ የሚናገሩት የትምህርት ጉዳይ ባለሞያዉ ዶ/ር ዣን ፍራንኮይስ፤ ለዚህ ተጠያቂዎቹ ተማሪዎቹም ወላጆችም ናቸዉ ይላሉ።

«ተማሪው ትምህርትን እንዲደግም ማድረጉ ትምህርቱን በደንብ እንዲረዳ ያግዘዋል። ፈተናውን ሲያልፍ እና ትምህርቱን በተጨባጭ ሳይረዳ ተማሪን ከክፍል ወደ ክፍል ማዛወርን መቀጠል ትክክል አይደለም። ተማሪዎች ምንም ሳይማሩ እና ግንዛቤ ሳይኖራቸዉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቅቃሉ። ለዚህ ደግሞ  አስተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸዉ» 

የሩዋንዳ የትምህርት ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ መልኩ ብቃትን መሠረት ባደረገ መመዘኛ ብቻ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል እንደሚያዛዉሩ ተናግረዋል። ተማሪዎች ለምን ፈተናቸውን እንደወደቁ እና ያለባቸዉን ችግሮች እንዴት ማስተካከል  እንዳለባቸዉ መንግሥት ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለዉም ገልፆአል። የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስትር ቫለንታይን ኡዋማሪያ ይህንኑ ያብራራሉ።

«በጣም አስፈላጊው እና ማወቅ ያለብን ነገር እነዚህ ተማሪዎች ለምን ትምህርታቸዉን ወደቁ የሚለዉን ነው። እስካሁን ያገኘነው ጥሬ መረጃ ተማሪዎቹ ለአሉበት ክፍል በጣም የበሰሉ መሆናቸዉን ነው። ያሉትን መርሆች እያየን እና ከአስተማሪዎቹ ጋር እየተነጋገርን ነው።  እናም  ምን ችግሮች እንዳሉባቸው እና እንዴት ማስተካከል እንደሚቻል እናያለን። ይህ ትንታኔ ካየን በኋላ በቀጣይ ምን መደረግ እንዳለበት ፖሊሲ አውጪዎች እንዲያዉቁት ይደረጋል»   

ያላለፉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይደግማሉ ያለዉ የሩዋንዳ የትምህርት ሚኒስቴር ፤ በሃገሪቱ ዉስጥ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ቁጥር ተማሪዎች ማለትም ወደ 60 ሺህ ተማሪዎች በየዓመቱ ትምህርታቸዉን እንደደገሙ ገልፆአል።

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW